ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አካሂዳ በአሸናፊነት አጠናቅቃለች፡፡ ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር፤ ኢትዮጵያውያንም ታላቅ ሕዝብ መሆናቸውን ከማሳየቱም በላይ፤ ኢትዮጵያ ዛሬም ከፊት ቀድማ የሥልጣኔና ዴሞክራሲ ብርሃን መሆን እንደምትችል ለዓለም ያረጋገጠ ነው፡፡ እናም ዕለቱ በካርድ ዴሞክራሲ የተተከለበት፤ በችግኝ ደግሞ አገር አረንጓዴ እንድትለብስ የተደረገበት እና ዓለም ከዚህ እንዲማር የሆነበት ነው፡፡
ምርጫው የትኛውም የውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያውያንን የተባበረ ክንድ ሊያጥፍ እንደማይችል በተግባር ያረጋገጠ ሆኖ አልፏል፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚያምኑትና የሚተማመኑበት ተቋም ካገኙ ያሰቡትን ከማድረግ፤ መብታቸውንም ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ አስገንዝቧል፡፡ ላመኑበት ዓላማና ለአገራቸው ሉዓላዊነት ምን ያህል የጸና አቋም እንዳላቸውም አስመስክረዋል።
ለዚህ አብይ ማሳያው ደግሞ በዕለቱ የነበሩት ረዣዥም ሰልፎች እና ሕዝቡም ብርድ፣ ፀሐይና ዝናብ ሳይበግረው ድምጹን መስጠቱ ሲሆን፤ ምርጫ ቦርድም ይሄን የሕዝብ ፍላጎትና ጽናት ከግንዛቤ በማስገባት ሳይመርጥ ወደቤቱ የሚመለስ ሰው እንዳይኖር የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት እንዲራዘም ማድረጉ ነው፡፡ ይሄም ሕዝቡና ቦርዱ ተናብበውና ተማምነው ለመስራታቸው ህያው ምስክር ነው፡፡
ሲጀመር ምርጫው ማንም አሸናፊና ተሸናፊ የሚሆንበት ሳይሆን፤ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አሸናፊነት ከፍ ብሎ የሚገለጽበት እንዲሆን ሁሉም ተስማምቶ የገባበት ነበር፡፡ ለዚህም ከምርጫ አስፈጻሚው ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ኅብረተሰቡ ይሄን ለማሳካት ሰርተዋል፤ አድርገውታልም፡፡ ይህ ሲሆን እኛ ካልታዘብንና እኛ ይሁን ካላልን ምርጫው ሊከናወን አይገባም፤ እናንተም ማድረግ አትችሉም ሲሉ የነበሩ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎችም ግምታው የተሳሳተ እንደነበር አሳይቷል፡፡
ይልቁንም እኛ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ ከምናደርገው ጉዞ ሊያግደን የሚችል ኃይል እንደሌለ በመግለጽ፤ ይልቁንም ከአገር ውስጥም፣ ከአፍሪካም፣ ከዓለም አቀፉ ተቋማትም ለመታዘብም፣ ለመዘገብም የሚፈልግ ካለ በሩ ክፍት እንደሆነ ግልጽ ተደረገላቸው፡፡ ሙያ በልብ እንደሚባለው የእኛን መነሳት የማይሹትን ልብ እስኪገዙ ቸል ብለን ዴሞክራሲያችንንም ችግኛችንንም ተከልን፡፡
በዚህም በብዙ ሚሊዮን የሚልቁ ኢትዮጵያውያን በነፃነት ወጥተው ድምጽ ሰጡ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለውጪው ጩኸት ጆሮ ሳይሰጡ ስለ አገራቸው ወሳኙ እነሱ ስለመሆናቸው ያረጋገጡበትን የምርጫ ተሳትፎ በማድረግ የሚያስመሰግናቸውን ተግባር ፈጸሙ፡፡ ምርጫውም ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ስለመከናወኑ፤ ሰላማዊ ሆኖ ስለመጠናቀቁም የታዘቡ ሁሉ በየፊናቸው አረጋገጡ፡፡
ቀሪው ጉዳይ በዚህ ምርጫ ማን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንዲያሻግር ተመረጠ? የሚለው ነው፡፡ ምንክያቱም ምንም እንኳን ምርጫው ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ እና ለኢትዮጵያ አሸናፊነትም ሁሉም የራሱን አሻራ ያሳረፈ መሆኑ ቢታመንም፤ አሸናፊዋን አገር እና እንድታሸንፍ ሁሉን በአንድ አስተሳስሮ በመምራት ወደ ላቀ ሁለንተናው ብልጽግና የሚያሸጋግር አንድ አካል እንዲኖር ግድ ስለሆነ ነው፡፡
ሕዝቡም በዚህ መልኩ በላቀ ፍላጎትና ጽናት በነቂስ ወጥቶ ሲመርጥ ይሄን እውን ለማድረግ ሲሆን፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት ያስተዳድረኛል፤ መርቶም ያሻግረኛል ያለውን ዕጩ/ፓርቲ መርጧል፡፡ ይሄንንም በነፃ ፍላጎቱ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዳከናወነ መስክሯል፡፡ ይህ ደግሞ ከታላቅ ሕዝብ የሚጠበቅ ተግባር ነውና፤ ኢትዮጵያውያን በዚህ ድርጊታቸው ታላቅነታቸውን ዳግም ለዓለም አሳይተዋል፡፡
በዚህ መልኩ ኃላፊነቱን የተወጣው ሕዝብ ግን አንድ ነገር ይፈልጋል፤ ድምጹ እንዲከበርለት፡፡ ለዚህ ደግሞ የምርጫ ቦርድ ላይ ያለውን አመኔታ አጠቃላይ በምርጫው ሂደት ያሳየ ሲሆን፤ ቀጣዩ ጊዜ ደግሞ የፓርቲዎችን ለሕዝብ መገዛት የሚመዝንበት ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ እናም ይሄን የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ለመመለስ የሕዝብን ድምጽ መቀበልና ሕዝብ በሰጠው ኃላፊነት ልክ መንቀሳቀስ ከፓርቲዎች የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል፡፡
ምክንያቱም፣ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ውሳኔው የሕዝብ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ እርግጥ ነው በርካታ ፓርቲዎች በሕዝብ ድምጽ ላይ ያላቸውን መተማመን ካሁኑ እየገለጹ ይገኛል፡፡ ይህ የሚመሰገንና የሥልጡን ፖለቲካ ጉዞ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ግን በተወሰኑ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች የሚባል ብቻ ሳይሆን፤ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይላት የሚመለከትና በዚሁ አግባብ እንዲቀጥሉም የሚጠበቅ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ላይ መተማመንና የሕዝብን ውሳኔ መቀበልን ሲለማመዱ፤ የተጀመረው ኢትዮጵያን አሸናፊ የማድረግ ጉዞ ከዳር ይደርሳል፤ ለነገ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ስር መስደድም የራስን አሻራ ለማሳረፍ ዕድል ይሰጣል፡፡ ከዚህም በላይ ይሄን ታላቅ ሕዝብ እንዳስተዳድር ዕድል ይሰጠኝ ብሎ እንደተፎካከረና በምርጫ እንደቀረበ ፓርቲ ቢያንስ ከሕዝቡ እሳቤ አንሶ ያለመገኘትን ልዕልና መላበስ ነው፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት የሕዝብ ውሳኔ መሆኑን አምኖ በመቀበል በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ትልቅ አሻራ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም