በአንተነህ ቸሬ –
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ (ምርጫ 2013) ባለፈው ሰኞ፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም፣ መካሄዱ ይታወሳል። በፀጥታና ሌሎች ምክንያቶች (በድምፅ መስጫ ወረቀት እና በምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀት ላይ በተፈፀሙ ጉድለቶች፤ እንዲሁም ከመመሪያ ውጭ በተሰሩ ስህተቶች ምክንያት) ሰኔ 14 ቀን ድምጽ መስጠት ባልተቻለባቸው በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የድምፅ መስጫው ቀን ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሆኗል። በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ የሚሰጥባቸው አካባቢዎችም ቀደም ሲል ይፋ ተደርገዋል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም፣ በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች የታየው የምርጫ ሂደት ሰላማዊ እንደነበር ምርጫውን ለመታዘብ ከውጭ አገራት የመጡ ቡድኖች ጭምር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከኢትዮጵያ ኪሳራ ትርፋቸውን እያሰሉ ‹‹ምርጫው ሰላማዊ አይሆንም›› ብለው ሲናገሩ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖችም በለስ የቀናቸው አይመስልም። ለምርጫው የዘገባ ሽፋን ለመስጠት የሞከሩ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከምርጫው ሂደት የፀብና የግጭት ወሬ ሲያጡ ‹‹ስለምርጫው ዘገብን›› ያሉባቸውን ዜናዎቻቸውን ሁሉ በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ችግር የሚያትቱ ጽሑፎችን አጭቀውባቸው ታዝበናል። ስለምርጫው ሁለት መስመር ጽሑፍ ጠቀስ ካደረጉ በኋላ ስለትግራዩ ‹‹ቀውስ›› ነው ያዥጎደጎዱት። ‹‹ምርጫው አይካሄድም›› ብለው እርግጠኛ የሆኑትም ጥቂት አልነበሩም። የሆነው ሆኖ ምርጫው የእነዚህን ወገኖች ግምት ፉርሽ ብቻ ሳይሆን ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ በማድረግ ድርጊቱን ለታሪክ ትቶት አልፏል።
በዘንድሮው ምርጫ ሂደት የታዩት የሕዝብ ተሳትፎ፣ ምርጫውን ያስፈፀመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥንካሬ እና በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች/ፖለቲከኞች ስክነት ለቀጣዩ አገራዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተስፋ ሰጪ ሆነው ታይተዋል። በተለይ የምርጫው ዕለት ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ ለሁሉም ትልቅ እፎይታ ነበር። በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች ካጋጠሙት የፀጥታ ችግሮች እንዲሁም ‹‹እኛ ሳንተሳተፍበት የሚካሄድ ምርጫ አገሪቱን ዋጋ ያስከፍላታል›› ብለው ሲዝቱ (እግረ መንገዳቸውንም ጉድጓድ ሲቆፍሩልን) የነበሩ ወገኖች ከመኖራቸው አንፃር ‹‹የምርጫው ዕለት እንዴት ሆኖ ያልፍ ይሆን?›› ብለው የተጨነቁና ስጋት የገባቸው ቅን አሳቢ ወገኖች ብዙ እንደነበሩ አይካድም። ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ ተካሄደና ‹‹የምርጫው ዕለት እንዴት ሆኖ ያልፍ ይሆን?›› ብለው የተጨነቁና ስጋት የገባቸው ወገኖችም ተረጋጉ፤ ‹‹ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ አይካሄድም›› ብለው አጀንዳቸውን ለማሳካት የቋመጡ አካላትም ዱብ’ዳ ወረደባቸው [በእርግጥ እነዚህ ወገኖች አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን የመበጥበጫ ሌላ ስልት እንደሚቀይሱ መጠርጠርና ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ የዋህ አያሰኝም]።
በምርጫው ዕለት የታየው የሕዝብ ተሳትፎ ብዙዎችን ያስደነቀና ያስገረመ ነበር። እንኳን ወጣቱ፣ አዛውንቱ ሁሉ ድካም፣ ብርድ፣ ፀሐይና ዝናብ ሳይበግረው ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ጠብቆ የተከበረ ድምፁን ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የድምጽ መስጫ ሰዓቱ እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት እንዲራዘም ያደረገውም ይኸው ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ነው። በቦርዱ መረጃ መሰረት ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከድምጽ መስጫ ወረቀት ጋር በተገናኘ፣ ጉድለት በታየባቸው የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የተመዘገበውን መራጭ ሳይጨምር፤ በጠቅላላው 37 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሕዝብ በመራጭነት ተመዝግቧል። ይህ በድምጽ መስጫው ዕለት የታየው የሕዝብ ተሳትፎ ለመራጭነት የተመዘገበው ሕዝብ ካርዱን ተጠቅሞ ‹‹ይሆነኛል/ይበጀኛል›› ያለውን አካል እንደመረጠ ማሳያ ነው።
ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ከሚያስፈልጉት የዴሞክራሲ ግብዓቶች አንዱ የሕዝብ ተሳትፎ መሆኑን ምሁራን ይገልፃሉ። ሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተሳትፎ ማድረጉ ፍላጎቱንና እሳቤውን ወደስልጣን ለማምጣት በምርጫ ላይ እምነት እንዳለው ያሳያል። ምርጫ ደግሞ ሰላማዊ የፉክክር መድረክና የዴሞክራሲ ስርዓት መገንቢያ መንገድ በመሆኑ በምርጫው ከፍተኛ ተነሳሽነት ያሳየው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ፍላጎቱን ዐሳየ ማለት ነው።
ምርጫና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ናቸው። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሕዝብ አሳታፊ የሆነ መንግሥት ከመመሥረቱም በላይ፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የማዕዘን ድንጋይ ይሆናል። ሁል ጊዜም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሚፈለገው የሕዝብ ፈቃደኝነት ሲሆን፣ ይህ ፈቃደኝነት የሚገለጸው በድምፅ ብቻ ነው። ዜጎች በመንግሥታት የፖሊሲና የስትራቴጂ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ከሚጠቀሙባቸው ወሳኝ ነጥቦች መካከል አንዱ ድምፅ/ምርጫ ነው። ሥልጡንና ተቀባይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ደግሞ የዜጎች ድምፅ ወሳኝ ግብዓት ነው።
በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን ያጋሩኝ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ‹‹… በዘንድሮው ምርጫ ሂደት የታየው የሕዝብ ቁርጠኝነትና ተሳትፎ፣ የንቃተ ህሊናና የመመዘን ዝግጁነትን የሚጠይቀውን የዘመናዊ ፖለቲካ ባህልን መስፈርት ያሟላ ነው። የሕዝቡ ተሳትፎ ከዚህ በኋላ ማኅበረሰቡ በግርግርና በጉትጎታ እየወጣ የሚመርጥ ሳይሆን ‹የምፈልገውን ያሳካልኛል› ብሎ በራሱ ፍላጎት ለመምረጥ ተነሳሽነት እንደሚያሳይ ያመለክታል። ይህ ደግሞ በምዝገባም ሆነ በምርጫ ወቅት ንቁ ተሳትፎ የሌላቸውን አካላትን የሚያነሳሳ፣ የፖለቲካ ባሕላችንን የሚቀይርና ለማስተማሪያም የሚሆን ነው …›› ብለውኛል።
ሕዝቡ ሰላማዊና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ግብዓት በሆነው በምርጫ ላይ እምነት አሳድሮ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉ ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያደርጋል። [‹‹ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ ታይቶበት የነበረው የ1997 ዓ.ም ምርጫ ለምን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ሳያሰፍን ቀረ?›› የሚለው ጉዳይ መታወስና ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል። ከዚህ እውነታ ጋር ስንጋፈጥ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማድረግ ብቻውን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መስፈን በቂ እንዳልሆነ እንረዳለን። ስለሆነም ዴሞክራሲን ማስፈን የመራጭነት ካርድ አውጥቶ በምርጫ ከመሳተፍ የተሻገረ ግብዓት እንደሚፈልግ በመረዳት ሌሎቹን ግብዓቶች ለማሟላት መትጋት ያስፈልጋል።]
ምርጫውን ያስፈፀመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከነጉድለቶቹም ቢሆን ያሳየው ጥንካሬ ለቀጣዩ አገራዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተስፋ ከሰጡ ግብዓቶች መካከል አንዱ ሆኖ ታይቷል። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የተቋማትን ጥንካሬ የሚፈልግ ተግባር ነው። ገለልተኛና በጠንካራ ባለሙያዎች የሚመሩ ተቋማት በሌሉበት አገር የዴሞክራሲ ስርዓትን ስለማስፈን ማሰብ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንደሚባለው ነው። የመንግሥታት ስርዓቶች በተቀያየሩ ቁጥር አቋማቸውን የሚቀያይሩ ተቋማት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዋስ ሳይሆኑ የአምባገነናዊነት ጠበቆች ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ምርጫውን ለማስፈፀም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ራሱን እንደገና ከማደራጀት የጀመረው የቦርዱ ስራ ምርጫውን ለማስፈፀም ያከናወናቸው ተግባራት ብዙ ድካም የጠየቁ እንደሆኑ ሁሉም ሰው በቀላሉ የሚረዳው ሃቅ ነው። የምርጫ ክልሎችን ማደራጀት፣ አስፈፃሚዎችን ማዘጋጀት፣ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ ግንዛቤዎችን መፍጠር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መመካከር፣ ቅሬታዎችን ማስተናገድና መፍታት … እነዚህ ሁሉ ተግባራት ብዙ ስራ የሚጠይቁ ናቸው። ቴክኒካዊ ግንዛቤ የሚፈልጉ ጉዳዮች ደግሞ ጥንቃቄና ብስለት ግድ ይላሉ።
ለአብነት ያህል ምርጫ ቦርድ ከድምፅ መስጫ ወረቀት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን መርምሮ ውሳኔ መስጠቱና ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የድምጽ መስጫው ቀን እንዲራዘም ማድረጉ የሚታወስ ነው። ይህ የቦርዱ ተግባር ቀላል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ይህ ተግባር ከፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበ ቅሬታ ብቻ የተወሰነ የአጭር ጊዜ ስራና የመልካም ፈቃድ ስጦታ ሳይሆን የድምፅ መስጫ ወረቀት እና የውጤት ማሳወቂያ ፎርሞች በጥንቃቄ በማመሳከርና የማመሳከሩ ውጤቶች ባሳዩት ጉድለቶች ምክንያት የተወሰነ ጥንቃቄን የሚፈልግ ስራ እንደሆነ መዘንጋት አያስፈልግም። ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በአገሪቱ በተደረጉት ‹‹ምርጫዎች›› ወቅት መሰል የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት ስለመኖራቸው እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ሲታሰብ፤ ይህ የቦርዱ ተግባር በቀላሉ የሚታይ ስራ እንዳይሆን ያደርገዋል።
ቦርዱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወናቸው የሕግ ማሻሻያ፣ አዳዲስ መመሪያዎችን የማውጣትና ሌሎች ተግባራት ለአገሪቱ ፖለቲካ ስርዓት ገንቢ ተደርገው የሚወሰዱ በጎ ክንውኖች እንደሆኑና ተቋሙ በብዙ ችግሮች ውስጥም ሆኖ ምርጫውን ማስፈፀም መቻሉ እንደድል የሚቆጠርና ‹‹ወደፊት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ከዚህ የተሻለና አመርቂ ሊሆን ይችላል›› የሚል እምነት የሚያሳድር እንደሆነ በብዙ ወገኖች እየተነገረ ነው።
የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የ13 አገራት ኤምባሲዎች ባለፈው አርብ ምርጫውን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ ላይም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተሻለ ሁኔታ ለማስፈፀም ላከናወናቸው ተግባራት እውቅና ሰጥተዋል፤ አመስግነዋል። አገራቱ በመግለጫቸው ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረገውን ትብብር እንዲሁም የምርጫ ሕግጋትን በማሻሻል ረገድ የሰራቸውን ስራዎች ጠቅሰዋል፤ የሲቪክ ማኅበራት ለመራጮች ግንዛቤ በመፍጠርና ምርጫውን በመታዘብ ላበረከቱት አስተዋፅዖም አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
ሌላው ከዘንድሮው ምርጫ ሊወሰድ የሚችለውና ለቀጣዩ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በጎ አስተዋፅዖ የሚኖረው ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች/ፖለቲከኞች ያሳዩት ስክነት ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች/ፖለቲከኞች በምርጫ ሂደት የሚያሳዩት ስክነትና መረጋጋት ከሁሉም በላይ ለአገር ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነው። የምርጫ ውጤት ከመገለፁ አስቀድመው ‹‹ምርጫውን አሸንፈናል … ምርጫው ተጭበርብሯል፤ ውጤቱን አልቀበልም …›› ብለው በስሜት የተናገሩ ፖለቲከኞች የንግግራቸው ውጤት ብዙ አሳዛኝ ዋጋዎችን እንዳስከፈለ ከበርካታ አገራት ተሞክሮ ዐይተናል።
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የተሳተፉ ብዙ ፖለቲከኞች በምርጫው ማግሥት ያስተላለፏቸው መልዕክቶች ዜጎችን ያስደነቁና ያስደሰቱም ጭምር ሆነው ታዝበናል። ‹‹ … የቻልነውን ሁሉ አድርገናል፤ የሕዝብን ውሳኔ እናከብራለን … ሰላማዊ ትግላችንን እንቀጥላለን …›› የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። በእውነቱ ይህ ዓይነቱ የሰለጠነ አካሄድ ተስፋ ሰጪና ሊበረታታ የሚገባው ነው! በመሸነፍ ውስጥም ማሸነፍ እንዳለና ከሁሉም በላይ የሕዝብ ውሳኔ/ፍላጎትና የአገር ጥቅም እንደሚበልጥ መገንዘብ ትልቅ የዴሞክራሲ ኃይል ነው።
‹‹በምርጫው ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳዩት መረጋጋትና ስክነት የሚደነቅ ነው። ይህ የመነጨው ከማኅበረሰቡ መረጋጋት ነው። ማኅበረሰቡ በቀላሉ ውዥንብር ውስጥ መግባት የማይችል መሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልካቸውን እንዲያውቁና በሕግና በስርዓት እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል። የምርጫውን ውጤት ላለመቀበል የሚያስገድዱ የሰላምና የፍትሐዊነት ችግሮች ስላልተከሰቱም ፓርተዎቹ እንዲሰክኑ አድርጓቸዋል። ፓርቲዎች የተረጋጋ አካሄድ እንዲመርጡ ያደረጋቸው የመንግሥት፣ የማኅበረሰቡና የራሳቸው የውስጥ አሰራር ድምር ነባራዊ ሁኔታዎች ናቸው። ይህ ለወደፊቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በጎ ሚና ስለሚጫወት ሊቀጥልና ሊበረታታ ይገባል›› በማለት ሃሳባቸውን ያጋሩኝ ምሁር፤ በዘንድሮው ምርጫ ሂደት የታዩና ለቀጣዩ አገራዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ግብዓቶችን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በምርጫው ሂደት የታዩ በጎ ተሞክሮዎችን በማጎልበት የድህረ ምርጫውን ጊዜ ሰላማዊ ማድረግና ቀጣዩን አገራዊ የዴሞክራሲያ ስርዓት ግንባታ በጠንካራ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ይገባል!!!