ገና ከጅምሩ በትግራይ ህዝብ ደም ስቃይና እንግልት እየነገደ በነጻነት ትግል ስም በብዙ ንጹኃን ደም ወደ ሥልጣን የመጣው አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን በህዝባዊ ትግል ከሥልጣን መንበሩ ከተወገደ ማግስት ጀምሮ በቀደመ ባህሪው በትግራይ ህዝብ ሞት ፣ ስቃይና እንግልት እድሜውን ለማርዘም ከፍያሉ ወንጀሎችን ፈጽሟል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተሰጠውን ሰላማዊ እድል ለመጠቀም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፣ ከዛም በላይ ለራሱ በሰጠው የተሳሳተ ግምት በተፈጠረ እብሪት በመከላከያ ሠራዊት ላይ ባደረሰው ጥቃት ሊወጣው ያልቻለው ፈተና ውስጥ ለመግባት ተገድዷል ።
በእብሪትና በማን አለብኝነት ልባቸው የደነደኑ የቡድኑ ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች በመከላከያ ሠራዊት በተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻ ዓመታት ያዋጉኛል ካላቸው የኮንክሪት ምሽጎች ጋር በ15 ቀናት ውስጥ በአብዛኛው ሙትና ምርኮኛ ሆነዋል። ከጀግናው የመከላከያ ኃይል በደረሰበት ምት መቼም አቅም ፈጥሮ ለሀገር አደጋ የማይሆንበትና ጢሻ ለጢሻ የሚንከራተት ተራ ሽፍታ ደረጃ ደርሷል።
ለያዥ ለገላጋይ ያልተመቹት በብዙ ንጹኃን ደም እጃቸውን ያጨማለቁ የቡድኑ ከፍተኛ የደህንነትና የፖለቲካ አመራሮች የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ በተካሄደ ወንጀለኞችን አድኖ ለፍርድ የማቅረብ ስራ አብዛኞቹ ሙትና ምርኮኛ ሆነዋል።
የቀሩትም ቢሆኑ በትግራይ በረሀ ከአንድ ዋሻ ወደ ሌላ ዋሻ እየተንቀሳቀሱ እንደቀደመው ዘመን የትግራይን ህዝብ ለህልውናቸው ጋሻ ማድረግ የሚያስችሉ የሴራ ተግባራትን ሲፈጽሙ፤ በፈጸሟቸው ሴራዎች መጠን እና ሴራዎቹ የትግራይን ህዝብ ባስከፈሉት ዋጋ መጠን አየር መተንፈስ የሚችሉበትን ዕድል ሲፈጥሩ ቆይተዋል ።
በአንድ በኩል ላለፉት 60 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ያለምንም አማራጭ በትግል ስም አስገዳጅ በሆነ መንገድ ይዘውት መጥተዋል ፤ ይኸው አማራጭ አልባ የረጅም ዓመታት አስገዳጅ መንገድ ደግሞ ህዝቡ የራሱን እጣ ፋንታ በነጻነት እንዳይወስን ከፍያለ ተግዳሮት ፈጥሮበታል ።
ከዚህም በላይ ቡድኑ ከበረሀ ጀምሮ በህዝቡ መሀል የዘረጋው በጭካኔና በክፋት የተሞላ መዋቅር በህዝቡ ውስጥ የፈጠረው በራስ ያለመተማመን እና ከፍ ያለ ስጋት አጠቃላይ በሆነው የክልሉ ህዝብ የፖለቲካ ሰነ ልቦና ላይ የፈጠረው ጫና ከፍ ያለ ነው።
ከዚህም በላይ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄር ፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር ተቀራርቦና ተስማምቶ እንዳይኖር በቡድኑ የተፈጠሩ የጥላቻ ትርክቶች በህዝቡ ውስጥ ተጠራጣሪነት ፈጥረዋል። ይህም በራሱ ህዝቡ ለአሻባሪው ህወሓት ሕልውና ጋሻ እንዲሆን አስገድዶታል ።
ይህ አሻባሪ ቡድን ከህግ ማስከበር ዘመቻው ማግስት ጀምሮ ከደረሰበት ከፍ ያለ ሁለንተናዊ ውድቀት ህይወት ለመዝራት ንጹሀን ዜጎችን በጠራራ ጸሀይ ከመግደል አንስቶ፣ የትግራይ ሕዝብ ነገዎችን የሚያጨልሙ አስከፊ ተግባራትን በተደጋጋሚ በአደባባይ ሲፈጸም ቆይቷል።
ቀደም ብሎ ገበሬው በብዙ ድካም አርሶ የዘራውን ሰብል ሳይሰበስብ ግጭት በመፍጠር ልፋቱን ከንቱ ማድረጉ ሳያንስ ፣ በተያዘው ክረምትም አርሶ ከተመጽዋችነት እንዳይወጣ ከማስፈራራት አንስቶ የእርሻ ስራዎች እንዳይጀመሩ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።
ከዚህም በከፋ መልኩ በችግር ላይ የሚገኘው የትግራይ ህዝብ የእርዳታ አቅርቦት እንዳይደርሰው መንገዶችን ከመዝጋት ጀምሮ ለሰብአዊ ተግባር የተሰለፉ የረድኤት ሰራተኞችን በመግደል የእርዳታ አቅርቦቶችን ሲያስተጓጉል ፤ በዚህም ነፍስ ለመዝራት ሲሞክር በአደባባይ ታይቷል ።
እነዚህን ሁሉ ወንጀሎች በአደባባይ እና በጠራራ ፀሀይ በጭካኔና ፍጹም አረመኔያዊ በሆነ ክፋት እየፈጸመ፣ድርጊቶቹን እንዳልፈጸመ ፤ ከዛም በላይ ድርጊቶቹ በመንግስት የተፈጸሙ በማስመሰል ከሀገር በዘረፈው ሀብት በገዛቸው የሚዲያና የሎቢ ቡድኖች የዓለም አቀፍን ማህበረሰብ በማደናገር ከደሙ ንጹህ ሆኖ ለመታየት ሞክሯል ።
ይህ ሙከራው በተለይም የሚያዩትንና በጆሯቸው የሚሰሙትን እውነታ ለመስማትና ለማየት ፈቃደኛ ባልሆኑና ለራሳቸው አጀንዳ ሀገራዊ ችግሩን እንደ ክፍተት ለመጠቀም በሚሞክሩ ሀገራት መንግስታት አቅም ገዝቶ በትግራይ ህዝብ ህልውናና ህይወት ላይ ተግዳሮት መፍጠር ችሏል።
ይህ ከፍጥረቱ ጀምሮ በንጹሃን ደም ፣ስቃይና እንግልት ሕይወት እየዘራ ዘመኑን የሚቆጥር የነፍሰ ገዳዮችና የከሀዲዎች ስብስብ ዛሬም በትግራይ ህዝብ ደም ፣ስቃይና እንግልት ሕይወት ዘርቶ ለመቆም ያለመው ሕልም ባላሰበውና ባልገመተው መንገድ ከንቱ ሆኗል።
በ1977 ዓ/ም እንደለመደው የትግራይን ህዝብ የረሀብ አደጋ ውስጥ በመክተት ከትግራይ ረሀብ ዳግም ለማንሰራራት ያሰላው ስሌት የሚወራረድበት መንገድ አሁን ተቀይሯል። ይህን የጭካኔና የክፋት ስሌት እንዳሰላው ራሱ የሚያወራርድበት እውነታ ውስጥ ወድቋል።
ከኢትዮጵያውያን በላይ ለትግራይ ህዝብ አሳቢ የሆኑ ሀገራት መንግስታት እና ተቋማት አሁን በትግራይ ውስጥ ሊከሰቱ ለሚችሉ ግድያዎች ፣ ዝርፊያዎች እና የአደባባይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ማን ላይ እጃቸውን እንደሚቀስሩ ሁላችንም ነገ ላይ የምናየው እውነታ ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013