በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ የመስጠት ሂደት ከተካሄደ ዛሬ ሳምንቱን አስቆጥሯል። በዕለቱ ምርጫ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን የሰጠበት እውነታ መላው ሕዝባችን የድምጹን ዋጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተረዳበት፤ በድምጹ አገሩን ለማሻገር ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያሳያበት ነው።
የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ውስን ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል፤ ይህም ከሁሉም በላይ ለመላው ሕዝባችን ትልቅ እርካታን ያጎናጸፈ ነው። በተለያዩ ወገኖችም ከፍ ያለ አድናቆት ተችሮታል። ለጀመርነው የዴሞክራሲ ግንባታ ጠንካራ መሠረት የጣለ እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል።
የድምጽ አሰጣጡ በመራጩ ሕዝብ፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ በመንግሥት፣ በምርጫ ቦርድ ፣ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የተረጋጋ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ መሆኑ ተመስክሮለታል። ከምስክሮቹም በላይ እውነታው የአገሪቱን አደባባዮች የሞላ ሆኗል።
የምርጫው ውጤትም ከማግስቱ ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ለሕዝብ ይፋ እየተደረገ ነው። እስከ አለፈው ቅዳሜ ድረስም ምርጫ ከተካሄደባቸው 440 የምርጫ ክልሎች መካከል 221 የምርጫ ክልሎች ጊዜያዊ ውጤት መለጠፋቸውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። ይህም 50 በመቶው ጊዜያዊ ውጤት መለጠፉን ያመለክታል።
የምርጫው ዋነኛ ተዋንያን የሆኑት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እስካሁን ባለው ሂደት የተለያዩ ችግሮች እንዳጋጠሟቸው ቅሬታዎችን ቢያሰሙም፤ ቅሬታዎቻችውን በተቀመጡ አሠራሮች ለመፍታት እየሄዱበት ያለው መንገድ በእጅጉ የሚበረታታ ነው። በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የጎላ ስፍራ ሊያጎናጽፋቸው የሚችል እንደሆነም ይታመናል።
ሕዝባችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በየዘመኑ ከከፈለው ከፍ ያለ ዋጋ አንጻር ይህንን የሕዝባችንን ትልቅ መሻት ወደ ህያው ታሪክ ለመለወጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስክነት፣ ነገሮችን ከማሸነፍና ከመሸነፍ ስሌት ወጥተው አገርና ሕዝብን አሸናፊ ወደሚያደርግ የአስተሳሰብ ስሌት መሻገራቸው ትልቅ አገራዊ ስኬት ነው።
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በአንድ ምርጫ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከያንዳንዱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሚገኝ የተሻለ ተሞክሮ እየዳበረ የሚሄድ፤ በየወቅቱ በሚካሄዱ ምርጫዎች ስኬት እየጎለበተ በሂደት በሚፈጠር የአስተሳሰብ ልህቀት የሚመዘን ነው።
በዚህ ምርጫ ሕዝባችን ያለ አንዳች አስገዳጅ ሁኔታ በምርጫው ለመሳተፍ ያሳየው መነሳሳት፤ ከዚህም በላይ ድምጹ መሪዎቹን ለመምረጥ ትርጉም ያለው አቅም እንዳለው ተረድቶ በነቂስ ወጥቶ መምረጡ፣ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ማራመድ የሚያስችል ተሞክሮ ነው።
ይህ ተስፋ አቆጥቋጭ ተሞክሮ የበለጠ ትርጉም የሚኖረው በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለታየው ለሕዝቡ መነሳሳት እና ቁርጠኝነት እውቅና መስጠት ፤ በምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን የምርጫውን ውጤት በጸጋ ተቀብለው እንኳን ደስ ያለህ ወደ መባባል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መሸጋገር ሲችሉ ነው።
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በፍጥረቱ ከማሸነፍና ከመሸነፍ ስሌት በላይ ለዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ከአስተሳሰቡ ለሚመነጩ ልምምዶች ዕድል መስጠትን ቀዳሚ የሚያደርግ ነው። በተለይ ደግሞ እንደኛ ላሉ ሥርዓቱን ለመገንባት ጅምር ውስጥ ላሉ ሕዝቦች ከምርጫ ውጤት ይልቅ ልምምዶቹ ወሳኝ እንደሆኑ ይታመናል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአደገ የዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ ባለመሆናችን በምርጫው ሂደት የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችል ይገመታል፤ ችግሮቹ በመሠረታዊነት ከአስተሳሰብ ክፍተት ሊመነጩ እንደሚችሉ ፤ ከዚህም በላይ የመጣንባቸው የፖለቲካ መንገዶች እና የፈጠሩት የፖለቲካ ባህል በራሱ በአንድ ምሽት የሚከስም ባለመሆኑ የችግሮቹ ሌላኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
በአገሪቱ ተጨባጭ እውነታ ከዚህ ችግር እራሱን ፍጹም ነፃ አድርጎ የሚያስብ የፖለቲካ ፓርቲ አይኖርም ። ከዚህ ተጨባጭ አገራዊ እውነታ በመነሳትም ሂደቱ ከሚፈጥረው ልምምድና ልምምዱ ከሚያስገኘው የአስተሳሰብ መለወጥ ይልቅ በማሸነፍና በመሸነፍ ስሌት ላይ ትኩረት ማድረጉ ተገቢ አይደለም ። ዘላቂ አገራዊ የፖለቲካ ፈውስም ሊያስገኝ አይችልም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013