የዘመናዊ እና የጥንት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ምሁነታቸው፣ ጸሐፊነታቸው፣ ሀያሲነታቸው፣ ተርጓሚነታቸው፣ የመካከለኛው ዘመን ታሪክን፣ የግዕዝ ቋንቋን አዋቂና አጥኚነታቸው፤ እንዲሁም በጥልቅ ጥናትና ምርምር ስራዎቻቸው ገዝፈው የሚታወቁት አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (1924–2013) በ89 ዓመታቸው ከባለፈው ሳምንት በፊት ባለው ሳምንት በሚኖሩበት ኒው ዮርክ ከተማ አርፈዋል።
የስድስት ልጆች አባቱ ፕሮፌሰር ጌታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩ ሲሆን፤ በቆይታቸውም በተለያዩ አስተጽዋቸው ይታወቃሉ። ከ20 በላይ መጻሕፍትንም (“በሙሉ” አማዞን ላይ ይገኛሉ) አዘጋጅተዋል።
ጥላሁን ገሠሠ “ከመሞት አልድንም …” እንዳለው ነውና ሁሉም ሂያጅ ነው። ልዩነት ቢኖር የጊዜ ጉዳይ ነው፤ ቴድ “ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው” እንዳለው ማለት ነው። በመሆኑም እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ሁሉ ፕሮፌሰር ጌታቸውም ከመንገደኛነቱ አልቀሩምና ላይመለሱ ሄዱ። “መሄድ ቢሉሽ መሄድ ነው ወይ …” እንደተባለው ከመሄዳቸው በፊት ያለውን ተግባር፣ ክንውናቸውንና ስኬታቸውን እንቃኛለን።
ብሩህ ዓለምነህ “በኢትዮጵያ የምሁራን ታሪክ ውስጥ ለሀገራቸው በብዙ የጥናት መስኮች ትልቅ አበርክቶ (በታሪክና ቅርስ ጥበቃ፣ በቋንቋና ሥነፅሁፍ፣ በፍልስፍናና በሥነ ትምህርት እንዲሁም በመንፈሳዊ ተጋድሎ) ካደረጉ ምሁራን ውስጥ የ1940ዎቹ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ተማሪዎችን የሚያክል የለም፡፡” በማለት ምስክርነቱን የሰጠለት ትውልድ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓም 4ተኛው የበጎ ሰው ሽልማት በአቤል ሲኒማ አዳራሽ ሲከናወን ከተሸላሚዎቹ አንዱ በመሆናቸው ስለ መሸለማቸው ምክንያቱ እንደሚከተለው ነበር በንባብ የቀረበው፤
መኖሪያቸውን በአሜሪካ አድርገው የነበሩት፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው የተወለዱት ግንቦት 24 ቀን 1924 ዓም በሰሜን ሸዋ ዞን ሸንኮራ ሲሆን እኤአ ከ1945-1951 ድረስ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተምረዋል፡፡ አኤአ በ1957 ከኮፕቲክ የነገረ መለኮት ኮሌጅ (ካይሮ፣ ግብጽ) በባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ የተመረቁ ሲሆን በዚያው ዓመት በካይሮ ከሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በቢ.ኤ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ እኤአ በ1962 ደግሞ ጀርመን ቱቢንገን ከሚገኘው ከኤበርሃርድ ካርልስ ዩኒቨርሲቲ በሴማውያን ቋንቋዎች ፊሎሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ጥንታዊ የብራና ጽሑፎችን በማጥናት፣ የካታሎግ ሥራ በመሥራትና በጉዳዩ የሚያጠኑትን በማማከር ይታወቃሉ፡፡ በሚኒሶታ የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ሪጀንተስ ኤሚሪተስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ በሂል ሙዝየምና የብራና መጻሕፍት ቤተ መጻሕፍት ደግሞ ኪዩሬተር ኤሚሪተስ ናቸው፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እኤአ ከ1962-1969፣ እንዲሁም ከ1971-1974 ዓ.ም የአማርኛ ሰዋሰው፣ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ የግዕዝ ሰዋሰው፣ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ፣ የዐረብኛ ሰዋሰው እና የሴም ቋንቋዎችን ሰዋሰው አስተምረዋል፡፡
እኤአ በ1976 ዓም በሂል ሙዝየምና የብራና መጻሕፍት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሥራ ጀመሩ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከ5000 የሚበልጡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትን በማጥናትና ካታሎግ በማድረግ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የብራና መጻሕፍት ካታሎግ ለሚያዘጋጁ ባለሞያዎች፣ የፓልግራፊ (paleography)፣ የተጻፉበትን ዘመን መወሰን (dating) እና ሌሎች ሥልጠናዎችን ሲሰጡ ኖረዋል፡፡ በእነዚህ ዘመናትም የተለያዩ የጥናት መጽሔቶች የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የግዕዝ ሀብታችንን በተመለከተ በታወቁ ዓለም ዓቀፍ የጥናት መጽሔቶች ላይ ከ200 በላይ የጥናት ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን አያሌ መጻሕፍትንም በአማርኛና በእንግሊዝኛ
አዘጋጅተዋል፡፡ አማርኛ መማሪያ ለጎልማሶች፣ አማርኛ መማሪያ ለጎልማሶችና ለመምህራን፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፣ ባሕረ ሐሳብ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ፣ ግዕዝ በአዲስ ዘዴ (ግዕዝ በቀላሉ)፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች በአማርኛ ካዘጋጇቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋም የጥናት ጽሑፎች አዘጋጅተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳነ ጥናት ባለሞያው የስነልሳን ሊቁ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በውጪው ዓለምም በግዕዝ ቋንቋ ላይ ላበረከቱት አስተዋጽዖ የማካርተር ፌሎውስ ፕሮግራም ጂኒየስ አዋርድ እና የኤድዋርድ ኡሌንዶርፍ ሜዳል ከካውንስል ኦፍ ዘ ብሪቲሽ አካዳሚ አግኝተዋል። (በመግቢያችን “መሄድ ቢሉሽ …” እንዳልነው፤ መሄድ ሲባል መሄድ ሁሉ አንድ አይደለምና የፕሮፌሰሩ ለየት ይላል።)
የኢትዮጰያ ሳይንስ አካዳሚም ከላይ በተዘረዘሩት በመስማማት የActa Aethiopica ጆርናል ኤዲተር የነበሩ መሆናቸውንም አስነብቧል።
ህልፈተ ህይወታቸውን በተመለከተም በእለቱ የተሰጡ አስተያየቶች በርካታ ሲሆኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ክብርት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሐዘን መግለጫ ተጠቃሽ ነው።
ምንም እንኳን “የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በታላቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ እና የግዕዝ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል” የሚለውን ዜና ተከትለን የሀዘን መግለጫውን ስናፈላልግ “በታላቁ የኢትዮጰያ ታሪክ ተመራማሪና የግእዝ [ቋንቋ] ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ የተሰማኝን ሀዘን እገልፃለሁ። ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ለኢትዮጵያ ታሪክ ምርምር በተለይም በግእዝ የተፃፉትን የግእዝ ሰነዶች በመመርመር፣ በመተርጎምም ሆነ በማሰናዳት ያደረጉት አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። ምን ግዜም የሚታወሱባቸውን ምርጥ ስራዎች ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ አበርክተው አልፈዋል። ለመላው ኢትዮጵያዊያንና ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ፤ ነፍስ ይማር።” በማለት በኦፊሺያል ትዊተር ገፃቸው ላይ ማስነበባቸውን እናገኛለን።
የፕ/ት ሳህለወርቅ መግለጫም እስካሁን ስለ ፕሮፌሰር ጌታቸው እያልን የመጣነውን ከማጠናከር አኳያ ግልፅ የሆነ ፋይዳ እንዳለው ግልፅ ስለሆነ የእሳቸውን ሀሳብ የሚያጠናክረውና አስቀድሞ የተሰጠን የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን “ፕሮፌሰር ጌታቸው የቋንቋ ሊቅ እንደሆነ አውቃለሁ።” የሚለውን አስተያየት ስንጨምርበት የፕሮፌሰሩን አካዳሚያዊ ሰብእና ጥሩ አድርጎ ይገልፃል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደው ዝም ተብሎ በቀላሉ “ምሁር” ተብለው የሚታለፉ ሰው አልነበሩም። “አንዱ በቃኝ” (“ደቂቀ እስጢፋኖስ” ብቻ ከአንድ መጽሐፍ በላይ የሆነ “መጻሕፍት” ነው ማለት ይቻላልና) የሚያስብሉ ስራዎችን ሲያበረክቱ የኖሩና ከምሁርም ከፍ ያሉ ምሁር (Guru) ነበሩ። እንደ ወዳጃቸውና ተገዳዳሪያቸው (ሁለቱም በእውቀት ጉዳይ ወዳጅነታቸውን ወደ ጎን በማድረግ አካዳሚያዊ በሆነ ጉዳይ የሚጠዛጠዙ) ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ሁሉ በቀላሉ የሚተኩ አይደሉም (መስፍን ባለመኖራቸው ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት እያየነው ስለሆነ ማለት ነው)። ምናልባትም ሁለቱ ያላቸውን ተመሳስሎና ልዩነት በሚገባና የሚመረምር አጥኚ ወደ ፊት ይመጣና ሁሉንም ያመለክተን ይሆናል በሚለው ካላለፍነው በስተቀር ሁለቱም የግንባር ስጋ፣ ሁለቱም ከአገራቸው በላይ የሚያስቀድሙት ምንም ነገር የሌላቸው፣ ሁለቱም ከፈረንጆቹ ይልቅ ወገኖቻቸው የሚበልጡባቸውና በሚያነቡት ቋንቋ የሚፅፉ፤ ሁለቱም ሙሉ ጊዜ፣ እውቀትና ጉልበታቸውን ለአገርና ህዝብ ጉዳይ የሰጡ፤ ሁለቱም ከጥናትና ምርምር ስራዎቻቸው ባለፈ ማህበረሰብን ለማንቃት፣ ዋልጌ አስተዳደርን ለመግራት በማሰብ በእለታዊ ጋዜጦችና መጽሔቶች፣ እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሀሳባቸውን ያለ ምንም ገደብና ፍርሀት የሚገልፁ፤ ሁለቱም የተዋጣላቸው ደራሲያን (ወደ ፊት የሚወጡ ስራዎቻቸውን ሳይጨምር ህይወታቸው እስካለፈበት እለት ድረስ መስፍን 19፤ ጌታቸው 20 መጻሕፍትን አሳትመዋል)፤ ሁለቱም ጊዜአቸውን ሙጥጥ አድርገው ጥግ ድረስ የተጠቀሙ፤ ሁለቱም ዘመንኛዎች (ኮንቴምፖረሪየስ)፤ ሁለቱም አብዝተው ለትውልድ የሚቆረቆሩና ወጣቱ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳይሆን የሚከላከሉና የተጣመመ ትውልድ እንዳይፈጠር የሚጥሩ (ይህን አቋማቸው በየስራዎቻቸው ላይ በጉልህ ይንፀባረቃል)፤ በ66ቱ ረሀብ ጉልህ የማጋለጥ ሚና የነበራቸው፤ ሁለቱም ከህዝብ እንጂ ከባለ ጊዜ ጋር ወግነው የማያውቁ፤ ሁለቱም ፈጣን መላሽ (ይህ ቀዳሚው የምሁር(ነት) ምልክት ወይም መገለጫ ነው)፤ ሁለቱም ህዝባዊ (የአደባባይ) ምሁር፤ ሁለቱም … ነበሩ (በመግቢያችን “መሄድ ቢሉሽ …” እንዳልነው፤ መሄድ ሲባል መሄድ ሁሉ አንድ አይደለምና የፕሮፌሰሮቹ ለየት ይላል።)። (ይህ ወደ ፊት እውነተኛውን “ያ ትውልድ” በሚል ርእሰ ጉዳይ ማጥናት ለሚፈልግ ጥሩ መነሻ እንደሚሆን አያጠራጥርም።)
የሁለቱን ፕሮፌሰሮች ተመሳስሎ ስንመለከት ነው እንግዲህ (የ91 ዓመቱ መስፍን ዓመት ሳይሞላቸው የተከተሏቸው) የ89ኙ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ወደ እማይቀረው መሄድ ሀዘኑ የሚሰማን፤ እንደ መስፍን ሁሉ የ”ማን ይተካቸዋል?” ሀሳብ የሚገባንና በተለይም ወደ ምሁራን፤ በተለይ በተለይም ወደ ህዝባዊ (የአደባባይ) ምሁርነት ሲመጣ፤ ወደ ምሁራን ደብር ብቅ ሲባል ነውና ጉዳዩን “ያሳስባል” ብለን ብንገልፀው አይገርምም።
ሌላው ስለ ፕሮፌሰር ጌታቸው የላቁ ስራዎቻቸውና ፋይዳቸው፤ ጥረት፣ ትጋትና ምሁራዊ ስኬት፤ ስለ የመሰራታቸው ምክንያትና አላማ በ”ደቂቀ እስጢፋኖስ” ጥልቅ፣ 15ኛውን ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ያገናኘ፤ የጊዜ፣ ስፍራና ትውልድን ያገናኘ ድልድይ የሆነ ስራቸው ላይ በ”ቀዳሚ ቃል” ስር የሰፈረውን የፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለን ሰፋ ያለ አስተያየት፤ እንዲሁም እራሳቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው በዚሁ መጽሐፍ “መቅድም” ስር ያሰፈሩትን አስተያየትና ሀሳቦች ማየት ተገቢ ይሆናል። ወደ “አረጉ እንጂ ሞቱ አትበሉ” የርእሳችን አጋዥ የሆነው ሀሳብ እንመለስ።
መቸም “አረገ እንጂ ሞተ አትበሉ” የሚለው የሚነገርበት ምክንያት፣ አውዱና የሚነገርለትን ሰው በተመለከተ ይህን ጽሑፍ በሚያነብ ሰው ደረጃ አያውቅም ብሎ እዚህ ለማብራራት አይሞከርም። በመሆኑም እዚህ ማለት የሚገባን አባባሉን ለምን ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ለመግለፅ ተጠቀምንበት፣ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚለውን ነው።
የዋዳጅ አድናቂዎቻቸውን ያህል ባይበዙም ስራዎቻቸውን የሚያጣጥሉ (በተለይ የታሪክ ግድፈት ሲፈፀም ዝም ብለው አለማየትና አለማለፋቸውን ተከትሎ) ተቃዋሚዎች ያላጡት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን አረጉ እንጂ … ስንል አባባሉ በቀጥታ የሚወስደን ወደ “ምን ምን ስራዎችን ቢሰሩ ነው ለዚህ አይነቱ ከበድና ጠንከር ያለ የሰማእትነት መገለጫ የበቁት?” እሚለው አጥንትና ጉልጥምት ያለው ጥያቄ ነውና ከዚህ በኋላ በዚሁ ለይ አተኩረን እንነጋገራለን፤ ከ”ደቂቀ እስጢፋኖስ”ም እንጀምራለን።
ደቂቀ እስጢፋኖስ (“የእስጢፋኖስ ልጅ”፣ “እስጢፋኖሳዊያን” ማለት መሆኑ እንዳለ ሆኖ) “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስርዓት ይከበር” ብለው በ15ኛው ክፍለ-ዘመን አዲስ ሀሳብ ይዘው የተነሱ የሀይማኖት “አህይዎና ተሀድሶ” አራማጆች የነበሩትን የሚመለከት የ15 እና 16ኛው ክፍለ ዘመን የአገራችን ታሪክ ነው። ወደ ዝርዝሩ መግባት ያለብን ባለመሆኑ ፕሮፌሰሩ በዚህ መጽሐፍ (ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትና ከቋንቋ ሊቅነታቸው ባለፈ ሁለገብነታቸውን በሚገባ ያሳዩበት ስራቸው) የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ደረጃ የት ድረስ እንደነበር ያሳዩበትና ከሁሉ ቀዳሚነቷን የመሰከሩበት ስራቸው ሲሆን በተለይም ያንን የሩቁን ዘመን ወደ እዚህ፤ አሁኑ ዘመን በማምጣት የትልውልድ ክፍተትን መሙላታቸው ብቻ እንኳን ለ”አረገ እንጂ ሞተ አትበሉ” ቢያበቃቸው ቢያንሳቸው እንጂ መላእክ የማድረግ እሳቤ አይሆንም። በተለይ በዚሁ መጽሐፍ መግቢያቸው ላይ ገልፀውት እንደሚነበበው ለአሁኑ ትውልድ፤ ከታሪኩ ለተፋታውና ከአገር በቀል እውቀት ለተጣላው ለወጣቱ ያሳዩት መቆርቆና ይህንንም ለመድፈን ወደ እዚህ ከባድ ስራ ውስጥ መግባታቸው ሲታከልበት የዜግነትም እንበለው የምሁርነት ኃላፊነትና ግዴታቸውን በመወጣታቸው፣ አሁንም እንድገመውና ለ”አረገ እንጂ ሞተ አትበሉ” ቢያበቃቸው ቢያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም (ወዳጃቸው ፕ/ር መስፍንን ጨምሮ)። ካስፈለገ ይህንን መሰሉን ህዝብን የማገልገል ብዕራዊ ተጋድሎ በባለ ቅኔው አንደበት ምን እንደ ተባለ፤ ሎሬቱ ምን ሲል እንዳብራራው ኤርሚያስ ባሰናዳው “እሳትና ውሃ” የመጨረሻዎቹን ገፆች መመልከት ጠቃሚ ነው። (ለ”አረገ እንጂ ሞተ አትበሉ” ማጠናከሪያ ከበደ፣ ሀዲስ፣ ገብረ ህይወት፣ በአሉ፣ አቤ፣ ዳኛቸው፣ ጥላሁን ወዘተርፈ እያሉ መጨመር ይቻላል።)
ለባለቤታቸው (ወ/ሮ ምሥራቅ) ልዩ ፍቅር፣ ክብርና አድናቆት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ታሪክ ላይ፤ በቀብር ስነ ስርዓት ላይ በሚነበብ የህይወት ታሪክ አነባበብ አቀራረብና ስልት ተጠቅመን “5000 የኢትዮጵያ ማንስክሪፕት አዘጋጅተዋል፤ አማርኛ፣ ግእዝ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ በእብራይስጥ፣ ላቲን፣ ግሪክ፣ ጀርመን፣ ኮፕቲክ እና የሱርስት (የሶሪያ) ቋንቋዎች ምርምር አድርገዋል፤ የበርካታ ምሁራንና ተቋማት ጥናትና ምርምር ስራዎች አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፤ የአሜሪካዊውን ጸሀፊ፣ ባለቅኔ፣ ስራ ፈጣሪ፣ አሳታሚ እና አስተማሪ ማርክ ትዌንን ስራዎች ተርጉመዋል (የመጀመሪያ የትርጉም ስራቸው ነው)፤ የእውቅና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች (ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ አንድ አፍታ ላውጋህ፣ የአባ ባህሪ ድርሰቶች፣ ባህረ ሀሳብ፣ ስለግእዝ የተሰበሰቡ ታሪኮች ወዘተ) አምራች፤ MacArthur የተባለውን አለም አቀፍ ሽልማት በማግኘት ከአፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ነበሩ።” የሚለውን ስናክልበት፤ የርእዮተ አለም አቋማቸውን በተመለከተም “በደርግ ጊዜ በነበራቸው የፖለቲካ “መስመር” ምክንያት የፀጥታ ሀይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ ሲጠይቋቸው አሻፈረኝ በማለታቸው (እና በመታኮሳቸው) በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ከቆሰሉ በኋላ እንግሊዝ አገር ሄደው እንዲታከሙ ቢደረግም ከዚያን ጊዜ ጀምሩ የሚንቀሳቀሱት በዌል ቼር ነበር።” ስንደርብበት ጌች በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ እንዳለፉ፤ የአልገዛም ባይነት ጠንካራ ሰብእና እንዳላቸው ወዘተ ሁሉ እንረዳለን።
በመጨረሻም፣ ጁን 10፣ 2021 (ሰኔ 4 2013 ዓ.ም) የአረፉትና ጁን 18፣ 2021 በአገረ አሜሪካ ቅዱስ ዮሐንስ ገዳም ስርአተ ቀብራቸው የተፈፀመው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እሳቸው እራሳቸው በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው “ከሞትኩ በኋላ ሰው ላይ ክፋት የማይሰራ ሰው ብለው ቢያስቡኝ ይበቃኛል።” ቢሉም እኛ ከዛ አለፍ በማለታችን የውለታ ጉዳይ ሆኖብን ነውና ይቅርታ እጠየቅን ከወራት በፊት የፕሮፌሰር መስፍንን ሞት የሰሙት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ትልቅ ሰው ነው ያጣነው፤ ምትኩን እንኳን ተካልን ማለት ሳይቻለን ነው ድንገት የተቀማነው።” ብለው ነበር። ይህ ጸሐፊም ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ይህንኑ እሳቸው ስለወዳጃቸው ሲባል የገለፁትን መልሶ ወደ እሳቸው እያዋለ፤ “ፕ/ር ጌታቸው በሥራዎቻቸውና የአገር ፍቅር ስሜታቸው ከሕይወት በኋላም ይኖራሉ።” የሚለውን የብዙዎቹን፤ እንዲሁም፣ “ፕሮፍ ጌታቸው በዚህ መጽሐፍ [ደቂቀ እስጪፋኖስ] አማካኝነት ላሳዩን intellectual courage ሁሌም ሳመሰግናቸው እኖራለሁ።” ያለውን የብሩህ ዓለምነህ አስተያየት እየተጋራ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን በማለት ይሰናበታል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013