መንግሥት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሃዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ ቆይቷል።ለዚህም ገና ከመነሻው ጀምሮ ይህንን ሥራ በኃላፊነት የሚያስፈጽመውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ የሄደበት ርቀት አንድ ማሳያ ነው።
የለውጡ መንግሥት ወደሥልጣን በመጣ ማግስት የሪፎርም ሥራ ከተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው።ቀደም ሲል የገዢው ፓርቲ አንድ ክንፍ በሚል ከሚወቀሱ ተቋማት አንዱ የነበረው ይህ ተቋም በለውጡ ማግስት በጠንካራና ጽኑ አቋማቸው ከእውነት ጋር ለመጋፈጥ ወደኋላ በማይሉ አመራሮች እጅ ገብቶ ሥራውን እንደ አዲስ ጀመረ።
ቦርዱ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮም ይህንን ምርጫ በነፃነትና በገለልተኝነት ለማከናወን በገባው ቃል መሠረት ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር እየመከረና ሕግን መሠረት እያደረገ ሥራውን ሲሰራ ቆይቷል።
ቦርዱ ምርጫውን ቀደም ሲል በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማከናወን ቁርጥ አቋም ቢኖረውም በአገራችንም ሆነ በመላው ዓለም በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለማካሄድ አልቻለም።በመሆኑም ሕጉን ተከትሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመነሻ ሃሳብ በማቅረብና በማስወሰን በሕጋዊ መንገድ ምርጫው እንዲራዘም አደረገ።
የቫይረሱ ስርጭት በአጭር ጊዜ የሚቆም ባለመሆኑና በነበረው ግንዛቤም ስርጭቱን እየተከላከሉ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል በታመነበት ጊዜ ምርጫው እንዲካሄድ በመወሰኑ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም የምርጫው ዕለት እንዲሆን ተወሰነ።
ያም ሆኖ ግን ይህ ዕለት እስከሚመጣ ድረስ ጥቂቶች ጥርጣሬ አልተለያቸውም ነበር።በተለይ ምርጫው እንዳይካሄድ ጫና ሲያደርጉ የነበሩት የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ አንዴ የምርጫ ታዛቢዎችን እንልካለን፤ ሌላ ጊዜ አንልክም በሚል ወዲህና ወዲህ ሲላጉ ስለነበር በዚህ ሁኔታ ትዝብት ሲያተርፉ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶችና መፈናቀሎች የተነሳ እንዲሁም ሸኔና ህወሓትን የመሳሰሉት አሸባሪ ኃይሎች ከውጭ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ምርጫው በሰላም እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚለው ስጋት ከብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልብ ውስጥ ነበር።
ሆኖም መንግሥት ሰላምን ከማስከበር አንጻር በቂ ዝግጅት ማድረጉን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።በተለይ አሸባሪ ቡድኖችም ሆኑ የውጭ ኃይሎች ይህንን ምርጫ እንዳያደናቅፉ በቂ ዝግጅት ከማድረጉም በተጨማሪ በዚህ ምርጫ ላይ ማንም ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ የራሱን ቅድመሁኔታ በተገቢው ሁኔታ ማሟላቱን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።
ከዚያም ባሻገር ምርጫው ገና ከመካሄዱ በፊት እንዲኮላሽ ለማድረግ የተሞከረበት ሁኔታም እንደነበር የሚታወስ ነው።ከነዚህም ውስጥ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅድመ ምርጫው በፊት በሰላማዊ መንገድ ተሳትፎ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ቅድመሁኔታዎችን በማስቀመጥ በምርጫው ላይ ላለመሳተፍ የወሰኑበት መንገድ ሲታይ ዛሬም በአቋራጭ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ስለመኖራቸው ማሳያ ነው።ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ረገድ ገለልተኝነቱን በማሳየት በቁርጠኝነት ሥራውን ሲሰራ ቆይቷል።
ቅድመ ምርጫ ሂደቱንና ምርጫውን ዋጋ ለማሳጣት የውጭ ኃይሎች እስከመጨረሻው ድረስ የሄዱበት ርቀት ቀላል አልነበረም።ለአብነትም እነዚያ ስለኢትዮጵያ ያገባናል በሚል በተለያዩ አግባቦች በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሲገቡ የቆዩ ኃይሎች ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በነቂስ ወጥቶና ተሰልፎ ምርጫ ሲያካሂድ የዋለውን ሕዝብ ግን ቦታ ሳይሰጡት ያለሃፍረት ትኩረታቸውን ሌላ ጉዳይ ላይ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።
የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎችና መላው ኢትዮጵያውያን ግን «ይህ ምርጫ የእኛ የኢትዮጵያውያን እንጂ የእናንተ የውጭ ኃይሎች አይደለም» በሚል ያስተላለፉት መልዕክት ለአገራችን የዴሞክራሲ እድገትም ሆነ ለአገራዊ አንድነታችን ጥንካሬ መልካም ጅማሮ ነው፡
በምርጫው ዕለት አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ለማስተላለፍ ለፈለጉት አፍራሽ አካሄድ ጆሮ በመንፈግ «የምንመርጠው እኛ፤ አገራችንም የኛ ናት፤ ስለዚህ ጉዳዩ የኛ ብቻ ነው» በሚል ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምርጫው ጠንካራ መልዕክቶች የተላለፉበት ነው።በአንድ በኩል አንዳንድ እኛ የሌለንበት ምርጫ ዴሞክራሲያዊ አይሆንም የሚለውን የከሸፈ አስተሳሰብ የሰበረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረትና ነፃነት በቅኝ ግዛት ዘመን ያስተላለፈችውን የይቻላል መንፈስን ያሰረጸ መልዕክት ነው።
የዘንድሮው ምርጫ በዚህ መልኩ ተጉዞ አሁን ላይ ደርሷል።አሁን ደግሞ የድህረ ምርጫ ወቅት ላይ እንገኛለን።በዚህ ውቅት አንዱና ትልቁ ነገር የምርጫ ውጤትን ይፋ ማድረግ ነው።
የምርጫ ውጤት መለኪያ ደግሞ የቅድመ ምርጫው እና የምርጫው ዕለት አጠቃላይ እንቅስቃሴ ነው።በሰላማዊ ሁኔታ የተካሄደና ጣልቃገብነት የሌለበት ምርጫ በድህረ ምርጫው ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ጫና ሊያሳድር አይችልም።የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን በቅድመ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ከሆነ ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆንበት ምርጫ መሆኑ እሙን ነው።
በዚህ መሠረት በዘንድሮ ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማን ቅድመ ምርጫውና የምርጫው ዕለት የነበረው ሁኔታ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር።በዕለቱ ያጋጠሙ ጥቃቅን ችግሮች ቢኖሩም እነዚህ ችግሮች በድህረ ምርጫው ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው።ከዚህ ውጪ ግን ወደንትርክና ሁከት የሚወስዱ በሮች ተዘግተዋል።እናም በዘንድሮ ምርጫ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ “ሁ—ሁ” ን መሠረት በማኖር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችላትን የመሠረት ድንጋይ አኑራለች።ይህንን መንገድ ይዞ መጓዝና ባህል ማድረግ ደግሞ የመላ የኢትዮጵያውያን ኃላፊነትና ግዴታ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም