መርካቶ ትተረማመሳለች፤ ሻጭና ገዢ ይዋከባል።የሚሰሩ፣ የሚለምኑና የሚዳብሱ እጆች፤ የሚሯሯጡ እግሮች፤ የሚወተውቱ አፎች፤ የሚቅለበለቡ ዓይኖች፤ ብቻ የአዳም ልጅ እንደየ ግብሩ ተሰባስቦ መርካቶን አጨናንቋታል።
ድንገት ዓይኔ ዘንቢልና ፌስታላቸውን አንጠልጥለው ላይ ታች ከሚሉት አዛውንት ላይ አረፈ።ገና እንዳየኋቸው ተደመምኩባቸው፤ በእርሳቸው ዕድሜ ያሉ የአካባቢዬን ሰዎች አሰብኳቸው።እውነት አሁን እንዲህ ዓይነት ሥራ ሰርታችሁ እራሳችሁን አስተዳድሩ ቢባሉ ይሰሩ ይሆን? ስል እራሴን ጠየቅሁ።እንጃ ብቻ ሊያደርጉትም ላያደርጉትም ይችላሉ፤ መልሱን ለእነርሱ እንተወው። ነገር ግን በአንድም በሌላም ምክንያት ዕድለኞች ሆነው በልጆቻቸው ይጦራሉ።
ሎሚ ቸርቻሪው አዛውንት ግን ለዚህ ወግ አልታደሉም።በሰባ ዓመታቸው የሥራ ልብሳቸውን ለብሰው ለዕለት ጉሮሯቸውና ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ ይሯሯጣሉ።ፊታቸውን ቅጭም አድርገው ሎሚ… ሎሚ… አለ በለው ሎሚ እያሉ መርካቶን ያዳርሳሉ፡፡
በምክንያት ላናግራቸው ስለፈለግሁ ብቻ «ሎሚው ስንት ስንት ነው?» አልኳቸው። ፈጠን ብለው «ሁለት ሁለት ብር» አሉኝ።ግን አልቆሙም።ሰውየው ቆሞ የማውሪያ ጊዜ ያላቸው አይመስሉም።ተከተልኳቸው።ማንነቴንና የሥራ ባህሪዬን ነግሬያቸው የሕይወት ተሞክሯቸውን እንዲያጫውቱኝ ጠየኳቸው።ሲበዛ ቅን ሰው ናቸው።ግርግር ከሚበዛበት ስፍራ ፈንጠር እንዳልን ሳያንገራግሩ ያወጉኝ ጀመር።ከአንደበታቸው የሰማሁትን ላካፍላችሁ ወድጃለሁና እንሆ።
ባርሄ ሙራረ ይባላሉ።የትውልድ ሀገራቸው ደቡብ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ ልዩ መጠሪያው ሙሁር ሃዋሪያት ነው።የሰባ ዓመት የዕድሜ ባለጸጋና የስምንት ልጆች አባት ናቸው።የትውልድ አካባቢያቸውን ትተው ወደ አዲስ አበባ የመጡት የዛሬ ሃምሳ ዓመት ማለትም በ1962 ዓ.ም ነው።ከትውልድ መንደራቸው ለመሰደድ ያበቃቸው ምክንያት ደግሞ አቅመ ደካማ እናታቸውን ለመርዳት በማሰብ ነበር።አዲስ አበባ ሃምሳ ዓመት ያህል ሲኖሩ አርባ ዓመቱን ሎሚ በመቸርቸር አሳልፈዋል።
መርካቶ አካባቢ ሎሚ ቸርቻሪውን ባርሄን የማያውቃቸው የለም።ዘወትር ማለዳ ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ዘንቢላቸውን አንጠልጥለው ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ተራ እየሄዱ በቅናሽ ዋጋ የሚገዙትን ሎሚ በትንሿ ዘንቢላቸው ከሞሉ በኋላ ድፍን መርካቶን እያካለሉ ይቸረችራሉ።አቶ ባርሄ የቁርስ ሰዓት፣ የምሳ ሰዓት፣ የራት ሰዓት የሚባሉትን ወጎች አያውቋቸውም።በጠዋት ወደሥራ ተሰማርተው ሲሰሩ ውለው የረሃብ ስሜት ሲሰማቸው እግራቸው በጣላቸው ቦታ ካገኟት ትርፍ ቆንጠር አድርገው ይመገባሉ።ጥሩ ገቢ ያገኙ ቀን እንጀራ በሽሮ፤ ገቢያቸው ጥሩ ካልሆነም አምባሻ ወይም ብስኩት በሻይ ይበላሉ።በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ አይበሉም። እንዲህ ዓይነት መስዋዕትነት የሚከፍሉት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲሉ እንደሆነ ይናገራሉ።ከስምንት ልጆቻቸው ውስጥ ሦስቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።ሦስቱ እራሳቸውን ችለውላቸዋል።ሁለቱ ግን አሁንም የቤተሰብን ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው።
ልጆቻቸው እናታቸውን በሥራ እያገዙ እዚያው ገጠር ትምህርታቸውን ይማራሉ።አንዲት ጥገት ላምና ሁለት በጎች አሏቸው።የእርሻ መሬት የላቸውም። ከአገር ያስወጣቸው አንዱ ምክንያትም የእርሻ መሬት ማጣት ነው።ቤተሰቦች በጓሯቸው ውስጥ እንሰት በመትከል በሚያገኟት ገቢ ለመተዳደር የሚጥሩ ቢሆንም በአመዛኙ ግን እርሳቸው ከአዲስ አበባ የሚልኩላቸውን ገንዘብ እየጠበቁ የሚኖሩ ናቸው።አቶ ባርሄ ከገጠር ወደ ከተማ የመጡበትን ሁኔታ እንዲህ ያስረዳሉ።
‹‹የልጅነት አስተዳደጌ እንደሌሎች ሰዎች በደስታ የተሞላ አይደለም።እናትና አባቴ ተለያይተው ይኖሩ ነበር።እናቴ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ ስላልነበራት እኔ የምኖረው ከአባቴ ጋር ነበር። አባቴ በግብርና ሕይወት የሚተዳደር ነው።በርከት ያሉ ላሞች፣ ፈረሶች፣ በጎችና የእርሻ በሬዎች ነበሩት።በልጅነቴ ዋናው ሥራዬ ከብቶችን ማገድ ቢሆንም አልፎ አልፎ አረም በማረምና እህል በመውቃት የግብርና ሥራዎችንም እሰራ ነበር።ከዚያም ከፍ እያልሁ ስመጣ በሬ ጠምጄ ማረስ ጀመርኩ።ከልጅነቴ ጀምሬ አባቴ ትምህርት ቤት እንዲያስገባኝ ብጠይቀውም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፊደል ሳልቆጥር ነው ያደግኩት።አብሮ አደግ ጓደኞቼ ትምህርት ቤት ውለው ሲመጡ እያየሁ እጓጓም፤ እቆጭም ነበር።በተለይም እዚህ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ማንበብና መጻፍ አለመቻሌ ብዙ አስቆጭቶኛል።ከአብሮ አደጎቼ ውስጥ የተወሰኑት በትምህርታቸው ገፍተው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።እኔ ሕይወቴ እንዲህ መሆኑን ሳስብ ሁሌም አባቴን እወቅሰዋለሁ፡፡
ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ኮብልዬ የመጣሁት ልክ የሃያ ዓመት ወጣት እያለሁ ነው።የአባቴን ቤት ጥዬ ለመውጣት ያበቁኝ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።በዚያን የልጅነት ዕድሜዬ የራሴ የሆነ ነገር ኖሮኝ እናቴን ለመርዳት አስብ ነበር።ለዚህም ስል አባቴ በግሌ መሬት እንዲሰጠኝ እና እንዲያቋቁመኝ እጠይቀው ነበር፤ እርሱ ግን ቆይ ልጅ ነህ፤ ትደርሳለህ፤ እያለ የእርሱን ሥራ ብቻ እንድሰራለት ይፈልግ ነበር።እንጀራ እናቴ የመሬት ጥያቄ ማቅረቤ ስላስከፋት ነው መሰለኝ ፊት ትነሳኝ ጀመር።እኔ ግን መሬት የጠየኩት ለራሴ ብዬ አልነበረም፤ ወላጅ እናቴ ተቸግራ ስትኖር ማየት ስለከበደኝ ነው›› ይላሉ አቶ ባርሄ ።
ሰውየው በትዝታ ተመልሰው ያለፈ ሕይወታቸውን መዘርዘራቸውን ቀጥለዋል።እኔም በትኩረት እየሰማኋቸው ነው።‹‹የእናቴን ኑሮ ለማሻሻል በማሰብ ነበር ወደ አዲስ አበባ የተሰደድኩት።ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ሳስብ ምንም ዓይነት ገንዘብ አልነበረኝም።ግን አንዲት በግ ነበረችኝ።የገበያ ቀን ጠብቄ በጌን ከሸጥሁ በኋላ ከአንድ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ጋር ተያይዘን ወደ አዲስ አበባ መጣን።
አዲስ አበባ ከደረስን በኋላ ከጓደኛዬ ጋር ተለያየን።እኔ አንድ ዘመዴ ቤት አርፌ ሥራ ማፈላለግ ጀመርኩ።ግን እንዳሰብኩት አልሆነም።ያለሥራ ሳምንታትን አሳለፍኩ።አማራጭ ሳጣ መርካቶ ሄጄ ዕቃ መሸከም ጀመርኩ።በማገኛት ሳንቲም ምግቤን እየቻልኩ ማታ ወደ አረፍኩበት ቤት እሄዳለሁ።የማገኘው ሳንቲም እናቴን ለመርዳት ይቅርና እራሴን ለማኖር የሚያስችለኝ አልነበረም።ከዚያም ሥራ ልቀይር ብዬ አናጢዎች ጋር በቀን ሠራተኝነት ተቀጠርኩ፤ አሁንም ሕይወቴን መለወጥ አልቻልኩም።ይህንንም ትቼ ዘበኝነት ተቀጠርኩኝ። ጭራሽ እስርቤት የገባሁ መሰለኝ።ከዚያ ግን ባገኝም ባጣም የግል ሥራዬን ብሰራ ይሻላል ብዬ ነው ሎሚ ወደ መቸርቸር የገባሁት።
ለአስር ዓመት ያህል የጉልበት ሥራ እየሰራሁ ካሳለፍኩና አዲስ አበባን በተለይም መርካቶን እያወቅኳት ከመጣሁ በኋላ ግን ሎሚ ከነጋዴዎች ላይ እየተረከብኩኝ አዙሬ በመሸጥ ዋናውን እየመለስኩላቸው በትርፏ መኖር ጀመርኩ።መርካቶ አካባቢ አንድ ባለሱቅ ዘመዴ እዚያው እንዳድርና እግረመንገዴንም ሱቁን እንድጠብቅ ማደሪያ ቦታ አዘጋጀልኝ።ከዚያም ሎሚዬን እየቸረቸርኩ ከቀን ወጪዬ የማገኛትን ሳንቲም ማጠራቀም ጀመርኩ።አልፎ አልፎ ከማገኛት ላይ ለእናቴ መላክም ጀመርኩ።
ከዓመታት በኋላ የተወሰነች ሳንቲም ጨብጬ ወደ አገሬ ተመለስኩኝ።አባቴ የቤት መስሪያ ቦታ ሰጠኝና ትዳር ያዝኩኝ።የሚታረስ መሬት ግን አልነበረኝም። የሥራ አማራጭ ሳጣ ባለቤቴን አገር ቤት ትቼ ተመልሼ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። እዚሁ መርካቶ የዘመድ ሱቅ ውስጥ እያደርኩኝ ሎሚዬን መቸርቸር ጀመርኩኝ።
በዚህ መሃል ልጆች ተወለዱ።የቤተሰቤ ቁጥር እየበዛ ሄደ።ከማገኛት የቀን ገቢዬ ላይ አብዛኛውን ለቤተሰቦቼ እየላክሁኝ የመስቀልና የፋሲካ በዓል ሲደርስ እጄ ላይ ያለችኝን ገንዘብ እየያዝኩ ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ።እንግዲህ እስከ አሁን ድረስ እንዲህ ዓይነት ሕይወት እየገፋሁ ኖሬያለሁ።አርባ ዓመት ያህል ሎሚ እያዞርኩ እሸጥና ማታ እዚያችው ሱቅ አጠገብ ሄጄ አርፋለሁ።
አሁን አሁን ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ኑሮ እየከበዳቸው እንዳለ አቶ ባርሄ ይናገራሉ።እስከ 1980ዎቹ ዓ.ም መርካቶ አካባቢ እንጀራ በሽሮ ወጥ ከሁለት ብር ባልበለጠ ዋጋ ይመገቡ እንደነበር ያታውሳሉ።አሁን ግን የአንድ እንጀራ በሽሮ ዝቅተኛ ዋጋ ከ25 እስከ 30 ብር ነው ይላሉ።
እርሳቸው የሚሸጡት ሎሚም ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት እንደታየበትም አልሸሸጉም።ከሰላሳ ዓመት በፊት በአምስት ሳንቲም ሦስትና አራት ሎሚ መሸጣቸውን ይናገራሉ።አሁን በሳንቲም ደረጃ የሚሸጥ ሎሚ እንደሌለ ይገልጻሉ።አንዷን ሎሚ ከሁለት ብር እስከ ሦስት ብር ይሸጣሉ።አምና እንዲያውም የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ እንደተከሰተ የሎሚ ዋጋ በጣም ተወዶ እንደነበር ይገልጻሉ።አንድ ሎሚ እስከ አምስት ብር ድረስ እንደተሸጠ ይናገራሉ።እርሳቸው ግን ወረርሽኙን በመፍራት አገር ቤት ገብተው ስለነበር የዚህ ዕድል ተጠቃሚ አልነበሩም።እንዲያውም ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ መርካቶ ሲመጡ በርካታ ሰዎች የሎሚ ነጋዴ ሆነው ስለጠበቋቸው ገቢያቸው እንደተቀዛቀዘ ይናገራል።የኮሮና ቫይረስ መከሰት ሎሚን በተናጠል ከመሸጥ ውጥቶ ሦስትና አራት ሎሚ በመደብ እየተደለደለ አስር አስር ብር እንዲሸጥ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።እሳቸው ግን ዛሬም ድረስ ሎሚ በዘንቢላቸው ሞልተው እያዞሩ እንደሸማቹ ፍላጎት ይሸጣሉ እንጂ እንደሌሎች አንድ ቦታ ቁጭ ብለው አይቸረችሩም።
አዘውንቱ ከሥራ ወዳዱ የጉራጌ ማህበረሰብ የወጡ በመሆናቸው እንደልመና የሚጠሉት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።የፈለገ ቢቸግራቸው ሰርተው ችግራቸውን ለማለፍ ይጥራሉ እንጂ ከሰው ምጽዋት አይጠብቁም።እንዲያውም ሙሉ አካል እያላቸው የሚለምኑ ሰዎችን ማየት እንደሚጠሉ ይናገራሉ።በሀብት የተንበሸበሹ የቅርብ ዘመዶች እንዳሏቸው እና ቢጠይቋቸው የፈለጉትን እንደሚደርጉላቸውም ያምናሉ።ግን ሰርቶ እንደመኖር እርካታ የሚሰጣቸው ስለሌለ አይቀርቧቸውም።
ጤና እስካላቸውና አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ ሎሚ መቸርቸራቸውን እንደሚቀጥሉበት ለራሳቸው ቃል ገብተው ነበር።አሁን አሁን ግን አቅማቸው እየደከመ በመምጣቱ በእጃቸው ዘንቢል አንጠልጥለው ከቦታ ቦታ መዟዟሩ እየከበዳቸው መጥቷል።በተለይም በክረምት ወቅት ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ መስራት ፈታኝ ሆኖባቸዋል።አቶ ባርሄ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጓዛቸውን ነቅለው ወደ አገራቸው ለመግባት አስበዋል።አዲስ አበባን በተለይም መርካቶ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ስላደረገላቸው ውለታው ያመስግኑታል።«አዲስ አበባ ሰርተው የሚድሩባት የደሃ አገር ነች» የሚሉት አቶ ባርሄ ሰው ሥራን ካልናቀና ካልኮራ ጦሙን አያድርባትም ይላሉ።ሀገር ቤት ቢኖሩ ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር ይቸገሩ እንደነበር የተናገሩት አዛውንቱ መርካቶ ሰርቶ ለማደር ለሚጥርባት ሰው አታሳፍርም ይላሉ።ለታታሪው አዛውንት ዕድሜና ጤና ተመኘን።ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013