ክፍል አንድ
የአንድ ሀገር ወይም ማህበረሰብ መሠረት ቤተሰብ እንደሆነ ይታወቃል።ይህ የሕብረተሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረተው በተለያየ መልኩ ቢሆንም መስራቾቹ ግን የህብረተሰቡ አካል የሆኑት ሰዎች (ወንድ እና ሴት) የሚፈጸሙት ጋብቻ ነው።ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም እንደ ተቋም ከመቋቋሙ አንስቶ እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ በሕግና እና ስርዓት መመራት ይኖርበታል።ለመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው የጋብቻና ፍቺ ህጋዊ አካሄድና ውጤቶቹ እንዴት ይታያሉ ስንል በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር የሆኑትን የህግ ባለሙያውን አቶ እንዳልካቸው ወርቁን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አቶ እንዳልካቸው እንደሚያብራሩት የቤተሰብ መመስረቻ የሆነው ጋብቻ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት እንዲዘልቅ ህብረተሰቡ ባወጣው ሕግ መሠረት መመሥረት ይኖርበታል።እንዲሁም በቆይታው ጊዜ የሚፈጠሩትን ግንኝነቶችና ውጤቶች እንዲሁም በሕግ መሠረት ከለላ ሊኖራቸው ይገባል።ለምሳሌ ያህል የልጅ አስተዳደግና አስተዳደር፣ በትዳር ውስጥ ስለሚፈጠሩ ንብረቶች፣ ከትዳር በፊት የነበሩ ንብረቶች፣ በባልና ሚስት መሀል ስለሚኖሩ ግለሰባዊ ግንኙነቶች፣ በዚህ ትዳር ውስጥ ሆኖ ማድረግ ስለተከለከሉ ነገሮች እና የመሳሰሉት በሕግ መሠረት መደንገግ ይኖርባቸዋል።
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ይህን የህብረተሰብ ምሰሶ የሆነውን ትዳር (ቤተሰብ) ሊያፈርሱት ይችላሉ።ትዳር ሲፈርስ ደግሞ እንደ የልጆች ቀለብ በትዳር ውስጥ የፈሩ ንብረቶች አከፋፈልና ሌሎችም ውሳኔ የሚሹ ነገሮችን ይዞ ይመጣል።በመሆኑም ይህ በሕግ መሠረት የተቋቋመው ተቋም መፍረስ ካለበት ሊፈርስ የሚገባውም በህግ አግባብ ነው።በዚህም መሰረት የተሻሻለውን የኢፌዴሪ የቤተሰብ ሕግ መሰረት በማድረግ ያለውን የሕግ ማዕቀፍና አተገባበር እንደሚከተለው እናያለን።
ስለ ጋብቻ (ቤተሰብ) አመሠራረት
ሀ. የጋብቻ ምንነት
አሁን ስራ ላይ ባለው የፌዴራል የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ውስጥ “ጋብቻ” ለሚለው ቃል ትርጉም በቀጥታ አልተሰጠም።ነገር ግን ከሕጉ የተለያዩ ድንጋዎች የቃሉን ትርጉም ማግኘት ይቻላል።አንዳንድ ሀገሮች ግን ለቃሉ በቤተሰብ ህጎቻቸው ትርጉም ለመስጠት ይሞክራሉ። ለምሳሌ የኢንዶኒዥያ የቤተሰብ ሕግ “ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መካከል መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥምረት በመፍጠር በፈጣሪ ፈቃድ ዘላቂና ደስተኛ ቤተሰብ ለመመስረት የሚደረግ ጥምረት ነው” በማለት ይተረጉመዋል።ነገር ግን ይህ ትርጉም ጋብቻ የሚለውን ቃል በምዕሉነት እየተረጎመ አይደለም።ለአብነት ለመግለጽ ያክል ተጋቢዎቹ በስምምነት የጋራ ቁሳዊ ጥምረት ሳይፈጥሩ በየግላቸው የግል ንብረቶችን እያስተዳደሩ በጋብቻ ተሳስረው መኖር ይችላሉ።በመሆኑም ጋብቻ ለሚለው ቃል ሁሉን በአንድ የሚያስማማ ትርጉም ማስቀመጥ አይቻልም።
የተሻሻለው የቤተሰብ ህጋችን ውስጥ በዋነኝነት በሦስት አይነት የጋብቻ ማስፈፃሚያ ስርዓቶች እውቅና ሰጥቷል።እነዚህም፡-
1. በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸም ጋብቻ፣
2. በሀይማኖት ስርዓት መሠረት የሚፈጸም ጋብቻ፣ እና
3. በባህል ስርዓት መሠረት የሚፈጸም ጋብቻ ናቸው። (በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 1 – 4)።
በውጭ ሀገር የተፈጸመ ጋብቻ በዛ ሀገር ጋብቻ አፈፃፀም ሕግ መሠረት የተፈጸመ ከሆነ እና የዚህን ሀገር (ኢትዮጵያ) ህዝብ ሞራል እስካልተቃረነ ድረስ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት ከላይ በተገለጸው ሦስት አይነት ስርዓቶች ከተፈጸሙ ጋብቻዎች ጋር እኩል እውቅናና ተቀባይነት አለው፡፡
ለ. ጋብቻን ለመፈጸም በቅድሚያ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች
ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ስርዓቶች ጋብቻ ቢፈጸምም ሦስቱም ዓይነት የጋብቻ መፈጸሚያ ስርዓቶች በቅድሚያ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ።እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መሰረታዊ የሆኑ ናቸው።
1. ፈቃደኝነት (Consent)
የሚጸና ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነፃና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ እንደሆነ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ ስድስት ላይ ተገልጿል።በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 34(2) ላይ “ጋብቻ በተጋቢዎቹ ነፃና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ ይመሰረታል ይላል።ስለዚህ በየትኛውም አይነት ጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት ጋብቻ ቢፈጸምም የተጋቢዎቹ ነፃ እና ሙሉ ፈቃደኝነት አስፈላጊ ነው፡፡
2. እድሜ
ጋብቻ ራሱን የቻለ ኃላፊነት የሚያስከትል በመሆኑ ወደ ጋብቻው የሚቀላቀሉት ተጋቢዎች ይህን ኃላፊነት መቀበል የሚችሉ መሆን አለባቸው። ስለዚህ በእድሜያቸው ብቁ መሆን አለባቸው።በዚህ በተሻሻለው ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7(1) ላይ ወንዱም ሆነ ሴቷ አስራ ስምንት ዓመት ሳይሞላቸው ጋብቻ መፈጸም እንደማይችሉ ይገልፃል።ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ይህ እድሜ ሳይሞላ በፍትህ ሚኒስቴሩ ከመደበኛ እድሜ ሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ ይችላል።ይህ የሚሆነው ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ብቻ ነው።
3. ዝምድና
ከህብረተሰቡ ሞራልና ከጤና ምክንያት የተነሳ ተጋቢዎች የቅርብ ዘመድ (የስጋም ሆነ የጋብቻ ዘመድ) መሆን እንደሌለባቸው እሙን ነው።ይህንንም በተመለከተ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 8 እና 9 ላይ ክልከላው በግልጽ የተቀመጠ ነው።
4. በጋብቻ ላይ ጋብቻ
የፀና ጋብቻ ያለው አንድ ሰው ይህ ጋብቻ ጸንቶ እያለ ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማይችል (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 11) ክልከላ ተጥሎበታል።
5. በብቸኝነት ለመኖር የተወሰነ ጊዜ
ይሄኛው ክልከላ ወይም ቅድመ ሁኔታ ከላይ ካሉት አራት ቅድመ ሁኔታዎች ለየት ባለ መልኩ በሴቶች ላይ ብቻ የተጣለ ነው።አንዲት ሴት አስቀድሞ የነበራት ጋብቻ ከቀረ በኋላ አንድ መቶ ሰማኒያ ቀን ካላለፈ በቀር ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማትችል ክልከላ ተጥሎባታል።ነገር ግን ይህ አንድ መቶ ሰማኒያ ቀን ሳይደርስ የወለደች እንደሆን ወይም ጋብቻ የምትፈጽመው ከቀድሞ ባሏ ጋር ከሆነ ወይም ዕርጉዝ አለመሆኗ በህክምና ከተረጋገጠ ወይም ይህን ጊዜ እንዳትጠብቅ በፍርድ ቤት የተወሰነ እንደሆነ ይህን ጊዜ ሳትጠብቅ ጋብቻ ልትፈጽም እንደምትችል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 16 (2) ላይ ተቀምጧል።ይህ ክልከላ በመሰረታዊነት የተቀመጠው የህፃናትን መብት ለመጠበቅ ነው።ህፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅና ከወላጆቻቸው እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው በህገ መንግስቱና አለማቀፍ ስምምነቶች ላይ የተቀመጡና የተረጋገጠ መብታቸው በመሆናቸው ነው።በመሆኑም ይህን ክልከላ በማድረግ የሕፃናትን መብት ለማስከበር የወላጆቻቸውን ማንነት ላይ አከራካሪ ሁኔታ እንዳይፈጠር ይረዳል፡፡
ሐ. ጋብቻ እንዳይፈጸም ስለመቃወም
ጋብቻ የቤተሰብ መመስረቻ መሰረታዊው እና ዋናው መንገድ መሆኑ ግልጽ ነው።ቤተሰብ ደግሞ የህብረተሰብና የሀገር መሠረት እና መሰሶ ነው።ይህ የህብረተሰብ እና የሀገር መሰሶ የሆነው ጋብቻ የተጋቢዎቹ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡና የሀገርም ጉዳይ ነው።ስለዚህም የህብረተሰብ እና የመንግስት ጥበቃና እንክብካቤ የሚያስፈልገው ተቋም ነው።ይህም በመሆኑ ነው ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊት መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ ወይም ክልከላዎች የተቀመጡት፡፡
በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት እነዚህ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔተዎች ሳይሟሉ ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል።ለምሳሌ፡- በሕግ ከደነገገው እድሜ በታች ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል፤ ወይም በቤተዘመዶች መካከል ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል።በዚህ ሁኔታ ቅድመ ሁኔታውን አሟልቶ ያልተፈጸመ ጋብቻ ካለ ወይም ሊደረግ እቅድ ካለ ይህን እንዳይፈጽም ወይም ሕጋዊ እርምት እንዲወሰድ ኃላፊነት ለመንግስትና ለህብረተሰቡ የተሰጠ አደራ ነው።ይህም ማለት በዓቃቤ ሕግ በኩል እና በተጋቢዎቹ ዘመዶችና በሌሎች በጉዳዩ ያገባናል በሚሉ የህጻናትና ሴቶች መብት አስከባሪ ድርጅቶችና በመሳሰሉ ድርጅቶች በኩል የሚከናውኑ ይሆናል፡፡
ጋብቻው እንዳይፈጸም መቃወም ወይም እንዲፈርስ ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉት ወገኖችን ማንነት የሚወስነው ለተቃውሞው መሠረት የሆነው ጉዳይ ማለትም ያልተሟላው ቅድመ ሁኔታ ነው።ለምሳሌ የመቃወሚያው መሠረት በጋብቻ ላይ ጋብቻ ከሆነ ይህን ቀድሞ የጸና ጋብቻ ያለው/ያላት ባለትዳር ወይም ዐቃቤ ሕግ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ይህ ጋብቻ ተፈጽሞ ከሆነ እንዲፈርስ የሚቀርበው አቤቱታ ለፍርድ ቤት ነው።(የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75(ለ) )።ነገር ግን ሊፈጸም የታቀደው ጋብቻ እንዳይፈጸም የሚቀርብ አቤቱታ ከሆነ የሚቀርበው ጋብቻውን ለሚያስፈጽመው ባለስልጣን ነው።ይህም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 19 ላይ ተገልጿል።ይህ መቃወሚያ በጽሑፍ መቅረብ ያለበት እጅግ ቢዘገይ ጋብቻው ሊፈጸምበት ከታቀደው ቀነ ቀጠሮ 15 ቀን በፊት መሆን ይኖርበታል።ይህ ተቃውሞ የቀረበለት ተቋምም በሕግ በተቀመጠው መሰረት በአምስት ቀን ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት።ውሳኔው ተቃውሞውን ውድቅ ያደረገ እንደሆነ ውሳኔው የመጨረሻ ነው።ነገር ግን ውሳኔው ተቃውሞውን በመቀበል ጋብቻውን እንዳይፈጽም የወሰነ እንደሆነ ጋብቻው እንዳይፈጸም ማድረግ ካለበት ይህንኑ ውሳኔ ወዲያው ለተጋቢዎች ማሳወቅ ይኖርበታል።በዚህ ውሳኔ ላይ ተጋቢዎቹ ይግባኛቸውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡
መ. ስለ ጋብቻ ምዝገባ
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት በየትኛውም የጋብቻ ማስፈፃሚያ ስርዓቶች የተፈጸመ ጋብቻ መመዝገብ እንዳለበት ያስገድዳል።የጋብቻ መፈጸሚያ ስርዓቱ የተለያየ ቢሆንም የምዝገባ ስርዓቱ ግን አንድ ብቻ ነው።ይህን የጋብቻ የመመዝገብ ኃላፊነት የተሰጠው ለክብር መዝገብ ሹም ጽህፈት ቤት ነው።ነገር ግን ይህ ጽህፈት ቤት እስኪቋቋም ድረስ የከተማ አስተዳደር መዘጋጃ ቤቶች ይህን ስራ ያከናውናሉ።በአሁኑ ሰዓት በአዋጅ ቁጥር 760/2004 ወሳኝ ኩነቶች ማለትም ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ የመሳሰሉት እንዲመዘገቡ ተደንግጓል።በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 278/2005 ደግሞ የወሳኝ ኩነቶች ጽ/ቤት ተቋቁሞ ስራዎችን ለመስራት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።ይህም ሆኖ ጋብቻ በሕጉ የተመለከቱትን ውጠቶች ማስከተል የሚጀምረው ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን ጋብቻው ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ነው።ከዚህ መረዳት የሚቻለው የጋብቻ ምዝገባ አስፈላጊነት ጋብቻውን ሕጋዊነት እና የሚጸና ነው አይደለም ብሎ ለመወሰን ሣይሆን ለማስረጃነትና ለሌላ ተዛማጅ ጉዳዮች ነው።ለዚህ ማስረጃ እንዲሆነን የሚከተለውን የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ እንመልከት።
«የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 41896 በአመልካች ወይዘሮ ታደለች ዋለልኝ እና ተጠሪዎች እነ ወይዘሮ አዲስ አለሙ መካከል በነበረው ክርክር የስር ፍርድ ቤት ጋብቻ እንዳለ የሚቆጠረው ጋብቻው በክብር መዝገብ ሹም ፊት ቀርቦ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ነው በማለት የሰጡትን ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለው በማለት በመሻር በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 28/3/ መሠረት ጋብቻው ሕጋዊ ውጤት የሚጀምረው ጋብቻው ከተፈጸመበት ቀን ጀምሮ ነው በማለት ወስኗል፡፡»
ሠ/ የጋብቻ ቅድመ ሁኔታ አለመሟላት የሚያስከትለው ውጤት
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ጋብቻ ከመፈፀሙ በፊት መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝረናል።ነገር ግን እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ጋብቻው ቢፈፀም የፍትሐብሔር እና የወንጀል ሕጋዊ ውጤቶች አሉት።እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሣይሟሉ ጋብቻ ከተፈፀመ ጋብቻው እንዲፈርስ አቤቱታ የሚቀርበው ለፍርድ ቤት ነው።አቤቱታውም የሚቀርበው እንደየጉዳዮቹ በተለያዩ አካላት ነው።በጉዳዩ ላይ የሚያገባቸው አካላት (interested party) ለፍርድ ቤት በሚያቀርቡት አቤቱታ ነው የትዳሩን እጣ ፈንታ የሚወሰነው።ነገር ግን እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አቤቱታው ላይ ፍርድ ቤቱ ጋብቻው ይፍረስ የሚል ውሳኔ እስካልሰጠ ድረስ እንዲፈርስ አቤቱታ የቀረበበት ትዳር እንደማንኛውም ሕጋዊ ትዳር ተቀባይነትና ሕጋዊ ውጤት እንዳለው ነው የሚቀጥለው።
የጋብቻ ውጤት
በዚህ ፅሁፍ መግበያ እና በክፍል አንድ ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ጋብቻ ሕጋዊ ድርጊት ነው።ሕጋዊ ድርጊት ደግሞ ሁልጊዜም ሕጋዊ ውጤትን ያስከትላል።ስለሆነም ጋብቻም ሕጋዊ ድርጊት እንደመሆኑ መጠን ሕጋዊ ውጤት የሚኖረው ስለመሆኑ የታወቀ ነው።እነዚህም ሕጋዊ ውጤቶች በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት (personal effect) ወይም በተጋቢዎቹ የንብረት ግንኙነት (pecuniary effect) የሚኖራቸው ናቸው፡፡
በየትኛውም የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት ጋብቻው ቢፈፀምም የሦስቱም አይነት ጋብቻ ውጤት አንድ አይነት ነው።(በተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 40) ተጋቢዎች ትዳራቸው ያስከተለውን ግላዊ ግንኙነት ውጤቶች ወይም የንብረት ግንኙነት ውጤቶችን በተወሰነ መልኩ በውል እንዲመራ ሊያደርጉት ይችላሉ።ይህም ማለት አንዳንዱ የጋብቻ ውጤቶች በውል ሊቀሩ ወይም ሊሻሻሉ የሚችሉ ናቸው ማለት ነው።ነገር ግን ሌሎች በውል ሊቀሩ ወይም ሊሻሻሉ የማይችሉ አስገዳጅ ውጤቶችም አሏቸው።ይህም በተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 42(3) ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013