አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ትገኛለች። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን (የመቼ መረጃ) መረጃ እንደሚጠቅሰው ደግሞ የነዋሪዎቿ ቁጥር 228 ሺህ 623 ነው። የስብሰባ ማዕከል እንደመሆኗ ገቢ ወጪዋ ብዙ ነው። የትላልቅ የጭነት መኪኖች መመላለሻና ማቋረጫ እና የንግድ እንቅስቃሴም የሚካሄድባት ናት።
በከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ኮከብ አክሊሉ እንደሚሉት ከተማዋ ካላት ከፍተኛ የቱሪዝም፣ የኢኮኖሚና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዞ በየቀኑ የምታመነጨው የቆሻሻ መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው። ከከተማዋ ከሚመነጨው ቆሻሻ 70 በመቶው ተመልሶ ወደ ኮምፖስት መቀየር የሚችል ነው። ከተማ አስተዳደሩ ይሄንኑ በመገንዘብ ቆሻሻውን ወደ ሀብትነት በመቀየር የከተማዋን ገጽታ ለማስዋብና ለወጣቶቿ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ለማድረግ ሥራ ከጀመረ ዓመታት እያስቆጠረ ይገኛል።
ቆሻሻን ወደ ሀብትነት መቀየር ከተጀመረባቸው ስድስት ከተሞች መካከል አራት ማህበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡት በ2011 ዓ.ም ነው። ማህበራቱ ቆሻሻውን ወደ ሀብትነት የመለወጥ ተግባር የሚያከናውኑት በዓመት አራት ጊዜ ነው። አሁን ላይ በዙሪያው የተፈጠረ የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረ የከተማ አስተዳደሩ ያመረቱትን ማዳበርያ እየወሰደላቸው ይገኛል። በዚህም አዳማ ከተማን አረንጓዴና ውብ ማድረግ ተጀምሯል።
ከተማዋ የስብሰባ ማዕከል እንደመሆኗ በየጊዜው ለስብሰባ በሚመጡ ተጠቃሚዎች አማካኝነት በየቦታው ወድቆ ቆሻሻ የነበረው የውሃ መያዣ ሃይላንድ ወደ ሀብትነት መቀየር ተችሏል። የሥራ ዕድል ከመፍጠርም አንፃር ወደ ሀብትነት የተቀየረው ቆሻሻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። በአራት ማህበራት ለተደራጁ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በየአንዳንዱ ማህበር አሥር አባላት በድምሩ 40 አባላት አሉ። እነዚህ አባላት ደግሞ በየፊናቸው ለተወሰነ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። እራሳቸውም ሥራ አጥ የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር የተፈጠረው የሥራ ዕድል በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እያንዳንዳቸው ቤተሰብ የመሰረቱና ልጆች ያላቸው በመሆናቸው የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠርና የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው በማድረግ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።
ፕሮጀክቱ ለዚህ እንዲበቃ ከፍተኛ እገዛ ያደረገው ደግሞ የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴሩ ቆሻሻን ወደ ሀብት በመለወጥ መልሶ የማልማት ሥራ ፕሮጀክት ከጀመረ ጀምሮ የሚያደርገው ድጋፍ የሚደነቅ ነው። ፕሮጀክቱ ከተጀመረ በኋላ ከፍተኛ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ ቆይቷል። ለከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት ዘርፍ ቆሻሻን መልሶ በማልማት ዙሪያ የሚደግፍ ባለሙያ የላከበት ጊዜ አለ። አገልግሎት ዘርፉም በበኩሉ ለማህበራቱ ድጋፍ የሚሰጥ ባለሙያ ራሱን በቻለ መልኩ የመደበበትና ባለሙያው ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ባለሙያ መመደቡ የተሻለ ሥራ እንዲሰራ አግዟል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ (የኮምፖስት) ዝግጅቱ ሦስት ሂደቶችን ነው የሚያልፈው። ይሄም ቤት ለቤት እየዞሩ ቆሻሻ መሰብሰብ፣ መጣያ ቦታ መውሰድና ወደ ኮምፖስትነት መቀየር ነው። ዝርዝር ዝግጅቱ ደግሞ ስታንዳርዱ በሚያዘው መሠረት ሆኖ የሚያስፈልገውን ሂደት ሁሉ የሚያልፍበትን ያጠቃልላል። አራቱ ማህበራት ቆሻሻን ወደ ሀብትነት በመቀየር የምርት ሂደቱን እያከናወኑ ያሉት በዚህ መንገድ ነው። በዓመት አራቴ ማምረት የሚያስችል አቅም አላቸው። ሆኖም የገበያ ትስስሩ ደካማ በመሆኑ ማህበራቱ በዚህ ልክ ተጠቃሚ ሆነዋል ማለት አያስደፍርም። ከወንጂ ስኳር ፋብሪካና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የገበያ ዕድሉን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ሆኖም ውጤት እያስገኘ ነው ለማለት አያስደፍርም። ቢሆንም ከተማ አስተዳደሩ ጥረቱን ቀጥሏል።
የማህበራቱ ሥራ በመገናኛ ብዙኃንና በተለያየ መንገድ እንዲተዋወቅ ማድረግ ከጥረቱ አንዱ ነው። ከአመራረቱ እስከ አጠቃቀሙ ድረስ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሰጥተውታል። በተጨማሪም ኅብረተሰቡ በተፈጥሮ ማዳበርያ ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ትምህርት ተሰጥቷል። ምርቱን ለከተማ ግብርና ለመጠቀም የተሞከረ ቢሆንም የከተማ ግብርና አዳማ ላይ የተቀዛቀዘ በመሆኑ እምብዛም ውጤታማ መሆን አልቻለም። በእርግጥ በነዚህ ሁሉ የግንዛቤ መፍጠሪያ ጥረቶች ለሥራው ኅብረተሰቡ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ተችሏል። ቁጥራቸው ውሱን ቢሆንም ከተማዋ ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተፈጥሮ ማዳበሪያውን የመጠቀም ፍላጎት አሳይተዋል።
በተለይ በከተማ ግብርና አካባቢ ተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተፈጥሮ ማዳበሪያውን የመጠቀም ፍላጎት የላቀ መሆኑ ታይቷል። በዚህ ዙሪያ ያሉ የምርቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ጨምሯል። በእርግጥ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተፈጥሮ ማዳበሪያው ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ነገር ግን ይሄ ጥርጣሪያቸው ከግምት ያልዘለለና ትክክል ያልሆነ ነው። ምክንያቱም አገልግሎት ዘርፉ ማህበራቱ የቆሻሻ ሀብቱን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት ሲቀይሩ በየትኛውም ሁኔታና ጊዜ እንደሚደረገው ሁሉ ምርቱ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ጠቀሜታው ተፈትሿል። ጥቅምና ጉዳቱን ታይቶም ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ሦስት ጊዜ ምርመራ እንዲሰራላት ተደርጓል። ከዚህ በኋላ ነው ጥቅም ላይ እንዲውል የተደረገው። አቶ ኮከብ እንዳሉት ለገበያ ትስስር ዝርጋታ ዋናው የግንዛቤ ፈጠራ ነው። የኅብረተሰቡን አመለካከት መለወጥ የሚቻለውም በዚሁ ነው።
በአዳማ ከተማ አስተዳደር ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት በመቀየር ሥራ ከተሰማሩ ማህበራት አንዱ የአዲስ ራዕይ ደረቅ ቆሻሻ መልሶ ማልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አልማዝ አሊ እንደነገሩን ከዚህ ቀደም በቤት ለቤት ቆሻሻ ሥራ ተሰማርተው በነበሩ ጊዜ በአመለካከት ችግር ምክንያት ይቸገሩ ነበር። የቤት ለቤት ቆሻሻ ሲሰበስቡ የሚያዩት ችግር ኅብረተሰቡ ቆሻሻን ለይቶ አለማስቀመጥ ነው። ‹‹ቆሻሻ ቆሻሻ ነው መለያየት ምን አመጣው›› ብለው የሚቆጡና የሚጣሏቸው ነዋሪዎች እንደነበሩ ይናገራሉ።
ቀደም ሲል ቆሻሻውን የሚበሰብስና የማይበሰብስ በሚል የመለየት ሥራ በመስራት ተጨማሪ ጊዜና ጉልበት ያባክኑ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ሆኖም አሁን በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የኅብረተሰቡን አመለካከት መለወጥ ተችሏል። ኅብረተሰቡ የፕላስቲክ ዕቃዎችን ከሌላው ቆሻሻ እየለየ በማስቀመጡ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት ለመቀየር አመቺ ሆኗል።
አዲስ ራዕይ ማህበር በዓመት አራት ጊዜ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማምረት አቅም አለው። ሆኖም አሁን ላይ እያመረተ የሚገኘው በዓመት ሁለቴ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ከፍተኛ የገበያ እጥረት ስለነበር አንድ ጊዜ ብቻ ማምረቱን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት ከተማዋን ከማስዋብ ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ለማዋል የገበያ ዕድል የፈጠረላቸው የአዳማ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ብቻ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ መሠረት ዘንድሮ በአንድ ዙር ካመረቱት የተፈጥሮ ማዳበሪያ 300 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት ችለዋል። ገቢው ዘላቂ ቢሆን እና በዓመት አራት ጊዜ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ቢችሉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ይችሉ አንደነበር ይናገራሉ።
እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ፤ ማህበሩ ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር በተለያየ መንገድ ሥራ እየሰራ ነው። ከሥራው አንዱም በከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተፈጥሮ ማዳበሪያን ማስተዋወቅ እና የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው ማስረዳት ነው። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለውም ሦስት ጊዜ መረጋገጡን፤ የአመራረት ሂደቱን ማስጎብኘትም ከግንዛቤ መፍጠሪያዎቹ አንዱ ነው። እንዲሁም የገበያ ትስስሩን ለማስፋት ማዳበሪያ መጠቀም ከሚያስፈልጋቸው የተለያዩ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ጋር ግንኙነት የመፍጠር ሥራ እየተሰራ ነው።
ቆሻሻን መልሶ ማልማት ፕሮጀክት እንደ እነሱ ላሉት የከተማዋ ሥራ አጦች ከፍተኛ ጥቅም እየሰጠ ነው። ወይዘሮ አልማዝ ራሳቸውን ምሳሌ አድርገው እንዳጫወቱን ‹‹በፋርማሲ ትምህርት በ2002 ዓ.ም ተመርቄያለሁ። በዚሁ ዘርፍ ሥራ ባለማግኘቴ ለዓመታት ሥራ አጥቼ ለመቀመጥና የቤተሰብ ሸክም ለመሆን ተገድጃለሁ። በ2008 ዓ.ም ታዲያ የቤት ለቤት ቆሻሻ ማንሳት ሥራ ላይ ተሰማርቻለሁ።›› ብለዋል።
ወይዘሮ አልማዝ ከ2011 ዓ.ም ቆሻሻን መልሶ ማልማት ማህበርን ከመሰረቱት መካከል አንዷ ናቸው። ከዚህ ሥራ በሚያገኙት ገቢ ከቤተሰብ ጥገኝነት በመላቀቅ የራሳቸውን ቤትና ትዳር መሥርተው ኑሮን ማጣጣም ጀምረዋል። አሁን የሦስት ልጆች እናት ሆነዋል። ‹‹የቆሻሻ መልሶ ማልማት ፋይዳ ቆሻሻውን ወደ ምርት መቀየር፣ ለከተማውና ለአካባቢው አረንጓዴ ልማት ጥቅም ላይ ማዋል ሲሆን በተለይም አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በወጪ መቀነስ ትልቅ ጠቀሜታ አለው›› ሲሉ ይገልጻሉ።
ሌላው የማህበሩ ኦፕሬሽን ማናጀር አቶ ሙሉጌታ ባዩ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ አባላቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት በዓመት አንዴ በሚመረት ገቢ ብቻ ነው። በአንድ ጊዜ 1ሺህ 660 ሜትሪክ ኪዩብ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረት ይቻላል። በዓመት አራት ጊዜ ማምረት ቢቻል ደግሞ ይህን መጠን አራት እጥፍ አድርጎ ማስላት ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ማምረት ይቻላል። ለዚህ ግን አስቀድሞ የገበያ ትስስር ሊኖር ይገባል። የከተማ አስተዳደሩም ሆነ ሌላው መንግሥታዊ አካል በዚህ ረገድ እገዛ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ይጠቅሳሉ።
የግሪን ኢትዮጵያ ፅዳትና ውበት መልሶ ማልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በድሉ ወንድሙ እንደሚሉት፤ ማህበራቸው 10 አባላት አሉት። አሁን ላይ እየሰሩ ያሉት ከከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ጋር ባላቸው ውል ነው። ውሉ ከቆሻሻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት ማቅረብ ነው። በውሉ መሠረት በዓመት አራቴ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። ነገር ግን ማዘጋጃ ቤቱ እየተቀበላቸው ያለው በዓመት አንዴ ብቻ ነው። ይሄንንም ቢሆን መውሰድ ያለበትን ያህል እየወሰደ አለመሆኑን ይናገራሉ።
ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ ሦስት ጊዜ ለማዘጋጃ ቤቱ በማቅረብ በተገኘው ገቢ በየዓመቱ አባላቱን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል። ዘንድሮ በአንድ ዙር ከተመረተው 66ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ገቢ በግላቸው 11ሺህ ብር ደርሷቸዋል።
ቆሻሻን መልሶ ማልማት እንደ ሀገር አዳማን ጨምሮ ስድስት ከተሞች ላይ እየተተገበረ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን የገለፁልን ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ላቀ አያሌው ናቸው።
አቶ ላቀ እንዳሉት፤ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አራት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ የተሻለ አፈፃፀም ማሳየት የቻሉት አዳማ ከተማ ላይ ያሉት አራት ማህበራት ናቸው። ሚኒስቴሩ አፈፃፀማቸውን በማሻሻል ከተሞች ኮምፖስት በዘመናዊ መልኩ በማምረት ቆሻሻን ወደ ሀብት መቀየር እንዲችሉ ለስድስቱም ከተሞች ስድስት ትራክተር፣ ተርነርና ሌሎች ለኮምፖስት ማምረቻ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በመግዛት አበርክቷል።
በዚህም 91 ሺህ ቶን ኮምፖስት ሊመረት ችሏል። እንዲሁም ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ በከተሞችና በከተሞች ዙሪያ የሚገኙ የተራቆቱ ቦታዎች መልሶ በማልማት እና ደን በማልበስ ነዋሪዎች በጎርፍ እንዳይጠቁ የመከላከል ሥራ ተሰርቷል። ከ55 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ሆኖም ሁሉም የገበያ ትስስር በሰፊው መሰራት ላይ ችግር እየታየ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚሰፋበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ለግብርና ምርት እንዲውል ማድረግና አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ መፍጠርና በዘርፉ የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013