አረም የግብርና ዘርፍን አንቀው ከሚያዙ ሳንካዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የዓለም ህዝብ የምግብ ፍላጎት ለማሟላት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ለሚደረገው ጥረት ዋነኛ ተግዳሮት እየሆኑ ካሉ ችግሮች አንዱ አረም መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃዎች ያሳያሉ፡፡አረም ከሰብሎች ጋር ንጥረ ነገሮችን፣ ብርሃን እና ውሃ በመሻማት፤ ለሰብሎች ተስማሚ ያልሆኑ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን በማመንጨት፤ እንዲሁም ጸረ ሰብል ተባዮች መራቢያ በመሆን የግብርና ዘርፉን ይፈታተናል፡፡
በአጠቃላይ አረም የግብርና ምርት ብዛት እና ጥራት እንዲቀንስ የአንበሳውን ድርሻ ከሚያበረክቱት አንዱ ነው፡፡የፋኦ መረጃ እንደሚያሳየው በአረም ምክንያት በሰብል ምርታማነት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከሀገር ሀገር፣ ከአህጉር አህጉር እንዲሁም ከቀጣና ቀጣና የሚለያይም ቢሆንም በየትኛውም ዓለም የግብርና ስጋት ነው፡፡ የሚከሰቱት ኪሳራዎች ባደጉት ሀገራት ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆን ግብርና ምርታማነት በአረም ምክንያት ሲባክን፤ በአንፃሩ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መጠኑ ከፍ ያለ ነው፤ በአረም ምክንያት በሰብል ምርት ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ከ20 እስከ 30 በመቶ ይደርሳል፡፡
ኢኮኖሚያቸው ከፍተኛ ደረጃ በግብርና ላይ በተመሰረተባቸው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ይህን ያህል የግብርና ምርታማነት በአረም ምክንያት ብቻ ኪሳራ መከሰቱ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ነው፡፡በመሆኑም አረም የምግብ ዋስትና እና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው፡፡
ለዓለም የግብርና ምርት ዋነኛው እንቅፋት የሆነውን አረምን ለማጥፋት አርሶ አደሮች እንደየ አካባቢያቸው የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡አረሞችን በእጅ ከመልቀም ጀምሮ የተለያዩ ኬሚካሎችን ይጠቀማሉ፡፡እነዚህ አረምን ማጥፊያና ማስወገጃ ዘዴዎች የየራሳቸው የሆነ አሉታዊ ጎን አላቸው፡፡አርሶ አደሮች አረምን ለማረም የሚያጠፉት ጉልበትና ጊዜም እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡እጅግ አድካሚና አሰልቺ ነው፡፡አንድ ሄክታር መሬት በእጅ ለማረም የሚያስፈልገው የሰው ጉልበት በአነስተኛ የገበሬ ቤተሰብ አቅም የሚሸፈን አይደለም፡፡በሌላ በኩል አረሞችን ለማጥፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች ስነ ምህዳር እና የሰብል ጥራትና ጤናማነት ላይ ጉዳቶችን ሲያስከትሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡
አረሞችን ከሰብል ውስጥ ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ሰብል ላይ ጉዳት በማያስከትል፣ ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ብክነት በማያስከትል መልኩ ማከናወን የሚቻልበትን ዘዴ ለመፍጠር በተለያዩ ሳይንቲስቶች የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡በቅርቡ በእንግሊዛዊያን የተሰሩ ሮቦቶች የብዙዎችን ቀልብ ስቧል፡፡በሀገረ እንግሊዝ ተቀማጭነቱን ያደረገ ስሞል ሮቦት የተባለ ተቋም አረሞች ያሉበትን የሚለዩ በኤሌክትሪክ የሚያጠፉ እና በሰብል የሚተኩ ሮቦቶችን አስተዋውቋል፡፡
የሮቦቶቹን አምራች ኩባንያ ዋቢ አድርጎ ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው፤ ያለ ኬሚካል እና ከባድ ማሽነሪ እገዛ አላስፈላጊ አረሞችን ድምጥማጣቸውን የሚያጠፉ ናቸው፡፡ሮቦቶቹ ሶስት አይነት ሲሆኑ፤ የየራሳቸው ስራ አላቸው፡፡አረም ያለበትን የመፈለግ፣ በኤሌክትሪክ የማጥፋት እና በቦታው ተፈላጊውን ሰብል የመተካት ስራዎችን በቅደም ተከተል ይከውናሉ፡፡
የመጀመሪያው ሮቦት 20 ሄክታር በቀን የመቃኘት አቅም ያለው ሲሆን በእርሻ መስኩ ላይ የት የት ቦታ አረሞቹ እንደሚገኙ መረጃ ይሰበስባል፡፡ የዚህ ሮቦት ስም ‹‹ቶም›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ቀጣዩ ሮቦት የተሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ አረሞቹን ስራቸው ድረስ ዘልቆ የሚገባ የኤሌክትሪክ ንዝረት በመልቀቅ የማጥፋት ተግባር ያከናውናል፡፡ይህ ‹‹ሮቦት ጽዲክ›› በሚል የተሰየመ ሲሆን፤ ሶስተኛውና የመጨረሻው በአረሞቹ ምትክ ተፈላጊውን ዘር እየተካ ይሄዳል፡፡ይህኛው ሮቦት ደግሞ ‹‹ሃሪ ››ይሰኛል፡፡በተለይም ሮቦቶቹ አረም በነበረበት ቦታ ተፈላጊ ሰብል የሚተኩ መሆናቸው ከዚህ ቀደም አረምን ለማጥፋት ጥቅም ላይ ሲውሉ ከነበሩ ሁሉም ዘዴዎች የበለጠ ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡
ሮቦቶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ የገበሬዎችን ወጪ 40 በመቶ በመቀነስ ጥቅም ላይ የሚያውሉትን የኬሚካል መጠን ወደ 95 በመቶ እንደሚያወርደው አምራች ኩባንያውን ዋቢ አድርጎ ሲ.ኤን.ኤን አስነብቧል፡፡ቴክኖሎጂው ለዓለም የግብርና ዘርፍ ልዩ ትርጉም ያለው ቴክኖሎጂ መሆኑን ታምኖበታል፡፡
ስሞል የተሰኘው ሮቦት አምራች ኩባንያ እ.አ.አ ከ2017 አረም የሚያጠፉ ሮቦቶችን ለማምረት ጥረት እያደረገ መቆየቱ የተነገረ ሲሆን ባለፈው ሚያዚያ ወር ቶም የተሰኘውን የመጀመሪያውን ሮቦት አምርቷል፡፡ቶም የተሰኘው የንግድ ሮቦት በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ሀገር በሶስት እርሻዎች ውስጥ አረምን የመለየት ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡ሌሎቹ ሮቦቶች አሁንም በሙከራ ደረጃ ላይ ናቸው ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው እ.ኤ.አ. በ2018 ስድስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአረም ማጥፊያ ካናሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ግብይት የተደረገ ሲሆን ዋጋቸው 38 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው ኬሚካል በየዓመቱ ጥቅም ላይ እንደሚውል ነው፡፡ኬሚካሎቹ አፈር ውስጥ የመቅረት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት የስሞል ሮቦት ኩባኒያ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ቤን ስኮት ሮቢንሰን፤ “የእኛ ሮቦቶች አርሶ አደሮች የተሟጠጡና የተበላሹ አፈሮችን ከኬሚካሎች እንዲላቀቁ ያስችላቸዋል” ብለዋል፡፡ኩባኒያቸው ሮቦቶችን በስፋት በማምረት አገልግሎቶችን በስፋት የመስጠት ህልም መሰነቁን አብራርተዋል፡፡
ኩባንያው ለዚህ አገልግሎት የሚውል በትንሹ ከ7 ሚሊዮን ፓውንድ (9.9 ሚሊዮን ዶላር) በላይ መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡ኩባንያው እስከ 2023 ድረስ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡በሄክታር ወደ 400 ዩሮ (568 ዶላር) በማስከፈል አገልግሎት የመስጠት ውጥን ይዟል፡፡
ቤን ስኮት ሮቢንሰን እንደሚሉት፤ ኩባንያው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በቅድሚያ የመቃኘት አቅም ያለው ሲሆን በእርሻ መስኩ ላይ የት የት ቦታ አረሞቹ እንደሚገኙ የመቃኘት ተግባር የሚፈጽም ሮቦት በማሳ ውስጥ ይለቀቃል፡፡መረጃ ይሰበስባል፡፡አረም ማረም አስፈላጊ መሆን አለመሆኑን መረጃዎችን ይሰበስባል፡፡ሮቦቱ በሚሰበስበው መረጃ ላይ በመመርኮዝ አረሞችን የሚያጠፉ እና በሰብል የሚተኩ ሮቦቶች ወደ ቦታው ይላካሉ፡፡በመጀመሪያ ከተላከው ሮቦት በሚገኘው መረጃ መሰረት ማረም እና በሰብል መተካት አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ ደግሞ ሮቦቶቹ አይላኩም፡፡
ስሞል የተሰኘው የግብርና ሮቦቶችን የሚያመርተው ኩባንያ በዩኬ ውስጥ ከሚገኝ ሩት ዌቪ ከተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር በመሆን አረም ማጥፊያ ቴክኖሎጂን በማምረት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ስኮት-ሮቢንሰን እንደሚሉት “በአረሞች ሥሮች ውስጥ በአፈሩ ውስጥ የሚያልፍ የኤሌክትሪክ ሀይል በመልቀቅ አረም ሙሉ በሙሉ ያጠፋል፡፡ለሰብል ስጋት የሆኑ አረሞች የሚገኙባቸው እያንዳንዱ ማሳ በመሄድም አረምን የማጥፋት ስራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮች ማሳቸውን በኬሚካል ካስረጩ በኋላ ኬሚካሉ አረሞችን ማጥፋት አለማጥፋቱን ወዲያው ለማረጋገጥ አዳጋች እንደሆነ የሚጠቁሙት ቤን ስኮት ሮቢንሰን አዲሶቹ ሮቦቶች የሚሰጡ አገልግሎት ውጤት ግን ወዲያው የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ሮቦቶቹ ወደ ቦታው ከሄዱ በኋላ ጠቃሚ ሰብሎችን ሳይነኩ አላስፈላጊ አረሞችን በመለየት ወዲያው እንደሚጠፉ
ተናግረዋል፡፡በሰብሎች ላይ ጉዳት የማያስከትሉ አረሞችን ሳይነኩ ማለፍ እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት፡፡
ኩባንያው ይህንን አረም ማስወገጃ ዘዴ “per plant farming” ወይም እያንዳንዱን ሰብል የማረም ዘዴ ብሎ የሚጠራው ሲሆን ይህ ዘዴ እያንዳንዱ እጽዋት የሚመዘገቡበት እና ክትትል የሚደረግበት ዘመናዊ የግብርና ዘዴ ነው፡፡
በሐርፐር አዳምስ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምህንድስና መምህር የሆነው ኪት ፍራንክሊን ለሲ ኤን ኤን ቢዝነስ እንዳሉት የኤሌክትሪክ ሀይል በመጠቀም አረምን ማጥፋት እንደሚቻል ጥርጥር የላቸውም፡፡ነገር ግን በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሄክታሮችን በመጠነ ሰፊ ርጭቶች መሸፈን ይቻላል፡፡በኤሌክትሪክ ከማጥፋት ይልቅ በኬሚካል ርጭት ማጥፋት ይቀላል፡፡ሮቦቶቹ የምርት መቀነስ እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋትም አላቸው፡፡በመሆኑም በሮቦቶቹ ውጤታማነት ላይ ጥርጥር አላቸው፡፡አዋጭነቱ ላይ ጥርጥር አለኝ ይላሉ፡፡ቤን ስኮት ሮቢንሰን ግን የኪት ፍራንክሊንን ስጋት መሰረተ ቢስ ነው ይላሉ፡፡አዋጭነት ላይ ምንም ጥርጥር የላቸውም፡፡አርሶ አደሮቹ ሮቦቶችን ሊወዱ የሚችሉበት በርካታ ምክንያቶች አሉ ይላሉ፡፡
“በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ በሆነ መንገድ የእርሻ ስራን ማከናወን አንዱ የውጤታማ የእርሻ መንገድ መሆኑ እየታመነበት መጥቷል” የሚሉት ቤን፤ አነስተኛ ግብአቶችን በመጠቀም፣ አርሶ አደሮች አረም ማጥፊያውን የት እና መቼ እንዳስፈለጋቸው አውቀው መጠቀም መቻላቸው አላስፈላጊ የገንዘብ ወጪን ሊያድን ከመቻሉም ባሻገር ለብዝሃ ህይወት ጥበቃና ለአርሶ አደሮች ህይወት መሻሻል የላቀ ሚና ይኖረዋል ይላሉ፡፡
እንዲሁም ኩባንያቸው አነስተኛ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ በመፍጠር የአፈር ጥራት እና ብዝሃ ህይወትን የመንከባከብ እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል
“የመኖሪያ ከባቢን እንደ ኢንዱስትሪ ሂደት መያዝ ውስብስብነቱን ችላ ማለት ነው” ያሉት ቤን ስኮት-ሮቢንሰን፤ ዓለም አስተራረሱን አሁን መለወጥ አለበት ብለዋል፡፡ያለዚያ በቀጣይ ጊዜያት የሚታረስ ነገር አይኖርም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013