በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ እምነት ተከታዮች እርስ በእርስ እንዲጋጩ የተለያዩ ሴራዎች ተካሂደዋል። የዕምነት ተቋማት ተቃጥለዋል። የተለያዩ አማኞች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ ሴራ ተሸርቧል። ሆኖም ለዘመናት የኖረው የሃይማኖት መቻቻልና የሕዝቦች መተሳሰብ ሁሉንም አክሽፎታል። የሃይማኖት ተቋማት አንድነትና መቻቻልም ጸንቶ ቀጥሏል። ለመሆኑ የግጭቶቹ መንስዔዎች ምንድን ናቸው? ህጸጾችስ እንዴት መታረም ይኖርባቸው ይሆን?
መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ፤ የሃይማኖት ተቋም አቃጥል የሚል ሃይማኖት የለም። ይህ የሚደረገው አስተሳሰብን በሌሎች ላይ በሃይል ለመጫን ነው። ይህን አስተሳሰብን በሌሎች ላይ የመጫን ተግባር የእምነት ተከታዮች አይደሉም ፈጣሪም አላደረገውም። የእምነት ተቋማትን ማቃጠል ምንጩ ቂም፤ ጥላቻ፣ በቀልና ክፋት በሰዎች አዕምሮ ሲያድር ነው። የዚህ ምንጭ የአማኒዎች አዕምሮ በሃይማኖቶቹ አስተምህሮት ከመገራት ይልቅ በከፉ ሥራ መሰልጠኑ ነው። በኢትዮጵያ ክፍት ቦታ ሲገኝ መስጊድና ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት መታገል እንጂ፤ በአማኒያን ክፍት ጭንቅላት ውስጥ ቁም ነገር ለመዝራት አልቻልንም፤ በማለት የሃይማኖት ተቋማትን የአስተምህሮ መጓደል ይተቻሉ።
አመለካከት አለመያዝ፣ ድህነትና ኋላ ቀርነት፤ የመጠቀሳቸውን ያህል በውጭና በአገር ውስጥ ድሆችን እያነደዱ ዳቧቸውን የሚያበስሉ ሰዎችም አሉ። ከዚህም በላይ፤ የሃይማኖት ተቋማት ተቻችለውና ተከባብረው የራሳቸውን መብት ተግባራዊ ሲያደርጉ የሌሎችን መብት በማክበር እንዲሄዱ የሚያስገድድ ስርዓት አለመዘርጋቱ፤ ተስፋ መቁረጥ፤ የተሻለ ሀሳብ አምጥቶ በሃሳብ ማሳመን ሲያቅታቸው አሳቢውን የማጥፋት አዝማሚያ ለድርጊቶቹ ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ያብራራሉ። የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ መህመድ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት እየጠነከረ ነው። እነዚህ ጥቃቶች የእምነት መሰረት አላቸው ለማለት አይቻልም። በየትኛውም ዕምነት ቤተ እምነትን አፍርስ የሚል መመሪያ የለም።
በየትኛውም የእምነት ቦታ የሚሰበከው ሰው እርስ በእርሱ እንዲከባበርና እንዲዋደድ ነው። በዚህ ቦታ ጥቃት የሚሰነዝር ሰውም ሆነ ቡድን የአማኒነት ችግር አለበት። ለዚህ ችግር አንዱ መነሻ ምክንያት ቤተ እምነቶች እሴቶቻቸውን ለአማኞቻቸው በትክክል አለማድረሳቸው ነው። የሃይማኖት ተቋማት አማኞቻቸውን የማስተማር ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸውም ማሳያ ነው። ሁሉም ቤተ እምነቶች የአማኝ ችግር የለባቸውም። የአማኝ ጥራት ግን የሁሉም ቤተ እምነቶች ችግር ነው። የእምነት ተከታዮች በወንድማቸው ላይ እጃቸውን ለጥፋት ያነሳሉ። ያሳድዳሉ፣ ይገፋሉ፣ ንብረት ያወድማሉ፤ ይባስ ብለው ቤተ እምነት ላይ ጥቃት ያደርሳሉ። ይህን ሲያደርጉ ግን በእነርሱ የእምነት ተቋም ተመሳሳይ ጥቃት ላለመድረሱ ማረጋገጫ የላቸውም። ይህ ችግር የሁሉም ችግር በመሆኑ ቤተ እምነቶች በልባዊ አንድነት በእምነታቸውና ተከባብሮ በመኖር ኢትዮጵያዊ እሴታችን ላይ መስራት ይገባቸዋል ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ፤ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሃይማኖት ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆኑ የእምነት ካርድ በመምዘዝ ግጭት የመፍጠሪያ ምክንያት ያደርጉታል። በእምነቶች መካከል ያለውን ልዩነት ለችግር መንስዔ ስለሚያደርጓቸው የእምነት ተቋማት ይህን ተገንዝበው መስራት አለባቸው ሲሉ ያብራራሉ። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ጂይላን አብዲ በበኩላቸው፤ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃት ተንተርሶ በተደረገው ጥናት በሃይማኖት መካከል ግጭት ለመፍጠር ከኋላ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ታውቋል። እናም አንዱን ሃይማኖት በሌላው ለማስነሳት ይሰራሉ። አሁንም ህዝባዊ ለውጡን ተከትሎ የማይደግፉና ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በሃይማኖት ተቋማት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ምክንያት መሆናቸውን ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ንጉሴ መሸሻ፤ የሃይማኖት ተቋማትን የማጥቃት ተግባር መነሻዎች ጠባብ አመለካከት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍላጎት፤ ሃሳባቸው አልገዛ ሲላቸው በሃይማኖት ለመጠቀም መሞከር፣ በማህበራዊ መገናኛ የሃሰት መረጃ በመልቀቅ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ግጭቱን ማባባስ መሆናቸውን ይናገራሉ። ዶክተሩ እንደሚሉት፤ መገናኛ ብዙሃን አሉታዊና አወንታዊ ሚና አላቸው። ስህተቶችን እንዲታረሙና ልማት እንዲፋጠን የማድርጋቸውን ያህል ዜጎችን በሃይማኖት፤ በብሄር በመከፋፈል የማይፈልግ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ይችላሉ። በአገራችንም በማህበራዊ ሚዲያ ይህ አይነት ችግር ተፈጥሯል። ማህበራዊ ሚዲያ ከአወንታዊ ተግባሩ ይልቅ ፖለቲካዊ ጥላቻ በማራገብ ግጭቶች እንዲባባሱ አድርጓል። በመሆኑም ይህን አካሄድ ፈር መያዝ እንዳለበት ይመክራሉ።
መጋቤ ሀዲስ እሸቱ በበኩላቸው፤ የእምነት ተቋማት አማኞቻቸውን በአስተምህሮ መቅረጽ አለባቸው። መስጊድ ወይም ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ገንዘብ ከማዋጣት ባለፈ የሚያቃጥለውን ጭንቅላት ለመለወጥ ግንዛቤ ማዋጣት አለብን። መስጊድ ወይም ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል እሰይ የሚል አማኝ በህግ ወንጀለኛ፤ በእምነት ሀጢያተኛ ስለሆነ ተጠያቂ ነው። የእምነት ተቋማት ይህን መስራት አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ። ከዚህም በተጨማሪ፤ መንግስትም በዕምነት ጉዳይ ላይ የጠራ አካሄድ መከተል አለበት። በየሰፈሩ የሚታየውን የድምጽ ብክለት የሚያስተካክል አሰራር ለሁሉም ሃይማኖቶች መዘርጋት ይገባዋል። በሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት በሚሰነዝሩ አካላትም ጠንካራ ርምጃ መውሰድ አለበት የሚል ሀሳብ ያነሳሉ። እምነትና ፖለቲካ አይቀላቀሉ የሚለው ሀሳብ ብዙ አልቀበለውም የሚሉት መጋቤ ሀዲስ እሸቱ፤ መነጋገር ያለብን በመጠኑ ላይ ነው ይላሉ። በሃይማኖት ተቋማት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ይንቀሳቀሳል። ብዙ ሰዎች ተቀጥረዋል። የሚንቀሳቀሰው ገንዘብም ሆነ የተቀጠሩት ሰዎች ከመንፈሳዊ ህይወት ይልቅ ለዓለማዊ ሁኔታ ይቀርባሉ። መንግሥት በሃይማኖት ቀኖና ገብቶ አይፈተፈትም እንጂ፤ ዓለማዊ ሁኔታዎች ሲጓደሉ ማስተካካል አለበት። በር ዘግተው ወንጀል መስራት የሚፈልጉ፤ “ይህን የእምነት ተቋም ከያዝን ስልጣናችን ይረጋል” የሚሉ ፖለቲከኞች ትክክለኛ መስመር መያዝ አለባቸው። በእምነት ተቋማት ያሉ አባቶችም ከፈጣሪያዎች ይልቅ የመንግስት ጥበቃ የሚያምኑ መሆን የለባቸውም።
አቶ ጂይላን በበኩላቸው፤ በሃይማኖት ተቋማት እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠር ስሜታዊ ሆኖ ወደርምጃ ከመግባት ይልቅ ህዝቡ ለምን ብሎ መጠየቅ አለበት። መወያያት ይገባዋል። በግርግሩ ጥቅማቸውን ለሚያሳድዱ ሰዎች እጅ መስጠት የለበትም። አጥፊዎችንም ለጸጥታ አካላት አሳልፎ መስጠት አለበት። የአገራችንን በሃይማኖት መቻቻል የዓለም ምሳሌነት ማስቀጠል አለበት። ከዚህ ውጭ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ለማንም አይጠቅምም ይላሉ። ኡስታዝ አቡበከርም፤ መንግሥት በቤተ ዕምነቶች ጉዳት ሲደርስ፤ ህግና ስርዓት ሲጣስ አስተማሪ እርምጃ መወሰድ አለበት። ህግና ስርዓት መኖሩንም አይተው እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ ይገባል። ሁሉም ዜጋ አገሪቱ ወሳኝ መታጠፊያ ላይ መሆኗን ተግንዘቦ ለውጡ እንዳይደናቀፍ መስራት አለበት። ለውጡን የማይደግፈው ወገን ለማደናቀፍ የአቅሙን የሚፍጨረጨርበት ጊዜ ነው። ለዚህ ትልቁ ካርድ ሀይማኖት በመሆኑ በመስጊድ ወይም በቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት ሲደርስ ከስሜት በመቆጠብ ችግሩን መፍታት ይገባል። ችግር እንዳይፈጠር ሁሉም መስራት አለበት። ይህን ማድረግ ሳንችል በጥፋት ውስጥ ከገባን ግን አገርም ታሪክም ይቅር አይለንም ባይ ናቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ