ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከትናንት በስቲያ ከፋና ብሮድ ካስት ኮርፖሬት ጋር በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል። እኛም የዚህን ቃለ መጠይቅ ሙሉ ቃል በተከታታይ ከዛሬ ጀምሮ የምናቀርብ ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡- 6ኛው አገራዊ ምርጫ እስካሁን ባለው ሂደት ውስጥ እንደ አገር መሪና እንደ ገዢው ፓርቲ ሊቀመንበርነትዎ ሂደቱን ምን ያህል ይከታተሉት ነበር፤ እንደ መንግሥትስ የምርጫው ሂደት አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ምን ዓይነት እገዛ አድርጋችኋል?
ዶክተር ዐቢይ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ምርጫ የይስሙላ መሆኑ ቀርቶ ዜጎች የሚያምኑበት ከንቱ ሙከራ ሳይሆን የተሻለ ሀሳብ ያለው ፓርቲ የሚወጣበት ምርጫ እንዲሆን አስበን ነው ስንሰራ የነበረው፡፡ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ፣ የተሻለ እና ተአማኒ ይሁን የሚለው ዋናውም የታገልንበት አንደኛው አጀንዳ ነው፡፡ እርሱን ማሳካትም የትግላችንን ፍሬ እንደማየት የሚቆጠር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በርካታ ሥራዎች ስንሰራ ቆይተናል፡፡
ከምርጫ ቦርድ ስንጀምር፤ ተቋሙን በሚመለከት አሁን ያለው ተቋም ከዚህ ቀደም ከነበረው ተቋም አንጻር ቢያንስ ከመንግሥት የሚደረግለት ድጋፍ ለውድድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በጥቂት ለማየት አሁን ምርጫ ቦርድ ያለበት ቢሮ ከዚህ ቀደም አንድ ካቢኔ ያለበት ቢሮ ነው፡፡ የተሻለ ቢሮ አላቸው፡፡ ከቢሮ ባሻገር አመራሩን በሚመለከት ሙሉ ለሙሉ ሁሉም የቦርድ አባላት ከመንግሥት ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት ውጪ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም በውይይት ያመጧቸው አባላት ናቸው፡፡ አንድም ሰው ላይ መንግሥት የራሱን ፍላጎት መጫን አልሞከረም፡፡ ስለዚህ ቦርዱ አመጣጡ በራሱ ከእኛ ውጪ በሆነ ምርጫና ሹመት የወጣ ነው ማለት ነው፡፡
ሦስተኛው በጀት ነው፡፡ ዘንድሮ ምርጫ ቦርድ የተሰጠው በጀት ባለፉት አምስት ምርጫዎች ከነበረው በጀት በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡ በበጀት፣ በአመራር በቢሮ ብቻ ሳይሆን ሕግ ጭምር አሻሽለናል። ከዚህ ቀደም የነበረው ምርጫ ቦርድ እንደ ቦርድ አልፎ አልፎ የሚገናኝ፤ በተቋም ደረጃ የሚመራም
አልነበረም፡፡ የአሁኑ ግን ሙሉ ጊዜ ሰጥተው የሚውሉ አመራሮች ናቸው የተመደቡት፡፡ የሠራተኞቹንም አቅም ለማሻሻል ተሞክሯል፡፡ በመንግሥት በኩል እነርሱ የሚፈልጓቸውን ድጋፍ ከማድረግ ውጪ በየትኛውም ውሳኔያቸው ጣልቃ ገብተን አናውቅም፡፡
በሥራቸው ውስጥ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር የእኛን ፍላጎት ለመጫን ሙከራዎች አልነበረም፡፡ ይህንን ምርጫ ቦርድ በደንብ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በድምሩ ተቋም እንዲፈጠር፣ የተሳካ ምርጫ እንዲካሄድ አስፈላጊ የሚባል ድጋፍ በመንግሥት በኩል ተሰጥቷል፡፡ እኛ አላማችን አራት ነው፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው በሁሉም መመዘኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ዜጎች የሚያምኑበት እኛም መልካም ሥራ ሰራን ብለን የምንኮራበት የተሻለ ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡
ሁለተኛው ቀድመው ይደረጉ የነበሩ ስህተቶች መቀነስ ነው፡፡ በገዢው ፓርቲ የሚደረግ ስህተት መቀነስ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ካሸነፍን ታምነን ማገልገል ከተሸነፍን ደግሞ አቅፈን፣ እጅ ስመን አመስግነን መስጠት ነው፡፡ እነዚህን አራት ግቦች ለማሳካት ከተቋም መፍጠር ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለው ሂደት በንጽጽር የተሻለ ጉዞ ተጉዘናል ብለን ለመናገር የሚያስደፍር ሥራ ተሰርቷል፡፡
ጥያቄ፡- 6ኛው አገራዊ ምርጫ በጣም ብዙ ሂደቶችን ያለፈ ነው፡፡ ብዙ ፈተናዎችንም የተሻገረ ነው፡፡ መጀመሪያ በኮሮና ምክንያት እንዲራዘም የሚል ሀሳብ መጣ ሕገመንግሥታዊ ትርጉም ተሰጠው፡፡ ሕገመንግሥታዊ ትርጉም ተሰጥቶት ምርጫው ይካሄድ ሲባል አይካሄድም የሚሉ ችግሮች ተፈጠሩ፡፡ አንዳንዶች የሽግግር መንግሥት እንዲፈጠር የሚጠይቁ አካላት ነበሩ፡፡በዚህ ሂደትውስጥ እንደ አገር መሪ እርስዎ እነዚህ ሀሳቦች ሲስተናገዱ የእርስዎ አቋም ምን ነበር?
ዶክተር ዐቢይ፡- ምርጫው በአንድ ዓመት እንዳይራዘም በጣም ጠንካራ አቋም ነበረኝ፡፡ በእኛ ደረጃ እንደዚያ ዓይነት አቋም የነበረው ፓርቲ ለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እኛ በከፍተኛ ደረጃ ውሳኔውን ለመቀበል ተቸግረን ነበር፡፡ ምርጫ መደረግ አለበት በጊዜው የሚል የጸና አቋም ነበረን፡፡ ነገር ግን ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረን ውይይት ምርጫውን በዚያ ጊዜ ኮሮና ተሰምቶ ሁለት ወር በቀረው ጊዜ ውስጥ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታና ብቃት የለኝም የሚል ሀሳብ ሲቀርብ ምንም እንኳን በወቅቱ እንዲደረግ የነበረ ፍላጎት ቢኖርም እነርሱ የማስፈጸም አቅም ሁኔታ አልተመቻቸልንም እያሉ ምርጫው እንዲደረግ መግፋት ውጤቱን ያማረ አያደርገውም፡፡
ጥያቄ፡- በወቅቱ ኮሮና በነበረበትና መጀመሪያ በተራዘመበት ወቅት የብልጽግና ፓርቲ አቋም ምርጫው በታቀደበት ወቅት እንዲካሄድ ማድረግ ነበር?
ዶክተር ዐቢይ፡- የጸና አቋም ነበረን፡፡ በጊዜው ምርጫው ይካሄድ የሚል የጸና አቋም ነበረን፡፡
ጥያቄ፡- በወቅቱ ሲቀርብ ከነበሩ ክሶች ብልጽግና የምርጫውን መራዘም ለበለጠ መዘጋጀት ይፈልገው ነበር የሚል ነበር?
ዶክተር ዐቢይ፡- እርሱ ውሸት ነው፡፡ አንደኛ ምርጫ ቦርድ በራሱ የምርጫ መራዘም ጉዳይን በሚመለከት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሲያወያይ የብልጽግና አቋም ምን እንደነበረ የተቀረጸ ቪዲዮ እነርሱ ጋር አለ፡፡ ከዚያ ባሻገር እኔ በምመራው መድረክ ላይ ከምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ጋር በነበረን ንግግር በግልጽ የነበረን ፍላጎት ምርጫው እንዲካሄድ ነው፡፡ ምርጫው እንዳይካሄድ የተስማማንበት ምክንያት በወቅቱ ምርጫውን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለምና አልችልም የሚል መከራከሪያ ሀሳብ በምርጫ ቦርድ ስላቀረበ ነው።
ገበሬው መሬቱ የሚቀበለውን ትቶ ራሱ የሚፈልገውን ዘራ እንዳይሆን፣ መሻት ብቻ እንዳይሆንና አጠቃላይ ውጤቱ የምንፈልገው ሳይሆን እንዳይቀር በመስጋት ምንም እንኳን መሸጋገሩን እንደ ጥሩ ነገር ባናይም ግን ተሸንፈን ትተነዋል፡፡ ተቀብለነዋል ሀሳቡን፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉ በርካታ የምርጫ ቦርድ ውሳኔዎች በሁሉም እኛ እንደመንግሥት እንስማማለን ማለት አይደለም፡፡ ብዙ የማንስማማባቸውና የማይዋጡልን ውሳኔዎች ይሰጣሉ፡፡
ጥያቄ፡- ለምንድነው የማይዋጡላችሁና የማይስማማችሁን ውሳኔ የምትቀበሉት?
ዶክተር ዐቢይ፡- የምንቀበለው ተቋም ለመመስረት ካለን ፍላጎት ነው፡፡ እኛ መንግሥት ነን፤ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን የምንቀይር፣ የምናሻሽል ከሆነ የምናስበውን ነፃና ገለልተኛ ተቋም አንገነባም፡፡ በዚያ ምክንያት ሀሳቡን ባንስማማበትም ተቀብለን እንፈጽማለን፡፡ ውሳኔዎቻቸው ላይ ጣልቃ የምንገባ ከሆነ የተቋሙን ነፃና ገለልተኛ መሆን ስለምንጫን በዚያ ምክንያት ብዙ ውሳኔዎች ሳናምንባቸው፣ ሳንፈልጋቸው የምንፈጽማቸው አሉ፡፡ በሙሉ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ውስጥ ብዙ ሰው የሚያስበው መንግሥት እንደወሰነ ነው፡፡ መንግሥት የማይዋጥለትና የሚቆረቁረው ውሳኔ ጭምር ነው የሚያስፈጽመው፡፡
አጠቃላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች መንግሥት እንደትክክለኛ ውሳኔ ወይም እንደጠቃሚ ውሳኔ አያያቸውም፡፡ ነገር ግን ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ሲባል ተቋም መገንባት ደግሞ አድካሚና አታካች እንደሆነም ስለምናውቅ አንዳንዱን ጉዳይ እየተሸነፍን፣ እየተቀበልን እናስፈጽማለን፡፡ ይህ ትዕግስት ባለው መንገድ አልፎ አልፎ እየተሸነፍን፣ አልፎ አልፎ እያለፍን ካልሄድን የምናስበውን ተቋም ልንፈጥር አንችልም፡፡ ያ ስለሆነ ነው አልፎ አልፎ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ከምርጫ ጊዜ መራዘም ጀምሮ እየተቀበልን ነው የመጣነው፡፡
የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚይጠቁ ኃይሎች ነበሩ ለተባለው የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የነበረው ሀሳብ አብዛኛው አገር በቀል አይደለም፡፡ ከውጭ የመጣ ነው፡፡ ቀድሞ እኛንም ሲያነጋግሩን የነበረ ሀሳብ ስለሆነ አገር በቀል ሀሳብ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ ሁልጊዜ ሰሞኑን የሰማናቸውን ነገሮች የእኛ አድርገን፣ ሀሳብ አድርገን የማምጣት ልምድ ስላለን እንጂ ብዙ ሰዎች የውጭ ሰዎች እንደዚህ ያለ ሀሳብ ያነሱ ነበር፡፡ በጽሑፍም ያካፍሉን ነበር፡፡
ጥያቄ፡- የሽግግር መንግሥት ምስረታን ጉዳይ መንግሥትዎት ያልተቀበለው ከውጭ የመጣ ስለሆነ ነው ወይስ ሀሳቡ ለኢትዮጵያ ስለማያስፈልግ ነው?
ዶክተር ዐቢይ፡- የሽግግር መንግሥት በኢትዮጵያ ማለት፣ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ዛሬውኑ ይቀደድ አላስፈላጊ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት በፍጹም መነካት የለበትም እንዳለ እንደ ሐውልት ሆኖ መቀመጥ አለበት፤ እንዲነካ ፣ እንዲታረም አንፈልግም፣ የለም ይህ ሀሳብ የሰዎች ሀሳብ ነው በጊዜ ብዛት እየመረመርን እየፈተሽን ለአገር በሚበጅ መንገድ እያረምን መሄድ እንችላለን የሚሉት ሦስት በተለያየ ጽንፍ ውስጥ ያሉ ኃይሎች አሉ፡፡
እነዚህን ነው በጋራ መንግሥት ይሁኑ እያልን ያለነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጫፍ የወጣ ምልከታ በሚኖርበት ጊዜና ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ሥራ ልትሰራ አትችልም፡፡ እንኳን እንደእነዚህ ያሉ ጽንፍ የያዙ አስተሳሰቦች ይቅርና እኛ በአንድ ላይ ለውጥ ብለን የመጣን ኃይሎችም ብንሆን በብዙ እንፈተናለን፡፡ የውጭ ጫናው አለ፤ የጂኦፖለቲካው አለ፤ አጠቃላይ አገራችን ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ትክክለኛው የሽግግር መንግሥት ሂደት ምርጫ ነው፡፡ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፡፡
ከዚያ ምርጫው ላይ የተሳተፉ ኃይሎች አሸንፈው ወንበር ስለያዙ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ያላቸውን ድምጽም ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች መስራት ትችላለህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መቶ ምናምን ፓርቲ ነው ያለው፡፡ ይህ ፓርቲ የቤተሰብ ይሁን፣ የሰፈር ይሁን፣ የዘር ይሁን፣ የሃይማኖት ይሁን ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ ፓርቲ ነው፡፡
ነገር ግን ለውድድር ቀርቦ አንዳንዱ 10 ሌላው 20 መቀመጫ ያሸንፋል፡፡ አንዳንዱ ካስቀመጠው የተሟላውን መቀመጫ ባያሸንፍ በብዙ ሺ የሚቆጠር ደጋፊ
ይኖሩታል፡፡ እነዚህን ታሳቢ እያደረግህ ይህ ሀሳብ እንዲታሰብ ከኋላ ደጋፊ ስላለው ከእነዚህ ኃይሎች ጋር እየመከርን አገር ብንመራ የሚል ሀሳብ ለመያዝም የሕዝብ ቀጥታ ተሳትፎን ይጠይቃል እንጂ ተሰብስቦ እኛ ፓርቲ ነን ስላሉ ብቻ እነርሱን ሰብስበህ የሽግግር መንግሥት ብናስበውም፤ አናሳካውም፡፡
በብዙ አገራትም እንዳልተሳካ ሁሉ እኛ አገርም አይሳካም፡፡ በዚያ ምክንያት ነው አይጠቅመንም፣ የሚጠቅመን በምርጫ ሕዝብ የሚፈቅደውን፣ የሚፈልገውን መንግሥት ቢመርጥ ይሻላል የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ እኛ የምናራምደው፡፡
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያውያን በዴሞክራሲያዊና በተአማኒ ምርጫ የሚመረጥ መንግሥት ይፈልጋሉ፡፡ በዴሞክራሲያዊና በፍትሀዊ ምርጫ ሥልጣንን የሚያሸጋግር ወይም ደግሞ የሚሰጥ ፓርቲም ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የፈለጉትን ቢመርጡ እርስዎ የሚመሩት ፓርቲ ውሳኔያቸውን ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ ነው?
ዶክተር ዐቢይ፡- የእኛ ዋነኛ ፍላጎት ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው በመረጠችው፣ የተሻለ ሀሳብ የተሻለ ልምድ፣ የተሻለ ብቃት እናም ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ሊያሻግር ይችላል ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያመነበት ፓርቲ መመረጡና መምራቱ የትግላችን ውጤትና ፍሬ ነው፡፡ ያ ማለት የግድ ብልጽግና ማለት አይደለም፡፡ ብልጽግናም ካሸነፈ በታማኝነት ማገልገል አለበት፡፡ ብልጽግና ባያሸንፍና ሌላ ፓርቲ ቢያሸንፍ ለዚያ ላሸነፈው ፓርቲ እኛ ወደን ፈቅደን አመስግነን መስጠትም የትግላችን አካልና ድል አድርገን ነው የምንቆጥረው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው እንቁላል ፍርፍር ሊበላ ከፈለገ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት እንቁላሉን መስበር ነው፡፡ እንቁላሎች ሳይሰበሩ እንቁላል ፍርፍር መብላትን ማሰብ አይቻልም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ኢትዮጵያ ውስጥ ማምጣት ግብ አድርገህ ተነስተህ ስትሸነፍ የማትሰጥ ከሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚባል ህልምና ፍላጎት በውስጥህ የለም ማለት ነው፡፡
አንድ ሰው ቤት ልገንባ ብሎ ተነስቶ ድንጋይ አልፈልግም፣ አፈርን ከጭድ ጋር አላገናኝም አላቦካም ቢል ቤት ሊገነባ አይችልም፡፡ እነዚያ ጉዳዮች ቤት ለመገንባት በጣም አስፈላጊ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ ለእኛም ማንም ያሸንፍ ማን ሕዝብ ለመረጠው፣ ለፈለገው፣ ለፈቀደው አካል ሥልጣን አሳልፎ መስጠት በራሱ የትግላችን ውጤትና ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ስለምናምን ካለምንም ጥርጥር ሕዝብ ከመረጠን በታማኝነት፣ በትጋት፣ ኢትዮጵያን አንድ አድርገን የበለጸገች አገር ለመፍጠር እናገለግላለን፡፡ ይህ ሀሳብ ትክክል አይደለም፤ የላቀ ሀሳብ አለኝ ፤ ከዚህ የተሻለ ሀሳብ
የምመርጠው አለኝ ካለ ሕዝባችን ካለምንም ጥርጥር እናስረክባለን፡፡ በዚህ ምንም ወደ ኋላ የምንልበት ሀሳብ አይደለም፡፡
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ወቅት ያለው አንዱ ችግር ፓርቲና መንግሥት የተቀላቀሉ በመሆናቸው በምርጫ ጊዜ የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ተጠቅመው የፓርቲውን ሥራ መስራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲና መንግሥት ድርብ ኃላፊነት ይኖርበታል በምርጫ ውስጥ፡፡ ይህንን አጣጥሞ ከመሄድ አንጻር ኢትዮጵያ ከነበረችበት ችግር የሚያላቅቅ ምን መንገድ ተከትላችኋል፤ ምንስ ሰርታችኋል፤ ድርብ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር?
ዶክተር ዐቢይ፡- ድርብ ኃላፊነት ፓርቲያችን አለው ስንል በአንድ በኩል መንግሥት ነው፤ በሌላ በኩል የሚፎካከር ነው፡፡ እኛ ከብዙ አገራት ጋር ባለን ንግግር ውስጥ የተሻለ አቅምና ጉልበት ካላቸው አገራት ጋር የማያግባባን ሚዛኑም እነርሱ መዛኙም እነርሱ ስለሆኑ ነው፡፡ እኛ ሱቅ ቤት ሄደን አንድ ኪሎ ስኳር የምንገዛው የምንተማመነው የሚሸጥልንን ባለሱቅ ሳይሆን ሚዛኑን ነው፡፡ ሚዛኑ በእርሱም በእኛም አልተሰራም፡፡ ሌላ ገለልተኛ አካል የሰራው ሚዛን ስለሆነ በዚህ ሚዛን ያለ የመስፈሪያ ሥርዓት ለሁለታችንም ሚዛናዊ ነው ብለን ነው አንድ ኪሎ ብለን የምንገዛው፡፡ ነገር ግን የምናውቀውን ሥርዓት ያለው ሚዛን መሆኑ ቀርቶ ያ ሰው በራሱ መመዘኛ ቆንጠር አድርጎ ይህ አንድ ኪሎ ነው ቢለን ልናምነው አንችልም፡፡ የዘንድሮ ምርጫ ሂደት እስካሁን ከነበረው የተሻለ ነው የተሻለ አይደለም የሚለውን ዜጎች አንተን ጨምሮ ሚዛናችን ሕዝብ ነው፤ ሕዝብ ሊያየው ይችላል፡፡
በእኛ በኩል ቀደም ብለን በርከት ያለ ገንዘብ ሕዝብ እንዲረዳን ጠይቀን ብዙ ገንዘብ ስላገኘን በእርሱ ነው ሥራ የምንሰራው፡፡ በተቻለ መጠንም መቀላቀል እንዳይኖር የመንግሥትን ንብረት ለዚህ ምርጫ አላማ እንዳይውል ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርጫዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት መልክ እንዳላቸው እናውቃለን፡፡ ያ ነገር እንዳይደገም አንዱ ግባችን ስለሆነም ጭምር የሥልጠናችን አካል የነበረው ሀሳብ ይህ ነው፡፡
ለካድሬዎቻችን የነገርነው አንዱ ነገር ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ሲደረግ የነበረው ምርጫ አንድ ዳቦ የሚቆርስ ሰው ዳቦውን አራት ቦታ ከከፈለው በኋላ አንደኛው ክፋይ ዳቦውን ላመጣው ሰውዬ አንደኛው ክፋይ ዳቦውን ለቆረሰው ሰውዬ አንደኛው ክፋይ ደግሞ ለማህበሩ ሊቀመንበር ሌላ የመጨረሻው ክፋይ ቀድሞ ለመጣ ብሎ አራቱንም የዳቦ ቁራሾች ለራሱ
ወሰደው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምርጫ የሚባል ነገር ተፈጥሮ ብዙ ሀብትና ጊዜ አባክነን መልሰን ዳኛ ሆነን የምንወስደው ነገር እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡
ቀድሞ ነገር አሸናፊ ወይም ተሸናፊ የሚባል ነገር የሚኖረው የመሸናነፍ ሜዳውም የጨዋታ ሥርዓቱም ለሁለቱም ቡድኖች የሚያጫውት ከሆነ ብቻ ነው፡፡ አንድ ቡድን ብቻውን ገብቶ ተጫውቶ አሸነፍኩ ሊል አይችልም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው አሁናዊ ሁኔታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ባለፉት አምስት ምርጫዎች ከተደረጉት እጅግ የተሻለ የውድድር አውድ አላቸው፡፡ ለዚያ የመጀመሪያው ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ መሆኑ ነው፡፡ እኛ እንደተፎካካሪ ፓርቲ ያለን ፍላጎት ብዛትና ልክ ሳይሆን ያንን የሚወስነው አካል ከሁሉም ኃይሎች ገለልተኛ ሆኖ ፣ ነፃ ሆኖ፣ ከመንግሥት ጫና ውጪ በራሱ እቅድና ፍላጎት ሥራ የሚሰራ መሆኑ ያንን አውድ የተሻለ ያደርገዋል፡፡ ያም ቢሆን ተቋሙ በሚፈለገው ደረጃ ቆሞ ጠንካራ ሆኖ ማስፈጸም እስኪችል እዚህም እዚያም ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን በንጽጽር እስካሁን ከነበሩት እጅግ የተሻለ ምርጫ ሥርዓት አለ ማለት ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በብዙ መንገድና በብዙ ምክንያት ፈተና በዝቶባታል፡፡ ለምንድነው ኢትዮጵያ ፈተና የበዛባት፤ ለምንስ ለዚህ ተዳረገች?
ዶክተር ዐቢይ፡- ኢትዮጵያ ፈተና በዝቶባታል የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡ እናም ለአንተም፣ ለአድማጩም ለሚመለከተንም ሰው አደራ ማለት የምፈልገው ስናልፍ ፈተናው እንዳይረሳ ነው፡፡ ፈተና እንዳለብን ማወቅ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ፈተናውን ስንሻገር መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡ ከመጣን ጊዜ ጀምሮ በየዕለቱ በፈተና የተሞላ ጉዞ ነበረን፡፡ ከምሥራቅ ሱማሌ ጀምሮ አልፈን ስንሻገር ይዘነጋል፡፡
ያ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሁለተኛ ብዙ የምንሰማው ድምጽ የጠላቶቻችን ድምጽ ነው፡፡ የሚቃረኑ ኃይሎች ድምጽ ነው፡፡ ጠላቶቻችን ገብቷቸዋል፡፡ የምንጓዝበት ጉዞ፣ ወዴት እያመራን እንደሆነ ጠንቅቀው
አውቀውታል፡፡ የብልጽግና ጉዟችን የማይቀለበስ መሆኑን ኢትዮጵያ ለአካባቢ አገራት መልህቅ የምትጥል መሆኑን ገብቷቸዋል፡፡ ይህንን ደጋግሞ ማፍረሻ መንገድ ብለው የሚያስቡት የጥላቻና ጠቃሚ ያልሆኑ ጉዳዮችን አየር ላይ ይሞላሉ፡፡ ነገር ግን የእኛ የሚባለው ሰው ደግሞ ጠላቶቻችን ደጋግመው የሚነግሩን ጉዳይ የውስጥ ድክመታቸው ጉዳይ እንደሆነ አያውቅም፡፡
ስለ ኢትዮጵያ መድከም፣ ስለ ኢትዮጵያ መፈተን ፣ ስለ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ መግባት ከሌላ የምንሰማው ድምጽ በእነርሱ ውስጥ ያለው ድካም መገለጫ አድርገን ካልወሰድን ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈውም አንስቼዋለሁ ብልጽግና መጥቶ አስቦ አቅዶ የሰራቸውን ጉዳዮች አላነሳቸውም፡፡ ለምሳሌ እንጦጦ ሰራን፤ እንትንን ሰራን ብዬ አልናገርም፡፡ እነርሱ ይቆዩልን፡፡ ነገር ግን በዚህ ፈተና ውስጥ ቀድሞ ሰላም ነበር፣ የተሻለ ጊዜ ነበር በሚባል ጊዜ ውስጥ የቆሙ የተበላሹ ሥራዎችን ብቻ እንይ፡፡ ህዳሴ በነበረው ሂደት በፊትም ብየዋለሁ በ20 ዓመት ውስጥም አያልቅም፡፡ ኤሌክትሮ ሜካኒካሉን እንዳለ አፍርሰን 450 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ሀብት አፍስሰን፣ አመራሩን፣ ሥርዓቱን፣ ካምፓኒውን ቀይረን ነው ህዳሴውን እየሰራን ያለነው፡፡
በሰላሙ በተሻለው ጊዜ ያንን ማድረግ ሳንችል ቀርተን አሁን በፈተናው ጊዜ እንዴት አደረግነው? ኮይሻ ሙሉ ለሙሉ ቆሞ ነበር፡፡ ህዳሴ እንኳን ከእነምናምኑም እንቅስቃሴ ነበረው፡፡ ኮይሻ ግን ሙሉ ለሙሉ ሥራው ቆሞ ነበር፡፡ አሁን ፈተና አለ በምንልበት ሰዓት፣ ችግር አለ በምንልበት ሰዓት ገንዘብም፣ ጉልበትም፣ ኃይልም፣ መሪም መድበን ኮይሻን እንደ አዲስ እየሰራን ነው፡፡ ሌላም ግድብ ማንሳት እችላለሁ፡፡ የግድብ ይብቃና ስኳርን እናንሳ፡፡ 10 ገደማ ስኳር ፋብሪካዎች ያኔ የተሻለ ሰላም፣ የተሻለ ጊዜ በሚባልበት ፈተና የለም በሚባልበት ሰዓት ተጀምረው ሊጠናቀቁ አልቻሉም፡፡ ከለውጡ በኋላ ሰባቱን አጠናቀናል፡፡ 92 ቢሊዬን ብር ገደማ ለዚህ አውጥተናል፡፡ በፈተና ውስጥ የምንቆም ሳይሆን ፈተናን፣ ችግርን ተቋቁመን የምንሻገር መሆናችንን ያለውን አንድምታ ማየት እንድንችል ነው፡፡
አራት አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ጀምረናል በአራቱ ክልሎች፡፡ በዚህ ፈተና ነው በተባለ ጊዜ ውስጥ ሦስቱን አጠናቀናል፡፡ ከሕንፃ፣ ከፕሮጀክቶች አንጻር በጣም በርካታ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ አንድ ሰው ተቀምጦ ዳገት እዚያ ማዶ እያየ እዚህ ዳገት ላይ ብወጣ ይደክመኛል፣ እዚህ ላይ ብጓዝ አደጋ ያጋጥመኛል፣ አውሬ ሊገጥመኝ ይችላል እያለ ተቀምጦ ሊያላዝን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ትንሽ እየወጣ ሞክሮ የዳገቱን ጥንካሬና ክብደት ፈትኖት ሊቆም፤ ሊመለስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ጨክነው የተራራው ጫፍ ላይ የወጡ ሰዎች ፈተናውን ማለፍ ብቻ ሳይሆን እዚያ የተራራ ጫፍ ላይ በመቆማቸው ምክንያት አሻግረው የሚያዩት አዳዲስ ተስፋ፣ አሻግረው የሚያዩት አዳዲስ ዕድል ይፈጠራል፡፡
እኛ የሚፈትነን ነገር እንዳይኖር አንፈልግም፡፡ የሚፈትነን ነገር እንዳያቆመን ነው የምንፈልገው፡፡ በፈተና መቆም አንፈልግም፡፡ በእርግጥ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ብንወስድ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውታል፡፡ በእርግጠኝነት የምናገረው ዛሬ ያለው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በኢትዮጵያዊነቱም፣ በውስጥ ጥንካሬውም፣ በተቋማዊ ግንባታውም ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ ካላት ወታደር በብዙ፣ በእጅጉ የበለጠ ነው፡፡ አሁን ወታደር ነው እየፈጠርን ያለነው፡፡ ሰላምታ የሚያውቅ፣ ሥርዓት የሚያውቅ፣ አገርን የሚወድ ፣ ባንዲራ የሚያከብር፣ ለባንዲራ መስዋዕት የሚሆን ወታደር ነው እየፈጠርን ያለነው፡፡
በእያንዳንዱ በተፈተንንባቸው አውድ ውስጥ የተሻለ ቁመና እየፈጠርን ለመሄድ ዕድል አግኝተናል፡፡ ፈተናዎቹን የምናየውም በዚህ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ሰሞኑን ካለው የኳስ ጨዋታ አንጻር እንኳን ወስደን ብንመለከት ሁለት የሚቃረኑ ቡድኖች በአንድ ሜዳ ውስጥ ኳስ ይጫወታሉ፡፡ በዚህኛው ቡድን ውስጥ ያለ በኤ ቡድን ውስጥ ያለ አጥቂ ሰው ኳሱን ይዞ ለማጥቃት ቢንደረደር ከሚቃረነው ኃይል ሊገጥመው የሚችለው ነገር ከሞላ ጎደል ይታወቃሉ፡፡ አንደኛው በብቃት በልጦ፣ በችሎታ በልጦ ኳሱን መቀማት ነው፡፡ ምንም ሕግ ሳይጣስ በተሻለ ብቃት ኳሱን ቀምቶ በወገን ኃይል ላይ ግብ እንዳያስገባ ማድረግ ነው፡፡
በብቃት የማትበልጠው ሰው አስቸጋሪ ከሆነ ሰውዬው የሚያጠቃው ግለሰብ ዳኛ ሳያይህ ራስህን ደብቀህ ጎንትለህ ጎትተህ ፣ ጠልፈህ ኳሷ እንድትቀር እንድትጨናገፍ ማድረግ ነው፡፡ በችሎታም ካልበለጥህ፣ ዳኛን ደብቀህም ማስቀረት ካልቻልክ ሦስተኛው ነገር ዳኛ እያየህም ቢሆን ፋውል መስራት ነው፡፡ ዘለህ እግር ውስጥ መግባት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ጉዳይ የተጫዋቾቹ ጉዳይ ሳይሆን የዳኛው ነው፡፡ ብቃት ያለው፣ በትክክል የሚቆጣጠር፣ በራሱ የሚተማመን ዳኛ ከሆነ ፋውል ሲያይ ቀይ ይሰጣል፣ ቢጫ ይሰጣል፣ ቅጣት ምት
ያዛል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምናየው ፋውል ተሰርቶ እያለ ዳኞች ሊያልፉት ሁሉ ይችላሉ፡፡ እኛ አሁን ባለው ፈተና ውስጥ እንፈተናለን፤ እንማርበታለን፤ ከተራራው ጫፍ እንወጣለን፤ አርቀን አሻግረን እንመለከታለን፤ ኢትዮጵያን ባለ ድል እናደርጋለን፡፡ ፈተና አልባ ጉዞ ሳይሆን በፈተና ውስጥ አሸንፈን የምንሻገርበትን አውድ ነው የምናየው፡፡ እናም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር በዚህ አግባብ ማየት ጠቃሚም ተገቢም ይመስለኛል፡፡
ጥያቄ፡- ፈተና ብሎ ኅብረተሰቡ ከሚያነሳው ውስጥ አንዱን ልጥቀስ፡፡ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት አልፎ መግባቱንና መሬት ወሮ መያዙን ነው፡፡ ሁለት ጥያቄም ይነሳል፡፡ አንዱ ኢትዮጵያ ጦሯ የት ሄዶ፤ ድንበሯ ተደፍሮ የሱዳን ጦር ሰራዊት ገባ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለምንድነው መንግሥት የተወረረ መሬቱን የማያስመልሰው ?
ዶክተር ዐቢይ፡- ቅድም እንዳልኩህ ፈተናን የሚያቆም፣ የሚያስቀር ሳይሆን የምትሻገርበት አድርጎ ወደላቀ ደረጃ የሚያወጣህ አድርጎ ማየት የተፈታኙ ድርሻ ነው ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ በትንሽዬ ወራጅ ኩሬ ውስጥ ብቅ ብሎ እንደሚታይ ድንጋይ መውሰድ ትችላለህ፡፡ በዚያ ኩሬ ውስጥ ብቅ ያለ ድንጋይ ካለ አላፊ አግዳሚው ውሃ ረግጦ ላለመሻገር ያንን ድንጋይ እየረገጠ መሻገር ይመርጣል፡፡ ያንን ድንጋይ ካልረገጠና ውሃውን ከረገጠ ልብስና ጫማው ይበላሽበታል፡፡
ጠንከር ያለ አለት በወራጅ ውሃ ውስጥ ወይም በትንሽ ኩሬ ውስጥ ካገኘ እርሷን ረግጠህ ትረማመዳለህ፤ እንደ ድልድይ እያደረግህ፡፡ አሁን እዚህም እዚያም ችግር ሲያጋጥም ኢትዮጵያን በዚያ መንገድ ማየት የሚፈልጉ የቅርብ የሩቅም ኃይሎች አሉ፡፡ ነገር ግን የሱዳንን በሚመለከት መከላከያው የት ሄዶ ነው ለሚለው ጥያቄ መከላከያው የት እንደነበረ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አልገምትም፡፡ በተደጋጋሚ ሳነሳው ስለነበር፡፡ ሱዳን ድንበር ላይ የነበረ ወታደር ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በነበረው ግጭት ወደዚያ ተሰማርቶ ስለነበር ነው የሱዳን ጦር ቦታውን የያዘው፡፡
የሱዳን ጦር ቦታውን ከያዘው በኋላ በቅርቡ አንድ የሱዳን ጦር ወታደራዊ አመራር እንዳሉት ምንም ዓይነት ግጭት ከኢትዮጵያ ወታደር ጋር አላደረጉም፤ እስካሁንም ድረስ፡፡ ምክንያቱም የሱዳን ሕዝብ ለእኛ ወንድም ሕዝብ ነው፡፡ የሱዳን ሕዝብ የኢትዮጵያን ሕዝብ
ይወዳል፡፡ ይህንን በተግባር የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የሱዳን ሕዝብ ከማንም ሕዝብ በላይ ለእኛ ቅርብ ሕዝብ ነው፡፡ ቅድሚያ የሰጠነው ዲፕሎማቲክ በሆነ መንገድ ጉዳዩን ማየት
ነው፡፡ ምክንያቱም የድንበር ጉዳይ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ሞክረዋለች፡፡
ከኤርትራ ጋር ሞክራ በጦርነት አሸንፋ ወደ ፍርድቤት ሄዳ የምናውቀው ነው ውጤቱ፡፡ እና አሁንም ሰው ገድለን ሰው ሞቶብን መሬት ከያዝን በኋላ ሄዶ ሄዶ ጉዳዩ ወደ ሕግ የሚቀርብ ከሆነ በዓለምአቀፍ ሕግጋቶች የሚታይ ከሆነ ቀድሞ ወደ ውጊያ መሽቀዳደም ጠቃሚ ነው የሚል ሀሳብ የለንም፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሱዳን ይጠቅማል የሚል ሀሳብ የለንም፡፡ እኛንም ሱዳንንም የሚጎዳ ሀሳብ ነው፡፡ ሰክነን በውይይት ማየት ይሻላል ብለን እናስባለን፡፡ ይህ ለእኛም ለእነርሱም እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም፡፡
ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ እኛም የምንጎዳበት እነርሱም የሚጎዱበት እንደሆነ ቅንጣት ጥርጣሬ የለንም፡፡ ለምሳሌ አንድ ምሳሌ ለማንሳት በአንድ ቁር ኃይለኛ ብርድ ወቅት በአንድ አካባቢ በርከት ያሉ ከብቶች ይኖሩ ነበር ይባላል፡፡ እነዚህ ከብቶች ብርዱን ለመከላከል እየተሻሹ፣ ተጠጋግተው አንዱ ለሌላኛው ሙቀት እየሰጠ በጋራ ያንን የመከራ ጊዜ ለማለፍ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ እናም እየተገፋፉ፣ እየተሻሹ፣ ሙቀት እየተቀባበሉ ሲኖሩ ከመተሻሸት ብዛት የአንደኛዋ ጀርባ ይላጣል፡፡ ወይም የአንዳንዶቹ ይላጣል፡፡ እናም ከሚላላጥና ቆዳዬ ከሚገፈፍ ራቅ ብዬ ብቀመጥ ይሻለኛል ብለው የመረጡ ከብቶች ራቅ ብለው ተቀምጠው ያ ሲያገኙት የነበረው ሙቀት ስለቀረባቸው በጊዜ ብዛት ሞቱ፡፡
ሞታቸውን ያዩ ሌሎች ከብቶች መልሰው ተጠጋግተው ሙቀት እየተሰጣጡ ለጊዜው መቁሰል ከመሞት ይሻላል፤ ከምንሞት ለጊዜው አንዳችን ለሌላችን ሙቀት እየሰጠን ብንዘልቅ ይሻላል ብለው መኖር ቻሉ ይባላል፡፡ የእኛና የሱዳን ጉዳይ እንደዚህ ነው፡፡ በመደጋገፍ ውስጥ ሱዳን ችግር ሲገጥማት ሮጠን ሄደን ደግፈን እንደ አገር እንድትቆም ሙከራ አድርገናል፡፡ ለምን ለእኛም ስለሚጠቅመን፡፡
ወንድም ሕዝብ ስለሆንን፡፡ አሁን ደግሞ እኛ ነካኩን ብለን ለዚህ ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ቅድሚያ ማየት የሚገቡንን ጉዳዮች ሳናይ ብንሄድ ሱዳኖች ይጎዳሉ፤ እኛም እንጎዳለን፡፡ ጉዳቱ ሁላችንንም ያጠፋናል፡፡ እንደዚያ እንዳይሆን ነው በትዕግስት ጉዳዩን እያየን ያለነው፡፡ በእኔ እምነት ከሱዳን ወንድም ሕዝብ ጋር ብዙ መከራ፣ ብዙ ችግር ስላሳለፍን፤ የሚወደን የምንወደው ሕዝብ ስለሆነ በጋራ ለማደግም በጣም መልካም ዕድሎች ያለን ሕዝብ ስለሆንን ጉዳያችን በንግግር ይፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በንግግር፣ በውይይት፣ በሕግ አግባብ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ በሁሉም ሙከራ ዝግ ከሆኑ ሁሉም ትዕግስት የማይመልሳቸው ከሆነ ያው እንደሚታወቀው ማንም ሰው፣ ማንም አገር ሱዳን ብቻ አይደለም ማንም አገር ከሕግ አግባብ ውጪ የኢትዮጵያን አንድ ስንዝር መሬት ወስዶ መቀመጥ አይችልም፡፡ ያንን ደግሞ ሱዳኖችም ያውቁታል እኛም እናውቀዋለን፡፡
ይህ ቦታ አከራካሪ ቦታ ነው፡፡ ድንበር የሚባለው ጉዳይ የእኛም የእነርሱም ጉዳይ ሳይሆን የገዢዎች መስመር ነው፡፡ በገዢዎች መስመር ምክንያት ግጭት መፈጠር የለበትም፡፡ በንግግር፣ ሰጥተን በመቀበል ልንፈታው እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ኬንያን ብትወስድ የቦረና ኦሮሞዎች ከፊሉ ኬንያ ውስጥ አለ ከፊሉ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፡፡ አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ግን ድንበር መሀል ላይ ከፍሏቸዋል፡፡ በሱማሌ ብትሄድ እንደምታውቀው ከፊሉ እዚህ ነው ከፊሉ እዚያ ነው፡፡ ጅቡቲ ብትሄድ ከፊሉ አፋር፣ ከፊሉ እዚያ ነው፡፡ ኤርትራ ብትሄድ ከፊሉ ትግራይ ከፊሉ ደግሞ እዚያ ይገኛል፡፡ ብዙ ብሔሮች እኛ አገር ላይ ግማሹ እዚያ ግማሹ እዚህ ይኖራሉ፡፡
አንድ ሕዝቦች፣ ቤተሰቦች ይከፈላሉ፡፡ በእኛና በሱዳን መካከልም እንደዚሁ የምንጋራቸው ባህሎች፣ ቋንቋዎች ሕዝቦች ይኖራሉ፡፡ ይህንን በንግግር መፍታት፣ በትዕግስት ማየት ለእኛም ለእነርሱም ስለሚበጅ በከፍተኛ ጥንቃቄ ጉዳዩን እየተመለከትነው ነው፡፡
ጥያቄ፡- በእስካሁን ሂደት ችግርን የመፍታት ሂደት የተሻለ ውጤት ወይም ደግሞ የሁለቱንም አገራት ጥቅምና ፍላጎት ባስከበረ መልኩ እንዲሄድ የሚያስችል ውጤት አይታችሁበታል?
ዶክተር ዐቢይ፡- እንግዲህ አንድ የላቀን ነገር ስትፈልግ ፤ የተሻለ ነገር ለማግኘት ስትፈልግ በትዕግስት፣ በውይይት ፣ በንግግር እፈታለሁ ስትል የቅዱስ ያሬድ ትዕግስት ካልተላበስህ በስተቀር ዘላቂ ድል አታመጣም፡፡ ቅዱስ ያሬድ እየወደቀ እየተነሳ ብቻ ሳይሆን እየወደቀች እየተነሳች ያያትን ትል የመውደቂያው መጨረሻ ሳይሆን ከውድቀት ውስጥ ተነስቶ መሻገር፣ ማለፍ እንደሚቻል አምኖ፣ ጸንቶ ባይመለስ ኖሮ ያ ወደ አክሱም የሚያደርገው ጉዞ ቢሰናከል አሁን የምናደንቀው ዓለም የሚደነቅበት ፈጠራው አይኖርም ነበር፡፡
ለትዕግስት ስትል ብዙ የምታልፋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከሱዳን ጋር ባለው የድንበር ግጭት እስካሁን በሰላማዊ መንገድ መሄዳችንን መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተለው ብቻ ሳይሆን ትክክል ነው ብሎ የሚያስበው ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን በንግግርና በውይይት ልንፈታው ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ይህ የመሬት ጉዳይ ብቻውን የቆመ ጉዳይ አይደለም፡፡ አብረው የሚከቡት በጣም ብዙ ጉዳዮች ስላሉ እያንዳንዱን ጉዳይ በየራሱ እይታ እየተመለከትን ካልፈታን በስተቀረ ዝም ብለን ዘለን የምንገባበት ፤ አንዱ አንደኛውን እየጎተተ የተወሳሰበ ጉዳይ ውስጥ አስገብቶን ባለድል ስለማያደርገን ትዕግስቱ አስፈላጊ፣ ተገቢና ጠቃሚ ነበር፡፡ ይቀጥላልም፡፡
የሚቀጥለው ትዕግስት ግን በቀጥታ ግቡ የኢትዮጵያን መብቶችና ግዛቶች የሚነካካ በሚሆንበት መንገድ ግን አይፈጸምም፡፡ በሕግ፣ በሕርዓት፣ በውይይት ፈር ይይዛል የሚል ጽኑ እምነት ነው ያለን፤ በዚህ አግበብ ነው እየሄድን ያለነው፡፡
ይቀጥላል….
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013