የ2013 በጀት አመት ሲገባ ከሌሎች ሥራዎች ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በአመቱ ውስጥ ሁለት አንኳር ጉዳዮችን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ይፋ አድርገው ነበር፡፡ አንደኛው በ2013 የሚካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ማድረግ ነው፡፡
በዓመቱ ውስጥ እነዚህን ቁልፍና አንኳር ጉዳዮች ለማሳካት መንግስትና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለበርካታ የውስጥና የውጭ ጫና ሳይንበረከኩ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ አከናውነዋል፡፡ የውጭም የውስጥም ጠላቶቻችን በ2013ቱ ምርጫ ይባላሉ፣ ይተራረዳሉ፣ ይበታተናሉ ብለው አሰፍስፈው ሲጠብቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማከናወን የአገራችንን ክፉ የሚመኙ ኃይሎችን አሳፍሯል።
በበርካታ ዓለም አቀፍ ጫናዎችና በውስጥ ፈተናዎች ውስጥ የተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሕዝብ ተሳትፎም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በነበረው የመከባበርና አገርን የማስቀደም ስሜት እስካሁን ከነበሩት ምርጫዎች ሁሉ የተለየ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ ከምርጫው ብጥብጥንና ሁከትን ጠብቀው ለነበሩ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የእግር እሳት ሆኖባቸዋል፤ የሆነውን ማመን ተስኗቸዋል። ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ታሪክ መስራት እንደሚችሉና የተናገሩትንም ወደ ተግባር መቀየር እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ ሆኗል፡፡
ሌላውና ትልቁ ቀሪ የቤት ስራ ደግሞ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የህዳሴ ግድብ ልማት ብቻ ሳይሆን የሉአላዊነት መገለጫ የሆነ የባንዲራ ፕሮጀክት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ መቆም የምትችል፤ በራሷ ያሰበችውንና ያቀደችውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የምትፈጽም ሉአላዊ ሀገር መሆኗን የምታሳይበት ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሄርና ሃይማኖት ሳይለየው የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስር የአንድነት አርማ ነው፡፡
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ እንድትፈርስና እንድትበታተን የሚሹ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የህዳሴ ግድብን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን ጉድጓድ በመማስ ላይ የተጠመዱት፡፡ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የህዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ የኢትዮጵያ አንድነት እንደሚጠናከርና ኢትዮጵያም ወደ ከፍታው ማማ እንደምትወጣ ስለሚያውቁ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ግድቡ እንዲኮላሽ የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ በተለይም ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ እንደ ዕድል ለመጠቀም አስበው የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ አሳፍሮ መልሷቸዋል፡፡ እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች አሁንም ቢሆን ተኝተው ስለማያድሩ የተጀመረውን ሰላማዊ የምርጫ ሂደት እስከ መጨረሻው አስጠብቆ መጓዝ ያስፈልጋል። ከዚህ ባሻገር ጠላቶቻችን በምርጫ 2013 ይባላሉ ብለው አሰፍስፈው ሲጠብቁ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማካሄድ እንዳሳፈርናቸው ሁሉ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ በጋራ መቆም ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት መርህን አንግባ ህዳሴ ግድቡን በሉዓላዊ ግዛቷ ክልል ውስጥ እየገነባች ያለችው ግድብ ቢሆንም ለዘመናት የአባይን ውሃ ለብቻዋ ተቆጣጥራ የመኖር ፍላጎት ያላት ግብጽ ያለ ይሉኝታ ይህ ኢ ፍትሃዊ ፍላጎቷን ኢትዮጵያውያን ላይ ለመጫን ዛሬም ድረስ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ሆኖም ግን በሉዓላዊነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ‹‹ውሻዎቹ ይጮሃሉ፤ግመሎችም ይጓዛሉ›› እንደተባለው የሀገራቸውን አንድነት እየጠበቁ የህዳሴ ግድብን ወደ ፍጻሜው እያቃረቡት ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ አይደለም አንድ ግድብ 100 ግድቦችን መገደብ ትችላለች ብለው ለግብጻውያን መልስ በሰጡ ማግስት ኢትዮጵያ 100 ግድብ ከመገደቧ በፊት ኢትዮጵያውያንን አባልተን ወደ አስር ትንንሽ አገራት እንቀይራታለን በሚል እየዛቱ ይገኛሉ።
በመሆኑም የህዳሴ ግድባችን የዚህ ትውልድ ዳግማዊ አድዋ አሻራችን መሆኑን ተረድቶ ለግድቡ የሚደረጉ ድጋፎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል ባሻገር ህብረተሰቡ ለሰላሙ ዘብ በመቆም የህዳሴ ግድቡን እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቅ ይገባል። ሁሉም በምርጫው አገሩን እንዳስቀደመው ሁሉ የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ለሰላሙ ዘብ መቆም አለበት። የውጭ ኃይሎች መንግስት በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የያዘውን አቋም በእጅ አዙር እጁን ጠምዝዞ ለማስቀየር በውስጥ ጉዳያችን ላይ የሚያደርጉትን የውጭ ጣልቃ ገብነት በጋራ ማውገዝ ይገባል። በጥቅሉ ለዘላለም ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ለማሳፈር በምርጫው እንደታየው ሁሉ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ መያያዝ አለባቸው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2013