ሴት ዳኛዋ ችሎት ተሰይመዋል። የህግን ሙያ ወደውና ፈቅደው የሚሰሩ ሴት ዳኛ ናቸው። ሥራቸው ዳኝነት ሆኖ የሙያቸውን ፍትህ ፍለጋ የመጡ ሰዎችን እየዳኙ ለፍትህ የሚሰሩ ቢሆኑም በትዳራቸው ጉዳይ ለእርሳቸው የሚዳኝ አጥተው ተቸግረዋል። ከባላቸው ጋር ያላቸው አለመግባባት ከዓመት ዓመት እየዘለቀ የትዳራቸው መፍረስ ጫፍ ላይ እንደደረሰም ያስባሉ። በተለይ የሳምንቱ የሥራ ቀናት አልቀው ቅዳሜ በመጣ ቁጥር የቤታቸው ጦርነት ፊሽካ ይነፋል። ለእርሳቸው ቅዳሜና እሁድ ሁለቱም የዓለም ጦርነቶች አንድ ላይ የሚከናወኑባቸው ቀናቶች ናቸው። ምናለ ከሰባቱ ቀናት ሁለቱ ተቀነሰው ቢቀሩም ሲሉ ይመኛሉ።
ዳኛዋ ሴት እንደወትሮቸው ችሎት ተሰይመው ሳሉ የእርሳቸው ዓይነት ጉዳይን የያዘች ሴት ፋይል ቀረበላቸው። ጉዳዩ የራሳቸው ቤት ጉድም መሰላቸው። ከሳሽ ሚስት ባሌ ቅዳሜ በመጣ ቁጥር በማባከን፣ እሁድ በመጣ ቁጥር በማባከን፣ ሰኞ በመጣ ቁጥር እኔ ላይ በመነጫነጭ አስቸግሮኛልና እባካችሁ ጋብቻውን አፍርሳችሁ ገላግሉኝ ወይንም ቅዳሜና እሁድን ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ አድርጉልኝ ይላሉ።
ሴቷም ዳኛ የቀረበላቸውን ፋይል ተመልክተው የራሳቸው ጉድ ፊታቸው ድቅን እያለ ስሜታቸው ተረበሸ። የራሳቸው ባል ላይም ፍርድ የሚሰጡ እንደሆነም ተሰማቸው። እርሳቸው ከባላቸው መለየት ባይፈልጉም ከቅዳሜ እስከ ሰኞ ያለው የቤታቸው ጉዳይ ግን ህመም እየሆነባቸው ዓመታት ማስቆጠራቸው ኀዘናቸውን አብዝቶታል። በዚህ ጉዳይ ላይ ፍርድ የምሰጠው እኔ ሳልሆን ምናለ አስጨናቂው ባሌም በሆነ ሲሉም አሰቡ።
ጉዳዩ ሲታይ ቆይቶ የፍርድ ውሳኔ ማሳለፊያ ቀንም ተቀጠረ። በፍርዱ ቀን ዳኛዋ ባላቸው ተገኝተው እንዲከታተሉም ፈለጉ። ግን ምን ያደርጋል ሲባንኑ ለካንስ ችሎት የነበሩት በህልማቸው ኖሯል። ሲባንኑ ዕለቱ ቅዳሜ ጠዋት ነው። ኡፍፍፍፍፍ … አሉ።
ቅዳሜ፣ እሁድ እና ሰኞን ከያዙት ለየት ያለ የቀን ቀለም አንጻር ቅኝት በማድረግ ስለ ልከኛ ሕይወት ልናነሳ ነው። ልከኛ ሕይወት እንደ አቅሙ የሚኖር፤ እንደ አቅሙ የሚዝናና፤ ማህበራዊ ሕይወቱም ብድር በምድር ከሚለው ይልቅ ሰው ተኮር የሆነለት ማለት ነው።
6ኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ የሚከናወነው ሰኞ በመሆኑ አንድ ሰው የዘንድሮ ሰኞ ያለወትሮዋ የምትናፈቅ ሆነች አሉ። በግለሰቡ ንግግር ውስጥ ሰኞ የምትናፈቅ ቀን አይደለችም የሚል ድምዳሜም ይሰማል። ከሳምንቱ ቀናት መካከል በአብዛኛው ቅዳሜና እሁድ የእረፍት ቀናት፤ ሰኞ ደግሞ የሥራ የመጀመሪያው ቀን ሆኖ ይቀርባል። በአብዛኛው ሀገራት ተመሳሳይ ስሜት እንዳለም ይታመናል። ከቅዳሜ እስከ ሰኞን ለመመልከት ከቅዳሜ ጀምረን ሰኞ ላይ እንድረስ፤ መነሻችንም ሆነ መድረሻችን በልከኝነት ውስጥ ሚዛኑን ስላደረገው ልከኛ ሕይወት መሆኑ ልብ ይባል።
ቅዳሜ
«ቅዳሜ ገበያ» የተሰኘ የራዲዮ ፕሮግራም መስማቴን አስታውሳለሁ። ገበያን ከቅዳሜ ጋር ያገናኘው የራዲዮ ፕሮግራም ምክንያቱ ግልጽ ሲሆን፤ እሱም በመላ ሀገሪቱ ትልልቅ ገበያዎች የሚቆሙት በዚሁ ዕለት በመሆኑ ነው።
ቅዳሜን በገበያ ቀኑ ወስደን ሁለት ነጥቦችን እናንሳ፣ ከሁለቱም ነጥቦች ልከኛውን ሕይወት ሚዛን እንዴት እንደሚመዝን እንመልከት፤
ሁሉ አማረሽን ገብያ አታውጧት
ወደ ገበያ የሚሄድ ሰው ፍላጎት እና አቅምን ይዞ ይሄዳል። ገበያ ከደረሰ በኋላ ሊገዛው በሚፈልገው ነገር ላይ የፍላጎት ለውጥ አድርጎ የሚገዛውን ሊያበዛ ከፈለገ ያሰበውን እንዳያደርግ ይከለክለዋልና ሁሉ አማራሽን … ተብሎ ይተረትበታል። ለሁሉም ፍላጎትን ገርቶ በአቅም መኖርን መልመድ አስፈላጊነቱ ለሁሉም ነውና፤ ልከኝነት የአኗኗር ዘይቤያችን አካል ይሁን።
ሰዎች ለምን የማያስፈልጋቸውን ሁሉ በመሰብሰብ ሸክምን ራሳቸው ላይ ያመጣሉ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ በልከኝነት ውስጥ ለመኖር ራስን አለማስገዛት ሆኖ እናገኘዋለን። የማህበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች የሌሎች ሰዎች ተጽእኖን ተቋቁሞ በራስ መንገድ መሄድ የውስጥ ጥንካሬን አስፈላጊነት ያነሳሉ። በቅርብ ጓደኞቻቸው ተጽእኖ የማያምኑበት ሕይወት ውስጥ እንደገቡ የሚናገሩ ግለሰቦች የሌሎች ተጽእኖ የጸጸታቸው ምንጭ አድርገው ሲናገሩ ይደመጣል።
በዙሪያችን ያሉ ግለሰቦች የሆኑትን ሁሉ እንሁን ብንል፣ ወደ ገበያ ሄደን ያየነውን ያማረንን ሁሉ እንግዛ ብንል፣ በማህበራዊ ሚዲያ የቀረበልንን ማስታወቂያ ሁሉ ተከትለን እንሂድ ብንል በሕይወታችን ውስጥ ምስቅልቅል ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ከልከኝነት የተፋታ ሕይወትን ተከትሎ የሚመጣ ምስቅልቅል።
ሁሉ አማራሽ ወደ ገበያ ብትወጣ፣
ልትገዛ ያሰበችውን ሳትገዛ፤ መግዛት የሌለባትን ልትገዛ ትችላለች፣
ለሌላ ጉዳይ የተያዘን ገንዘብ ለአሁን በማያስፈልጋት ላይ ልታወጣው ትችላለች፣
ሁሉም የአማራት ነችና፤ አንዱን ሳታጣጥም ኪሳራ ውስጥ ትገባለች፣
ቅዳሜን በገበያ ቀን ወስደን የምናነሰው የልከኝነት ሚዛንን የሚያሳየን ነጥብ …
ችኩል ሸማችን ገበያ አታውጧት
ወደ ገበያ የሚገባ ችኩል ሸማች ተዘርፎ ሊመለስ ይችላል። የሚገዛውን ዕቃ ጥራት፣ ዋጋውን እንዲሁም አጠቃቀሙን በሚገባ ሳይረዳ በችኮላ ግዢውን ሲፈጽም ሰለባ ሊሆን የሚችል። መኪና ገዢ ሆኖ የሚነሳን ሰው ከእርሱ በፊት መኪና የገዙ ሰዎች የሚያደርጉለት ተመሳሳይ ምክር አለ፤ «አትቸኩል» የሚል። ለመኪና ግዢ የሚመከረው አለመቸኮል እንደየሁኔታው ለሁሉም ገበያተኛ ይሆናል። እናቶች አስቤዛ ሊገዙ ወደ ገበያ ሲገቡ የሚያደርጉት ማጣራት እና በእርጋታ ግብይት ሲያደርጉ ያስደምማሉ። ገበያ ላይ ሆነው የሚያዋክባቸውም ምቾት አይሰጣቸዋም።
በማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥም ነገሮችን በችኮላ ሳይሆን በእርጋታ የማድረግን አስፈላጊነት እንረዳበታለን። ልከኛ ሕይወት በእርጋታ ውስጥ ስለሚመዝን። በጥቅሉ ቅዳሜን ከገበያ ጋር አገናኘነው እንጂ በእያንዳንዱ ቀን ውስጥ ልዩ ልዩ ገበያዎች ወይንም ልውውጦች አሉ። በእርጋታና በማስተዋል ውስጥ ውሳኔን ማሳለፍ አስፈላጊነቱን የግድ የሚሉ።
ችኩሏ ሸማች ገበያ ብትወጣ፣
የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል እንደሚባለው ችኩልነቷ የማይሆን ነገር ላይ ሊጥላት ይችላል፣
በችኮላ ውስጥ ለሌባ ሲሳይ መሆንም እንዲሁ።
ዳኛዋ የተቸገረችበት ባል የቅዳሜ ውሎ በማህበራዊ መስተጋብሩ ሲታይ ገበያ ብሎ ሄዶ የማያስፈልገውን የሚገዛ፣ የሚያስፈልገውን የማይገዛ፣ ያማረውን ሁሉ የሚሰበስብ፣ ለሌባ የተጋለጠ፣ በገበያ ዕለት በጋራ መዝናናት ውስጥ ገንዘቡን የሚበትን ራሱን መሆን ያልቻለ አሳዛኝ ሰው ማለት ነው። የልከኝነት ሚዛን ጠፍቶት ማምሻውን እየተንገዳገደ የቤቱን አቅጣጫ የሚፈልግ። ይህን በመሰለው የቅዳሜ ዕለት የግድ የሚሰክሩና የእሁድ አጥቢያቸውን ከቤተሰብ ጋር መበጣበጫ ቋሚ ዕለት አድርገው የሚኖሩትንም ቤት ይቁጠራቸው።
14ቱ አልፎ እነሆ ሌላው ሰኞ መጣ። ሌሎች ሰኞዎችም ይቀጥላሉ። ጥያቄው በልከኛ ሕይወታችን በተገራ ቅዳሜና እሁድ ቀጥሎ የሚመጣ የፈካ ሰኞ ወይንስ የተለመደው? የሚለው ነው።
ልከኛን ሕይወት በመሆን ፍሬን የምንሻ ሰዎች፣
ማባከንን የምንጸየፍ፣
የሚያስፈልገንን ብቻ የምንሸምት፣
ከሰዎች ጋር ያለን መዝናናት መስመሩን የምንጠብቅ፣
ሥራችንንም ሆነ ሸመታችንን በእርጋታ የምናደርግ፣
የምንሸጥም ሆነ የምንገዛ ብንሆነ በሌሎች ጫማ ውስጥ እራሳችንን ጨምረን ስንሰራ የእኛ ቅዳሜ በመጠን በመኖር ዘወትር የእረፍት ሕይወትን እንድንኖር የሚያደርግ ሆኖ እናገኘዋለን።
የእረፍት ቀናቸው ቅዳሜና እሁድ ለሆነላቸው ሰዎች ምክራችን በልከኛ ሕይወት ውስጥ ሁሉንም ቀን የእረፍት ቀን አድርጉ የሚል ነው። በመጠን ለሚኖሩ ሰዎች በእያንዳንዱ ቀን ውስጥ የእረፍት ወይንም ከጭንቀት የተላቀቀን ኑሮ ለመኖር ዕድላቸው የሰፋ ስለሆነ። ከሠርጋቸው ማግስት ወደ ጸብ የሚገቡ ጥንዶች ባልተገራ ቅዳሜነት የመጣ አድርገን ልንቆጠር እንችላለን። ቅዳሜነት የገበያ፣ የትጋት፣ የሥራ፣ የሸመታ ብቻም ሳይሆን የማባከን፣ በመዝናናት ስሜት የሱስ መጠመጃ የመሆን፣ በችኩልነት ለሌባ ሲሳይ የመሆን ወዘተ እንዳይሆን ማሰብ ያስፈልጋል።
ሁለተኛውን የእረፍት ቀን፣ እሁድን በአጭሩ እንመዝነው፣
እሁድ
በዳንኪራ ጩኸት ያመሸው አካባቢ ዕለቱ እሁድ ከሆነ በለስላሳ ዝማሬ ይሞላል። ቤተክርስቲያን የሚሄደው እንደ እምነቱ አድርጎ ከሰዓት በኋላው የማህበራዊ ሕይወት በስፋት የሚፈጽምባት ሆና እንድታልፍ ይደረጋል። ለመዝናናት ቲያትር ይሁን ኳስ፤ ወይንም ተሰብስቦ መጨዋወት ለእዚህ በዋናነት የተመረጠች የምትመስለው እሁድ ትወለዳለች።
በልከኛው ሚዛን ውስጥ በመጠን መኖርን ስናነሳ በመጠን መዝናናትንም እናገኛለን። በመጠን ወደ ገበያ መግባት የተገባ እንደመሆኑ መዝናናትም በመጠን ውስጥ መሆን አለበት። በመጠን መዝናናት ማለት አካልን እየጎዱ ያይደለ፤ ለሱስ ተጋላጭ የማያደርግ፤ በመዝናናት ስም የሚወጣው ገንዘብ ኑሮን ከመምራት ቀውስን የማያመጣ የሆነ ማለት ነው። እሁድ ቀን በተወሰነ ደረጃ የበዓል ዕለትንም ያስታውሰናል። በበዓል ዕለት ከቤተሰብ፤ ከጎረቤት ጋር በደስታ ለማሳለፍ ተብሎ የሚደረገው ጥረት ሌሎች ቀኖችን በእዳና በጭንቀት የሚጨምር እንዳይሆን ይጠይቃል።
እሁድን ከመንፈሳዊ መርሃ-ግብርና ከመዝናናት እልፍ ብለን ስናይ ከማህበራዊ ኸይወት አንጻርም ትርጉም አላት።
ማህበራዊ ሕይወት
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ስለ ማህበራዊ ሕይወት የሚነግረን የሚያስፈልገን አይመስልም። በብዙ አቅጣጫ ማህበራዊ ሕይወትን የተማርን፤ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥም ብዙ ያተረፍን መሆኑ ግልጽ ነው። ማህበራዊ ሕይወታችን በአብዛኛው አብሮ በመብላት፣ አብሮ ደስታን በመካፈል እንዲሁም አብሮ ኀዘንን በመጋራት ውስጥ የሚመዝን ነው። በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ከልብ ኀዘንን ከመካፈል ወይንም ደስታንም ከመጋራት እንደ ግዴታ ቆጥሮ ግዴታን መወጣት ደረጃ ላይ መድረሱ እንደ ግለሰብ እያንዳንዱ ሰው ሊያስብበት የሚገባም ነው።
ማህበራዊ ሕይወታችን የልከኛ ኑሮ እንቅፋት እንዳይሆን ሁሉት ነጥቦችን ወደ ሚዛኑ እንጨምር፤
ከልብ ማድረግ – ለቅሶ የደረሰኝን ለቅሶ መድረስ አለብኝ ከሚለው ይልቅ ከምክንያት በላይ ያዘኑትን ማጽናናት ይገባል ብሎ ማሰብ ይሻላል። የእኔን ሰርግ ከበላ እርሱም ሰርግ ሊጠራኝ ይገባል ከማለት የእከሌን ደስታ ተካፋይ ብሆን ደስ ይለኛል ብሎ ማሰብ ይገባል። ከልብ የሆነ ማህበራዊ ሕይወት ሲሆን ሰዎች ብድር ለመክፈል ሳይሆን የሚያደርጉት ማድረግ የሚገባቸው ተግባር በመሆኑ ነው። ማድረግ የሚገባንን ለማድረግ እንድንችል ውስጥን ማዳመጥ ይገባል። ላደረገልን ማድረግ፤ ላበላን ማብላት፤ የጎበኘንን መጎብኘት ብድር መከፋፈል ሲሆን ይህን ማድረግ የማይችለው የሚደርስለት የሌለ ይሆንና ጉዳዩ ሚዛን ይስታል።
ሰውን ማእከል ማድረግ – ሰውን ማእከል ያደረገ ማህበራዊ ሕይወት ማለት ግዴታዊ ማህበራዊ ሕይወትን መወጣት ብቻም ሳይሆን ጥግ ድረስ አስቦ ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣትን የሚጠይቅ ማለት ነው። ሰው ሲሞት ለቅሶ እንደርሳለን፤ ጥሩ ነው። የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ የሆነን አንድ ሰው ያጣን ቤተሰብ ኀዘን መጋራት ማለት ለቀስተኞች ለቅሶ በተቀመጡባቸው ቀናቶች ውስጥ ብቻ ለቅሶ መድረስ ከሆነ ስህተት ነው። ይህ ቤተሰብ አንድ ለእናቱ የሆነ፣ የገቢ ምንጩ የሆነን ግለሰብ ያጣ ከሆነ የዚህ ቤተሰብን ቀጣይ ሕይወት ማሰብ ይገባል ማለት ነው። ለቅሶ መድረስ እንደ ግዴታ ተደርጎ እየታሰበ ባለበት ሁኔታ ሁሉም ለቅሶውን ሊደርስ ይችላል፤ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ያንን ቤተሰብ ማሰብ ማለት ሰውን ማእከል ያደረገ ማህበራዊ ሕይወትን መኖር ማለት ነው።
እሁድ ቀንህን ተጠቅመህ ማህበራዊ ሕይወትን ልትኖር ስትነሳ የምትሄድበት ማህበራዊ ሕይወት ከልብ የሆነ እንዲሁም ሰውን ማእከል ያደረገ መሆኑን መርምር። ሁሉንም ሰው ችግር ላትፈታ ትችላለህ፤ ምናልባትም ቅዳሜህን በአግባቡ መግራት ከቻልክ ግን ከልከኛው ኑሮህ የምታተርፈው ጥቂቷ ገንዘብ ከልብህ ጋር ሆነህ የምትደርሰው ሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ ተስፋን ታጭራለች።
በስተመጨረሻ ሰኞን …
ሰኞ
በመነሻችን ላይ አንድ ግለሰብ ስለ ሰኔ 14ቱ ሰኞ የተናገረውን አንብበናል። ሰኔ 14፣ 2013 ምርጫ ቀን ሆኖ ያለፈ ሰኞ በመሆኑ «ልዩ ሰኞ» ተባለ። ምክንያቱም ሰኞ በብዙ የሚናፈቅ ቀን ስላልነበር በምርጫው ምክንያት የተናፈቀም ስለሆነ። ሰኞን በልከኛ ሕይወት ውስጥ ሆነን ለማየት ስንነሳ፤ በቅድሚያ ለሰኞ በተሰጠው ትርጉም ላይ ጥያቄ እናንሳ።
ሰኞ የሥራ ቀን መጀመሪያ መሆኑ ሊናፈቅ ነበር የሚገባው ወይንስ አሁን እንዳለው ፊት የሚጠቁርበት ቀን? እኔ ሊናፈቅ ይገባዋል ባይ ነኝ። ሕይወት መዝናናት ብቻ ሊሆን አለመቻሉ ግልጽ ነው። ሕይወት ማህበራዊ ሕይወት ብቻ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ሕይወት የሥራም ክፍል አለው።
በሁሉም ሀገር እስኪባል ድረስ ለሰኞ የተቀመጠው ትርጉም በውስጣችን ሥራ ጠልነተን ከሚያበረታቱ አስተሳሰቦች አንዱ እንዳይሆን ልንፈራ ይገባል።
ወደ ሥራ ስንሄድ በደስታ እንድንሄድ ምን ማድረግ እንዳለብን ማሰብ አለብን። ሥራችን የሌሎችን ሕይወት እንዴት መቀየር እንዳለበት ማሰብም አለብን። በሥራችን ፍሬ ለመደሰት ውጤትን ግብ አድርገን የምንሠራ መሆንም አለብን። ሥራ ትልቁ የሕይወታችን ክፍል ነውና!!!
ፍትህን ፈልጋ ወደ ሴቷ ዳኛ ያቀናቸው የህልም ባለጉዳይ የባሏ ሰኞ መገለጫው በእርሷ ላይ በመነጫነጭ የሚገለጽ እንደሆነ ገልጻለች። ምክንያቱም በቅዳሜና እሁዱ ብኩንነት የሚበሳጭ ባል ብስጭቱን የሚገልጸው እርሷ ላይ በመሆኑ።
የሥራ ሕይወትን ስናስብ፣
እድገትና ለውጥ ከሥራ የሚገኙ መሆናቸውን እንረዳለን፣
የማይሰሩ ሰዎችን መደገፍ የምንችለው ስንሠራ መሆኑን እናስባለን፣
እረፍት ትርጉም የሚኖረው መሥራት የሚገባው ነገር ሲኖር መሆኑን እንገነዘባለን።
መውጫ
ሰኞ አመሻሹን ለሥራ ዝግጁ የሆነውን ሰው እናገኛለን። በነቃ ሁኔታ ሥራውን ሰርቶ ለሌላ ቅዳሜ፣ እሁድና ሰኞ የመሄድ ዙረት። አስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ካለ፤ ሕይወትን በዓላማ ስንኖር፣ ሕይወትን በመጠን ስንመራ፤ … ወዘተ ቅዳሜም እሁድም፣ ሰኞም ሆነ ማክሰኞ ሁሉም ቀናት ትርጉም ያላቸውና ሁሉም የበሩ ይሆናሉ። ሰኞ ቀን የሚናፍቃቸው ሠራተኞች ታውቃለህ? አዎን በጣም ብዙ አሉ። እነርሱ ቅዳሜንም ሆነ እሁድን እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያውቁ እየሰሩ የሚያርፉ፤ እያረፉም የሚሰሩ ናቸው። ልከኛ ሕይወት በሁሉም ቀናቶቻችን ላይ ይሁኑ። ልዩው ሰኞ ማለትም የሰኔ 14ቱ አልፎ እነሆ ሌላኛው ሰኞ መጣ። ሌሎች ሰኞዎችም ይቀጥላሉ። ጥያቄው በልከኛ ሕይወታችን በተገራ ቅዳሜና እሁድ ቀጥሎ የሚመጣ የፈካ ሰኞ፣ ወይንስ የተለመደው? የሚለው ነው። ቸር እንሰንብት።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2013