የቶንሲል ህመም (ቶንሲል) በቶንሲል እብጠት መቆጥቆጥ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን በሽታው በባክቴሪያና በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት ተላላፊ የጤና ችግር ነው። በጉሮሮአችን ውስጥ የሚገኙት የቶንሲል እጢዎች በጀርሞች ተጠቅተው ሲቆጡና ሲያብጡ የሚከሰተው ህመም ቶልሲላይተስ ተብሎ ይጠራል። እነዚህ እጢዎቻችን እንዲቆጡና እንዲያብጡ በማድረግ ህመም እንዲሰማን የሚያደርጉት ባክቴሪያና ቫይረሶች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ በማህበረሰቡ ዘንድ የቀዘቀዘ ምግብን ወይም መጠጥን አብዝቶ መጠቀም፤ አሊያም በሃይለኛ የፀሐይ ሙቀት በመመታት ይከሰታል ተብሎ የሚታሰበው የቶንሲል ህመም መነሻ ምክንያቱ ከእዚህ በእጅጉ የተለየና ተገቢውን ህክምና በወቅቱ ካላገኘም እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ የጤና ችግር ነው።
ቶንሲል በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እጅግ የተለመደና በየጊዜው የሚያጋጥም የህመም አይነት ነው። አንድ ሰው በየዓመቱ በአማካይ እስከ አራት ጊዜ ያህል በቶንሲል ህመም ሊጠቃ ወይንም ቶንሲላይትስ ሊይዘው ይችላል። የቶንሲል ህመም በቫይረስና በባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰት ህመም ሲሆን ቫይረስ አመጣሹ ቶንሲላይት በአብዛኛው በቀላል የቤት ውስጥ ህክምናዎች ማለትም ጨው በተቀላቀለበት ሞቅ ያለ ውሃና በሎሚ ጭማቂ ደጋግሞ የጉሮሮ ውስጠኛውን ክፍል በማፅዳት፣ በዝንጅብል የተፈላ ሻይና ትኩስ ነገሮችን ደጋግሞ በመጠጣት ሊድን የሚችልና ምንም ዓይነት መዘዝን የማያስከትል ህመም ሲሆን በባክቴሪያዎች በተለይም ደግሞ ስትሬፕቶኮክስ ፓዮጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ የሚመጣው የቶንሲላት አይነት ግን ለከፍተኛ ህመምና ሥቃይ የሚዳርግ ከመሆኑን በላይ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ነው። በሽታው ለኩላሊት መድከም (APSGN)፣ ለልብ ህመም(RF) ብሎም ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
የቶንሲላይተስ ምልክቶች፦
የቆሰለ ጉሮሮ – በመዋጥ ወቅት ህመም፣ የቀላ እና ያበጠ ቶንሲል፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ ራስ ምታት፣
ለመዋጥ መቸገር፣ ጆሮ እና አንገት ላይ የሚፈጠር ህመም፣ የድካም ስሜት፣ እንቅልፍ መቸገር፣ ሳል፣ የብርድ ስሜት፣ እንዲሁም አገጭ ስር የሚገኙ ሊምፍ ኖዶች ላይ የሚፈጠር ማበጥ ናቸው።
የሚከተሉት ምልክቶች ለቶንሲል ህመም የተለመዱ ባይሆኑም አንዳንድ ሰዎች ላይ ሊፈጠሩ ይችላሉ።
ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ የሆድ ህመም እና ማስመለስ፣ ማቅለሽለሽ፣ የድምጽ መለዋወጥ፣ መጥፎ የአፍ ጠረን፣ እና አፍን ለመክፈት መቸገር።
አንዳንድ ጊዜ ቶንሲሎሊቲስ ወይም የቶንሲል ጠጠር ሊፈጠር ይችላል። የቶንሲል ጠጠር በቶንሲል ጉድጓዶች ውስጥ የሚከማቹ ንጥረ ነገሮች በሚፈጥሩት ክምችት የሚፈጠር ነገር ነው። የቶንሲል ጠጠሮች ብዙ ግዜ ትናንሽ ናቸው። አንዳንድ ግዜ ግን እስከ 3 ሴንቲሜትር ወይም ከዛም በላይ የሚደርሱበት ሁኔታ አለ። የቶንሲል ጠጠር የህመም ስሜት የሚፈጥር እና ለማስወገድ የሚከብድ ቢሆንም ጤናን አደጋ ላይ አይጥልም።
መቼ ነው ሀኪም ጋር መታየት ያለብን?
በጣም ያልተለመደ ቢሆንም ቶንሲላይተስ የሚፈጥረውን እብጠት ጨምሮ መተንፈስ የምንቸገርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ሃኪም ቤት በአስቸኳይ መሄድ ይኖርብናል። ከዛም አልፎ ከሚከተሉት ምልክቶች አንዱ እንኳ ከታየ ሀኪም ማማከር ያስፈልጋል። ምልክቶቹም – ከ103 ዲግሪ ፋራናይት በላይ ማተኮስ፣ የአንገት መጨራመት፣ የጡንቻ መዳከም እና ከሁለት ቀን በላይ የሚቆይ የጉሮሮ መቁሰል ናቸው።
ህክምና
ቶንሲላይተስን ቤት ውስጥ ማስታመም ካልተቻለ የሚከተሉትን የህክምና አማራጮችን መከተል ያቻላል።
1. መድሃኒቶች፦ እንደ አሴታሚኖፌን አይነት የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በመጠቀም የህመም ስሜቱን መቀነስ ይችላል። የቶንሲላይተስ መንስኤ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ከሆነ ሀኪም አንቲባዮቲክስ ያዛል። መንስኤው የቫይረስ ኢንፌክሽን ከሆነ ግን አንቲባዮቲክስ
አይታዘዝም። የታዘዘውን መድሃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ያስፈልጋል። በፍጹም ተሻለኝ ብለን ማቆም የለብንም። መድሃኒቱን ማቋረጥ ኢንፊክሽኑ እንዲዛመት እድል በመስጠት ለሪውማቲክ ትኩሳት እና የኩላሊት በሽታ ሊዳርገን ይችላል።
2. ቀዶ ጥገና፦ ቶንሲልን በቀዶ ጥገና ማስወገድ ቶንሲላይተስን ለማከም አዘውትሮ የሚውል ህክምና ነበር። በአሁኑ ግዜ ግን በሽታው የሚደጋገምባቸው ሰዎች ላይ (በአንድ አመት ውስጥ 7 ግዜ ያህል የሚደጋገምባቸው ሰዎች ወይም ለ3 አመት በየአመቱ ሶስት ግዜ ለሚታመሙ ሰዎች የሚታዘዝ መፍትሄ ነው።) ብቻ የሚውል ህክምና ነው። በቶንሲል ህመም ምክንያት የሚከተሉትን የጤና ችግሮች ካስተናገድን ቀዶ ህክምና ሊያስፈልገን ሲሆን እነሱም፤ በእንቅልፍ ወቅት መተንፈስ መቸገር፣ መተንፈስ ወይም መዋጥ መቸገር፣ ለማከም የሚከብድ እብጠት መፈጠር፣ የቶንሲል ኢንፌክሽን ወደ ሌላ የሰውነት አካሎች መዛመትና የፈሳሽ ክምችት መፈጠር ናቸው።
የቶንሲል መቆረጥ በተለያዩ መሳሪያዎች ሊፈጸም የሚችል ቀዶ ጥገና ነው። በሌዘር፣ የሬዲዮ ጨረር፣ አልትራሶኒክ ሃይል፣ በቅዝቃዜ ወይም በኤሌክትሪክ የጋለ መርፌን በመጠቀም ቶንሲልን ማስወገድ ይቻላል። ቀዶ
ጥገና የመጨረሻ ህክምና አማራጭ ነው። የቀዶ ጥገናው መጥፎ ገጽታዎቹ ከጥሩ ገጽታዎቹ በላይ ሊከብዱ ይችላሉ። ለብዙ ሰዎች ግን ቶንሲላይተስ በራሱ ግዜ የሚጠፋ መድሃኒት እንደመሆኑ ቀዶ ጥገና አያስፈልገውም።
የቤት ውስጥ መፍትሄዎች
የሚከተሉትን የቤት ውስጥ መፍትሄዎች በመጠቀም የቶንሲላይተስን ህመም ማስታገስ እንችላለን።
• በቂ እረፍት መውሰድ ሰውነታችን ኢንፌክሽኑን በተሻለ አቅም እንዲዋጋ ይረዳል፤
• በቂ ፈሳሽ መውሰድ ጉሮሮ እንዳይደርቅ እና የህመም ስሜት እንዳይጨምር ይረዳል። ሰውነት ኢንፌክሽንን በሚዋጋበት ጊዜ ከወትሮው በላይ ፈሳሽ ያስፈልገዋል። የቡና ይዘት የሌላቸው ሙቀት የሚሰጡ መጠጦችም ይረዳሉ፤
• በጨው ውሃ ጉሮሮን ማጽዳት፤
• ሞቃት አየር ወይም ስቲም ያለበት ቦታ ውስጥ መቀመጥ፤
• ሲጃራ እና ጭስ ያለበት ቦታ አለመሄድ፤ እንዲሁም፣
• የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች መውሰድ በመፍትሄነት ያገለግላሉ።
ምንጭ ፦ከጤናችን ማህበራዊ ገጽ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013