ባለፉት ሶስት አመታት ትልቅ ስኬት ከተመዘገበባቸው በርካታ ስራዎች መካከል የመንገድ ዘርፉ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በዘርፉ ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ የፕሮጀክቶች መጓተቶችን በማስቀረት፣ ተጀምረው የቆሙ መንገዶችን በማጠናቀቅ፣ በርከታ አዳዲስ ዋና ማሳለጫ መንገዶችን እንዲሁም የእግረኛ መንገዶችን አቅዶ በመገንባት የመንገድ መሰረተ ልማቱን ከማሳደግ ባለፈ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ሆኗል።
ከዚህ ቀደም ያልነበሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን፣ የኮንደሚንየሞች መግቢያዎችን በአስፋልት ደረጃ በመገንባት፤ ለእግር ጉዞ ምቹ ያልነበሩ የዋና መንገዶችና መጋቢ መንገዶች የእግረኛ መተላለፊያዎችን ከዛም አልፎ የብስክሌት ማሽከርከሪያ መንገዶችን በመገንባት ተሽከርካሪዎች ያለምንም ችግር በፍጥነትና እንዲጓዙ የትራፊክ ፍሰቱን እንዲሻሻል ማድረግ ተችሏል፡፡
ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም አንድ መንገድ ሲጀመር ማነው የያዘው ሲባል የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሰልጣን ሲባል፣ አይ መቼም አያልቅማ ብሎ ተስፋ ይቆርጥ የነበረበትን ሁኔታ በመቀየር ተቋማዊ አደረጃጀቱንና ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የማጠናቀቅ አቅሙን አሳድጎ ዛሬ ላይ በራስ አቅም ሰርቶ የማጠናቀቅ ብቃትን እያሳየ ህዝቡም አመኔታውን እየቸረው ይገኛል፡፡
እኛም በከተማ ደረጃ ያለውን የመንገድ ዘርፍ እንቅሳቃሴ አስመልክተን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡን አነጋግረናቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት ሶስት አመታት በከተማ ደረጃ በመንገድ ዘርፉ ላይ ምን ዓይነት ስራዎች ተሰርተው ፤ ምን ዓይነት ለውጥ መጣ?
ኢንጂነር ሞገስ፦ ባለፉት ሶስት አመታት እንደ ከተማ በመንገድ መሰረተ ልማት ለውጥ ለማምጣት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። በተለይም ቀደም ብሎ ተጀምረው ያለተጠናቀቁትን የመንገድ ፕሮጀክቶች የማጠናቀቅ ፣አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የመያዝና ወደ ስራ የመግባት ተግባራት ተከናውነዋል።
ከዚህ አንጻር ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫችን የነበረው የብዙኃን ትራንስፖርትን ማስፋፋት ነበር ። ለዚህ የሚሆን ምቹ የእግረኛ መንገዶችና ብስክሌት መጓዣዎች እንዲኖሩን የተሰራባቸው አመታት ናቸው።
በነዚህ አመታት ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛ መንገዶችን መልሶ የመገንባትና ለጉዞ ምቹ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል። ይህ ደግሞ የከተማዋን ገጽታ ከፍ ከማድረጉም በላይ ህብረተሰቡ በተመቻቸ ሁኔታ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ ብሎም አካል ጉዳተኞች ያለምንም ችግር ወጥተው እንዲገቡ በማድረግ በኩል ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት ነው።
እግረኞች ወደዋና መንገድ በመግባት የትራፊክ ፍሰቱን ከማወክ እንዲቆጠቡ አድርጓል። እግረኞች ምቹ የሆነ የእግረኛ መጓጓዣ መንገድ ሲኖራቸው ወደመኪና መንገድ እንዲገቡ ስለማይገደዱ በመኪና አደጋ ምክንያት የሚጠፋ የሰው ህይወት፣ የሚጎል አካልና የሚወድም ንብረትን በከፍተኛ ሁኔታ ማዳን የተቻለባቸውም ስራዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት ሶስት አመታት ምን ያህል ፕሮጀክቶች ስራቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት በቁ ?
ኢንጂነር ሞገስ፦ ባለፉት ሶስት አመታት በተለይም ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ነው ስራዎች ሲከናወኑ የነበረው ምንም ዓይነት ስራ ተጀምሮ እንዳይጓት ኪሳራ እንዳያመጣ ህብረተሰቡን እንዳያማርር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ስራዎችን ሲያከናውን ነበር ። በዚህም ከ57 በላይ የሚሆኑ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀን ለትራፊክ ከፍት ማድረግ ችለናል።
በጠቅላላው እነዚህ 57 ፕሮጀክቶች የ 110 ኪሎ ሜትር ርዝመትና እስከ 40 ሜትር የሚደርስ የመንገድ ስፋት ያላቸው ናቸው። የእነዚህ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ደግሞ የከተማዋን ገጽታ በመቀየር የጉዞ ጊዜን በማሳጠር እንዲሁም ለወጣቶች የስራ እድልን በመፍጠር በኩል ሚናቸው ላቅ ያለም ነበር።
መንገድ ለከተማ የደም ስር እንደመሆኑ ህብረተሰቡም የትኛውንም ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቶችን ሊያገኝና ተደራሽ ሊሆንለት የሚችለው መንገድ ሲኖር ብቻ ነው ። ከዚህ አንጻር የእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቃቸው የማይተካ ሚና ነበራቸው። በተመሳሳይ መንገዶቹ ኢኮኖሚው ላይ የሚኖራቸው ቀጥተኛ አስተዋጽኦና አበርክቷቸውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
አዲስ ዘመን ፦ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራችሁ ነው ፣ ወጪያቸውስ ምን ያህል ነው?
ኢጂነር ሞገስ፦ በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ይዘን እየሰራን ነው። ወጪያቸውም ከ 28 ቢሊየን ብር በላይ ይሆናል ። ፕሮጀክቶቹ እነዚህም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን ሁሉም በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ የሚገነቡ ናቸው። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እነዚህን ፕሮጀክቶች መጀመር ብቻ ሳይሆን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲያውም ባጠረ ጊዜ ማጠናቀቅ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ እየሰራም ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት እቅድን በአግባቡና በተያዘለት ጊዜ ከመፈጸም አንጻር የመጡ ለውጦች እንዴት ይገለጻሉ?
ኢንጂነር ሞገስ፦ ባለፉት ሶስት አመታት በመንገድ ዘርፍ የታዩ ለውጦች በጣም አንጸባራቂ ናቸው። ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነው ፕሮጀክቶች በታቀዱበት ፍጥነት ወደ ስራ እየገቡና ተጠናቀውም አገልግሎት እየሰጡ ያሉት። ከላይ ያነሳኋቸው 57 ፕሮጀክቶችም አዳዲስና ተጀምረው የነበሩት ናቸው በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ በዚህን ያህል ፍጥነት መጠናቀቅ መቻላቸው ማቀድ ብቻ ሳይሆን የመፈጸም ብቃታችንም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የሚያሳይ ነው።
ባለፉት ሶስት አመታተ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ያላቸውን አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ማስገባት የቻልንባቸው ዓመታት ነበሩ። እነዚህ ዋና ዋና አቋራጭና አገናኝ እንዲሁም የኮንደምንየም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ያጠቃልላል። እስከ ዛሬ ድረስ የነበረው መሰረታዊ ችግር በተለይም ዋና ዋና መንገዶች እርስ በእርስ በአገናኝና በአቋራጭ መንገዶች ያልተገናኙና ያልተያያዙ በመሆናቸው በመንገድ መጋጠሚያና መገናኛዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ መታየቱ ነበር።
ይህንንም ለማስቀረት በአሁኑ ወቅት ከሰባት በላይ ማሳለጫና ዋሻዎች እየተሰሩ ነው። ለዚህም ማሳያው የፑሽኪን ጎተራ መንገድ ላይ የሚሰራው ከመሬት ውስጥ (አንደር ግራውንድ) ዋሻና ተሻጋሪ ድልድይ ይጠቀሳል፤ በተመሳሳይ በከተማችን የተለያዩ ቦታዎች ላይ የውስጥ ለውስጥ ማለፊያ ዋሻዎችና ድልድዮች እየተገነቡ ነው። በቀጣይም ሶስት አዳዲስ ተሻጋሪ ድልድዮችንና የውስጥ ለውስጥ ማለፊያዎች የሚገነቡ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ አቅዶ በመፈጸም አንጻር በተደረገው ርብርብ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የአዲስ አበባ የመንገድ መሰረተ ልማት 7 ሺ 613 ኪሎ ሜትር በ7 ሜትር አማካይ ስፋት ላይ ደርሰናል። ይህም ትልቅ ስኬት ቢሆንም በዚህ ብቻ መገደብ ስለሌለብን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ባለፉት ሶስት አመታት የታየው ነገር ከፍተኛ አቅዶ የመፈጸም ብቃት እንዳለ ሆኖ አሁንም ከተማዋ የሚስተዋልባትን ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ለማስቀረት በርካታ ስራዎች መሰራት በዘላቂነትም ችግሩን ለመፍታት ሰፊ ስራ እንደሚጠብቀን ተገንዝበናል። በተለይም የብዙኃን ትራንስፖርት ምቹ አስተማማኝና ቀልጣፋና እንዲሆን ከማድረግ አንጻር አዲስ የተጀመረው የፈጣን አውቶቡስ መጓጓዣ መንገድ አለ፤ ይህም ባለፉት ሶስት አመታት ከመጡ ለውጦች መካከል ተጠቃሽ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ከጀሞ አንድ እስከ ጀሞ ሶስት ድረስ ያለው በአስፋልት የተሸፈነ ሲሆን ከጀሞ አንድ እስከ ጀሞ ሚካኤል ድረስ ያለው ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአስፋልት የሚሸፈን ይሆናል።ይህ ደግሞ በሚቀጥሉት አስር አመታት የፈጣን አውቶቡስ መንገድ ግንባታን እውን በማድረግና ወደ 15 የሚደርሱ ተመሳሳይ ግንባታዎች የሚከናወኑ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ በከተማ ደረጃ በአፈጻጸማቸው እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች እንደ ምሳሌ የሚነሱ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
ኢንጂነር ሞገስ፦ በርካታ ተምሳሌት የሚሆኑ መንገዶች አሉን፤ አንዱና ዋነኛው ግን የፑሽኪን ጎተራ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ነው፤ ይህ መንገድ ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ወይም የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት በ2 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ነበር፤ ነገር ግን በተደረገው ክትትል፣ ርብርብና ትኩረት በአንድ አመት ከስምንት ወር ውስጥ ዲዛይኑን ጨምሮ የዋሻ ስራው የተጠናቀቀበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህ ደግሞ በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ከመሆኑም በላይ በከተማ ውስጥ የመጀመሪያው የመንገድ ዋሻ ሆኖ የሚነሳም ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ለኮንትራክተሮች ሰጥተን ከምናሰራው ውጪ በራሳችን ሀይል የምንሰራቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ፤ በዚህም በጣም በፍጥነት ተሰርቷል ብለን የምንይዘው በስድስት ቀን ውስጥ ሶስት መቶ ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው ለላፍቶ ገበያ ማዕከል የሰራነው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ነው። እዚህ ላይ 110 መኪናን በአንዴ ማቆም የሚያስችል የመኪና ማቆሚያም ተሰርቷል። ይህ ደግሞ በተቋም ደረጃ የተገነባውን ከፍተኛ የሆነ የመፈጸም አቅም የሚያሳይና በሪከርድ ደረጃም የተመዘገበ ነው። የቁስቋም እንጦጦ መንገድ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመገንባት ተምሳሌት የሆነ ስራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶ በቀጣይ ጊዜ ሊሰራቸው ያቀዳቸው ስራዎችስ እንዴት ይገለጻሉ?
ኢንጂነር ሞገስ፦ በቀጣይ እንግዲህ አዲስ አበባ ተደራራቢ የሆነ የመዲናነት ሚና ያላት በመሆኑ አሁን ላይ ያላት የመንገድ መሰረተ ልማት በቂ አይደለም ፤ በመሆኑ አሁን ያለንን 7 ሺ 613 ኪሎ ሜት ርዝመት በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 16 ሺ 125 ኪሎ ሜትር ለማድረስ እንሰራለን። ከዚህም በተጨማሪ የብዙነህ ትራንስፖርቷ አስተማማኝ ፈጣን ወጪቆጣቢና ዝቅተኛ ኑሮ ላይ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ እንዲሆን እናደርጋለን።
ከ15 በላይ እንደ ፑሽኪን ጎተራ ያሉ ኮሪደሮችን የምንገነባ ይሆናል። በተመሳሳይም አዳዲሶቹን ከመገንባት ጎን ለጎን የተገነቡትን መንከባከብ ጥገና ማድረግ መሰረተ ልማቶቹን የመጠበቅ ከሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማት ጋርም በቅንጅት የሚሰራ ይሆናል።
በተጨማሪም በአለም ባንክ ድጋፍ የብልህ ትራንስፖርት ስርዓትን እየሰራን ነው ። ይህ ሲስተም ደግሞ ከ250 በላይ የመንገድ መጋጠሚያዎችን የሚያዘምን በአንድ ማዕከል የትራፊክ ማሳለጥ ስርዓቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው ።
ባለስልጣኑ አዲስ አበባ ተደራራቢ የሆነ የመዲናነት ሚናዋን አንድታሟላና ለክብሯ የሚመጥን የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲኖር ለማስቻልም በትኩረት እየሰራ ይገኛል ። ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።
ኢንጂነር ሞገስ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2013