ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ማለት ከአንድ ሀገር ተነስቶ የሌሎችን ሀገሮች ድንበር የሚያቋርጥ ዓለም አቀፍ ወንዝ
ነው፡፡ ይህ የከርሰ ምድር ውሃንና ገባር ወንዞችን አይመለከትም፡፡ ቀደም ሲል የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ውሃ እና የውሃ ሀብትን ለመከፋፈልም ሆነ ግልጋሎትን በተመለከተ መንግስታትን ግዳጅ ውስጥ የሚያስገባ የዓለም አቀፍ ህግ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይህ ጽንሰ ሀሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሂደት እየተገነባ መጣ፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት በወንዝ ለሚከናወን የመጓጓዣ አገልግሎት ቅድሚያ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ወንዝ ያለው ሚና ትኩረት እያገኘ መጥቶ በቅርቡ “የወንዝ ተፋሰስ” እና “ድንበር ተሻጋሪ ውሃ “ ወይም “ዓለም አቀፍ ፈሳሽ ውሃ” ጽንሰ ሀሳቦች ቀረቡ፡፡ ይህ የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ጽንሰ ሀሳብ በመልከዓ ምድር ስፋትና ከተለያዩ ግልጋሎቶች አኳያ የሚታይ ሂደትን የሚመለከት ሲሆን፤ እነርሱም ከመጓጓዣ ወደ ኢኮኖሚ ሚና፣ የተፋሰስ ጽንሰ ሀሳብ፣ የዓለም አቀፍ ፈሰስ “ሲስተም” እና ዓለም አቀፍ ፈሰስ ሲባል የወንዝ ክፍሎች በተለያዩ መንግስታት ግዛት ውስጥ ሲገኙ ነው፡፡ ስለሆነም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ከመርከብ መጓጓዣ ሌላ ሁሉንም ግልጋሎቶች ያጠቃልላል፡፡
ይህ በእርሻ፣ በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ ማህበራዊና ለዕለት ተዕለት ኑሮ ጭምር ያሉትን ግልጋሎቶች ያካትታል ማለት ነው፡፡ የተባሉት ግልጋሎቶች የውሃውን መጠንም ሆነ ጥራት የሚለውጡ ስለሆነ የሚያስከትሏቸውም ዉጤቶች እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮችና ተግዳሮቶች የሚፈቱና የሚያስተካክሉ ህጎች፣ ስምምነቶች እና ፕሮቶኮሎች አስፈላጊ መሆናቸው ተገለፀ፡፡
ከዚህ አንፃር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የሚመለከቱ መርሆች ፍትሐዊና አግባብ ባለው መንገድ የመጠቀም መርሆ፤ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ፤ በወንዙ ላይ የተወጠኑትን ዕቅዶች በጽሁፍ የማሳወቅ፣ የመመካከርና የመደራደር መርሆ፤
በትብብር የመስራትና መረጃ የመለዋወጥ መርሆ እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምድ የሚሉት ናቸው፡፡
የዓለም አቀፍ ሕግ
የዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ሕግ የመጀመሪያው መንግስታት እርስ በርስ ለብዙ ዓመታት በመሰረቱት ግንኙነት በተሻጋሪ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ያዳበሩት እንደ ሕግ የሚቆጥሩት አሰራር አለ፡፡ ይህም ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ / Customary International law / ይባላል፡፡ በልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ማንኛውም የተፋሰሱ አገር ወንዙን ለጋራ ጥቅም ፍትሐዊና አግባብ ባለው መንገድ / In a reasonable and equitable manner / መጠቀም እንዳለባቸው ያስገድዳል ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በበርካታ ሀገሮች የሚፀድቁ ነገር ግን ገና በእያንዳንዱ አባል ሀገር ያልተፈረሙና ሕግ ይሆኑ ዘንድ በፓርላማዎቻቸው ያልፀደቁ ስምምነቶች / International Conventions / በተለያዩ ጊዜያት እየዳበሩ መጡ፡፡ ከፍ ሲል ከጠቀስነው ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ብዙም ሳይርቁ ፍትሐዊና አግባብ ያለው አጠቃቀም የሚለውን መርህ ይዘው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የወንዙን ብዝኃ ሕይወታዊ ተፈጥሮ አጠባበቅ ላይ በርከት ያሉ ድንጋጌዎችን ያሰፈሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ሶስተኛው የዓለም አቀፍ ሕግ ገጽታ ደግሞ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚያቋርጧቸው ሀገሮች ወንዞቹን በተመለከተ በመካከላቸው እንደ ሕግ ሆኖ የሚፀና ሌሎቹ ግን ( በግልጽ ካልተቀበሉት በቀር ) የማይመለከታቸው ስምምነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስምምነትም በፈራሚዎቹ አገሮች መካከል እንደ ዓለም አቀፍ ሕግ ሆኖ ይሰራል፡፡
ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች ( ስምምነቶች )
እ.ኤ.አ በ1815 የቬና ኮንግረስ በደነገገው ደንብ መሰረት አንድ ወንዝ ዓለም አቀፍ የሚሆነው ከአንድ ሀገር ጠረፍ አልፎ ወደ ሌላ የሚሸጋገርና በተለይ በመርከብ ጉዞ ብቻ ሲወሰን ነበር፡፡ የሌሎቹን የወንዝ ግልጋሎቶች ማለትም መስኖ ወይም ለኃይል ማመንጫ የመሳሰሉትን የቬናው ስምምነት አይሸፍንም ነበር፡፡
እንዲሁም በ1923 የፀደቀው የጀኔቫው ኮንቬሽን (ስምምነት) ሀገራት የሚጋሩትን የወንዝ ሀብት ለማስተዳደር መንግስታት ያፀደቁት ሰነድ ነው፡፡ በተለይ በመካከላቸው ችግር ቢፈጠር ጉዳዩን በድርድር እንዲጨርሱ
ያስገድዳቸዋል፡፡ ስምምነቱ የየአንዳንዱን መንግስት የግዛት ሉዓላዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ የሌሎችን የወንዙን ተጋሪ ሀገሮች መብት በማክበር መተግበር እንዳለበት ኮንቬንሽኑ ያመለክታል፡፡
በዓለም አቀፍ ህግ በመመራት በግዛቱ ክልል ለኃይል ማመንጫ የሚያገለግል የግንባታ ስራ እንደማይከለክል የመጀመሪያው አንቀጽ ያረጋግጣል፡፡ ይህ ኮንቬንሽን እ.ኤ.አ ከሰኔ ወር 1925 ጀምሮ በአስር ሀገሮች ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊጸና ችሏል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሀገሮች የማይዋሰኑ በመሆናቸው ስምምነቱ እምብዛም ተግባራዊ አልሆነም፡፡
በተጨማሪም ከመጓጓዣ አገልግሎት ውጭ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ጥቅም ላይ ስለ ማዋል በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1997 የፀደቀው የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን የተፋሰሱ ሀገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በድንበሮቻቸው ክልል አግባብ ባለውና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ / In a reasonable and equitable manner / እንዲጠቀሙ ያስገድዳል፡፡ አግባብ ያለውና ፍትሐዊ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ውኃ አጠቃቀም ሥርዓት ከሀገሮቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ የሚኖረው የውኃ ክፍል ተጨባጭ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት፣ እንዲሁም የወንዙን ውኃ ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ውኃውን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በተለይም ማንኛውም የተፋሰሱ አገር በሌላው አገር ጥቅም ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንዳያደርስና በመሳሳብ ሳይሆን በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖር ኮንቬንሽኑ ያስገድዳል፡፡ የእያንዳንዱ ሀገር ጥቅምና የውኃ ፍላጎት ከአካባቢያዊና ከብዝኃ ሕይወታዊ ጥቅም በላይ መታየት እንደሌለበት ዓለም አቀፍ ሕግ
ያስጠነቅቃል፡፡ ልዩ ልዩ ዝርዝር ድንጋጌዎችንም አስፍሯል፡፡ ስለዚህም የውኃ ብክለትን፣ ወንዞችን ከጨረራማና ኑክሌር ፍሳሾች፣ ከኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት ዝቃጮችና ኬሚካላዊ ጭሶች ነፃ እንዲሆኑ የተፋሰሱ ሀገሮች ተደጋግፈው እንዲሠሩ ዓለም አቀፍ ሕግ ያሳስባል፡፡
የዓለም አቀፍ የወንዝ ሕግ ልዩ ባህሪያት
የዓለም አቀፍ ሕግ ሚና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ግልጋሎት ዙሪያ የሚነሱ ስጋቶችን ለማስወገድ የተፋሰሱ ሀገሮች ያላቸውን መብትና ግዴታ እንዴት መወስን እንዳለበት ለማወቅ ይረዳል፡፡ የእያንዳንዱ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የራሱ የተለየ ባህሪ አላቸው፡፡
የህግ አዋቂዎች ይህንኑ የወንዞችን የተለያዩ ባህሪዎች በሚከተለው አኳኋን ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ አ.ነ.ካዉንት የተባሉት ጸሐፊ ስለ ዓለም አቀፍ ወንዞች በፃፉት መጽሐፋቸው “አንድ ወንዝ በሕግም ሆነ በኢኮኖሚ ራሱን የቻለ ባህሪ እንዳለው ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህም ለየት ያለ ባህሪ ከዚህ ቀደም በተመራማሪዎች በቸልታ ቢታይም በህግ አሰራር ግን ከፍ ያለ ጥቅም እንዳለው አይካድም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ወንዝ በራሱ ተነጥሎ መጠናት አለበት፡፡
የጂኦግራፊና የፖለቲካ ሁኔታ የወንዙን ህጋዊ አቋም ለመወሰን ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡” በጠቅላላው ሲታይ የዓለም አቀፍ ወንዝ ሕግ ዋናው ምንጭ የተለያዩ ወንዞችን በስም ለይቶ በመውሰድ በመንግስታት የተፈረሙ ሰነዶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ግብፅ እና ሱዳን ከናይል ወንዝ ጋር ተያይዞ የተፈራረሙ ቢሆንም፤ ከላይ በተጠቀሰው ከዓለም አቀፍ ህግ አንፃር ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት በመሆኑ ስምምነቱን ኢትዮጵያ እንድትቀበለው አትገደድም፤ በእርሷ ላይም ተግባራዊ ሊሆን አይችልም፡፡
ምንጭ:- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013