የዛሬ 53 ማለትም በ1960 ዓም ነበር ወደዚህች ምድር የተቀላቀሉት:: በአዲስ አበባ ከተማ ጎፋ አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት:: በወቅቱም በአካባቢያቸው ባለው የነጻነት ጮራ ትምህርት ቤት በመቀላቀል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አንድ ብለው ጀመሩ፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲጨርሱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት አብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ነው:: ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን አሰፋ ::
የዛሬው የህይወት እንግዳችን ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን አሰፋ በተለይም በታዋቂ ሰዓሊነትና በሞዛይክ አርት ስራቸው ከአገር ውስጥ እስከ ውጪው አለም ድረስ ታዋቂና በርካታ ስራዎችንም የሰሩ ናቸው በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገሰላም የስነ ጥበብና የዲዛይን ትምህርት ቤት በመምህርነት እያገለገሉ በርካታ ጥበበኞችንም እያፈሩ ይገኛሉ:: እኛም ጥበብንና የጥበብ ህይወታቸውን በተመለከተ ቆይታን አድርገናል::
አዲስ አበባ ላይ ተወልደው ያደጉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ከልጅነታቸው ጀምሮ የስዕል ፍቅር እንደነበራቸው ይናገራሉ:: ስዕልን በዚህ ያህል ደረጃ ሲወዱትና ሲሰሩትም እንጀራቸው ማድረግን ያስቡ እንደነበር ይናገራሉ:: በአንደኛ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳሉም በስዕል ችሎታቸው ከእኩዮቻቸው በላይ ከፍ ብለው ይታዩም ስለነበር በተለይም ሳይንስና ህብረተሰብ መጻህፍት ላይ ያሉ ስዕሎችን በትምህርት ቤት ግድግዳዎች ላይ እንዲስሉ ይታዘዙ ነበር:: ይህም ብቻ ሳይሆን የስዕል ችሎታ የሌላቸውን መምህሮቻቸውንም ለማስተማሪያ ይረዳ ዘንድ በጥቁር ሰሌዳ ላይ ስዕል በመሳል ያግዙም እንደነበር ይናገራሉ::
“….. ይህ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስዕል ተሳትፎዬ ደግሞ ውስጤ ሰዓሊ የመሆን ህልም እንዳለኝ አሳወቀኝ፤ ሰዎችም ይመሰክሩልኝ ጀመር:: ይህም ቢሆን ግን ትምህርቴን በፍጹም ችላ ያላልኩ ከመሆኑም በላይ በትጋትም እማር ነበር” ይላሉ::
” ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ በሁለት ሀሳብ ተውጬ ነበር፤ አንድ ልቤ ስዕል ትምህርት ቤት ግባ ሲለኝ ሌላው ልቤ ደግሞ ተግባረዕድ ገብተህ የቴክኒክ ሰው ሁን ይለኝ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ስዕሉ አመዘንኩና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ በቀጥታ ወደ “በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገሰላም ” የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መጣሁ” ይላሉ::
በሚወዱት የጥበብ ስራ እዚህ ለመድረሳቸው ደግሞ የቤተሰባቸው ከተቃውሞ የጸዳ ድጋፍ ከፍተኛ የሆነ እገዛን እንዳደረገላቸው የሚገልጹት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን እንደውም ” ስዕል ጥሩ ነው፤ እንጀራ ያወጣል” ሁሉ ይባሉም እንደነበር በመግለጽ ይህ ሁኔታ ደግሞ የሚፈልጉትን ለመሆን እድል ስለሰጣቸው በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ :: ተሳክቶልኛልም ይላሉ::
ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ወደ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ ለመምጣት የወሰኑት ውስጣቸው ያለውን የስዕል ስሜት በማዳመጥ ነበር እንደውም ይላሉ” በወቅቱ እንኳን ትምህርት ቤቱን አራት ኪሎን እንኳን አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን የእኔን ችሎታ የተመለከቱ ሰዎች ወደዛ ሄጄ ችሎታዬን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳሻግር ገፋፉኝ፤ እኔም ገባሁበት ” ብለዋል::
ወደ ትምህርት ቤቱ ከመጡ በኋላም የሚፈለግባቸውን የትምህርት ማስረጃ እንዲያቀርቡ የትምህርት ቤቱን የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉን የሚያስታውሱት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን እነዚህን ሁሉ ካሟሉና ፈተናውንም ከወሰዱ በኋላ በቀጥታ ትምህርት ቤቱን መቀላቀል መቻላቸውን ነው የሚናገሩት::
“ወደ ትምህርት ቤቱ ስመጣ የትምህርት ማስረጃዬን ከተቀበሉኝ በኋላ የፈተናውን ቀን ነግረውኝ ወደቤቴ ተመለስኩ፤ ከዛም ፈተናውን በመውሰድ አልፌ ትምህርት ቤቱን ተቀላቀልኩ፤ በነገራችን ላይ ወደ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ የመጡ ሁሉ አይገቡም ነበር፤ ምክንያቱም ፍላጎት ያለውን ብቻ ሳይሆን ብቃት ያለው ይመረጥ ስለነበር ብዙዎች ፍላጎት ቢኖራቸውም የሚሰጠውን ስልጠና እንዲሁም ፈተና ስለማያልፉ አይገቡም ነበር፤ እኔ ግን እድለኛ ሆኜ በመጀመሪያው ዙር ፈተናዬን አልፌ ትምህርት ቤቱን በ1976 ዓም ተቀላቀልኩ” ይላሉ::
በወቅቱ በስነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ እጅግ በጣም እውቀት ያላቸውና ከኢትዮጵያ ውጪ ተልከው ትምህርታቸውን አጠናቀው የመጡ መምህራን ስለነበሩ ከእነሱ ጋር በመገናኘት ጥሩ እውቀትን ለአራት አመታት ቀስመው በዲፕሎማ ደረጃ መመረቃቸውን ይናገራሉ::
በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ስለነበራቸው የትምህርት መረጃቸውን ለስኮላር ሺፕ ከፍተኛ ኮሜቴ በማስገባት በአመቱ የከፍተኛ ትምህርት እድል እንዳገኙም ይናገራሉ:: የትምህርት ማስረጃቸው ታይቶና ተገምግሞም ወደቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት የአሁኗ ሩሲያ በማቅናት ትምህርታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲከታተሉም ተፈቀደላቸው::
በ1980 ዓ.ም በተሰጣቸው ነጻ የትምህርት እድል (ስኮላር ሺፕ) አማካይነት ወደ ሩሲያ አቀኑ፤ በወቅቱ ጉርምስና እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብ ተለይቶ ሩቅ አገር መሄድ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ እንደተፈታተናቸው የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ይህ ሁኔታ ደግሞ እስከ አንድ አመት ያህል አስቸግሯቸውም ነበር::
በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ ተነስቶ እጅግ ቅዝቃዜ ወዳለበት ሩሲያ መሄድና አየሩን መለማመድ በጣም ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ ይህም ቢሆን ግን አላማ ነውና ሁሉንም በጽናት ተቋቁሞ ማለፍን አቅደው ግባቸውን ለመምታት መጣጣራቸውን ይ ናገራሉ::
በሌላ በኩልም ከአገር ሲወጡ ምንም ዓይነት የቋንቋ ዝግጅት አለማድረጋቸው ከዛም በላይ ደግሞ ትምህርቱ የሚሰጠው በሩሲያኛ መሆኑ ሌላው መታለፍ የሚገባው ፈተና ሆኖ እንዳጋጠማቸውም የሚያስታውሱት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ፤ ነገር ግን ድል ያለ ፈተና የማይሆን ነገር ነውና ይህንን የቋንቋ ችግራቸውን የተመለከተው ትምህርት ቤቱ አንዱን ዓመት የቋንቋና የሙያ ዝግጅት ትምህርት እንዲያደርጉ አመቻቸላቸው:: ይህም ቢሆን ግን ቀላል እንዳልነበር የሚገልጹት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን በአንድ አመት ውስጥ ቋንቋቸውን ተምረው ጨርሰው ወደ አካዳሚው መግባት ስለነበረባቸው እንደምንም ትምህርቱን መጀመራቸውን ያስታውሳሉ::
“…በወቅቱ እነዚህን መሰል ፈታኝ ነገሮች ይኑሩ እንጂ ከእኛ የሚጠበቀው መማርና መማር ብቻ ነበር፤ እነርሱ ምግባችንን߹ መኖሪያ߹ አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት ግብዓቶችን ያሟላሉ ፤ በመሆኑም የቋንቋውን ችግር ከፈታን በኋላ የአንደኛ ዓመት ትምህርታችንን ጀመርን ፤ ከአገሪቱ ዜጎች ጋርም እኩል መኖር ቻልን ” ይላሉ::
በሌላ በኩልም ሩሲያውያን በትምህርት ስርዓታቸው እጅግ የሚያስቀኑ ከመሆናቸውም በላይ ማንም ሰው የመማር ፍላጎት ካለው ጥሩ ሆኖ የሚወጣበት መሆኑንም ይናገራሉ፤ ከዛም በላይ ደግሞ በተለይም እርሳቸው ከአለ ፈለገሰላም የቀሰሙት የስዕል ጥበብ እውቀት እጅግ እንዳገዛቸውና አካባቢ ይቀየር እንጂ ለትምህርቱ ምንም አዲስ እንዳልሆኑ ነው የሚናገሩት::
“…በነገራችን ላይ” ይላሉ “አዲስ አበባ አለ ፈለገሰላም የስዕል ትምህርት ቤት ሲያስተምሩኝ የነበሩ መምህራን እዛው ሩሲያ ሄደው ተምረው የመጡ ኢትዮጵያውያን ናቸው:: እነሱም የሩሲያውያኑን የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ተከለትለው ምንም ሳይሰስቱ ሳይቆጥቡ እውቀትን ሲሰጡኝ የነበረ በመሆኑ እዛም ያለው ትምህርት ያን ያህል ከባድ ሆኖ አላገኘሁትም ” ብለዋል::
በሌላ በኩልም እኛ ኢትዮጵያውያን በነጮች አገዛዝ ውስጥ አለማለፋችን በትምህርትም ይሁን በስነ ልቦና የበላይነት ለመያዝ የምንችል ነን ፤ከእኔ ጋር በትምህርት ላይ የነበሩ አፍሪካውያን Õደኞቼ ግን የቅኝ ተገዥነት ስሜት ስለነበራቸው ነጮቹን ሲያዩ የመፍራት የመሸማቀቅ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የማየት ሁኔታ ይታይባቸው ነበር፤ እኛ ደግሞ እንደዛ አይደለንም:: አንዳንድ ጊዜ እንደውም ራሴን በመስታወት እስካላየሁት ድረስ ጥቁርነቴን ራሱ እረሳውም ነበር:: ይህ ደግሞ ትምህርቴንም በአግባቡ እንድከታተል አግዞኛል ይላሉ::
” …. እንግዲህ ሩሲያ አንዱን ዓመት በቋንቋ ትምህርት አሳላፍኩ; ስድስቱን ዓመት ግን በጣም ጠንካራ ተማሪ በመሆን አጠናቀቅሁ፤ በሩሲያ የትምህርት ህግ መሰረት ደግሞ በስድስቱ ዓመት የትምህርት ጊዜ ውስጥ በውጤት ላይ ምንም ዓይነት’ ሲ ‘ ( c ) ያላመጣ ተማሪና የመጨረሻ የመመረቂያ ስራውን ‘ኤ’ (A) ያመጣ ተማሪ ውጤቶቹ ይደመሩና በመደበኛነት ከሚሰጠው ዲግሪ በተጨማሪ (የቀይ ኮከብ ዲግሪን) እንዲያገኝ ይሆናል:: እኔም በዚህ ማዕረግ ውስጥ አልፌ ትምህርቴን በቀይ ኮከብ ዲግሪ ደረጃ ለማጠናቀቅ ችያለሁ” ይላሉ::
ለሰባት አመታት በትምህርት አንድ አመት ደግሞ በተጨማሪ ጊዜነት ያሳለፉትን የሩሲያ ቆይታቸውን አጠናቀው ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ አገሬ ገብቼ ያስተማረኝን ህዝብ ላገልግል በማለት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ::
ኢትዮጵያ ውስጥ ስዕልን ሰርቶና ለገበያ አቅርቦ መተዳደር በጣም ከባድ ቢሆንም ልሞክረው በማለት ስራውን ጀመሩት፤ በዚህም ለስድስት ወር ያህል ከሰሩ በኋላ ሁኔታዎች ባሰቡት ልክ ስላልሆኑላቸው ሌላ ስራ ወደመፈለግ አመሩ::
” ወደ አገር ከገባሁ በኋላ ያሉት ስድስት ወራት እጅግ የምወዳቸው ጊዜያት ነበሩ ፤ ጠዋት ከመኝታዬ ተነስቼ ስዕሌን እሰራለሁ፤ ምሳ በልቼ ቡናዬን ጠጥቼ ተመልሼ ስዕሌ ላይ ነኝ፤ ይህ ለእኔ በጣም ምርጥ ጊዜ ነበር፤ ግን ደግሞ በዚህ መልኩ መቀጠሉ ትንሽ ስለከበደኝ ወደ ሌላ ስራ ገባሁ”::
በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኮምፒውተር ግራፊክስ ባለሙያ ይፈልግ ነበር፤ እርሳቸው ደግሞ ሩሲያ ከስዕል ትምህርታቸው ጎን ለጎን የኮምፒውተር ግራፊክስ ሙያውንም ተምረውት ስለነበር ይህንን የሚያውቁ ሰዎች ጥቆማ ሰጡላቸው ፤ እርሳቸውም ወደ ዲጂታል ዓለም ለመግባት እየተንደረደረ የነበረውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእውቀታቸው ለማገዝ በጊዜያዊ ሰራተኝነት ተቀጠሩ ::
“…. ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ስራውን ብጀምርም እኔ ሰዓሊ ነኝ; ቅድሚያ የምሰጠውም ለሙያዬ ነው; በመሆኑም አንድ ቀን እሰራለሁ; በሁለተኛው ቀን ስዕሌን እሰራለሁ፤ በዚህ ከተስማማችሁ እንቀጥል አልኳቸው; እነሱም ተስማምተው ስራውን ጀመርኩ:: ስራዬን በነጻነት እየሰራሁ አሁን ላይ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ እንደ አውደ ሰብ ߹የዜና መግቢያዎች ߹ ስኬት እና ሌሎችንም ፕሮግራሞች ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ ሙዚቃውን፤ እኔ ደግሞ ግራፊክሱን በመስራት ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ ስራዎቹም እስከ አሁን ድረስ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው” ይላሉ::
በዚህ ሁኔታ ለአራት ዓመታት ስራውን ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ድርጅቱ በቋሚነት ተቀጥረህ ስራውን መስራት አለብህ አላቸው ምንም እንኳን ይህ ሁኔታ ከሚወዱት ስራቸው ጋር የሚጋጭና የማይፈልጉት ቢሆንም ጫናዎች ስለበዙባቸው እሺ ብለው ተቀበሉ፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገሰላም የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህራን እፈልጋለሁ የሚል የስራ ማስታወቂያን አወጣ ፤ ይህንን ማስታወቂያ አይተው ቢመጡም የደመወዙ ልዩነት ከፍተኛ ስለሆነባቸው ሳይስማሙ ቀሩና እዛው ቴሌቪዥን ላይ መስራትን ቀጠሉ::
ነገር ግን ቴሌቪዥን ክፍያው ጥሩ ቢሆንም የስራው ባህርይና ከስራ ሀላፊዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ብዙም አስደሳች ስላልሆነላቸው ልባቸው ወደ ማስተማሩ አዘነበለ ፤ እድለኛም ሆኑና ትምህርት ቤቱ ያንኑ ማስታወቂያ በድጋሚ አወጣ ፤ አሁን ወደሚወዱት የጥበብ ስራ በመምህርነት የመቀጠርን እድል አገኙ::
“….. መጀመሪያም ማስታወቂያውን አይቼ ከመጣሁ በኋላ በደመወዝ ምክንያት መመለስ አልነበረብኝም፤ ግን ያንኑ ቀጥሎ ሲያወጡ አይኔን ሳላሽ ነው መጥቼ የገባሁት:: እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የትምህርት ቤቱ የደመወዝ ስኬልም ተስተካከለና ጥሩ ሆነ፤ በዚህም በጣም ደስተኛ በመሆን ስራዬን ጀመርኩ” ይላሉ::
በትምህርት ቤቱም በጣም ጥሩ ጊዜን ማሳለፋቸውን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ተማሪዎቻቸውን እያስተማሩ፣ እያበቁና እያስመረቁ ከማውጣት ጎን ለጎን ያልተለመደውን የኮምፒውተር ግራፊክስ ስራ እንዲለመድ በማስተማር ባለሙያዎችን በማፍራት ከአንድ ኮምፒውተር ተነስተው ብዙ ኮምፒውተሮች በትምህርት ቤቱ እንዲኖሩ በማድረግና የኮምፒውተር ግራፊክስ የትምህርት ክፍል ራሱን ችሎ ተደራጅቶ ባለሙያዎችን እንዲያፈራ በማድረግም በኩል ከፍተኛ የሆነ ሚናንም ተጫውተዋል::
“… ማስተማር ወይም አስተማሪ መሆን እጅግ በጣም ደስ ይላል፤ ለምሳሌ እኔ በአንድ የትምህርት ዘመን አስር ተማሪን አስተምሬ የማስመርቅ ከሆነ አስር አይነት ሀሳብን እቀበላለሁ፤ ይህ ደግሞ ለእኔ የቤት ስራዬ ነው፤ በዚህ መካከል ደግሞ ይህንን የቤት ስራ ይዤ ሄጄ እንዴት ነው ቅርጽ የማስይዘው የሚለውን ለመስራት ብዙ መጽሀፍትን አገላብጣለሁ ፤ በዛ ውስጥ ደግሞ ለእኔም የማውቀው ነገር ብዙ ነው ለራሴም የፈጠራ ስራ በጣም ስለሚረዳኝ ማስተማር ህይወቴ ሆኖ አብሮኝ ኖሯል”::
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገሰላም የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት አሁን ላይ በዓመት በጣም ጥቂት ተማሪዎችን ብቻ ነው የሚቀበለው ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ለስዕል ስራ (ማስተማሪያ) የሚሆኑ ቁሳቁሶች በጣም ውድ ከመሆናቸው ߹ በቀላሉ ካለመገኘታቸውና ቶሎ ቶሎም የሚያልቁ ከመሆኑ አንጻር ትምህርት ቤቱ ብዙ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዳያስተምር አድርጎታል ይላሉ::
“….. እንደነገርኩሽ ማስተማር እጅግ የሚያስደስት ብዙ ነገር የሚገኝበት ሁሌም አዲስ የሚያደርግ ነው:: የእኛ የጥበብ ትምህርት ቤት ደግሞ ከሌሎች ሙያዎች ለየት ይላል በዚህ ምክንያት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ግዢዎች ሲዘገዩና አንዳንድ ነገሮች ሲፈጠሩ ትምህርቱ እንዳይስተጓጎል እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ከኪሳችን ሁሉ እያሟላን የምንሰራበት ጊዜ ብዙ ነው” በማለት ለትምህርት ቤቱና ለሙያው ያላቸውን ፍቅር የማስተማር ፍላጎታቸውን ይናገራሉ::
“የአገር እድገት የሚለካው በዋና ዋና ከተሞች አካበቢ በሚገነቡ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ብቻ አይደለም የጥበብ ስራዎችም በጣም ወሳኝ ናቸው”፤ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን “ሌላው ደግሞ ከከተማ ግንባታ አንጻር በተለይም የሞዛይክ አርት ወሳኝ በመሆኑ እንደ አገርና ህዝብ ገላጭ የሆኑ ቋሚ የስነ ጥበብ ስራዎች ሊኖሩን ይገባል” ይላሉ:: ይህ ደግሞ በድሮ ጊዜም ጀምሮ በአገራችን በህንጻዎች አደባባይ በቤተ እምነቶችና በሌሎችም ቦታዎች ላይ ስናሰፍራቸው የኖርን ነው፤ አሁንም ይህንን ሁኔታ አስቀጥሎ ህዝቡ የኔ የሚለው መገለጫ እንዲኖረው መስራት ያስፈልጋል::
በሌላ በኩልም የከተሞቻችን እድገት እኛነታችንን የጠበቀ ይሆን ዘንድ በተለይም ፖሊሲ አውጪዎች በሚሰሯቸው በእያንዳንዱ ስራዎቻቸው ውስጥ ለጥበብ ስራ ትኩረት ቢሰጡ መልካም ነው:: ሲሉ ይመክራሉ::
በተለይም አሁን እንደ አገር የጀመርነው ለውጥ ለጥበብ ትኩረት የሰጠ ከመሆኑ አንጻር የእኛ ትምህርት ቤት ሚና ላቅ ያለ ስለሚሆን መንግስት ከላይ ከላይ ብቻ ሳይሆን ወደውስጥ ዘለቅ ብሎ አይቶ ባለሙያዎችን ነቅሶ አውጥቶ ጥበቡን ቢጠቀምበት በተለይም የሚሰሩ ቋሚ የሆኑ የስነ ጥበብ ውጤቶች ላይ ትኩረት ቢሰጥ መልካም ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን አንዳንድ ጊዜ አንድ የጥበብ ስራ ተሰርቷል ለማለት ብቻ በችኮላ ይሰራና ኋላ ላይ ለማፍረስ እንኳን አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ ይስተዋላል፤ በመሆኑም ጥበብን በአግባቡና በልኩ ራሳችንን ልንገልጽበት ይገባል::
” ….በእኔ ልምድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ላይ ብዙ ስራዎች ሰርቻለሁ፤ ወላይታ ሶዶ ላይ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የወላይታን ህዝብ የሚወክል ሀውልት አቁመናል፤ ይገርምሻል ይህንን ሀውልት ስንሰራው መጀመሪያ ወደህዝቡ ወርደን ሀሳብ ነው የሰበሰብነው ፤ ይህ ሀሳብ ደግሞ በወላይታ ባህል “ገሟአ” የሚባል እሴት ሲሆን ይህ ምን ማለት ነው፤ አንዲት ታታሪ ሴት ብዙ ከብቶችን ማርባት ስትችል በማህበረሰቡ ውስጥ ልዩ ክብር ታገኛለች ፤ እናም ይህንን ስራ ከህዝቡ ውስጥ አውጥተን በሞዛይክ ጥበብ ከሽነን ሀውልት አድርገን አቆምነው በህዝቡ ዘንድም በጣም ተወዳጅ ሆነ” ይላሉ::
እንደዚህ ዓይነት ስራዎች ዝም ተብለው አይደለም ህዝብ ላይ መጫን ያለባቸው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን መቅደም ያለበት እነሱ ምን አላቸው? እኔ ደግሞ በስነ ጥበባዊ ውበት ምን ላውጣ? የሚለው በከፍተኛ ሁኔታ ሊታሰብ ይገባል ::
እዛው ወላይታ ላይ የንጉስ ጦናን የጀግንነት ታሪክ የሚዘክር ሀውልት እንድንሰራ በክልሉ መንግስት ስንጠየቅ መጀመሪያ ያደረግነው የቱጋ መኖሪያ ቤታቸውን ነበር߹ የቅርብ ሰዎቻቸው እነማን ናቸው? የልጅ ልጆች ካሉና የሚናገሩት ታሪክ ካለ በማለት ብዙ ጥናት ተደርጎ በመጨረሻም የልጅ ልጃቸው ተገኝቶ ምን እንደነበሩ ምስላቸው መንፈሳቸው ምን አይነት እንደሆነ በመረዳት ባህል ማዕከላቸው አዳራሽ መግቢያ ላይ 7 ሜትር በ 7 ሜትር የሚሆን ሞዛይክ መስራታቸውን ይናገራሉ::
በዚሁ መሰረት ሀዋሳ ላይ የባህል አዳራሹን ጨምሮ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ያለውንና የሀዋሳ ልዩ ምልክት የሆነውን የእንሰት ሙሽራ በአደባባዩ እንዲሁም እዛው ሀዋሳ ላይ ብዙ ታሪክ ያላቸውን የወልደአማኑኤል ዱባለ ሀውልት ገላጭ በሆነ የጥበብ ስራ በመንደፍ የህዝብ ማስታወሻ እንዲሆን አድርገዋል::
በሌላ በኩልም የስዕል ስራዎቻቸው በተለያዩ ድርጅቶች ፣ በሸራተን አዲስ ሆቴል የውድ እቃዎች መቀመጫና በኮሪደሮች ግራና ቀኝ ተሰቅለውም አስደናቂ ውበታቸውን ለተመልካቾቻቸው እየገለጹ ይገኛሉ::
በአለም አቀፍ ገበያ ላይም ተወዳዳሪ የሆኑ የስዕል ስራዎች እንዳሏቸው የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ከሁለት ወር በፊት ለንደን ላይ ስራቸው ተሸጦ ለአገርም የውጭ ምንዛሪ ማምጣቱን በመግለጽ ወደፊትም ሌሎች በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ፕሮሞተሮች እየጠየቁ በመሆኑ በቀጣይ ሁኔታዎች እየታዩ ለአገርም ለራስም ጥቅም እንደሚሰራ ተናግረዋል::
በእኛ አገር እንደዚህ አይነት የህዝብ የሆኑ በትክክል ማንነትን የሚገልጹ የጥበብ ስራዎችን ለመስራት ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች አሉ ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ይህ የሆነው ደግሞ ፖሊሲ አውጪዎቹም ሆኑ ህዝቡ ጥበብን የሚረዳበት አተያይ በጣም ገና መሆኑ ነው :: ይህም ቢሆን ግን ትንሽ ቀዳዳ ስትገኝ እሷን በማስፋትና እንስራ ብለን ገፍተን በመሄድ እየሰራን ነው ይላሉ::
አዲስ አበባ የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ መናኸሪያ እንደመሆኗ እንደዚህ አይነት የጥበብ ስራዎች በብዛት መሰራት አለባቸው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን አሁን ከለውጡ በኋላ እንደዚህ አይነት አሻራ የሆኑ ነገሮችን የመስራት ፍላጎት አለ፤ ግን ደግሞ ስራው የሚሰራው በችኮላና ጥራቱን ባልጠበቀ ሁኔታ ብሎም በስራው ብዙ ልምድ ባላካበቱ ባለሙያዎች በመሆኑ ገላጭነቱ ላይ የራሱን መጥፎ ሁኔታ እየፈጠረም መሆኑን ነው የሚናገሩት::
” ….መዲናችን እያደገች ነው፤ የአፍሪካ መዲና ናት፤ የምንመኘውም ብዙ ነገር ነው፤ ከዚህ አንጻር ስራዎች ከተሰሩም በባለሙያ (ፕሮፌሽናል) በመሆነ መልኩ ቢሆን ጥሩ ነው:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ የእኛ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ እኔንና እኔን መሰል ባለሙያዎች አሉ፤ በነዚህ ሰዎች ነው ሊሰራ የሚገባው የችኮላና የለብለብ ስራ ኋላ እያየነው ይወድቃል:: በመሆኑም ስራዎችን ከባለሙያ ማግኘት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ከመሆኑም በላይ እኛነታችንን ለተቀረው አለም በሚገባ ለማስተዋወቅ ያግዛል” በማለት አሁን ላይ የሚያዩትን የጥበብ ስራ ግድፈት ይናገራሉ::
ጥበብ የማይገባበት፣ የማይሆነው ነገር የለም ፤ ሁሉም ሰው በዚህ ውስጥ ቢያልፍ መልካም ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን አሁን ላይ የስነ ጥበብ ትምህርት በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካቶ ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ሊሰጥ ነው ተብሏል፤ ይህ የግድ የሚያስፈልገንም ነው ምክንያቱም አንድ ሰርጅን ምስልን ማገናዘብ ካልቻለ የቱጋር ቆርጦ የት እንደሚቀጥል ፤ አንድ ደም ስር የት ጀምሮ የት እንደሚያበቃ ለማወቅ ይቸገራል:: መካኒክም ለመሆን ስዕል መቻል ወሳኝ ነው በመሆኑም ይህ ሁለገብ የሆነን ጥበብ በተቻለ መጠን በሁሉም ዘንድ እንዲሰርጽ ማድረግ ይገባል:: እንደተባለውም በትምህርት ስርዓት ውስጥ የሚገባ ከሆነ በጣም ጥሩ ነው::
በጠቅላላው ከተሞቻችን እያማሩ መሄድ አለባቸው ከተባለ የስነ ጥበብ ውጤቶቹ ጥራታቸውን የጠበቁ ሊሆኑ ይገባል:: የለብ ለብ ስራ የትም ስለማያደርሰን ፖሊሲ አውጪዎችና ስራውን የሚያሰሩ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ባለሙያዎችን መጠቀም አለባቸው በማለትም ሙያዊ ምክራቸውን ይለግሳሉ::
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን በስራቸውም በኑbቸውም ስኬታማ እንደሆኑ ይናገራሉ:: “አሁን ባለሁበት ሁኔታ ግን እኔ ስኬታማ ነኝ:: በጥበብ ስራዬም አሻራዬን እያስቀመጥኩ ነው ብዬ አስባለሁ” በማለት ስለራሳቸው ይናገራሉ::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም