ባለፉት ሁለት ተከታታይ እትሞቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ማቅረባችን ይታወሳል በዛሬው እትማችን የቃለ መጠይቁን የመጨረሻ ክፍል እናቀርባለን።
ጥያቄ፡- እርሱ ላይ የሚነሳው ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ካረጋገጠ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በተፈጸመበት ልክ እና ዕውነታን መሰረት አድርጎ የሕግ እርምጃ ለመውሰድና ለማስተካከል ምን ያህል ዝግጁና ቁርጠኛ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– ዝግጁነት ሳይሆን ወስዷል:: ወታደሮች እኮ አሁን እስር ቤት አሉ :: የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ግዳጅ ሕግ “ሩል ኦፍ ኢንጌጅመንቱ” በዚህ ዘመቻ “ኦፕሬሽን” ውስጥ እያንዳንዱ ወታደር በምን ዓይነት አግባብ ተልእኮውን “ሚሽን” መፈጸም እንዳለበት መከላከያ ሕግ አለው:: ያንን ሕግ የተላለፈ ወታደር እስር ቤት ነው ፤ አሁን በሕግ እየተጠየቀ ነው :: ይሄ ማንም ሰው የሚነግረን ጉዳይ ሳይሆን እንደ መንግስት ያለብን ኃላፊነት ነው ፤የዜጎችን መብት ማስከበር ግዴታችን ነው ፤ተግባሩ የማንፈልገው ጉዳይ ነው:: እዚያ አካባቢ በነበረው ግጭት አንኳር የግጭቱ ባለቤትና ቀስቃሽ የጁንታው ኃይል ነው::
የጁንታው ኃይል ያኔ የፈጠረብን ነገር ሳያንስ አሁን እያደረገ ያለው ነገር ደግሞ ፕሮፖጋንዳው አጠቃላይ በጦርነቱ ያጣውን ድል በፕሮፖጋንዳ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ደግሞ ልክ አንድ እብሪተኛ ጎረምሳ አንድን የጎረቤት ልጅ በጥይት ገድሎ ከገደለ በኋላ ለአካባቢ ሽማግሌዎች ይከስሳል:: የክሱ ጭብጥ የጥይቴን ዋጋ ቤተሰቦቹ ይክፈሉኝ የሚል ነው:: ልጃቸውን በጥይት ገድሎ ሲያበቃ የጥይቴን ዋጋ ቤተሰቦቹ ካልከፈሉልኝ በስተቀር አለቅቃቸውም የሚል ክስ አቅርቦ ሽማግሌዎችን የጥይት ዋጋ ያስከፈሉበትን ታሪክ ነው የሚያሳየው:: የተወጋን፣ የተዘረፍን፣ የተደፈርን እኛ ነን:: ከዚህ ቀደም አንስቸዋለሁ:: የጁንታው ኃይል የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሴት ወታደሮችን በመኪና በታንክ ሄዶባቸዋል::
ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተካሂዷል:: ወታደሮችስ ጠላት ናችሁ ተብለዋል ብለን እንውሰድ ችግር የለውም ትክክልም ባይሆን ፤ በሞራልም በሕግም ትክክልም ባይሆን:: ማይካድራ ላይ ከጉዳዩ ጋር ምንም ትስስር የሌላቸው አገሬ ነው፣ ክልሌ ነው ብለው የሚኖሩ ሕዝቦች በዘር ምክንያት ብቻ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል::
እርሱ ትክክል አይደለም እንደምንለው ሁሉ በእኛም ወገን በተለይ ንጹሐን ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም አንፈልግም:: ለዚህ ማረጋገጫው ማይካድራ ላይ የጁንታው ኃይል የፈጸመውን ዓይነት የጅምላ ሰብዓዊ መብት ጭፍጨፋ በአንድም ቦታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አልፈጸመም:: በጅምላ ሰብስቦ ሰው አልገደለም:: እዚያም እዚያም የተጠቁ እዚህም እዚያም የተጎዱ ግለሰቦች አሉ:: እነርሱን በሚመለከት አጥርተን እርምጃ ወስደናል ፤ እየጠየቅን እንገኛለን::
ትክክል አይደለም እርሱም ቢሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም አንፈልግም:: ሕዝባችን እንዲቸገር አንፈልግም:: ለዚያ እኮ ነው ችግር መጣ በተባለበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት የረዳውን እርዳታ ያክል የየትም አገር መንግሥት አልረዳም:: ኃላፊነታችን ስለሆነ ወደፊትም እናደርጋለን:: እናግዛለን ያጠፉ በሕግ እንጠይቃለን ፤ትግራይን መልሰን እንገነባለን:: ይህ ሥራችን ነው::
የትግራን ሕዝብ ከድህነትም ከጁንታው ፖለቲካዊ ጫናና የውሸት ፕሮፖጋንዳም ነጻ አውጥቶ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ኮርቶ እንዲኖር ማድረግ ግዴታችን ነው:: ይሄን የምናደርገው ትግራይ ውስጥ ከጁንታው የተሻለ የተማሩ ትግራይን መቀየር የሚፈልጉ ኢትዮጵያን መቀየር የሚፈልጉ ወጣቶች እየተሰባሰቡ በአዲስ ሃሳብ በአዲስ እሳቤ ከወንድም ሕዝቦች ጋር ተባብረው ትግራይንም ኢትዮጵያንም እንዲያለሙ መድረኩን በማመቻቸት ነው:: ያው በዚህ አግባብ እየተሰራ ይገኛል:: አብዛኛው ነገር መስመር እየያዘ ይሄዳል የሚል ዕምነት ነው ያለኝ::
ጥያቄ፡- ትግራይ ውስጥ ሰው ሰራሽ ረሃብ ሊከሰት ይችላል የሚሉ ሃሳቦችና ድምዳሜዎች በተለያዩ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦችና በመገናኛ ብዙሃን እየተገለጹ ነው:: በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥትዎት ምን ይላል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡- ትግራይ ውስጥ ባለፉት ሁለት ሦስት አስርተ ዓመታት ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ በያመቱ ይታገዛል:: በምግብ ራስ መቻል የሚባለው አንኳር ችግር ያለው ትግራይ አካባቢ ነው:: አምናም፣ ካች አምናም ፤የዛሬ አምስት ዓመትም ፣ አስር ዓመትም በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው እህል ይሰጠዋል::
አሁን ይሄ ውጊያ ከመጣ በኋላ ከዚህ ቀደም በሴፍቲ ኔት የሚታገዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ድጋፍ አያስፈልጋቸውም ትግራይ ምግብ በሽበሽ ነው እያልን አይደለም ያለነው:: ከዚህ ቀደም የሚቸገሩ ሰዎች አሉ፤ በጦርነት ምክንያት ደግሞ የሚጨመሩ ሰዎች አሉ:: ነገር ግን ትግራይ ውስጥ የሚያጋጥመውን የምግብ እጥረት ምግብ በማቅረብ መሸፈን የማንችልበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለነው ::
የተሰደዱ ሰዎች አሉ ለመመለስ ሰፊ ስራ እየሰራን ነው :: ከሁሉም ክልሎች ጋር ተነጋግረን ከአማራም፣ ከትግራይም፣ ከቤኒሻንጉልም፣ ከኦሮሚያም ከየትም የተሰደደ ሰው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመለስና ክረምቱ የእርሻ ጊዜ ሳያልፈው እንዲሰራ ጥረት እየተደረገ ነው:: ትግራይ ክልል ውስጥ ከሰባ ፐርሰንት በላይ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር ቀርቦላቸው እርሻ ውስጥ እንዲገቡ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ፤ ታውቃላችሁ ብዬ አስባለሁ::
ይሄም ሆኖ ትግራይ የሚመረተው ምርት ለትግራይ ሕዝብ በቅቶ አያውቅም ፤ አሁንም አይበቃም:: እርሱን እናግዛለን ነገር ግን ረሃብ ሊገባ ይችላል መንግስትም ረሃብን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ይጠቀምበታል የሚለው ግልጽ “ፒዩር” ፕሮፖጋንዳ ነው:: በምንም መመዘኛ አልተረጋገጠም:: የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ባቀረባቸው መመዘኛዎች አንድ አካባቢ ላይ ከስንት ሰው ምን ያክል ሰው ሲሞት፤ ምን ያክል ህጻናት ሲሞቱ ነው ረሃብ “ፋሚን” የሚባለው ፤ መመዘኛዎች “ክራይቴሪያስ” አሉት :: ያን የሚያሟላ አንድም የተጨበጠ መረጃ “ዳታ” የለም:: በብዙ ወረዳዎ ች ምግብ እያደረስን ነው ፤ እርሱ ይቀጥላል::
ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሃሳብ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘበው የሚያስፈልገው፣ 1977 ዓ.ም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ድርቅ ሲያጋጥም ያንን ድርቅ ጁንታውም ሌላውም ኃይል መጠቀሚያ አድርጎታል:: እስከ 1977 ድረስ ቲ.ፒ.ኤል.ኤፍ አንዲት ከተማ አንዲት ዞን የኔ የሚለው አልነበረውም:: ጠንካራ የሚባል ውጊያም አድርጎ አያውቅም:: የደርግ መንግስት ፈተና የነበረው እስከ 1977 ድረስ የሻዕቢያ ወታደር የሚባለው እንጂ የወያኔ ወታደር ራስ ምታት “ሄዴክ” አልነበረም::
ነገር ግን 1977 ረሃቡ መጣ ሲባል የምናምን ኮሪደር ይከፈት በሱዳን በኩል ተብሎ የደርግ መንግሥት እንዲወድቅ የሚፈልጉ ኃይሎች በአካል ጭምር በረሃ ገብተው በስትራቴጂውም፣ በስልጠናውም፣ በሃሳቡም በገንዘቡም በትጥቁም አብረው ሆነው ከ1977 በኋላ ነው ወያኔ ተጠናክሮ በ1981 ሽሬን እንኳን መቆጣጠር የቻለው::
ጥያቄ፡- ድርቁን ተጠቅሞበታል እያሉኝ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– በደንብ
ጥያቄ፡- አሁንም ረሃብንና ድርቅን የመጠቀም ፕሮፖጋንዳ ላይ ነው የሚሉኝ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– አሁን ጁንታው ብቻ ሳይሆን የዚያን ጊዜ ይሄን ሃሳብ አምጥተው ወያኔን አስታጥቀው የደርግ መንግሥት እንዲወድቅ ያደረጉ ኃይሎችም አዲስ ፈጠራ መፍጠር አልቻሉም:: እዚያው ነው የቆሙት ። የዛሬ ሠላሳ አርባ ዓመት በሰሩት ታክቲክ አሁንም መጠቀም ይፈልጋሉ:: ይሄ መቼም አይሆንም፣ መቼም አይሆንም:: ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ “አክሰስ” ተፈቅዷል:: ለማንኛውም ኤን፣ጂ.ኦ ።ዛሬ ከ200 በላይ ኤን፣ጂ.ኦ እና ዩ.ኤን ስታፎች ትግራይ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ:: የውጭ ሚዲያዎች ይንቀሳቀሳሉ::
አክሰስ በብዙ ቦታ ክፍት ነው። ሁለት ቦታ ብቻ ነበር እንደ ፈተና ያየው እሱን ቦታ የአገር መከላከያ ሰራዊት እያጀባችሁ አድርሱ ሲባሉ አይፈልጉም መታጀብ:: ምክንያቱም የሚያስቡትን ዓላማ ስለማያሳካ::
ጥያቄ፡- መንግሥት ይህን ያክል ጥረት ካደረገና ድጋፍ ካደረገ ለምንድነው አሁንም ቢሆን የሰብዓዊ እርዳታዎችን/ ድጋፎች ለማድረስ በሮች ሁሉ ይከፈቱ የሚል ውትወታ የሚሰማው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡- በነገራችን ላይ አንድ ኪሎ ስንዴ አምጥቶ ያንን ለሕዝባችን እንዳያደርስ የተከለከለ አንድም ዓለም አቀፍ ተቋም ወይም ኤን፣ጂ.ኦ የለም ፤ አንድም ኪሎ ብትሆን:: የመጡትን በሰጠናቸው ቀጠና አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገን እየረዳናቸው ነው:: ይሄ ጥያቄ ግን ምንድ ነው መጀመሪያ “ኮሙዩኒኬሽን ጋጀት” ያስፈልገናል አሉ:: በቁጥር ያሉት ሁለት መቶ ምንምን ቢሆኑም ሦስት መቶ ሃምሳ….ተፈቀደላቸው:: አልበቃቸውም የተወሳሰበ የኮሙዩኒኬሽን ዕቃ ይጠይቃሉ::
ለምን የሚለውን ቅድም አንስቸልሃለሁ:: አክሰስ በሚመለከት መጀመሪያ ይፈቀድልን አሉ ይፈቀድላችኋል የፈለጋችሁበት በነጻ ሂዱ ችግር ያጋጥመናል የምትሉበት ቦታ ደግሞ መከላከያ ያጅባችኋል:: አይ መታጀብ አንፈልግም፤ ለምን? ብቻችንን ማድረስ ስለምንፈልግ:: ብቻችሁን ማድረስ የምትፈልጉበት ቦታ ደግሞ ሂዱ እኛ አንጠይቃችሁም ስንላቸው የተለየ ኮሪደር ካልተፈጠረ ይላሉ:: ይሄ ቅድም ያልኩህ ዓላማ አካል ነው፡ ቪዛን ኢሹ አድርገው ነበር ሦስት ወር ካልተደረገልን ብለው ሦስት ወር ያህል ጊዜ ሰጠናቸው:: ቪዛ ጠየቁ መለስን፣ ኮሙዩኒኬሽን ጠየቁ መለስን፣ አክሰስ ጠየቁ መለስን፣ የሚቆም አይደለም:: ለምን የሚለውን እነርሱን መጠየቅ ነው የሚሻለው እኔን መጠየቅ ዋጋ የለውም::
ለማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ዜጎች እንዳይራቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚችለው ሁሉ ኢትዮጵያውያን ካላቸው የዕለት ጉርስ ቀንሰውም ቢሆን ሕዝባችን በረሃብ ምክንያት እንዳይጠቃ እያደረጉ ነው፤ እናደርጋለን:: በዚህ ስጋት የለንም:: የውጭ መንግሥታት የሚደግፉን የሚተባበሩን ጋር በትብብር ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁዎች ነን:: የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚቃረን መልኩ የሚደረግ ድራማ ግን አናስተናግድም:: አላስተናገድንም ወደፊትም አናስተናግድም:: ይሄ ትክክል አይደለም፤ ከዚህ ውጭ ያለውን ደግሞ በሂደት እያየን እያረቅን ፤ እያረምን የምንሄድ ይሆናል::
ጥያቄ፡- ከአሁን በፊት በምርጫ ወቅት ሲናገሩ ብልጽግና ፓርቲ የማይሰራውን ነገር የማይጀምር የመሰረት ድንጋይ የማያስቀምጥ ነው ብለው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር:: አሁን በዚህ የምርጫ ወቅት ብዙ ፕሮጀክቶች ሲመረቁ፣ ብዙ የመሰረት ድንጋዮች ሲቀመጡ አያለሁ:: ካሁን በፊት ከተናገሩት ቃል አንጻር ምንድነው አሁን እየሆነ ያለው? ይሄ ሁሉ ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ነው የሚመረቀው፤ የሚቀመጠውስ የመሰረት ድንጋይ የሚሰራ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– እኛን ፕሮጀክት ጀምሮ በመጨረስ ለማማት ትንሽ የሚከብድ ይመስለኛል:: ያልነውን ለመፈጸም የማንተኛ፣ ያልነውን ለመፈጸም በእጅጉ የምንተጋ መሆናችንን በተደጋጋሚ አሳይተናል:: ሁለት ጥያቄ ነው ያነሳኸው:: አሁን መሰረት ድንጋይ የሚቀመጥባቸው ፕሮጀክቶች ይጠናቀቃሉ:: ለምሳሌ ጎርጎራ ይጠናቀቃል:: ኮይሻ ይጠናቀቃል:: ወንጪ ይጠናቀቃል::
ምንም ጥርጥር የለውም:: አቅደን፣ ቦታ አዘጋጅተን፣ ገንዘብ አዘጋጅተን፣ ሰው አዘጋጅተን የጀመርናቸውን እንጨርሳቸዋለን:: ሪባን እንቆርጣለን ምንም ጥያቄ የለውም :: የማንጨርሰውን አንድም የጀመርነው ስራ የለም:: በእርግጥ አሁን የበዛው መጀመር ሳይሆን ማስመረቅ ነው:: ማስመረቅ ነው እዚህም እዚያም የሚታየውና ምናልባት እሱ ለምርጫው ነው ወይ ምርቃት የበዛው የሚል ከሆነ ጥያቄህ ከምርጫ በኋላም ይቀጥላል:: ምርጫው ሰኞ ነው ከሰኞ በኋላ ያሸነፈው ፓርቲ መንግስት የሚመሰርተው መስከረም መጨረሻ ነው:: እስከ መስከረም መጨረሻ እንዲሁ እያስመረቅን እንቀጥላለን:: እስካሁንም መጥተናል አሁንም ይቀጥላል:: በጣም ብዙ ያልበሰሉ ተጥደው የተረሱ ድስቶች ስለነበሩ እነሱን ሽንኩርት ቀይረን እያበሰልን ስለነበረ ብዙ ፕሮጀክቶች ነው ያሉት::
በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባ ውጭም:: ከምርጫው ማግስት ጀምሮ እየተመረቀ ይቀጥላል:: ሥራችን ይቀጥላል:: እየተመረቀ ይቀጥላል:: በነገራችን ላይ ብልጽግና በዚህ ምርጫ ባያሸንፍ ከሰኞ ምርጫ ጀምሮ እስከ መስከረም መጨረሻ ሰኞ ድረስ እንዳስመረቅን እንደሰራን እንደጨረስን ለሚመጣው መንግስት አመቻችተንና ጠርገን እናስረክባለን እንጅ እዳ አናስረክብም:: እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ ፕሮጀክቶቹ ይጠናቀቃሉ እሱን በጋራ የምናየው ይሆናል::
ጥያቄ፡- በቀጣይ የአገር ባለቤት ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ልጆችና ህጻናት ስለ ኢትዮጵያና ስለ ነገ ተስፋዋ የሚነገራቸው ተስፋ ምንድነው የሚለውን ለሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎችም እጠይቃለሁ:: ለእርስዎም የምጠይቀው ለእነዚህ ህጻናት እንዴት ያለች ኢትዮጵያ ናት የሚኖራቸው? የነገ ተስፋቸውስ ምንድነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– አሁን እየመጣ ያለው ትውልድ ” ጀኔሬሽን “ዕድለኛ ነው:: ያንተ ትውልድ አደገኛ ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ ነው:: ኢትዮጵያ ብሎ ለመጥራት በሚታፈርበት፣ ታሪኳን ማንሳት በሚያሸማቅቅበት፣ የአባቶቻችን ገድል ማንሳት ነውር በነበረበት ጊዜ የተፈጠርክ ስለነበርክ:: እነርሱ ግን ታሪካቸውን ትናንትናቸውን እንዲያውቁ እየተደረገ ነው:: ትናንትናቸውን እንዲያውቁ ብቻ ሳይሆን መሰረት እንዲይዙ ላይብረሪ እየገነባን ነው፣ ሳይንስ ሙዚየም እየገነባን ነው:: ትምህርት በጣም እያስፋፋን ነው:: ትምህርት ቤት ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ እንዲሆን እያደረግን ነው:: እነዚህ ሁሉ የምናደርገው የተሻለች ኢትዮጵያን ተቀብለው ለማሻገር የሚያስችሉ መሰረቶችን ለመጣል ነው:: እንግዲህ ለልጆች ያለኝ መልዕክት እኔ ተዘጋጁ ነው::
ጥያቄ፡- ለምን ይዘጋጁ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡– ልጆች መዘጋጀት ያለባቸው በትምህርት ቤት ሰው ከአንደኛ ክፍል ወደ ሁለተኛ ክፍል የሚተላለፈው ፈተና “ቴስት”፣ የዓመቱ አጋማሽ “የሚድ ተርም” ፈተናዎችና የመጨረሻ ” ፋይናል” ፈተና ወስዶ እነዚያ ይሰበሰቡና ከሃምሳ በላይ ካለው ወደ ሚቀጥለው ክፍል ይሸጋገራል:: ኮሌጅም ሲገባ ተለያዩ ኮርሶች ይወስድና የኮርሶቹ ውጤት ድምር ከሁለት በላይ ጂ.ፒኤ ያለው ከሆነ ጨርሰሃል ተብሎ ጋዋን ይለብሳል፣ ጨርሰሃል ተብሎ ሰርቲፊኬት ይሰጠዋል፣ ዲግሪ አለህ ማስተርስ አለህ ይባላል:: ተምሮ አጥንቶ ተፈትኖ በፈተናው ባመጣው ውጤት ነው ሰው ዲግሪ አለህ አስረኛ ነው ወይም ማስተርስ አለህ የሚባለው::
ነገር ግን ሌላ ዝግጅት የሚፈልግ ነገር አለ:: ለምሳሌ አገር መሪ በምትሆንበት ሰዓት እኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ይሄን አገር እንዳገለግል ስመረጥ፤ ስሾም የዚያን ቀን ነው ዲግሪዬን የወሰድኩት፤ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰርቲፊኬት የወሰድኩት:: ነገር ግን ፈተናውንና ትምህርቱን የጀመርኩት “አፕሪል ” 3 ነው በማግስቱ:: ቀድሜ ተመርቄ ከማግስቱ ጀምሮ ግን እየተፈተንኩ፣ እየወደቅኩ፣ እየተነሳሁ እየተማርኩ እየወደቅኩ፣ እየተነሳሁ ያ የተመረቅኩበትን ማዕረግ የተመረቅኩበትን ሰርተፍኬት ለማሟላት ነው የምተጋው ወደፊት:: በትምህርት ግን የተገላበጠ ነው:: ተምረህ ተመርቀህ ነው ብቁ “ሰርቲፋይ” የምትሆነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ስትሆን ግን መጀመሪያ ሰርቲፊኬት ወስደህ፣ መጀመሪያ ጋዋን ለብሰህ፣መጀመሪያ ማዕረጉን ለብሰህ ስታበቃ ከዚያ ነው ፈተናው ትምህርቱ የሚመጣው:: ቀድመህ ተምረህ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነህ ተለማምደህ መመረቅ የሚባል ስለሌለ ማለት ነው:: ልጆች ኢኮኖሚያችን እያደገ ነው:: በዓለም ያለን ተፅዕኖ እያደገ ይመጣል:: በምድራችን ያሉ ዕድሎች እየሰፉ ይሄዳሉ:: ምድራችን የምትፈለግበትም ፣ የምትፈተንበትም ዘርፍ እየበዛ ይሄዳል:: ይሄንን ዛሬ አስበው እየተዘጋጁ ካልሄዱ ነገ ዱብ እዳ ከወደቀባቸው እነሱም አገርም ፈተና ውስጥ ይወድቃሉ::
ምን ማለት ነው ይሄ ታሪካቸውን በደንብ ያጥኑ፣ ቋንቋቸውን፣ እምነታቸውን የእያንዳንዱን ብሔር አኗኗር ዘይቤ ባህል ለማወቅ ይሞክሩ:: ብዙዎቻችን አገራችንን አናውቅም:: ሰፈራችንን ነው የምናውቀው:: ኢትዮጵያን እየዞርኩ ባየሁበት ቁጥር የገባኝ ነገር ብዙዎቻችን ፖለቲከኛም እንሁን፣ መምህርም እንሁን ፣ ነጋዴም እንሁን ከወጣንበት ሰፈርና ከውስን ቦታዎች ውጭ አገራችንን አናውቅም:: አገራችንን በደንብ እያወቅን ብንሄድ ለአገራችን ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል:: አገራችን የመለወጥ አቅማችን እያደገ ይሄዳል:: ያልታዩ ዕድሎች ለማየት አጋጣሚ ይጥርልናል:: እና ልጆች መዘጋጀት አለባቸው:: የበለጠ ኢኮኖሚ፣ የበለጠ ጠንካራ አገር በሚፈጠርበት ሰዓት ኃላፊነትም በዚያው ልክ እየሰፋ ስለሚሄድ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው::
ለምሳሌ የመከላከያ ሰራዊት ቅድም እንዳነሳሁት መከላከያ የሚባል ተቋም በከፍተኛ ደረጃ እየዘመነ እየተቀየረ ነው :: የሚያጓጓ ተቋም ነው ፣አንተ እንኳን አለፈብህ እንጂ ብትገባ የሚያጓጓ ተቋም ነው:: ይሄን ልጆች ከወዲሁ አይተው ዓመትም ሁለት ዓመትም ፣አምስት ዓመትም መከላከያን ለማገልገል ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል:: ለምን አገርህን የምትወድ ከሆነ በዚያም መከራ ውስጥ በዚያም ችግር ውስጥ ማለፍ አንዱ ወሳኝ ምሰሶ ስለሆነ:: እና ልጆች መዘጋጀት አለባቸው:: መማር አለባቸው፣ ማንበብ አለባቸው፣ ታሪክ ማወቅ አለባቸው፣ መመስረቻቸውን ማወቅ አለባቸው፣ አብሯቸው የሚኖረውን ጎረቤት ማወቅ አለባቸው:: በዚህ ውስጥ ዕውቀታቸው እያደገ ፈተና የሚባሉ ጉዳዮችን ቀድሞ ለመተንበይ የሚያስችል ብቃት እየፈጠሩ ከሄዱ የተሻለች አገር፣ ከእኔ የተሻለች አገር እንደሚረከቡ ምንም ጥርጣሬ የለውም::
ጥያቄ፡- አንድ ሦስት ሽህ ብር ደመወዝ ያለው ሰው አምስት ሊትር ዘይት ለመግዛት ስድስት መቶ ብር ያወጣል:: የደመወዙ ሃያ በመቶ ማለት ነው:: የዋጋ ንረቱና ግሽበቱ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል:: ሕዝቡ ስለ ዋጋ ግሽበትና ዋጋ ንረት መንግሥት ምን መፍትሔ እንዳለው ጥያቄ አለው:: ምንድነው ምላሽዎት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡- የዋጋ ንረትን በሚመለከት በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ ያስቀመጥናቸው ስልቶች አሉ:: ከአጭር ጊዜ አንጻር በገበያ ውስጥ አነስተኛ ሸቀጦች ማስገባት እነዚያ ሸቀጦች እንዳይገቡ የሚያስተጓጉሉ ኃይሎችንና አርቲፊሻል የዋጋ እጥረት የሚፈጥሩ ኃይሎችን ደግሞ መቆጣጠር ነው :: በእርግጥ ችግሩ አለ ብዙ የለፋንበት የሰራንበት ጉዳይ ቢሆንም የተሻለ ውጤት ካላመጣንባቸው ጉዳዮች አንዱ የዋጋ ንረት ነው:: በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በብዙ እየተፈተኑ እየተቸገሩ ይገኛሉ::
ጥያቄ፡- መንግሥት ይሄ ስሜታቸው ይገባዋል፣ ይጋራል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡- እንግዲህ ባይገባው አይናገረውም ብዬ ነው:: በደንብ ይገባዋል ያውቃል ችግሩን:: በስግብግብ ነጋዴዎች የሚደረገውን እነሱን በማረቅ ፣በማረም የሚጎድሉ ሸቀጦችን በማስገባት ለመፍታት ይሞክራል:: ለምሳሌ ነዳጅን ብቻ ፣ማዳበሪያን ብቻ እንደ ምሳሌ ብወስድልህ ማዳበሪያ በዚህ ዓመት አምና ከነበረው ሰላሳ ፐርሰንት ነው የጨመረው:: የዓለም የገበያ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል:: ያን እንዳለ ከውጪ እናስገባለን “ኢምፖርት” እናደርገዋለን:: ማዳበሪያ ሰላሳ ፐርሰንት ሲጨምር ያን እንዳለ ወደ ገበሬው ማሻገር ስላልተፈለገ መንግሥት ያንን ሸክም “በርደን” ለመሸከም ሙከራ አድርጓል::
ነዳጅን በሚመለከት ባለፉት ወራት በሙሉ በወር ቢያንስ እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር መንግሥት እየደጎመ ነው የመጣው:: ያ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ጉዳት እንዳያስከትል በነዳጅና በማዳበሪያ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት መንግሥት መድቦ ነው ለመሸፈን እየሞከረ ያለው:: ውጭ ያለው የገበያ ዋጋ ማሻቀብም እኛ ላይ ጫና ስላለው:: ለዚህ ከአጭር ጊዜ አንጻር ማዳበሪያም ይሁን ዘይትም ይሁን ስኳር የሚጎድለንን እያመጣን ነው ያለነው::
እናመጣለን፣ እያመጣን ነው ያለነው በዚያ ለማረጋጋት ይሞከራል:: ዋናው መፍትሔ ከረጅም ጊዜ አንጻር ያለው ነው :: የዋጋ ግሽበትን የምንፈታበት አንዱ መንገድ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው:: በተለይ ከምግብ ጋር ተያይዘው ያሉ የምግብ ሸቀጦች እራሳችንን የምንችልበትን መደላደል “ግራውንድ” ብንፈጥር አብዛኛው ችግር ይፈታል:: ስንዴ በበቂ ደረጃ ማምረት ብንችል ሰሊጥና ኑግ አምርተን አሁን ፋብሪካዎች ተከፍተዋል፤ ዘይት በአገር ውስጥ ማምረት ብንችል ፣መስኖ አስፋፍተን ሌሎችንም ነገሮች ማምረት ብንችል፣ በፍራፍሬ “ፍሩት” ላይ የጀመርነውን ማንጎ ፤አቦካዶ ፣ፓፓያ በስፋት እየተከልን ነው ፤ እነሱን ወደ ምርት የሚሸጋገሩበትን መንገድ ብንፈጥር እነዚህ በምግብ አንገብጋቢና አስፈላጊ ጉዳዮች በአገር ውስጥ ብናመርት የውጭ ገበያ የሚያመጣብንን ጫና ለመከላከል እድል ይሰጣል። እነሱን ከረጅም ጊዜ አንጻር የምንሰራቸው ስራዎች ናቸው ፤ አብዛኛው እዚህ ላይ ማተኮር ነው::
የአረንጓዴ አሻራም በቀጥታ ከዚህ ጋር ይያያዛል:: የአረንጓዴ አሻራ ዝም ብለን ባህር ዛፍና ጥድ ብቻ አይደለም የምንተክለው በጣም ብዙ የፍራፍሬ “ፍሩት” ተክሎች እንተክላለን:: በምግብ ራስን ለመቻል ስለሚያግዘን:: ዝናብ በበቂ ማግኘት እንድንችል ስለሚያግዘን፤ ዝናብ በበቂ ካገኘን ደግሞ አርሰን ምርታችንን ለማሳደግ እድል ስለሚሰጠን:: የውሀ ሀብታችን “የወተር ባንኪንጋችን” ላይም ተጨማሪ ጠቀሜታ ስላለው ። በጥቅሉ በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ በብዙ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶች ያመጣናቸውን ጥገናና ማሻሻያዎች በዋጋ ግሽበት ላይ አላመጣንም::
የያዝነው የሞከርነው ሰፋፊ እርምጃዎች አሉ:: ነገር ግን የሚቀሩን ነገሮች አሉ እየሰራንበት እንገኛለን:: አብዛኛው ምርት እያደገ ሲሄድ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ አለ:: ግን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ለምሳሌ ሱዳንን ብንወስድ የዛሬ አምስት ስድስት ወር አንድ ዶላር ስድሳ ፓውንድ በእነርሱ ይቀየር ነበር:: ዛሬ አንድ ዶላር ሦስት መቶ ስድሳ አካባቢ ፓውንድ ይቀየራል:: አምስት ስድስት እጥፍ በልጧል:: እያንዳንዱ ጎረቤት አገር ቢኬድ እንደዚህ ዓይነት ችግር አለ:: አጠቃላይ ዓለም ላይ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ሁኔታ ባላደጉ አገራት ላይ የሚያስከትለው ጫና አለ:: በእኛም ላይ ያ ጫና አለ:: ያንን ጫና ለመከላከል የምናደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ ሆኖ አሁንም ቢሆን የድሃውን ህብረተሰብ ክፍል ችግር ለመፍታት ሰፋፊ ሥራዎችን መስራት ይጠበቅብናል፤እሰራን ነው እንገኛለን::
ለምሳሌ የሸገር ዳቦን ስንጀምር አንዱ በረከሰ መንገድ ዳቦ ከተማ ውስጥ እንዲዳረስ ለማድረግ ነበር:: ሸገር ዳቦን ሰርተንም የዳቦ ፍላጎት ሊሟላ ስላልቻለ አሁን ከምርጫ በኋላ ለምርጫው ብሎ እንዳይመረቅ ስላልከኝ ከምርጫው በኋላ ተጨማሪ ፋብሪካ እናስመርቃለን ።በቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ዳቦ የሚጋግር ፋብሪካ:: ከውጪ በተገኘ ድጋፍ በቀዳማዊ እመቤት ቢሮ በኩል “በፈርስት ሌዲ ኦፊስ ” የተገነባ ነው:: ይህም አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የዳቦ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ተብሎ ይታሰባል:: ዘይት ፋብሪካዎች ሰሞኑን እየሰማችሁ ነው ስናስመርቅ እነሱ ምርታማነት ግብዓት ኖሮ ዘይት አገር ውስጥ ብናመርት ፣ስንዴ አምርተን ዳቦ አገር ውስጥ ብናመርት እነዚህ ጉዳዮች በዋጋ ላይ ያለውን ጫና እየቀነሱ ይሄዳሉ::
ግን ስራዎቹ በአንድ ምሽት “ኦቨር ናይት” የሚሰበሩ አይደሉም፣ መሰረታዊ ስራ ስለሚፈልጉ በእነዚያ ምክንያት ጊዜ ወስዷል:: መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት እያደረግን ነው:: ውጤት እንደምናመጣም ተስፋ አደርጋለሁ::
ጠያቂ፡- ከተጣበበ ጊዜዎት ላይ ቀንሰው ይህን ቃለ መጠይቅ እንድናደርግ ስለፈቀዱልን በጣም እናመሰግናለን::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡- እድል ስለሰጣችሁኝ እኔም አመሰግናለሁ :: እግዜር ያክብርልኝ:: እንግዲህ አገራችን ኢትዮጵያ ከእኛ ጥረት ከእኛ ልፋት ከእኛ ሙከራ በተጨማሪ ፈጣሪ በልፋቶቻችን ሁሉ እንዲያግዘን አገራችን እንዲጠብቅ አገራችን እንዲባርክ ሰላማችን እንዲያረጋግጥ ህብረታችንና አንድነታችንን እንዲጠብቅ ጸሎታችን ሁል ጊዜም መኖር ይኖርበታል::
ኢትዮጵያ ፈጣሪ አላት፣ ኢትዮጵያ ሕዝብ አላት፣ ኢትዮጵያ መንግሥት አላት በዚህ ምክንያት ተቀናጅተን እየጸለይንም እየሰራንም እንሻገራለን የሚል ሙሉ እምነት ነው ያለን:: ኢትዮጵያን የሚያሰጉ ጊዜዎች አልፈዋል:: ኢትዮጵያን የሚያስጨንቁ ጊዜዎች አልፈዋል:: ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚችል ኃይል የለም:: ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልገው ኃይል ሁሉ ፈርሷል:: አሁን ኢትዮጵያውያን ተደምረን ማፍረስ ያለብን ጉዳይ ድህነትን ነው:: ለዚህ ደግሞ ተባብረን አብረን ከሰራን ውጤታማ ጊዜ ከፊታችን አለ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2013