ኢትዮጵያ በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት እና ለመስኖ ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ወንዞች አሏት። ይህን መሬትና ውሃ በመጠቀም በዝናብ ከሚለማው መሬት ጎን ለጎን የመስኖ ልማት ሥራዎችን በማከናወን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ እጥረት ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም ለኤክስፖርት አስተዋጽኦ በማድረግ የኅብረተሰቡን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ከባድ ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል።
በተለይም ከለውጡ በፊት በነበሩ ጊዜያት የፋይናንስ ምንጭ ሳይለይ፣ የልማት ተነሺዎች ካሳ ሳይከፈል፣ የወሰን ማስከበር ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች ይጀመሩ ስለነበር ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ አዳጋች ሆኖ ቆይቷል። በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ከስምንት ዓመታት በላይ ከቆዩ በኋላ እንኳ ማጠናቀቅ ከባድ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንድ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ከአገራዊ ሪፎርም በኋላ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ችግሮቻቸው እንዲፈቱ በማድረግ እንዲጠናቀቁ ማድረግ ተችሏል።
በሌላ በኩል ከለውጡ በኋላ የተጀመሩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ይበል የሚያሰኝ አፈጻጸም እየታየባቸው ነው። ለዚህ እንደማሳያ ሊነሱ ከሚችሉ አዳዲስ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር በአንጎለላና ጠራ ወረዳ በአጂማ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የአጅማ- ጫጫ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የመስኖ ፕሮጀክት አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
የግድቡ ርዝመት 371 ሜትርና ከፍታው 45ነጥብ5 ሜትር የሚኖረው ሲሆን በአለትና በውስጥ በኩል በሸክላ አፈር የሚገነባ እና የግድቡ ውሃ የመያዝ አቅም 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው። በግድቡ የሚያዘው ውሃ ወደ ኋላ አምስት ኪሎሜትር ድረስ በመተኛት 680 ሄክታር መሬት ይሸፍናል።
የግድቡ ግንባታና ተያያዥ ሥራዎች በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን በሦስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል። በዚሁ መሠረት ጥቅምት 2016 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ይሆናል። 2013 በጀት ዓመት ዘጠነኛው ወር ድረስ 17በመቶ ለማከናወን ታቅዶ 14.44 በመቶ ወይም የዕቅዱን 84.94 በመቶ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል።
የፕሮጀክቱ ዋና ዋና ሥራዎች የግድብ ግንባታና ተያያዥ ሥራዎች፣ ከወንዙ ቀኝ በኩል 3000 ሄክታር የሚያለማው ዋና ቦይና የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም ከወንዙ ግራ በኩል 4000 ሄክታር የሚያለማው ዋና ቦይና የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ናቸው። በተጨማሪም ከወንዙ ቀኝ በኩል 3000 ሄክታር ዋና ቦይና የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታን አንድ የውጭ ኩባንያ እየሰራ እንደሚገኝ የመስኖ ልማት ኮሚሽን የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ያስረዳሉ።
በወንዙ ግራ በኩል 4000 ሄክታር ዋና ቦይና የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታን የሚያከናውነውን ኮንትራክተር ቅጥር ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑን ያብራሩት አቶ ብዙነህ፤ የግድብ ግንባታና ተያያዥ ሥራዎች አካል ከሆኑት ውስጥ የግድብ ቦታ ጠረጋና ቆረጣ፣ የትርፍ ውሃ ማስተንፈሻ፣ የመስኖ ውሃ ማስወጭያና የመስኖ ውሃ ማስገቢያ ማማ ሥራዎች መጀመሩንም አብራርተዋል። በተሻለ ፍጥነት በአሁኑ ወቅት ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ነው።
የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ የአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን አማካሪው አማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት ነው። እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቱ ለአዲስ አበባ-ደሴ ዋና አስፋልት መንገድ ቅርብ መሆኑ ፣ ለአዲስ አበባና ዞን ከተማ ቅርበት ያለው መሆኑ፣ አካባቢው ለቢራ ገብስና ለሌሎች ገበያ ተኮር ምርቶች አመቺ መሆኑ የፕሮጀክቱ ምቹ ሁኔታዎቹ ናቸው።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለልማት ካላቸው ጉጉት እና ልዩ ቦታ የተነሳ የካሳ አከፋፈል ሂደት ሳይጠናቀቅ ለመስኖ የሚውል ቦታ መልቀቃቸውም ከምቹ ሁኔታዎች ውስጥ ተጠቃሽ ነው። ይህ የአካባቢው ሕዝብ ተግባር የመንግሥትና ሕዝብ ትብብር የልማት ቁልፍ መሆኑንም አመላካች ነው።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ በፕሮጀክቱ የግድብ ግንባታና ተያያዥ ሥራዎች ጋር በተያያዘ በኮንትራክተሩ በኩል ያሉ ተግዳሮቶች የመሠረት ማጠናከሪያ ሥራ በወቅቱ አለመጀመሩ፣ የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ሲሆኑ ተቋራጭ ድርጅቱ በፍጥነት የመሠረት ማጠናከሪያ ሥራ የሚያከናውን ንዑስ ተቋራጭ ድርጅት ቅጥር እንዲያጠናቅቅ አቅጣጫ የተሰጠው ሲሆን፤ ሲሚንቶ ከፋብሪካ በቀጥታ መግዛት እንዲችል የድጋፍ ደብዳቤ ተፅፎለታል። በተጨማሪም አማራጭ መንገዶችን ተጠቅሞ ሲሚንቶ እንዲያቀርብ የሥራ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013