ምርጫ ለመምረጥ የወጣው ህዝብ መብዛት፤ ሥፍር ቁጥር የሌለው ህዝበ የሀገሩን መፃኢ እድል በድምፁ ሊወስን መነቃነቁ ይበል የሚያሰኝ መሆኑ ባይካድም ዘመን አመጣሹ ቫይረስ፤ ደስታችንን እንደልብ መግለፅ አንዳንችል አድርጎናል። መተቃቀፍ፣ መጨባበጥ … የደስታችን መግለጫ ሊሆን ቀርቶ መጥፊያችን መሆናቸውን በመገንዘብ ደስታና ጥንቃቄን ማቻቻል የግድ ሆኖብናል።
የምርጫ ቦርድም ህብረተሰቡ ሊመርጥ ወጥቶ በሽታ ይዞ እንዳይመለስ በማሰብ የመከላከያ ቁሳቁሶችን ከማቅረቡ ባሻገር የህብረተሰቡን ርቀት የሚያስጠብቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አሠማርቶ የነበረ መሆኑን ሰምተናል።
የጉለሌ ምርጫ ክልል ሀላፊ ወጣት ሣራ ሞገሴ እንደሚሉት በክፍለ ከተማው ባሉ 188 የምርጫ ጣቢያዎች ኮቪድን ለመከላከል የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ርክክብ የተደረገ ሲሆን፤ ርቀት የሚያስጠብቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ተሰማርተዋል።
በምርጫው እለትም ከበር ላይ የተሰለፉ መራጮች ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሣኒታይዘር በመርጨት ማክስ እንዲያደርጉ በመንገር ተራርቀው እንዲቀመጡ የማድረግ ሥራዎች ሲሰሩ ነበር። በዚህ ሁሉ መካከል ግን ህብረተሰቡ የሚነገረው ለራሱ መሆኑን ባለማሰብ የኮቪድ ፕሮቶኮሎችን ላለመጠበቅ ሲያንገራግር ተመልክተናል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ የኮቪድ ወሬ ቀዘቀዘ፤ ሥርጭቱ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? በማለት የኢትዮዽያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ጋር ደውለናል። እንደሳቸው ገለፃ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባለፉት ሁለት ወራት የቀነሰ ቢመስልም ሦስተኛው ወረርሽኝ በሀገራችን እንዳይቀሰቀስ ማህበረሰቡ የተለመደ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል።
የኢትዮዽያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው የኮቪድ ወረርሸኝ ከግንቦትና ሰኔ መጀመሪያ ጀምሮ በሀገራችን እየቀነሰ የሚገኝበት ሁኔታ መኖሩንና ማህበረሰቡ በቁጥሩ መቀነስ ተዘናግቶ ጥንቃቄውን ላይ ቸል ማለት እንዳማይኖርበት አሳስበዋል። ይህ ሲባል በየእለቱ ከሚመረመረው ሰው መካከል ቫይረሱ የሚገኝበት ሰው ቁጥር ከአምስት በመቶ በታች የደረሰ ሲሆን፤ ይህም ከግንቦት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን የሰኔ አጋማሽ ድረስ ይህ የምርመራ ውጤት በተከተታይ እየታየ ነው፤ ይህም ለሀገሪቱ መልካም የሚባል ዜና ነው ብለዋል።
ከወራት በፊት በተለይም ከጥር አንስቶ እስከ ሚያዝያ ድረስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ከአሥራ አምስት በመቶ በላይ የነበረ ሲሆን፤ በሆስፒታል የተኙ ፅኑ ህሙማን ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነበር። የሟቾች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ የነበረ ሲሆን፤ በሆስፒታሎችም ላይ የነበረው መጨናነቅ አስከፊ ደረጃ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ግን ከባድ ህመም የሚገጥማቸው ቁጥር፤ የሟቾች ቁጥርም እየቀነሰ መሆኑ ቢያስደስትም የቀነሰበትን ምክንያት በውል ተረድቶ መጠንቀቅ የሚገባ መሆኑን ነው የሚናገሩት። ሰዎች በፀና ሥላልታመሙ የሞት ወሬ በየቀኑ ስላልተሰማ ቫይረሱ ከህዝቡ መካከል ወጥቷል ለማለት የማይቻል መሆኑን የተናገሩት ዶክተሩ ሁሌም ጤናማ ሆኖ ለመቀጠል ጥንቃቄ ያሻል ብለዋል።
ወረርሽኞች በተፈጥሯቸው አንዴ መጥተው በዚው መቀጠል ሣይሆን የሥርጭት መጠናቸው ከፍ ዝቅ የማለት ባህሪ ያላቸው መሆኑን ታሪክ እንደሚያሳይ የተናገሩት ዶክተር ተግባር በኮቪድ 19 በሕንድ፣ በብራዚል፣ በደቡብ አፍሪካና በመሳሰሉት ሀገራት ሦሰተኛ ዙር የመምጣት አዝማሚያም ማሳየቱን አስረድተዋል።
ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ቁጥር መብዛት፤ የበሽታው ባህሪ ማለትም በሽታው በየጊዜው ባህሪውን የሚቀያይር መሆኑ፤ ሌላ በበሽታው ያልተያዙ ሰዎች መብዛት፣ ለበሽታው ምቹ ሁኔታ መፈጠር፤ ይህም ሲባል በዓላት፣ ስብሰባዎች፣ ሠልፎች መኖራቸው በሽታውን ድጋሚ ሊቀሰቅሱት የሚችሉ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ ጥንቃቄውን አጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑን አሳስበዋል።
አሁንም ያለው ስጋት ከሌላው ሀገር ልምድ እንደሚታየው ክትባቱ ላይ ካልተበረታ፤ ጥንቃቄው ላይ ማለትም ርቀትን መጠበቅ፣ ማክስ ማድረግ፣ እጅ ማፅዳት ላይ ትኩረት ካልተደረገ ድጋሚ ሊከሰት የሚችል መሆኑን ነው የተናገሩት። የጥንቃቄ ርምጃዎችም በሽታው ዓለም አቀፍ ወርርሽኝነቱ እስኪቀንስ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
“ክትባቱ ለመቀነሰ ምክንያት ይሆናል ወይ?” ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “ከሀገሪቱ ህዝብ ሁለት ከመቶ የሚሆን ሰው ባልተከተበበት ሁኔታ ይህ ይሆናል ማለት አይታሰብም” የሚል መልስ የሰጡት ዶክተር ተግባር የወረርሽኝ ባህሪ ማለትም ተፈጥሯዊ ባህሪው የማህበረሰብ የመከላከል አቅምን፤ ለበሽታው ምቹ ሁኔታ አለመኖርና ሌሎች ምቹ የመስፋፊያ ሁኔታ አለማግኘቱን በመገንዘበ ህብረተሰቡ ጥንቃቄው ላይ መቀጠል ይኖርበታል በማለት ይመክራሉ፤ ያሳስባሉም።
ምንም ነገር ከጤና አይበልጥምና እንቅስቃሴያችን ሁሉ በጥንቃቄ የተመራ ይሁን። በጤና ያሠንብተን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013