የሐዋሣ ከተማ በ1952 ዓ.ም በቀዳማዊ ንጉሠ ነግሥት አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተመሠረተች ሲሆን አመሠራረቷም ከአካባቢው ልምላሜ ጋር ተያይዞ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለመዘርጋት ታሣቢ ያደረገ እንደነበረ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ 500 ሺ ሰዎች በላይ ህዝብ እንደሚኖሩባት የከተማዋ አሃዛዊ መረጃዎች ይጠቁማል፡፡
የሀዋሳ ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው ከሀዋሣ ሐይቅ ሲሆን ቃሉም ከሲዳምኛ ቋንቋ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ሀዋሣ›› ማለት አቻ የአማርኛ ትርጉሙ ‹ሰፊ የውሃ አካል› ማለት ሲሆን ከተማዋ ይህንን አሁን የምትጠራበትን ስያሜ ከማግኘቷ በፊት ‹አዳሬ› እየተባለች ትጠራ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ‹አዳሬ› ም በሲዳምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ‹የግጦሽ ቦታ› ማለት እንደሆነ ይታመናል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በሐዋሳ በርካታ ህዝብ የሚኖርባት ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም አዳዲስ ግንባታዎች ከሚከናወንባቸው ከተሞች በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡
በዛሬው ዕትማችን የሀዋሳ ከተማ አጠቃላይ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ጋር ያደረግነው ቆይታ እነሆ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ከተማ መስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ዓብይ ትኩረቶች ምንድን ነበሩ?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– የከተማ አስተዳደሩ ዓመቱን ሙሉ በየዘርፉ ውጤታማ ሥራዎችን ሰርቷል:: ከተማው ሠላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን በትኩረት ሰርተናል:: ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ ሆናለች:: ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር፣ የማደግና የመልማት ጥያቄዎች እልባት ለመስጠት አበክሮ ሲሠራ ቆይቷል:: በዚህም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍና በበጀት ዓመቱ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የመሰረተ ልማት፣ የጤና ጣቢያዎች፣ አስፋልትና የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገዶች፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያፋጥኑ መሠረተ ልማቶች በብዛትና በጥራት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል::
ከተሞች በዘመናዊና በትክክለኛው መንገድ ተመርተው ሲያድጉ ትልቅ የምጣኔ ሃብት እና የስልጣኔ ምንጭ የመሆን ዕድል እንዳላቸው በሳይንስ የሚታመን እውነታ ነው:: ሐዋሳ ከተማም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለእድገቷ ሲሠራ ቆይቷል:: በተጨማሪም በዙሪያዋ ያሉ የወረዳ ከተሞችን አጎራባች ቀበሌዎች ወደ ከተማነት ለማደግ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የሚገጥማቸውን የዘመናዊነትና የአስተዳደር ችግሮች ለማቃለል የሐዋሳ ከተማ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የቀሰምናቸውን ልምዶች በማካፈል ብሎም ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነትን እየተወጣን ነው::
አዲስ ዘመን፡– ከገቢ አሰባሰብ አኳያ አበረታች ነበር የሚያስብለው የተለየ ሥራ ምንድን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– ከተማ አስተዳደሩ ከምንም በላይ ባለፉት 11 ወራት ውስጥ ከተማዋ የተረጋጋች እንድትሆን፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖርና ሁሉም የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ሲሠራ ቆይቷል:: በተጨማሪም የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ነበር:: በገቢ ደረጃም በ2013 በጀት ዓመት በ 10 ወር ብቻ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ 380 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው::
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉም ሰፋፊ የሥራ ዕድሎች መፍጠር ተችሏል:: በዓመቱ ለ 22 ሺ 300 ዜጎች ሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቦ የነበረ ሲሆን ይህንን በአስር ወር መድረስ ተችሏል:: ሐዋሳ ከተማ በንፅፅር ሲታይ በርካታ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላትና ለብዙ ከተሞች መመስረትም እንደ መነሻ እያለገለች ነው:: ሐዋሳ ከተማን መሠረት አድርገው በቅርቡ ለሚመሰረቱ አዳዲስ ከተሞች ድጋፍ እያደረገች ሲሆን ይህ ደግሞ የሕብረተሰቡን ትስስር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያፋጥን ነው::
አዲስ ዘመን፡– ሐዋሳ ቀደም ሲል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ስጋት መነሻ አሁንም ተመሣሣይ ችግር ይኖራል የሚል ስጋት ያላቸው አካላት አሉ:: እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– በአሁኑ ወቅት ሐዋሳ ውስጥ ምንም ዓይነት ስጋት የለም ፍፁም ሠላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ ነው ያለው:: ከተማዋን ለሁሉም የምትመች እናደርጋታለን:: ያለፈው ክስተት እንደ ሀገርም መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ቢሆንም አይደገምም:: ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለስ ብቻ ሳይሆን ከነበረበው ሁኔታ በብዙ እጥፍ ተሽላ ርቃ ሄዳለች:: ኢንቨስትመንት እንዲያንሠራራ ከተማዋን የማስተዋወቅና ባለሃብቶችን የመሳቢያ መንገዶች ላይ ትኩረት አድርገን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውነናል:: ተጨማሪ እውቀትና ሃብት ወደ ከተማዋ እንዲመጣ ስንሠራ ቆይተናል::
አዲስ ዘመን፡– የከተማዋ ኢንቨስትመንት እንዲያንሰራራ ምን ተሠራ?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– ከተማ ውስጥ ያሉ ባለሃብቶች ብዙ ናቸው፤ ሌሎችንም ለመሳብ ደግሞ ለዚህ በቂ ዝግጅት አድርገናል:: በየመድረኩ ብዙ ውይይት አካሂደናል:: ለኢንቨስትመንት የሚውል የመሬት ልየታ ጨርሰናል:: በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ዶክመንተሪዎችን ሰርተናል:: ከዚህ መነሻነትም ወደከተማዋ ለመጡ ባለሀብቶች በቅርቡ የሚተላለፉ ሰፋፊ መሬቶች አሉን::
ለምሳሌ በሀይቅ ዳርና ሃይቅ ማዶ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችና ወተር ፓርኮች እንዲስፋፉ ዝግጅት አድርገናል:: በእነዚህ አካባቢዎች ምቹ ቦታዎች አሉ:: ከአሁን በኋላ ለከተማዋ ትልቅ ትርጉም ያላቸውንም ኢንቨስትመንቶች ነው የምናስገባው:: ሐዋሳን በጣም ውድ እና የተመቸች እንጂ፤ ርካሽ ከተማ አናደርጋትም:: ሀይቅ ዳርን የማልማት ሥራ አጠናቀናል:: ሃይቅ ዳር የማልማት ፕላኑንም በተመሳሳይ መልኩ ጨርሰናል:: ከአሞራ ገደል እስከ ጥቁር ውሃ አምስት ኪሎ ሜትር የማልማት ሥራውን አጠናቀናል በቅርቡ ወደ ሥራ እንገባለን:: በዚህ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች እንዲመጡ እየሠራን ነው::
ከሃይቅ ማዶ ያለውን በማልማትና የውሃ ትራንስፖርት ለመጀመር ሁለቱ መንገዶች እንዲገናኙ መሥራት ያስፈልጋል፤ በሌላ በኩልም ከተማዋ እንድትሰፋ መሰራት አለበት:: ይህንን ለማድረግ የሚያስችለውን የከተማውን የ10 ዓመት እቅድ አጠናቀናል::
በጠቅላላው አሁን ላይ በከተማዋ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት እያንሰራራ ነው:: በየቀኑ አዳዲስ አሰራሮችና ሃሳቦች እየገቡ ነው::
አዲስ ዘመን፡– ኢንቨስትመንቱ በሃይቁ ዳር ብቻ የተወሰነ ነው ወይስ ወደ ሐዋሳ ሃይቅ ውስጥም ይገባል?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– በእኛ እዚህ ደረጃ ላይ አልደረስንም እንጂ መጠቀም ይቻላል:: በሌላው ዓለም ባህር ውስጥም ኢንቨስት እየተደረገ ነው:: እኛ ሀገር ለብዝሃ ሕይወት እና ተፈጥሮ ሃብት ትኩረት መስጠት ብሎም ጠብቆ መጠቀም ብዙም አልተለመደም:: እውነታው ግን ተፈጥሮን በጠበቅን ቁጥር ነው የምንጠቀመው:: ስለዚህ ተፈጥሮን ጠብቀን ሃይቁ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይቻላል:: ባደጉት አገራት ደረጃ ይህ እየተሰራበት ነው:: እኛ ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ እዚህ ላይ የተለየ ነገር የለም::
አሁን እያሰብን ያለነው ሃይቁን ዙሪያውን ማልማትና ምቹ ማድረግ፣ ከከተማዋ የሚወጣውን ቆሻሻ ወደ ሃይቁ እንዳይገባ ማድረግ እና በርካታ ‹‹ፖንዶችን›› አዘጋጅተን ውሃ አጣርተን መጠቀም ነው የምንፈልገው:: ፍቅር ሃይቅ አካባቢ ዓሳ ከማጥመድ ውጭ ሌላ ሥራ የለም:: በመሆኑም እዚህ አካባቢ ወደብ ሰርተን የውሃ ላይ ትራንስፖርት ለመጀመር አስበናል:: ከፍቅር ሃይቅ እስከ ሌላኛው ማዶ ድረስ የጀልባ ትራንስፖርት መጀመር አለበት ብለንም እየሰራን ነው:: በእቅዳችን መሰረት እጅግ ዘመናዊ የውሃ ትራንስፖርት ወደ ሥራ እናስገባለን:: ባደጉት ሀገራት ውሃ ውስጥ ሆቴሎች እየተገነቡ ነው:: እኛም ዓቅማችን እዛ ላይ ሲደርስ ውሃው ላይ የምንፈልገውን ከመሥራት የሚያግደን አይኖርም::
አዲስ ዘመን፡– ሐዋሳን ከበው የተቀመጡ ተራሮች ለከተማዋ እድገትና ውበት እንዴት ለመጠቀም አስባችኋል?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– ታቦር ተራራን ጨምሮ በዙሪያው ከአሞራ ገደል እስከ ጥቁር ውሃ ድረስ ያለውን በደንብ እናለማለን:: መንገዱ ለእግር ጉዞ እና ለሳይክል ምቹ እንዲሆን ይደረጋል:: የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት አካባቢ እንዲሆንም ይሰራል:: ዕቅዳችን ሐዋሳን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ በመሆኑ የከተማዋን ፀጥታ አረጋግጠንና የቱሪዝም መዳረሻችን አስፍተን ለመገኘት በደንብ አስበንበታል:: ትልልቅ ሃሳቦችን እያመነጨን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እየገነባን ነው የምንጓዘው::
ቢቻል ሀዋሳ ሃይቅን አቋርጦ የሚያልፍ ድልድይ ለመገንባት ሀሳብ አለ:: ይህንን ለማድረግ ግን በከተማ መስተዳድሩ አቅም ብቻ የሚከናወንና የሚወሰን አይደለም:: በመሆኑም የፌደራል መንግስት እገዛ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ከሃይቅ ማዶ ሌላ ከተማ የመገንባት ሥራ ተጀምሯል:: በተለይም በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶች እየተከናወኑ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዓላማቸው ሃዋሳን ውብ፣ ምቹና ትልቅ ከተማ ማድረግ ሲሆን የተሰጠን የሥራ መመሪያም ይህንኑ የሚያመላክት ነው:: እኛም በዚህ ላይ እየሠራን እንገኛለን:: በዚህ በጀት ዓመት ብቻ በ 31 መንደሮች የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ የመስራት߹ በ25 መንደሮች የመብራት አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ መሰረተ ልማቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው:: እነዚህ ከተሟሉ ደግሞ ዕድገትን የሚከለክል የለም:: ሃዋሳ ከተማ የምታድገውም ብቻዋን ሳይሆን ወንዶ ገነት እና ባቅራቢያዋ ያሉ ሌሎች ከተሞችን ይዛ ነው::
አዲስ ዘመን፡– በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ እንቅስቃሴና ወጣቶች የሚበዛባት ከመሆኑ አንጻር የሚሠራው ሥራ የተናበበ ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– ህዝብ እየጨመረ አልፎ አልፎም ወጣቶች አላስፈላጊ ቦታ እየዋሉ ነው:: እንደ ከተማ የወጣቶችን ሥነ ምግባር የማነፅ አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ለማድረግ በስምንቱም ክፍለ ከተሞች ሥብዕና መገንቢያ ማዕከላት እየተገነቡ ነው:: በሌላ በኩልም ወጣቶች እንዲማሩና ራሳቸውን እንዲለውጡ ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሠራን ነው::
አዲስ ዘመን፡– ሐዋሳ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ይነሳልና ይህ ለከተማዋ ዕድገት ስጋት አይሆንም?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– ከተማ ውስጥ ህዝብ እየጨመረ ነው:: አንደኛው የወሊድ ምጣኔ ከፍ ማለት እንዲሁም ከሌሎች ቦታዎችና አጎራባች ከተሞች ወደ ከተማዋ በሚፈልሱት ሰዎች ቁጥር መጨመር ለጎዳና ተዳዳሪዎች መበራከት አስተዋጽኦ አድርጓል:: ነገር ግን በቅርቡ 6 መቶ ያህሉን ከጎዳና በማንሳትና ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ የሚገቡ ይሆናል:: ከደቡብ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማና ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ ሐዋሳ በየቀኑ የሚመጡ በርካታ ሰዎች ስላሉ ጫናው ከፍተኛ ቢሆንም ችግሮቹን ለማቃለል እንደ ከተማ ብዙ መሥራት እንዳለብን እንገነዘባለን:: እነዚህ ሰዎች ከጎዳና ተነስተው የከተማዋ ህጋዊ ነዋሪ የሚሆኑበት መንገድ እየሰራን እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡– ቀደም ሲል የሐዋሳ ከተማ ካቢኔዎች የነበሩት አብዛኞቹ ተቀይረዋል ይህ እንደ ከተማ ያመጣው ለውጥ እንዲሁም ለመቀየራቸው ምክንያቱ ምንድን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– በየጊዜው አመራሮችን እየፈተሹ ክፍተቶችን እየሞሉ ከዚህ ውጪ የሆኑትን ደግሞ ተልዕኮና አገልግሎትን የሚፈፅም ብቃት ባላቸው የመተካቱ ስራ እየተሰራ ነው:: ምክንያቱም ከተሞችን ለመምራት ትልቅ አቅምና ትጋት ስለሚያስፈልግ ነው:: ቀደም ሲል ከተማዋን የሚመሩት የተቻላቸውን አድርገዋል:: ከእኔ የተሻለ ተልዕኮ፣ አገልግሎት፣ አመራርና ሥምሪት የሚቀበል ካለ መቀየር የተለመደ ነው:: ወደፊትም ሪፎርሙ ይቀጥላል::
አዲስ ዘመን፡– በየጊዜው አመራር መቀየሩ በሥራ ላይ ተፅዕኖ የለውም?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– እውነት ነው:: እኛ ኃላፊነትም አለብን:: የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ሲመሰረት እንደ ጥያቄ ሲነሳ የነበረው “ከንቲባዎች ተረጋግተው ሥራ እንዲሰሩ እየተደረገ አይደለም”:: ይህ ማለት አንድ ከንቲባ የተወሰነ ጊዜ አይቶ ከተማዋን አውቆ ተረጋግቶ ሊሠራ ሲል መሄድ የለበትም:: የተወሰነ ጊዜ ያስፈልገዋል:: ተብሏል፡፡ እኔም በግሌ የማምነው አንድ ከንቲባ የተወሰነ የተረጋጋ ጊዜ ኖሮት መስራት አለበት፤ ምክንያቱም ሥራው አድካሚ፤ ብዙ ጥረትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው:: አንድ ከተማ ውስጥ 500ሺ የሚኖር ከሆነ ጥያቄ የእነዚህ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም:: ብዙ ባለድርሻ አካላት አሉ::
ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የተለመደው በአንድ ቦታ መኖር ፍላጎት አለ:: ግን መሪነት አገልግሎት መስጠት ከሆነ አንዴ አስተማሪ ሌላ ጊዜ ከንቲባ ሆኖ በተለያየ ሞያና ልምድ ማገልገል ይገባል:: ከተማ እና ሀገር የሚያድገው በቅብብሎሽ ነው:: ይህን በሚገባ መገንዘብ ይገባል:: እንደ መርህ ግን ከንቲባዎች ተረጋግተው እና የጊዜ ገደብ ኖሯቸው ቢሰሩ ብዙ ነገር ማስተካከል ይችላሉ፤ ብዙ ልምድም ያገኛሉ:: በዚያው ልክ ደግሞ አንድ ሰው ከንቲባ ተደርጎ ሲሾም ከተማን የሚያውቅ፣ ከተማን በደንብ የሚረዳ መሆኑ ተጠንቶ መሆን አለበት:: በሌላ ጎኑ ደግሞ ሁሌም ባለስልጣን ነን ብሎ ማሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ መለመድ የለበትም::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሐዋሳ ከንቲባ ነዎት:: ሐዋሳ ደግሞ የሲዳማ ክልል፣ የደቡብ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዋና ከተማ እንዲሁም የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መናኸሪያ መሆኗ ለአመራር አያስቸግርም?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡- አንተ ከተናገርከው በላይ ብዙ ነገሮች አሉ:: ከተማዋ በጣምና ብዙ ፍላጎቶች የሚንፀባረቁባት ናት:: የሁለት ክልል መንግስታትና ብዙ ማህበረሰቦች ይኖሩባታል:: ስለዚህ የመሪነት ትልቁ ፈተናም እዚህ ላይ ነው:: እነዚህን አቻችሎ እና ፍላጎቶችን በሚገባ አስማምቶ መምራት ያስፈልጋል:: እኔ እነዚህን ነገሮች በአግባቡ በመያዝና ፍላጎቶችን አስተሳስሬ ለመምራት እየሰራሁ ነው::
እኔም እዚህ ከተማ 17 ዓመት ስለኖርኩና ሁኔታዎችን በሚገባ ስለምረዳ ነገሮችን ቀላል አድርጎልኛል:: ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ስለነበርኩም የራሱ የሆነ ልምድ አግኝቼበታለሁ:: በእርግጥ እነዚህ ነገሮችን ወደ ህዝብ ስንወስዳቸው ህዝቡ በጣም ጥሩ ህዝብ ከመሆኑም በላይ ከጎናችን ከመቆም ሌላ አጀንዳ የለውም:: ከተማችንም ሠላም ሆኖ የሚቀጥል ነው:: ሃዋሳን ከዚህ የተሻለች ማድረግም እንችላለን ብዬ አስባለሁ::
አዲስ ዘመን፡– ሐዋሳ ላይ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ በርካታ ባዶ ቦታዎች አሉ:: በዚህ ላይ ምን እየተሠራ ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– በከተማዋ ዙሪያ በህገ ወጥ መንገድ ቦታን እየሰፉ ያሉ በጣም ብዙ ቦታዎች አሉ:: በዚህ ዓመት ግን ህገ ወጥ የመሬት ወረራን በደንብ ተከላክለናል:: ከዚህ በፊት በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡትን ምን እናድርግ የሚለው ደግሞ ውሳኔ የሚጠይቅ በመሆኑ ወደፊት መልስ ያገኛሉ:: በከተማዋ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ሰፋፊ መሬቶችና በህገ ወጥ መንገድ መሬት ወረራ አሁን ላይ የጎላ ችግር አይደለም::
በሀዋሳ ዙሪያ 12 የገጠር ቀበሌዎች አሉ:: ይህም አርሶ አደሮች ለቤት መስሪያ ቦታ ፈላጊዎች ሲሸጡ ቆይተዋል:: በዚህ ዓመት በዚህ ህገ ወጥነትን በሚገባ ስንከላከል ነበር:: በቦታው ላይ ካሉ ነባር አርሶ አደሮች በተጨማሪ ሌሎች ከአርሶ አደር መሬት ገዝተው ቤት እንዳይሠሩም ክልከላ ተደርጓል:: ህግን ማስከበርና በህግ መመራት ግዴታ ነው:: ህገ ወጥነት ላይ ከተማው አይደራደርም:: በቀጣይ ህጋዊነት ብቻ እንዲኖር አበክረን እየሠራን ነው::
ሀዋሳ ውስጥ ለዓመታት መሬት አጥረው ያስቀመጡ በመኖራቸው 85 ሄክታር መሬት ያለ ሥራ ተቀምጧል:: ከዚህ ውስጥ ብዙ መሬት አስመልሰናል:: ችግሮችን ለማወቅና ለመፍትሄ ባለሃብቶችን ጠርተን አወያይተናል:: መሬት ውስን ሃብት ከመሆኑም በተጨማሪ ያለ ሥራ ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች የከተማ ውበት እየተበላሸ በመሆኑ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል:: መሬት የሀገር ሃብት መሆኑን በመረዳት ኢንቨስትመንት መፋጠን እንዳለበት ከመግባባት ላይ ተደርሷል:: በእርግጥ እኛ መሬት መንጠቅ ትክክል ነው ብለን አናምንም:: ባለሃብቱም ኃላፊነት አለበት:: ኢንቨስት ማድረግ አለባቸው:: ይህ ካልሆነ ግን ከተማ አስተዳደሩ በራሱ መንገድ ይሄዳል::
ለብዙ ጊዜ ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ባለሃብቶች ተጨባጭ ለውጥ የሚያሳይ ሥራ እንዲሰሩ የስድስት ወራት ጊዜ ተሰጥቷል:: በእነዚህ ወራቶች ውስጥ አመርቂ ሥራ ማከናወን ያልቻሉትን መሬቱን ነጥቀን ለመሬት ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ ተወስኗል:: በሁሉም አቅጣጫዎች ከተማዋ ተፈጥሮዋ ተጠብቆ ለም እና ውብ ሆና እንድትቀጥል እየሠራን ነው:: ራዕያችን ሐዋሳ የኢትዮጵያ ከተሞች የፍሰሃ እና የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ ነው:: በነፃነት ሰርተው የሚንቀሳቀሱባት እና የሚኖሩባት ከተማ እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ የሐዋሳ ከተማ ተስፋ እና ስጋቶች ምንድን ናቸው ብለው ያስባሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– አካባቢው በተፈጥሮ የታደለና ውብ ነው:: በባህሪ ኢንቨስትመንትን የሚስብ ነው:: በንጽፅር ጥሩ መሰረት ልማት አላት:: ሐዋሳ የፍቅር፣ ሠላም እና አንድነት ከተማ ብሎ ነው የሚረዷት:: ይህ ለእኛ ክብር ነው:: ይህን መለያ ይዘን ሐዋሳን ከፍ ማድረግ ስለሚያስፈልግ አዳዲስ ሃሳቦችንና አሠራሮችን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ተረድተናል:: በሚቀጥለው ዓመት በአዲስ ሪፎርም፣ ዕቅድ፣ ንቅናቄ፣ አሠራርና አካሄዶች ይኖሩናል:: የተወሰነ ፈተና የሚሆንብን ሃብት ነው:: ከተማው በራሱ ገቢ ነው የሚተዳደረው ስለዚህ ነዋሪዎቿ ባለሃብቶች መተባበር አለባቸው:: ሐዋሳን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት ማድረግ ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሥም አመሰግናለሁ::
ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ፡– እኔም የዝግጅት ክፍላችሁ እዚህ ድረስ መጥቶ ከተማዋን አስመልክቶ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምስጋና አቀርባለሁ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013