ዴሞክራሲያዊ ስርአት በአንድ ታሪካዊ ክስተት ተገንብቶ የሚያበቃ ነገር አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃም ስርአቱን ገንብቶ የጨረሰ የለም። ሁሉም በሂደት ላይ ናቸው። ልዩነቱ አንዳንዶች ስርአቱን በመገንባት በሄዱበት ርቀት እና በርቀቱ ውስጥ በብዙ ልምምዶች ያካበቷቸው ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን ነው። እሱም ቢሆን በራሱ ማስተማመኛ እንደማይሆን በየጊዜው የሚስተዋሉ ዓለም አቀፍ ክስተቶች ማሳያ እየሆኑ ነው።
የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በቀጥታ ከአስተሳሰብ ግንባታ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአስተሳሰብ መዛነፎች በተስተዋሉባቸው ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ውስጥ ቀደም ብለው የተገነቡ ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም።
ለዚህም በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ከፍ ያለ ስፍራ እንደያዙ የሚነገርላቸውና ራሳቸውን የስርአቱ ሀዋርያ አድርገው የሚመለከቱ ሀገራት ጭምር በየዘመኑ በሚከሰቱ የተዛነፉ አስተሳሰቦች ምክንያት ዴሞክራሲያቸው ለአደጋ ሲጋለጥ ተስተውሏል። በቅርቡ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት የታየውና ዓለምን ግራ ያጋባው ክስተት ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ የሚሆን ነው።
ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ከፍ ባለ ደረጃ ገንብተናል የሚሉትም ሆኑ ፣ ሥርአቱን ለመገንባት በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የሚገኙ የሶስተኛው ዓለም ሀገራት ሕዝቦች፣ ስርአቱን ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ከፍ ያለው ተግዳሮት የሚመነጨው ከተዛነፉ አስተሳሰቦች ነው። እነዚህ አስተሳሰቦች ገደብ አልባ ከሆነ ራስ ወዳድነትና ከዚህ ከሚመነጭ ስግብግብነት የሚመነጩ ናቸው።
እነዚህ አስተሳሰቦች አንድም በብሄራዊ ጥቅም ስም ሰፊ በር ተከፍቶላቸው እንዳሻቸው ገዥ የሚሆኑበት መንገድ የሚመቻችላቸው ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህዝብ ተስፋና ተፈጥሯዊ የመሆን መሻት ተለጥፎላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በሀገር ደረጃ ዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን በከፋ መልኩ ሲገዳደሩ ማየት የተለመደ ነው።
የኛም ሀገር ተጨባጭ እውነታ ቢሆን ከዚህ በብዙ የተለየ አይደለም። ካለን የሀገረ መንግስት ግንባታ የሺዎች አመታት ታሪክ አንጻር አሁን ያለንበት ሁኔታ የሚመጥነን እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
ለዚህ ደግሞ የመጣንባቸው መንገዶች ፣ መንገዶቹ የተዋቀሩባቸው የአስተሳሰብ ጡቦች የተዛቡ መሆናቸው ዋነኛ ምክንያቶቻችን ናቸው። እነዚህ የተዛቡ አስተሳሰቦች እንደ አንድ ሀገርና ህዝብ ወጥ የሆነ ማህበረሰባዊ ስነልቦና እንዳይኖረን አድርገውናል። ሀገራዊ መግባባት እንዳንፈጥርም ተግዳሮት ሆነውብናል።
እነዚህ የተዛቡ አስተሳሰቦች የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታችን ላይ ብቻ ሳይሆን ከዚህም ከፍ ባለ ደረጃ እንደ ሀገር የምንቀጥልበትንም ማህበረሰባዊ መስተጋብሮቻችንን ጭምር አደጋ ውስጥ የከተቱበት ሁኔታ ስለመፈጠሩ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል። በዚህም ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገደናል።
የቅርቡን ታሪካችን እንኳን ብንመለከት በ1950ዎቹ ዓ.ም ማብቂያ ላይ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በብዙ መነቃቃት የተነሳው ትውልድ፤ የተዛቡ አስተሳሰቦች በተሸከሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ከፍ ያለ መስዋዕትነቱ በታሪክ ምእራፍ ውስጥ የሽንፈት እና የቁዘማ ምእራፍ ሆኖ ተጠናቋል።
ከዚያም በኋላ የነበረው የታሪካችን ምዕራፍም ቢሆን በህዝብ ተስፋና በዴሞክራሲ ስም የተጀመረ፣ ከብዙ መስዋእትነትና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በድል ማግስት በቡድኖች የተዛባ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ በወለደው ራስ ወዳድነት መክኖ የቀረ ነው።
በተስፋ በመጸነስና በተዛቡ አስተሳሰቦች መጨናገፍ የተሞላው የሀገራችን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዛሬ ላይ ግን በሌላ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ላይ ይገኛል። ይህንን ታሪካዊ ምዕራፍ በአግባቡ አጢነን የሚመጥነውን ታሪክ መጻፍ ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ነው። ሊጻፍ የሚገባው ታሪክ በደም ቀለም የሚጻፍና የህይወት መስዋእትነት የሚጠይቅ አይደለም።
ከዚህ ይልቅ ከራስ ጋር መታረቅን፣ በዘመናት ከተጋባነው ራስ ወዳድነት መፋታትን፣ በህዝብ ተስፋ ከመቀለድ እርግማን መውጣትን የሚጠይቅ ነው። ራስን ለህዝብ እውነተኛ ፈቃድና ተስፋ በድፍረትና በቁርጠኝነት መስዋዕት አድርጎ መስጠትን የሚፈልግ ነው።
የተለመደው የሴራና የጥፋት መንገድ ሀገርንና ህዝብን በየዘመኑ ካስከፈለው ከፍያለ ዋጋ ፣ ካመከነው የትውልዶች ተስፋ በአግባቡ መማር፣ ከሴራና ከጥፋት መንገድ ማንም አትራፊ እንደማይሆን ካለፈው ታሪካችን መረዳት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው።
ከመጣንበት ዋጋ አስከፋይ መንገድ ፣ መንገዱ ከፈጠረው የጥፋት አዙሪት ለመውጣት ዛሬ ላይ በአግባቡ ቆሞ በሰከነ መንፈስ ማሰብ ፣ መጪውን ትውልድ ከዚህ አዙሪት ለመታደግ የተሰጠን የጊዜው ትልቁ የመሻገሪያ ዕድላችን ነው።
በተለይም በሀገሪቱ ያሉ ልሂቃን ፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ያለጦር መሳሪያ ፣ ያለ ደም መፋሰስ ከራስ ጋር በመታረቅና የራስን ፍላጎት መስዋእት በማድረግ ህዝብን የማሻገር እድል በመጠቀም በፍቃድ ላይ መጨከንን ሊማሩበት ይገባል። ይህ የአዲሱ ትውልድ አዲሱ የጀግንነት ታሪክ ትልቁ እሴት ነው። የማይናወጥ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዋነኛ ጡብም ይሄው ከራስ ጋር መታረቅና የራስን ፍላጎት መስዋእት ማድረግ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም