በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን አቅመ ደካማዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሁሉም ቦታዎች እየተቀጣጠለ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው፡፡ መንግሥትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩትን በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ሥራ እያከናወነ
ነው፡፡ ይህም እንቅስቃሴ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ተግባር
ነው፡፡ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራት ማህበራት እየተበራከቱ
ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኅብረተሰቡን ችግር ከመፍታት አኳያ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ወጣት በብዛት ከሚገኝባቸው አገራት (ወይም «የወጣት አገር» ከሚባሉት) መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ወጣቱ ክፍል ከመስራትና አገርን ከማሳደግ ይልቅ ባልባሌ ትርክቶች ተጠምዶ እርስበርስ ሲጋጭ ማስተዋል ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይህ የሆነው በአገሪቱ የሚሰራ ሥራ ጠፍቶ ሳይሆን አለመስማማቶች በመበራከታቸውና የሚሰሩ እጆች ለጥፋት በመዋል ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ ከሕግ አኳያ በመንግሥት ደረጃ ጠንከር ያሉ ሥራዎች ባለመሰራታቸው ዝርፊያና ቅሚያ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህን ጉዳይ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት፡፡ ለጥፋት የሚውሉ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ተግባራት የሚሰነዘሩም እንዳሉ ለማሳየት ነው፡፡ የተቸገሩ አረጋውያንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፉና አለንላችሁ የሚሉ በርካታ በወጣቶች የተመሰረቱ ማህበራት እንዳሉ በዚሁ አምዳችን መግለፃችን ይታወሳል፤ አብዛኛዎቹ ማህበራትም እውቅናና ፈቃድ አግኝተው እርዳታ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውንም እንደዚያው፡፡
ሰው ከፍ ያለ አስተሳሰብ የሚያራምድ አእምሮ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት በርካታ አስገራሚ የሆኑ ሥራዎችን እንዲያከናውን አስችሎታል፡፡ ይህ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ለሰዎች በምናደርገው ሰብአዊ ድጋፍ ነው። በአገራችን ሰዎችን መርዳት እንደ ጠንካራ ባህል የሚወሰድ በጎ ተግባር ነው። በበዓላት ወቅት ከመንግሥት ጀምሮ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ድጋፍ ሲደረግ
ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለፈውን የትንሳኤ በዓል ማንሳት በቂ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት ይሁን ሌሎች ግለሰቦች በዓላትን ብቻ በመጠበቅ ስጦታ መስጠትን እንደ ባህል ይዘውታል፡፡ ድጋፍ ማድረጉ ጥሩ ተግባር ቢሆንም ሁል ጊዜ አለመቀጠሉ ተረጂውን የከፋ ችግር ውስጥ ይከተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት በጎ ተግባራት አሁን አሁን ከተወሰኑ ምክንያቶች ጋር ብቻ እየተያያዙ የሚጠፉበት ሁኔታ ይስተዋላል።
ሰውን ለመርዳት የግድ ሀብታም ወይም የሚሰጥ ነገር መኖር የለበትም፡፡ ሰው ሰውን ለመርዳት ቅንነትና ፍላጎት በቂ ናቸው፡፡ የሚረዳቸው ሰው ያጡ አረጋውያን፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች በየቦታው ወድቀው ይታያሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር የመረዳዳቱ ሁኔታ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት እንዳልጠፉ ለማስረዳት በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በተለይ በቅርቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን።
ይሄን ሐቅ በተግባር ቋንቋ ከሚነግሩንና ከሚያስረዱን በርካታ ተግባራት መካከል በማህበራት ተሰባስበው ለወገኖቻቸው ጉልበት እና እስትንፋስ የዘሩ ብዙ ናቸው። በተመሳሳይም ፖለቲካው ዘርቶ፣ አጠጥቶ፣ አብቅሎ፣ ኮትኩቶ፣ ለፍሬ ያበቃቸውን አልፎ አልፎ በአገሪቱ የሚስተዋሉ መጥፎ ድርጊቶች በእምነቶች መካከል፣ በብሔረሰቦች መካከል፣ በማህበረሰቡ መካከል የሆኑ፣ የተደረጉና የተፈጠሩ አድርገው የሚነዙ አካላት አይጠፉም። ይሄ የኢትዮጵያዊነትን ገመድ፣ የእርስ በርስ ትስስር፣ የመዋደድ፣ የአንድነት፣ የፍቅር ማሰሪያ ውል በጮርቃ ፖለቲካዊ ሚዛን ከመለካት የሚመነጭ የድንቁርና እሳቤ ውጤት ነው።
‹‹ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድም›› እንዲሉ ከልብ ካዘኑ ሌሎችን ማገዝ የሚያስችል አቅም ከእያንዳንዱ ሰው እጅ አለ። ከላይ እንዳልነው፣ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ሐብታም መሆንን አይጠይቅም። ሐብታም እስኪሆኑ ከንፈር በመምጠጥ ማለፍም ለተራበ ሰው ጉራሽ ሆኖ የታጠፈ አንጀቱን አያቃናለትም። ሰዎች ባላቸው አቅም ለችግሮች ለተጋለጡ ወገኖቻችን ለመድረስ ቁርጠኛ ሲሆኑ አቅም ያገኛሉ። ሰዎች ካላቸውና ከራሳቸው ቆርሰው ለሌሎች ሲያጋሩ ቅንጣት ታህል የእነሱ አይቀንስም። ይልቁንም በሚያገኙት የመንፈስ እርካታ ሕይወታቸው በብርሃን እንዲሞላ በፍቅር እንዲንበሸበሽ ይሆናል። ለመስጠት የልብ ቁርጠኛ መሆን እንጂ ብዙ የሚሰጥ ነገር መያዝን አይሻም።
ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠት ባህል የነበራትና በፍጹም ወንድማማችነት ዜጎች የሚኖሩባት ችግራቸውን በጋራ በመተባበር የሚያሳልፉባት አገር ነች። ይህ በመስጠት የሚገለጸው በጎ ፈቃደኝነት የአገሪቱ ነባር ባህል ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት ልማድና ወግም ነበር። ሲወልድ የግምዶ፣ ሲያዝን የዝን ብሎ ከመስጠት ጀምሮ ሲዘምት የስንቅ፤ ሲመለስ የደስታ፤ ሲሻር የሹመት፤ ሲሾም የምስራች ብሎ እስከመስጠትም የረቀቀ ነው። ከነዚህ ሁኔታዎች አንፃር በመመልከት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የበጎ አድራት ማህበራት እየተቋቋሙ ይገኛሉ፡፡
በተለያየ ዘርፎች ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት መትጋት በጎነትና ልበ ቀናነት የሚፈጥረው የአዕምሮ እሳቤ ውጤት ነው:: ከሀሳብም ዘልሎ በተግባር የሚገለጽ በጎነት ደግሞ በወጣትነት ሲሆን ያስደስታል:: ምክንያቱም ወጣትነት ለመልካም ሲውል አካባቢን ቀርቶ አገርን ብሎም ዓለምን የመለወጥ አቅም አለውና ነው:: ይህ ደግሞ ከወጣትም በላይ በሴት ወጣቶች ትምህርት ተፈጥሮለት ሲተገበር ውጤቱን የሚያጎላው መሆኑ እሙን ነው:: ከነዚህም ውስጥ የ08 ወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር ይጠቀሳል፡፡
ማህበሩ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ችግረኛ ሰዎች ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ በችግር ላይ ለሚገኙ ሰዎች ቤት በማደስና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በመርዳት በተቻለው አቅም እየሰራ ይገኛል፡፡ ለሕፃናት ተማሪዎች አስፈላጊውን የጤና እንክብካቤ እያደረገ ይገኛል፡፡ የ08 ወጣቶች የበጎ አድራጎት ማህበር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታነህ ተስፋዬ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
የማህበሩ አመሰራረትና ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ የተመሰረተው በኮልፌ አጠና ተራ በአካባቢው በሚገኙ ቅን አሳቢ ወጣቶች ነው፡፡ የተመሰረተው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ «የ08 ወጣቶች የበጎ አድራጎት ማህበር» ጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ ተመሰረተ። በዋነኝነት ዓላማው አድርጎ የተነሳው በአካባቢያቸው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ ነው። በሌላ በኩል በትምህርት ጥሩ የሆኑ ልጆችን መደገፍ የጤና እንክብካቤም የማድረግ ሥራ ነው።
የማህበሩ የሎጎ ትርጉም የእጁ ትርጓሜ የማህበሩን ለጋሽነት እና በጎ ማድረግን ይገልፃል፡፡ 08 በእጅ ላይ መኖሩ ለአካባቢው ነዋሪዎች «እኛ ለእናንተ ከጎናችሁ ነን» የሚለውን ይገልፃል፡፡ የተፈነጠቀው ብርሃን ተስፋን ይገልፃል፡፡ ከታች ያለው ሪቫን አዲስ ጅማሬ መሆኑን፤ ሁለት ዓይነት ቀለሞችን የተጠቀሙ ሲሆን አንደኛው ቀይ ቀለም ኃይል፣ ተስፋን፣ ተግባር እና ቀና መሆንን ያመለክታል፡፡ ሁለተኛው ቀለም ማሮን ሲሆን እሱም በራስ መተማመን፣ ጥንካሬን፣ አዲስ እሳቤን እና በጎነትን ይገለጻል።
ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ ከዚህም ውስጥ በአሁኑ ወቅት ለስድስት ቤተሰብ ወርሃዊ ድጋፍ፣ አንድ ተማሪ ማስተማር፤ እንዲሁም በበዓላት ወቅት ለበዓል ማሳለፊያ የሚሆኑ ድጋፎችን ማድረግ ላይ ነው። በጠቅላላው ለ50 ሰዎች ድጋፍ ተደርጓል። ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በጋራ ከመስራት አኳያ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እንቅስቃሴዎች አሉ። መንግሥት በአካባቢው በጀመረው የቤት እድሳት ላይ የማህበሩ አባላትን በማስተባበር የማደስ ሥራ በጋራ ተሰርቷል። ከተስፋ የበጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር ለአንድ ታዳጊ የዊልቸር ድጋፍ ተደርጓል።
በማህበራችን የበዓል ጉብኝት ወቅት ለአስራ ሁለት ዓመታት ከቤት ውስጥ ሳይወጣ ያገኘነው ሕፃን የአብስራ በሳቱ የዊልቸር እንዲሁም የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በገለፅነው መሠረት ለ20 ዓመታት ኮልፌና አካባቢዋ የሚገኙ አረጋውያንን፣ ሕፃናትንና ሌሎችንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደግፈው «ተስፋ ማህበረሰብ አቀፍ ልማት ማህበር» ፈቃደኛ በመሆን ለሕፃን የአብስራ የሚሆን ዊልቸር አበርክቶልናል። በቀጣይም አስፈላጊውን ሕክምና እስኪያገኝና ማህበራችን በሚሰራቸው ማናቸውም የበጎ ሥራዎች ላይ በጋራ እንደሚሰራ ቃልም ገባልን። ቀጠለና የኮልፌ 05 በጎ አድራጎት ማህበር የዳይፐር፣ የሴሪፋምና ሌሎችንም ድጋፍ አበረከተልን። የወረዳ 10 አስተዳደር እነዚህን አካላት ከማህበራችን ጋር በመሆን በማስተባበር ሕፃን የአብስራ በሳቱን ለመደገፍ ስለተባበራችሁን እናመሰግናለን።
የኅብረተሰቡ አቀባበል
የበጎ አድራጎት ሥራዎች ሲሰሩ የማህበረሰቡ አቀባበል ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንዱ በደንብ ተረድቶ ገብቶት የማህሩን ሀሳብ ለመደገፍ የሚጥር ሲሆን፤ የተወሰነው የማህበረሰቡ ክፍል ደግሞ የማህበሩ ሥራ አጠራጣሪ ወይም ደግሞ ሥራውን የሚሰራው ለግል ጥቅም እንጂ ለማህበረሰቡ አስበው አይደለም ብሎ የሚያምን
ነው፡፡ የኮልፌ አጠና ተራ ከነዋሪዎች ተሳትፎ አንፃር በሀሳብ፣ በገንዘብ በተለይም በጉልበት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። የማህበር የአባላቱ መዋጮ እንዳለ ሆኖ «አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ» በሚል መርህ ሦስት ቤተሰቦች በግለሰቦች ቀጥተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑም ይህን ማህበር ከሌሎች ለየት ያደርገዋል።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
እነዚህን የበጎ አድራጎት ተግባራት በተሻለ መልኩ ለማከናወን የገጠሙ አክሎች ከማህበሩ ድጋፍ የሚፈልጉ እንዲሁም ማህበሩን ለመደገፍ የሚፈልጉ ግለሰቦችን ተቀብሎ ለማነጋገር የቢሮ እጥረት/ችግር መኖር፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ እጥረትም በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ በቀጣይ ያሰበው ነገር በአካባቢው የቤተ መጽሐፍት ማደራጀት፣ የወጣቶች የሥነልቦና ድጋፍ እና ሥራ ዕድል ፈጠራ የተሻለ ኑሮ ያላቸው ነዋሪዎችን በማስተባበር ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስተሳሰር ሥራ የመስራትን ነው።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013