ዓለማችን ባለፉት 200 ዓመታት በተፈጠሩ የተዛቡ አመለካከቶች እና አመለካከቶቹን በህዝቦች ላይ ለመጫን በተፈጠሩ ሴራዎች እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል ተገድዳለች። የሴራዎቹ ሰለባ የሆኑ የዓለም ሀገራት ህዝቦችም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ማቆሚያ በሌላቸው የተንሰላሰሉ ሴራዎች ከፍ ባለ ግራ መጋባት ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። ይህ ግራ መጋባት ደግሞ ዕጣ ፈንታቸውን እንዳይወስኑ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል።
ከዚህ ድርጊት የተነሳም የነዚህ ሀገራት ህዝቦች የረሀብ፣ የድንቁርና ፣ ያለመግባባትና የግጭት ትርክት መነሻ ለመሆን ተገደዋል። ትርክቶቹ እነዚህ ሕዝቦች በብዙ ሴራ የተፈጠሩና ብዙ ዋጋ ያስከፈሏቸውንና እያስከፈሏቸው ያሉ ችግሮች ባለቤት እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሆኑ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል።
እነዚህ ህዝቦች ላልፈጠሯቸውና ባለቤቶቹ እነማን እንደሆኑ በአግባቡ ላላወቋቸው ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ የሄዱባቸውም መንገዶችም ቢሆኑ ተጨማሪ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጡላቸው አልቻሉም። ለችግሮቻቸው መፍትሄ ማምጣት አለመቻላቸው ደግሞ ሌላ መፍትህ አፈላላጊ አካል እንዲቃርሙ አድርጓቸዋል።
አሳዛኙ ዓለም አቀፋዊ እውነታ እነዚህ ህዝቦች ከገቡበት ግራ መጋባት የተነሳ መፍትሄ ፍለጋ የችግሮቻቸው ባለቤት ወደሆኑት አካላት የመሄዳቸው፣ ከችግሮቹ ባለቤቶች የመፍትሄ ሀሳብ የመጠበቃቸው እውነታ ነው። በዚህም ከመጀመሪያው ስህተታቸው / የችግሩ ባለቤት እኛ ነን ብለው ከመቀበላቸው / የበለጠ እና የከፋ ስህተት ለመስራት ተገደዋል።
ከዚህም የተነሳ የነዚህ ሀገራት ህዝቦች የረሀብ፣ የድንቁርና፣ ያለመግባባትና የግጭት ማእከል ለመሆን ተገደዋል። በታሪክ አጋጣሚ የችግሩን ባለቤቶች አውቀው ከችግሮቻቸው ለመውጣት ያደረጓቸው ጥረቶችም ብርቅዬ መሪዎቻቸውን በባንዳዎች አማካኝነት በህይወት እንዲያጡ አድርጓቸዋል።
ይህን ማድረግ ባልተቻለበት ሁኔታም የነዚሁ ሀገራት ሕዝቦች ዓይን ለመክፈት ጥረት የሚያደርጉ መሪዎችን ከማጥላላት ባለፈ በባንዳዎችና በባንዳነት እውቅና ባገኙ የገዛ ዜጎቻቸው በኩል የተለያዩ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን በመክፈት ዐይን የመግለጥ ተልእኮቻቸው ውጤት እንዳያመጣ ላለፉት 60 እና ከዛም በላይ አመታት ሰፊ ስራዎችን ሰርተዋል ፣አሁንም እየሰሩ ነው።
የነዚህ የተዛቡ አመለካከቶች ባለቤት የሆኑ አካላት ዛሬም ቢሆን “ ብሄራዊ ጥቅም “ በሚል ዘመናዊ ቋንቋ ጀርባ ሆነው የቀደመውን ዘመን ያልተገባ ጥቅም ለማስቀጠል ከፍ ባለ የሴራ ፖለቲካ ዳግም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያለይሉኝታ ወገባቸውን ይዘው ሲሞግቱ ይታያሉ።
ራሳቸው ላልታመኑላቸው ሰብአዊ እና ማህበራዊ አሴቶች ጠበቃ የመሆን ድፍረት ተሞልተው ፤ እኛ የምንለውን እንጂ የምናደርገውን አይመለከታችሁም በሚል ሞራል አልባ እሳቤ ተመልሰው አዲስ የቅኝ አገዛዝ ስርአት ለመፍጠር በእነዚህ ህዝቦች ላይ ሁለንተናዊ ጫናዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ይህ ፍጹም ራስ ወዳድነት የተሞላበት ፣ ህዝቦችን ፍትሀዊ ባልሆነ የመመዘኛ ሥርአት ግራ በማጋባት ፤ ግራ ከመጋባታቸው በሚመነጭ መከራና ስቃይ ፤እንግልትና ተስፋ መቁረጥ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ አስተሳሰብ ባለንበት ዘመን ሊያበቃ ይገባል። ዘመናዊነታችን ፤ መሰልጠናችንም ከዚህ ሊጀምር ይገባል።
እነዚህ ህዝቦች በቅኝ አገዛዝ ዘመን ያካበቷቸው የህይወት ተሞክሮዎቻቸው ከማንም በላይ እኛ እናውቅልሀለን የሚለው የትናንት የሞግዚትነት አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ያስከፈላቸውን ዋጋ ፤ ከከፈሉት ዋጋ በላይም አስተሳሰቡ የፈጠረው የማንነት ግራ መጋባት እና የጠባቂነት መንፈስ ዛሬ ድረስ ዋጋ እያስከፈላቸው እንዳለ ይረዳሉ።
ይህንን እውነታ ለመለወጥ እነዚህ ህዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳችው ለመወሰን የጀመሩት መራራ ትግል ሊያስከፍላቸው የሚችለው ዋጋ የቱንም ያህል የከበደ ቢሆን አስካሁን ከከፈሉት ሊበልጥ እንደማይችል ይታመናል። ትግሉ በራሱ ሰብአዊ መብት የማስከበር ትግል ነውና።
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከሰብአዊ መብቶች ሁሉ ከፍ ያለው መብት ነው። በዚህ መብት ላይ ከባለቤቱ በላይ ባለቤት ሊሆን የሚችል አካልም ሊኖር አይችልም። ይህንን መብት በአደባባይ እየተገዳደሩ ስለሰብአዊ መብቶች ጠበቃ መሆንም አይቻልም። የነዚህ መብቶች ጠበቃ ሆኖ በመቅረብም ያልተገቡ ጥቅሞችን ለማስቀጠል አይቻልም ።የትውልዱ ንቃተ ህሊናም አይፈቅድም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2013