ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከዓለም ዓቀፍ የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሸቀጦች የዋጋ ንረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ህልውናቸውን እስከ መፈታተን እየደረሰ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ምርጫው ከመድረሱ ከአንድ ሳምንት በፊት እጅግ በተጋነነ ዋጋ መጨመር የጀመረው የዘይት፣ የሥጋ፣ የምስር፣ የእንቁላል እና ሌሎችም በየወሩ የሚሸመቱ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት ያሳሰባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤‹‹መፍትሄው ምን ይሆን? በማለት›› የሚመለከተውን አካል ጠይቁልን ያሉት የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ወንደሰን ሲጃ ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደጠቀሱት፤ ዘይት እስከ ስድስት መቶ ብር፣ ምስር በኪሎ ከ60 ብር ወደ 90 ብር ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ ከ90 ብር ወደ 110 ብር ከፍ ብሏል፡፡ የሥጋ ዋጋም ከ240 ወደ 360 አሁን ደግሞ በኪሎ ከ400 ብር በላይ በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ የአንድ እንቁላል ዋጋ ከስድስት ብር ወደ ሰባት ብር አሁን ደግሞ ወደ ዘጠኝ ብር አድጎ የከተማዋ ሸማቾችን ትዕግስት እየተፈታተነ ይገኛል፡፡
በአንድ የግል ትምህርት ቤት እያስተማሩ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት አቶ ወንደሰን ምንም እንኳ ባለቤታቸውም መጠነኛ ገቢ ያላቸው ቢሆንም፤ ገቢያቸው የቤት ኪራይ ከፍሎ ለቀለብ የማይበቃበት ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ፡፡ አገር ሲረጋጋ ሰላም ሲሰፍን ለውጥ ይመጣል በሚል ተስፋ ቢጠብቁም፤ አሁንም የዋጋ ንረቱ ጭራሽ እያሻቀበ በመሆኑ የሚመለከተው አካል የዋጋ ንረቱ የሚቆመው መቼ እንደሆነ በትክክል እንዲገለፅ -ጠይቁልን ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አስተዳደሩ ኑሮን ለማረጋጋትና ጤናማ የንግድ ስርዐት እንዲኖር እየሰራ ነው፡፡ ሥራውን ከተለያዩ አካላት ጋር ማለትም ከነጋዴዎች እና ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በማቀናጀት በመተባበር የሚሰራ ሲሆን፤ አሁን ላይ ነጋዴዎችም የተለያዩ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ቢሮ ለእነርሱም እውቅና
ሰጥቷል፡፡ የመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶች በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ በመደረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለይ ዘይት ፣ጤፍ ፣የስንዴ ዱቄት እና መሰል አስፈላጊ ፍጆታዎች በሸማች ተቋማት እንዲቀርቡ በመደረግ ላይ ነው፡፡
እንቁላል፣ ቅቤ፣ አይብ እና የመሳሰሉ ምርቶችም ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ መሆኑን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በተለያየ መልኩ ድጋፍ በማድረግ የግብርና ምርቶች ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት እንደሚያግዝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በከተማው ውስጥ 10 ሸማች ዩኒየንና ከ140 በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት ያሉ ሲሆን ምርቶቹ ለህብረተሰቡ የሚተላለፉበት ሁኔታ መኖሩን ቢሮ ይገልጻል፡፡
እንደአጠቃላይ በአገር ደረጃ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት፤ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል መንግስት የረዥም እና የአጭር ጊዜ ስልቶችን አስቀምጧል፡፡ ከአጭር ጊዜ አንጻር በገበያ ውስጥ አነስተኛ ሸቀጦችን ማስገባትን እንደአንድ መፍትሔ እያየው ነው፡፡ በሌላ በኩል መሰረታዊ ሸቀጦች እንዳይገቡ የሚያስተጓጉሉ ሃይሎችን እና ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን የሚያስከትሉትን ለመቆጣጠር እየሰራ ነው፡፡ መንግስት በዚህ ላይ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ብዙም የሚፈለገውን ውጤት አላገኘም፡፡
በስግብግብ ነጋዴዎች የሚደረገውን በማረም የሚጎድለውን ሸቀጥ በማስገባት ለመፍታት ሞክሯል፤ ወደ ፊትም ይቀጥላል፡፡ ማዳበሪያ እና ነዳጅን እንደምሳሌ በመውሰድ ማዳበሪያ በዚህ ዓመት 30 በመቶ በዓለም ላይ ሲጨምር ያንን ሸክም ወደ አርሶ አደሩ ላለመውሰድ መንግስት ደጉሟል፡፡ ነዳጅ ላይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጭማሪ አለ፡፡ ስለዚህ መንግስት በወር ከሶስት ቢሊየን ብር እየደጎመ ቆይቷል፡፡ በውጪ የተፈጠረው የዋጋ ማሻቀብ ዜጎችን እንዳይጎዳ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከአጭር ጊዜ አንጻር ዘይትም ሆነ ስኳር ማንኛውም ሸቀጥ የሚጎድለው ከውጪ እንዲመጣ ይደረጋል፡፡ አሁንም እየመጣ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ለማረጋጋት ይሞከራል ብለዋል፡፡
ከረዥም ጊዜ አንፃር ግን ችግሩ የሚፈታበት ዋነኛው መንገድ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡ በተለይ ከምግብ ጋር ተያይዞ ያሉ ሸቀጦችን ማምረት የሚቻልበት መሰረት ቢፈጠር አብዛኛው ችግር ይፈታል፡፡ ስንዴ በበቂ መጠን ማምረት ቢቻል፤ ሰሊጥና ኑግ በብዛት ቢመረት ዘይት ፋብሪካ እየተከፈተ ነው ችግሩ ይቃለላል፡፡ በመስኖ አትክልቶችን በብዛት ማምረት ቢቻል፤ ማንጎ፣ አቮካዶ እና ፓፓያ እየተተከሉ ቢሆንም በስፋት ወደ ማምረት የሚመጡበት ሁኔታ ቢፈጠር በአገር ውስጥ አንገብጋቢ የሆኑ ምርቶችን ማምረት እና የምግብ ፍጆታ ቢሸፈን የውጭ ገቢያ ውድነት የሚያመጣውን ጫና ለመከላከል ዕድል እንደሚሰጥም ነው የገለፁት፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ከምግብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ የሚተከለው ጥድና ባህር ዛፍ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ የፍራፍሬ ዘሮች እየተተከሉ ነው፡፡ መተከላቸው ምርት ከማስገኘት በተጨማሪ ዝናብ በበቂ መጠን እንዲገኝ ያግዛል፡፡ ዝናብ በበቂ መጠን ከተገኘ ደግሞ በማረስ ምርትን ለማሳደግ ዕድል የሰጣል፤ የውሃ ክምችትንም ለማሳደግ ይረዳል፡፡ ስለዚህ በጥቅል ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ብዙ ሥራ ቢሰራም ዋጋ ግሽበት ላይ የተጠበቀው ውጤት አልመጣም፡፡ ነገር ግን የተወሰዱ ሰፋፊ እርምጃዎች ቢወሰዱም አሁንም የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ ምርት እያደገ ሲሄድ ችግሩ ይቃልላል የሚል ተስፋ አለ ብለዋል፡፡ ጨምረውም ስራዎቹ በአንድ ቀን መፍትሔ የማያገኙ መሆናቸውን በማመልከት፤ አሁንም ትዕግስት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013