
ስፖርቶች መሰረት መሆናቸው ይታወቃል:: በመላው ዓለምም ከሦስት ሺህ የሚልቁ ባህላዊ ስፖርቶች እንደሚገኙ ጥናቶች ይጠቁማሉ:: የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባሕል ድርጅት (UNESCO) እነዚህን ስፖርቶች በቅርስነት የመዘገባቸው ሲሆን፤ በዓለም አቀፉ የስፖርት ለሁሉም ማህበርም ዕውቅና ተሰጥቷቸው የሚጠበቁ ናቸው::
ጨዋታዎች፣ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን፣ ውድድሮችና፣ ዳንስ እንዲሁም የአክሮባት እንቅስቃሴዎችም በባህላዊ ስፖርቶች ሥር ይጠቃለላሉ:: ተቋማቱም በህብረት እንዲሁም በተናጥል በመሆን በሚያዘጋጇቸው የተለያዩ መድረኮች ላይም የባህል ስፖርቶች ትውውቅና ሌሎች ተግባራት ይከናወናሉ::
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች የሚገኙባቸው፣ ባህልና ታሪክ ጠገብ የሆኑ ሃገራት ደግሞ የተለያዩ ባህሎችና እሴቶች አሏቸው:: ከእነዚህ እሴቶችና የማንነት መገለጫዎች መካከልም ባህላዊ የስፖርት ክንዋኔዎችንም ማካተት ይቻላል:: እንደየአካባቢውና የአኗኗር ሁኔታው የተለያዩና ከጥንት ትውልድ ከትውልድ ሲቀባበላቸው የኖሩ ባህላዊ ስፖርቶችም በርካቶች ናቸው:: በርግጥ ከስልጣኔና ከዘመናዊነት ጋር ተያይዞ ባህላዊ ስፖርቶች እየተረሱና በሚገባቸው ልክም እየተዘወተሩ ባይሆንም፤ ከከተማ ውጪ በሆኑ አካባቢዎች ግን አሁንም ድረስ ይከናወናሉ::
በከተሞች አካባቢም ውድድሮችን በማዘጋጀት ትውልዱ ባህሉን እንዲያውቅ የንቅናቄ ሥራዎች ይከናወናሉ:: እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ግን አሁንም ድረስ ስፖርቱ ዕውቅና አግኝቶ ነዋሪው ድረስ ዘልቋል ለማለት አያስደፍርም:: በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ስፖርቶቹ እንዳይጠፉና ህዝቡም እንዲያዘወትራቸው ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል:: ከእነዚህ መካከል አንዱ አሰልጣኞችንና ዳኞችን በማሰልጠን ስፖርቱ ህግና ደንብ ኖሮት በስልጠና እንዲደገፍ ማድረግ ነው:: ከሰሞኑም የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርቶችን ማስፋፋትና ተሳታፊ ዜጋን መፍጠር መሰረት ያደረገ የባህል ስፖርቶች አሰልጣኝነት ስልጠና ተከናውኗል::
ስልጠናው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጋር በመቀናጀት ያከናወነው ሲሆን፤ በባህል ስፖርቶች የሁለተኛ ደረጃ አሰልጣኝነት መሆኑንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን በድረ ገጹ አስነብቧል:: የስልጠናው ዓላማ የባህል ስፖርቶችን ከማስፋፋት ባሻገር፤ ባህሉንና እሴቱን ያወቀ ተወዳዳሪ እንዲሁም ተሳታፊ ዜጋ ለመፍጠር ነው:: በዚህም መሠረቶቹን በከተማዋ ክፍለ ከተሞች፣ በወረዳና በትምህርት ቤቶች ለማስፋት እንደሆነም በዘገባው ተጠቁሟል።
ለተከታታይ 10 ቀናት (ከሰኔ 08 – 18/2013 ዓ.ም) በቆየው ስልጠናም፤ 23 ሰልጣኞች የሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና መከታተላቸውን የሚገልጽ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትና ዕውቅና አግኝተዋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ሦስቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ 20ዎቹ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውንም በመረጃው ተጠቁሟል:: ተሳታፊዎቹ የተሰጣቸውን የተግባር ልምምድና የንድፈ ሀሳብ የጽሁፍ ፈተና በብቃት አጠናቀዋል::
ስልጠናው በ11 የባህል ስፖርቶች ማለትም በገና፣ በትግል (ግብግብ)፣ በገበጣ ባለ12 ጉድጓድ፣ በገበጣ ባለ 18 ጉድጓድ፣ በኩርቦ፣ በቡብ፣ በሻህ፣ በፈረስ ሸርጥ፣ በፈረስ ጉግስ፣ በቀስት እንዲሁም በሁሩቤ የተሰጠ ነው:: ስልጠናውን በንድፈ ሀሳብና በተግባር ልምምድ የሰጡትም በዘርፉ የካበተ ልምድና ዕውቀት ያላቸው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ በአቶ በላይነህ ኃይሌ መሆኑም ተገልጿል።
ስልጠናው በዋናነት የባህል ስፖርቶች ታሪካዊ አመጣጥ፣ ምንነት፣ በኢትዮጵያ አጀማመር፣ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እንዲሁም ከአሰልጣኝ የሚጠበቁ ባህሪያት፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ የስልጠና ዕቅድ ዝግጅት፣ ዘዴዎች፣ ምልመላ እና አመራረጥ ዙሪያ ያተኮሩ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃደ ጫካ ናቸው።
ስልጠናውን የሰጡት የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሌ በበኩላቸው፤ የባህል ስፖርቶች ሣይንሳዊነትን በመከተል ለዘመናዊ ስፖርቶች መፈጠርም ምክንያት መሆናቸውን ገልፀዋል:: በኢትዮጵያ 293 ህግና ደንብ ያልወጣላቸው እንዲሁም በየአካባቢው የሚዘወተሩ የባህል ስፖርቶች ቢኖሩም፤ ከነዚህ ውስጥ ህግ፣ ደንብና የአተገባበር መመሪያ ወጥቶላቸው የሚዘወተሩት 11 የባህል ስፖርቶች ብቻ እንደሆኑ ገልፀዋል::
በብርሃን ፈይሳ