በውጊያ ችሎታቸው፣ በተለይም በመድፍ አተኳኮስ ጥበባቸው፣ እጅግ ተደናቂ ጀግና ነበሩ፡፡ለዚህ ምስክሩ ደግሞ የአድዋ ተራሮችና ወርቃማው የአድዋ ድል ናቸው፡፡እስከ ‹‹… ተተካ ባልቻ …›› ድረስ የተገጠመላቸውም በዚሁ በደፉት የጀግንነት አክሊል
ነው፡፡ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በድፍረት በወረረበት ወቅት የ75 ዓመት አዛውንት ሆነው ሳለ ‹‹አገሬ በጠላት ስትደፈር ዐላይም!›› በማለት ዳግም ለአርበኝነት መሰማራታቸውና የጠላት ራስ ምታት መሆናቸው ደግሞ እጅግ ያስገርማል፤ ያስደንቃልም፡፡እኝህ ጀግና ከጦር መሪነታቸው ባሻገር በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ በአስተዳዳሪነት በመስራት በአገሪቱ ህግና ስርዓትን ያሰፈኑ ታላቅ የአገርና ህዝብ ባለውለታ ናቸው … በ1854 ዓ.ም የተወለደው፤ የመድፉ ጌታ፣ ጀግናው ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ)!!
ንጉሥ ምኒልክ ኃይለመለኮት (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) የሸዋ ንጉሥ ከሆኑ በኋላ የመጀመሪያ ካደረጓቸው ዋና ዋና እቅዶቻቸው መካከል በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ወደ መቅደላ ተወስደው በነበረበት ወቅት በቀሰሙት የአስተዳደር ልምድ መሰረት በአያታቸው በንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ (ንጉሰ ሸዋ) ተጀምሮ የነበረውን የሸዋን ግዛት የማስፋፋት ሂደትን ማጠናከር አንዱ ነበር፡፡ለዓላማቸው መሳካት ይረዳቸው ዘንድም ከሸዋ ግዛቶች በጦርነት የላቀ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ የጦር አበጋዞችን በመመልመል ወደ ተለያዩ የሸዋ ግዛቶች ላኩ፡፡ከተላከው የንጉሥ ምኒልክ ጦር መካከል አንዱ ባልቻ የተባለ ታዳጊ የሚገኝበትን ጦር ማረከ፤ ባልቻም ተማረከ፡፡
ከዚህ በኋላ ባልቻ ለምኒልክ ቤተ መንግሥት ቅርብ ሆኖ አደገ፡፡ምኒልክም በግምጃ ቤታቸው እንዲሰለጥን አደረጉት። ባልቻም የመድፍ አተኳኮስን ጨምሮ ሌሎች የውጊያ ትምህርቶችን ተምሮ ተደናቂ ጦረኛ ለመሆን በቃ፤ በማኅበረሰቡ ዘንድም እንዲታወቅ አስቻለው።
በ1888 ዓ.ም፣ የኢጣሊያ ጦር የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ መጣ፡፡ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ኢትዮጵያውያን በኅብረት ሆነው አገራቸውን ከጠላት እንዲከላከሉና ለክብራቸው እንዲፋለሙ ባስነገሩት የክተት አዋጅ መሰረት ሁሉም ወደ ዓድዋ ለመዝመት ሲነሳ በጅሮንድ ባልቻም ለአገራቸው ክብርና ነፃነት ለመፋለም ወደ ዓድዋ ዘመቱ፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጦርነቱ ተጀመረ … ለአገርና ለራስ ክብር መዋደቁም ቀጠለ፡፡ታዲያ በዚህ መሐል ከወቅቱ ስመጥር የጦሩ መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት፤ በተለይም ከዓድዋ ጦርነት ሦስት ወራት ያህል ቀደም ብሎ (ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም) በተከናወነው የአምባላጌ ጦርነት ላይ የማይረሳ ገድል የፈፀሙት ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራ) ከጠላት ወገን በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ሞቱ፡፡የአባ ጎራን መሞት ያዩትና ሞታቸውም ያንገበገባቸው በጅሮንድ ባልቻ፣ ከወጣትነታቸው ጀምሮ የሰለጠኑበትን የመድፍ መተኮስ ስልጠና በተግባር ለማሳየት ከዚያች ቀን የተሻለ ጊዜ እንደሌለ አረጋገጡ፤ ወደ ተግባርም ገቡ፡፡መድፋቸውን እያመቻቹ በኢጣሊያ ጦር ላይ ያዘንቡት ጀመር፡፡ብዙ የጠላት ጦር ወታደሮችም በበጅሮንድ ባልቻ የመድፍ ተኩስ ዒላማ ውስጥ እየገቡ አለቁ፡፡በጅሮንድ ባልቻም ቀኑን ሙሉ እልህ አስጨራሽ የሆነ ውጊያ ተዋጉ፡፡የማታ ማታም ድሉ የኢትዮጵያ ሆነ፡፡በፊታውራሪ ገበየሁ ሞት ምክንያት ንጉሰ ነገሥቱና መኳንንቱ ሁሉ እጅግ አዝነው ስለነበር ‹‹ገበየሁ ቢሞትም ባልቻ አለልዎ›› ለማለትና በጅሮንድ ባልቻም በጦርነቱ ላይ ባሳዩት የጀግንነት ውጊያ ምክንያት እንዲህ ተብሎ ተገጠመላቸው፡፡
‹‹ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፣
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፡፡››
ጀግናው በጅሮንድ ባልቻ የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡ጣሊያናዊው የታሪክ ፀሐፊ ኮንቴ ሮዚኒ ስለፊታውራሪ ገበየሁ አሟሟትና ስለተተኪዎቹ ስለነበር በጅሮንድ ባልቻ ተጋድሎ እንዲህ ሲል ጽፏል፡፡
‹‹ … በውጊያው መሐል ቀይ ልብስ የለበሰው ፊታውራሪ ገበየሁ ፊቱን ወደ ሰዎቹ አዙሮ ‹ … የአምባላጌው አሸናፊ ፊታውራሪ ገበየሁ በምን አኳኋን እንደሞተ ወደ ሸዋ በሕይወት የሚመለሱት ይናገሩ …› ብሎ ተናግሮ እንደ አንበሳ ተወርውሮ ወደ ጣሊያኖቹ መስመር ገብቶ ሲዋጋ ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ላይ በመድፍ ተመትቶ ከኪዳነ ምኅረት በር ላይ ወደቀ፡፡የእርሱም ሞት ሰዎቹን አስደንግጦ ግማሾቹ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ቢያደርጋቸውም ግማሾቹ ግን ተኩሳቸውን ቀጠሉ …
አልቤርቶኒ ድሉ እንደተቃረበ ተስፋ አደረገ … ነገር ግን በዚህ ጊዜ ወደ ጦርነቱ ግንባር የመጡት ንጉሰ ነገሥቱ አፄ ምኒልክ ያደፋፈሯቸው ወታደሮች ወደፊት እየገፉ መጥተው ውጊያው ተጠናክሮ ሲቀጥል ጦርነቱ ከበፊቱ የበለጠ ሆነ፡፡ከሰባተኛና ከስምንተኛ ባታሊዮን ተዋጊዎች ጋር ትልቅ እልቂት ሆነ … ከሦስት ሰዓት ተኩል በኋላ ሁኔታው እየከፋ ሄደ፡፡ከአባ ገሪማ የወረዱት ወደ ጦርነቱ እየቀረቡ ባደረጉት ውጊያ ከጣሊያኖቹ ወገን በመድፍና በጠመንጃ በብርታት ቢከላከሉም የሀበሾቹ ኃይል እየጠነከረ ሄደ … ጀኔራል አልቤርቶኒም በሀበሾቹ ተማረከ …››
ታዲያ በዚህ የወገን ጦር ድል አድራጊነትም ሆነ የመሐለኛው የኢጣሊያ ጦር አዝማች የጀኔራል ማቴዎስ አልቤርቶኒ መማረክ ሂደት የመድፉ ጥበበኛ የበጅሮንድ ባልቻ ሳፎና አጋሮቻቸው ሚና እጅግ የላቀና በዋጋ የማይተመን እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም፡፡
የደጃዝማች ባልቻ የጀግንነት ታሪክ በተለይ ከዓድዋ ድል በኋላ እየገነነ ሄዶ የመድፈኛ ክፍል ኃላፊ ከመሆን ጀምሮ፤ በኋላም ንጉሰ ነገሥቱ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲያቋቁሙ የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ሆነው የኢትዮጵያን የጦር መሳሪያ በዓይነት በዓይነት ማስቀመጥ እንደጀመሩ ታሪካቸው ያስረዳል።
በ1889 ዓ.ም ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ የሲዳሞ ግዛት ገዢ ሆነው ተሾሙ፡፡በ1900 ዓ.ም ደግሞ የራስ መኮንን ልጅ ደጃዝማች ይልማ መኮንን በመሞታቸው ምክንያት ደጃዝማች ባልቻ የሐረርጌንና የባሌን ግዛቶች አንድ ላይ ለማስተዳደር ወደ ሐረር ተዛወሩ፡፡[በነገራችን ላይ ደጃዝማች ባልቻ ወደ ዓድዋ ሲዘምቱም ሆነ የሲዳሞና የሐረርጌ ገዢ ሆነው ወደ’ነዚህ ቦታዎች ሲዘዋወሩ በዓድዋ ጦርነትና በ(ሁለተኛው) ፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜያት ከጠላት ጦር ጋር የተፋለሙት ፊታውራሪ ገብረማርያም (በኋላ ደጃዝማች) /አባ ንጠቅ ገብሬ/ ከደጃዝማች ባልቻ ጋር አብረው ተጉዘው ነበር፡፡ደጃዝማች ባልቻ የሲዳሞ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው በቆዩባቸው ዓመታት ፊታውራሪ ገብረማርያም ልዩ ረዳትና የአውራጃ ገዢ በመሆን (እስከ 1900 ዓ.ም ድረስ) አገልግለዋል፡፡እስከ 1902 ዓ.ም ድረስ ደግሞ ፊታውራሪ ገብረማርያም በሐረርጌ የደጃዝመች ባልቻ ረዳት ሆነው ሰርተዋል፡፡ወጣቱን ገብረማርያምን የቤተ-መንግሥትን ስርዓት በማስተማር ታማኝ ወታደር ብቻም ሳይሆን ብቁ አስተዳዳሪም እንዲሆን ያደረጉት ደጃዝማች ባልቻ ናቸው]
በ1902 ዓ.ም ደጃዝማች ባልቻ በድጋሜ ፊታውራሪ ገብረማርያምን ይዘው ተመልሰው ወደ ሲዳሞ ተጓዙ፡፡ልጅ ኢያሱ ደግሞ በ1907 ዓ.ም የሲዳሞን ግዛት ከደጃዝማች ባልቻ ነጥቀው ለእህታቸው ባል ለቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ሰጧቸው፡፡በዚህ ሹም ሽር ሳቢያ አገር ለማቅናት ሲደክሙ የነበሩት የዓድዋ ጀግኖች ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ እና ባለሟላቸው ፊታውራሪ ገብረማርያም ጋሪ ከመንግሥታዊ ስራ ውጭ በመሆናቸው ወደትውልድ ስፍራቸው ሄደው በርስታቸው ላይ እያሳረሱ መኖር ጀመሩ፡፡
በመስከረም 1909 ዓ.ም የተደረገው ሹምሽር (የልጅ ኢያሱ ከዙፋን መነሳትና የዘወዲቱ መሾም) ደጃዝማች ባልቻና ፊታውራሪ ገብረማርያም ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ስራ እንዲመለሱ አጋጣሚን ፈጠረ፡፡በሹም ሽሩ የተናደዱት የልጅ ኢያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል አሊ ከማዕከላዊው መንግሥት ጦር ጋር ሲዋጉ ደጃዝማች ባልቻ አዲስ አበበ ከተማን አንዲጠብቁ ኃላፊነት ተሰጣቸው፤ ፊታውራሪ ገብረማርያም ደግሞ ከማዕከላዊው መንግሥት ጦር ጋር ዘመቱ፡፡ፊታውራሪ በሰገሌው ጦርነት ላይ ቢቆስሉም ድሉ የማዕከላዊው መንግሥት ጦር ሆነ፡፡
ውሎ አድሮ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክና በአልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) መካከል የተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ደጃዝማች ባልቻን አላስደታቸውም ነበር፡፡ዝነኛውና ኃይለኛው የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ዲነግዴ (አባ መላ) በ1919 ዓ.ም ካረፉ በኋላ አልጋወራሹ መሰናክል ይሆኑብኛል ብለው ካሰቧቸው አንጋፋ መኳንንት መካከል አንዱ ደጃዝማች ባልቻ (ከደጃዝማች አባውቃውና ከንግሥቲቱ የቀድሞ ባለቤት ከራስ ጉግሳ ወሌ በተጨማሪ) ነበሩ፡፡
‹‹አባ ነፍሶ›› በሚባለው የፈረስ ስማቸው የሚታወቁት ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመግባባት፣ ከንግሥቲቱ ጎን ቆመው ታማኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡በወቅቱም የደጃዝማች ባልቻና የአልጋ ወራሹ ልዩነትም በግልፅ ታየ፤ አልጋ ወራሹም የደጃዝማቹን ታማኞች ማስከዳትጀመሩ፡፡ደጃዝማች ባልቻን ከሁሉም አስበልጦ የጎዳቸው የባለሟላቸው የፊታውራሪ ገብረማርያም ወደ አልጋ ወራሹ ማዘንበላቸው ነበር፡፡
ሐረርጌ የአልጋወራሽ ተፈሪ አባት (ራስ መኮንን) ግዛት ስለነበር በ1900 ዓ.ም የራስ መኮንን ልጅ ደጃዝማች ይልማ መኮንን (የአልጋወራሽ ተፈሪ ወንድም) ሲሞቱ ደጃዝማች ባልቻ ሐረርጌን እንዲያስተዳድሩ መሾማቸውና ወደ ሐረር መሄዳቸው አልጋወራሽ ተፈሪ ዘንድ ቅሬታን ሳይፈጥር እንዳልቀረ በአንዳንድ የታሪክ መዛግብት ላይ ተጽፏል፡፡በሌላ በኩል ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን አልጋወራሽ ተደርገው ከተሾሙ በኋላ ስልጣናቸውን ለማጠናከርና ለመጠቅለል በወሰዷቸው ፈጣንና በሴራ የታጀቡ እርምጃዎች ምክንያት የንግሥቲቱ ታማኝ ደጋፊ የነበሩትን ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ተቀይመው ነበር፡፡
ልጅ ኢያሱ የሐረርጌን ገዢነት ለደጃዝማች ባልቻ የሰጡት ሁለቱን (ደጃዝማች ባልቻንና ደጃዝማች ተፈሪን) በማጋጨት የራሳቸውን ስልጣን ለማደላደል ነው ተብሎ የሚነገር ታሪክም መኖሩንም ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ያም ሆነ ይህ አልጋወራሹ የንግሥቲቱን ስልጣን እየገዘገዙ ሁሉንም ስልጣን ለራሳቸው መጠቅለላቸው ክፉኛ አበሳጭቷቸዋል፡፡ደጃዝማች ባልቻ የአልጋወራሹ ስልጣን ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከረ መሄዱን ዕያዩ እንኳ ታማኝነታቸውን ለንግስቲቱ እንጂ አንድም ቀን ለአልጋ ወራሹ ማሳየትን አልመረጡም፡፡
ደጃዝማች ባልቻ የሲዳሞ ገዥ በነበሩበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተነገራቸውና ጦራቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ገሰገሱ፡፡ደጃዝማች ባልቻ ጦራቸውን በከተማው አካባቢ ከሚገኘው ፉሪ ተራራ ላይ አስፍረው ከጥቂት አጃቢዎቻቸው ጋር በመሆን እጅ ለመንሳት ወደ ቤተ መንግሥት በሄዱበት ቅፅበት አልጋወራሹ በምስጢር ደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤልን (በኋላ ራስ ብሩ) የሲዳሞ ገዢ አድርገው በደጃዝማች ባልቻ ላይ ሾሙባቸው፡፡ፉሪ ተራራ ላይ የሰፈረው የደጃዝማች ባልቻ ጦርም አዲሱን ገዢ ደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤልን ተከትሎ ወደ ሲዳሞ ሄደ፡፡ደጃዝማች ባልቻም ብቻቸውን ቀሩ፡፡ላመኑበት ነገር የማይበገሩት ቆራጡ ደጃዝማች ባልቻ ብቻቸውን እንደቀሩ እያወቁ እንኳ ለአልጋወራሹ ፍላጎት ታዛዥ ሊሆኑ አልቻሉም ነበር፡፡
ይህም ሆኖ ግን ደጃዝማች ባልቻ በወቅቱ በነበሩት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንደተከበሩ በትውልድ አካባቢያቸው መኖር ጀመሩ። ከነሙሉ ክብራቸው በአካባቢው ህዝብ እንደተወደዱ ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም ጋር ወደ ሌላ ፀብ ሳይገቡ ከነልዩነታቸው መኖር ጀመሩ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም አገር እያስተዳደሩ፤ ደጃዝማች ባልቻም የተጣላ እያስታረቁ እስከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ድረስ ዘለቁ።
በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደገና ወረረች፡፡ የዓድዋው ጀግና፣ የመድፉ ጌታ፣ በአገራቸው ነፃነት የማይደራደሩት፣ ላመኑበት ነገር የማይበገሩት … ጀግናው ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ በወቅቱ የ74 ዓመት አዛውንት ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ባልቻ የአገራቸው ነገር አይሆንላቸውምና ጠላትን ለመፋለም ታጥቀው ተነሱ፡፡ የአካባቢው ሰው ሁሉ በድርጊታቸው በጣምተገረመ፡፡ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸውም ‹‹ … እንግዲህ እርስዎ አርጅተዋልና መዋጋት አይችሉም፤ ለኢጣሊያ ይደግፉ … በእርጅና ዘመንዎ አይንገላቱ …›› አሏቸው፡፡እርሳቸው ግን ‹‹አዎ ሸምግያለሁ፤ መሞቴም አይቀርም፤ በሰማይ ቤት ጌታዬ ምኒልክ ‹በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ ማነው የተቀመጠው?› ብለው ቢጠይቁኝ ምን ብዬ እመልሳለሁ? …›› ብለው በሃሳባቸው ፀንተው ጦር በማሰባሰብ ከጠላት ጋር መዋጋታቸውን ቀጠሉ።
ኢትዮጵያውያን አርበኞች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አዲስ አበባ በመዝለቅ የፋሺስትን አስተዳደር ለመውጋት በተነደፈው እቅድ መሰረት ደጃዝማች ባልቻ ጦራቸውን ይዘው ከትውልድ አካባቢያቸው ከአገምጃ (ወሊሶ) ተነስተው አዲስ አበባ ደረሱ፡፡ይሁን እንጂ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአርበኞች ሰራዊት ላይ በአውሮፕላን የታገዘ ጥቃት ከፍቶ የታሰበው ሁሉ ሳይሳካ ቀረ፡፡ደጃዝማች ባልቻም ብዙ ተዋጊ አለቀባቸው፡፡በመጨረሻ ጥቂት ወታደሮቻቸውን ይዘው ወደ ኋላ አፈገፈጉ።
የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ታሪክ በጣልያኖች ዘንድ ሲወራ ብዙዎችን አስገረመ። የኢጣሊያ ጋዜጦች ‹‹ … በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከምኒልክ ጋር ሆኖ ከተዋጉት ሰዎች መካከል ባልቻ አባ ነፍሶ የሚባል ሽማግሌ ሰው አሁን በሕይወት አለ። በደቡብ በኩል ጦር እያደራጀ ነው … ›› ብለው ሲዘግቡ የኢጣሊያ መንግስት ‹‹…ይህን ሰው እንፋረደዋለን። ከነህይወቱ ይዛችሁ እንድታመጡት … ›› የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈ። የፋሺስት ጦርም ደጃዝማች ባልቻን ለመማረክ እርሳቸውን ተከታትሎ ወደ አገምጃ ዘለቀ፡፡
በወቅቱ ከፋሺስት ጦር ጋር ሲፋለሙ የነበሩት ሻለቃ መስፍን ስለሺ (በኋላ ራስ) ለንደን ለነበሩት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በጻፉት ደብዳቤ ስለደጃዝማች ባልቻ አሟሟት እንዲህ በማለት ገልፀውላቸዋል፡፡
‹‹ … የጠላት ጦር ክቡር ደጃዝማች ባልቻ እስከነበሩበት አገምጃ ድረስ በመዝለቅ ዘመተባቸው፡፡ሕዝቡም ከዳቸው፤ ወታደሮቻቸውም ለህይወታቸው ሲሉ ሸሹ። እርሳቸው ደጃዝማች ባልቻ እና ሁለት አሽከሮቻቸው (ከእርሳቸው ጋር ሶስት ሰዎች) ብቻ ቀሩ። ያ ሁሉ የኢጣሊያ ጦር ከበባቸው። በመጨረሻም አንድ ፈረንጅ ወደ ደጃዝማች ባልቻ ዘንድ መጥቶ። ‹ደጃዝማች ባልቻ ማለት አንተ ነህ?› አላቸው። ደጃዝማቹም ‹አዎ እኔ ነኝ!› ሲሉ፤ ፈረንጁ ‹በሉ ይማረኩ፤ ሽጉጥዎንም ያስረክቡኝ› አላቸው። ደጃዝማች ባልቻም ‹እኔ እጅ የምሰጥ ሰው አይደለሁም! ትጥቄንም አልሰጥህም!› ብለው ሽጉጣቸውን አውጥተው ነጩን የኢጣሊያ ጦር መኮንን ገደሉት። ከዚያም በራሳቸው ሽጉጥ የራሳቸውን ሕይወት አጠፉ። ከደጃዝማች ባልቻ ጋር አብረው የነበሩትም ወታደሮች ስቃይ ሳይበዛባቸው በየተራ ወደቁ፡፡››
የወራሪን ወታደር በመድፍ ጥቅት በሙቁላትና በ75 ዓመታቸው ከጠላት ጋር በመፋለም በአገራቸው ነፃነትና ክብር እንማይደራደሩ በተግባር ያስመሰከሩት ጀግናው ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ጥቅምት 27 ቀን 1929 ዓ.ም
አረፉ፡፡ለኢትዮጵያ ነፃነትና እድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦም ትምህርት ቤትና ሆስፒታል በስማቸው ተሰይመውላቸዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013