ስድተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያውያን ብዙ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ከምርጫም በላይ የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የሚያሥጠበቅ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ይህንኑ የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በምርጫው ተሳትፏል፡፡ የጠላቶቹን አንጀት አሳርሯል፤ የወዳጆቹን ልብ በደስታ ሞልቷል፡፡
በተለይም እራሱ በለኮሰው ጦርነት የጋየው የአሸባሪው ህወሓት ቅጥረኞችና ጀሌዎች ይህ ሀገራዊ ምርጫ እንዳይካሄድ ገንዘባቸውን ከስክሰዋል፤ ተባባሪዎችን በከፍተኛ ገንዘብ ገዝተው አሰማርተዋል፤ አለም አቀፍ ሚዲያዎችን ሳይቀሩ በገንዘባቸው ደልለው ኢትዮጰያ ላይ አዘምተዋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን ለምርጫው ከመድረሳቸው በፊት እርስ በእርስ በብሄር እንዲባሉና ሀገሪቱ እንድትፈርስ ብዙ ጥረዋል፡፡ በከፍተኛ ረብጣ ዶላር የተገዙትም ሎቢስቶች(አግባቢዎች) ወገባቸውን አስረውና ሽንጠታቸውን ገትረው ኢትዮጵያ በብሄር እንድትባላ ያለ ማፈር በታዋቂ ሚዲያዎች ጭምር አሳፋሪ ንግግሮችን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አንዱ ማሳያም የሚከተለው ነው፡፡
አውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲከታተሉ እና ከኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች ጋር እንዲመካከሩ የሾማቸው የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒካ ሀቪስቶ የዛሬ ሳምንት አካባቢ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ኮሚቴ ጋር በነበራቸው የጥያቄና መልስ መርሃ ግብር ላይ ፍጹም ያልተጠበቀ እና አስደንጋጭ የሆነ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ልኡክ ጆሴፍ ቦሬል በልዩ ልኡክነት ወደ አዲስ አበባ የላኳቸው ሀቪስቶ ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር በነበረኝ ቆይታ የኢትዮጵያ መሪዎች “ትግሬዎችን ለቀጣይ 100 አመታት ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፉ ዝተው ነግረውኛል ” ሲሉ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የሰውየው ማብራሪያ ዓርብ እለት ይፋ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የሀቪስቶን ሪፖርት ክፉኛ የኮነነ ሲሆን ከአሁን በኋላ የአውሮፓ ህብረት እሳቸውን በመልዕክተኝነት እንዳይልክም አሳስቧል፡፡ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ዲፕሎማቱን ቀጣፊ እና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ናቸው ያለ ሲሆን ሰውየው ለህብረቱ ፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ ላይ የተጠቀሟቸውን ገለጻዎችም በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተቃኙ ናቸው ብሏቸዋል፡፡ በመግለጫው የተኮነኑት ገለጻዎችም ሰውየው በሽብር ቡድንነት በኢትዮጵያ ፓርላማ የተፈረጀውን ህወሓትን “ተቃዋሚ(opposition)” ብለው መጥራታቸው፤ ከ37 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውን የሚሳተፉበትን ምርጫ “ምርጫ ተብዬ (so called election)” ማለታቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስትን ከአሸባሪው ህወሓት እኩል በማስቀመጥ የተኩስ አቁም እንዲፈጸም ሁለቱም ወገኖች አልፈለጉም ማለታቸው እንዲሁም “በክልሉ የግብርና ስራ እንዳይካሄድ ሆን ተብሎ እየተጣረ ነው” ማለታቸውን
ነው፡፡ መግለጫው በጥቅሉ የሀቪስቶ ማብራሪያ የኢትዮጵያን መንግስት ያስቆጣ እንደሆነ የታየበት ሲሆን የሰውየው የኢትዮጵያ ተልዕኮ መጠናቀቁንም ያሳየ ነበር፡፡ በዚህም ላይ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን አንድነት ምን ያህል እንደሚያሳምማቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ሌሎቹን ጉዳዮች ወደ ጎን ትተን ሰውየው የኢትዮጵያ መሪዎች ለቀጣይ 100 አመታት ትግሬዎችን ከምድረ ገጽ እናጠፋለን አሉ ብለው የተናገሩትን ስንመረምረው አንዳንድ አስገራሚ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ ሀቪስቶ ወደ አዲስ አበባ ሁለት ጊዜ የመጡ ሲሆን ከሁለተኛው በመጀመሪያው ጉብኝታቸው ከመንግስት መሪዎች ጋር ተነጋግረው በሁለተኛው ጉብኝታቸው ደግሞ ወደ ትግራይ ተጉዘው ጉብኝት አድርገው ነበር የተመለሱት፡፡ ከሁለተኛው ጉብኝታቸው በኋላ በወርሃ ሚያዝያ ለህብረቱ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርትም የኢትዮጵያ መሪዎችን ለውይይት ክፍት ሆነው እንዳገኟቸው፤ ያደረጉት ውይይትም ጠቃሚ እንደነበርገልጸው ነበር፡፡ በወቅቱ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ያደረጉትን ውይይት “the discussion , also on sensitive issues were constructive. All interlocuters expressed a willingness to continue their dialogue with the EU”(“በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ያደረግነው ውይይት ገንቢ ነበር፡፡ ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊ አካላትም ከአውሮፓ ህብረት ጋር ውይይታቸው ለመቀጠል ተስማምተዋል ”) ብለው ነበር፡፡
የእናጠፋቸዋለን ዛቻው በየካቲት ተደረገ ያሉት ሀቪስቶ ከላይ የተገለጸውን የሙገሳ ሪፖርት ያቀረቡት በሚያዝያ ወር ሲሆን በዚያን ወቅት ስለ ዛቻው ምንም አላሉም ነበር፡፡ ሰኔ ላይ ግን ከሚያዝያው ሪፖርታቸው የሚቃረን አዲስ ሪፖርት ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ለምን? ምናልባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳለው ሰውየው ሌላ የተሰወረ አጀንዳ አላቸው አልያም ለተመደቡበት ተልእኮ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ሰውየው በማክሰኞ እለቱ ማብራሪያቸው ቀጠል ያረጉና በክልሉ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ባለፈው ከነበረው የተሻሻለ እንደሆነ ይገልጻሉ ፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ድጋፍ ማጠናከር እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
ታዲያ እነዚሁ ከምድረ ገጽ እናጠፋለን ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች በእርግጥ አላማቸው እሳቸው እንደሚሉት ህዝቡን ከምድረ ገጽ ማጥፋት ከሆነ ስለምን እርዳታ በገፍ እንዲገባ ፈቀዱ? ሀቪስቶ ለዚህ መልስ ያላቸው አይመስልም፡፡መልሳቸው ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያን በህቡእ ማተራመስ ነው፡፡
የሀቪስቶ የሚያዝያ እና ሰኔ ሪፖርት መደበላለቅ የሚያሳየው ሰውየው ምናልባትም በሚያዝያው ሪፖርታቸው ማሳካት ያልቻሉትን ነገር በሰኔው ሪፖርታቸው ለማሳካት አቅደው ሊሆን ይችላል፡፡ ያ አላማም ምናልባትም የአውሮፓ ህብረት እና አጋሮቹ ሌላ ጨከን ያለ እርምጃ በኢትዮጵያ ላይ እንዲወሰዱ መገፋፋት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ መንግስት ፍጹም ቅጥፈት ነው ያለውን ዘር ማጥፋት ክስ በማቅረብ ሊያሳኩት ሞክረዋል፡፡
ሀቪስቶ በማብራሪያቸው ላይ ሌሎችም ብዙ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነገሮችን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ከጠቆማቸው “የምርጫ ተብዬው” እና “የተቃዋሚ” ገለጻዎች ባለፈ ኢትዮጵያ ኤርትራ እና ሶማሊያ የፈጠሩትን ወዳጅነት “አደገኛ ወዳጅነት” ያሉ ሲሆን ወዳጅነቱ ለሌሎች የቀጠናው ሀገራት ስጋት ነውም ብለዋል፡፡ እስካሁን ሌሎች የቀጠናው ሀገራት የሶስቱ ሀገራት ወዳጅነት አደጋ ፈጥሮብናል ሳይሉ ሀቪስቶ ይህን ማለታቸው እና እሳቸው ማን ከማን ጋር ሲወዳጅ በጎ እና መጥፎ እንደሆነ ሊበይኑ መሞከራቸው ስለ ሰውየው የአስተሳሰብ መንገድ የሚጠቁመው ብዙ ነገር አለ፡፡
የህዳሴ ግድቡንም በተመለከተ ሀቨስቶ የጦር ሀይሏን እያደራጀች እና አደገኛ ንግግር እየተናገረች ነው ካሏት ግብጽ ይልቅ አበክረው መናገር የፈለጉት ስለ ኢትዮጵያ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ መረጃዎችን እና ቴክኒካዊ ዳታዎችን ማቅረብ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ወገን እንደሚያውቀው ግድቡን በተመለከተ ለሁለቱም ሀገራት ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ጥያቄ ካቀረበች እንደቆየች ነው፡፡እዚህም ላይ ደግመን የምናስተውለው የልኡኩን የግንዛቤ እና የአረዳድ እጥረት ነው፡፡
የሆነ ሆኖ አሁን የዲፕሎማቱ እና የኢትዮጵያ መንግስት ግንኙነት ተጠናቅቋል፡፡ ሰውየው ከአሁን በኋላ ምናልባትም በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው እንጂ በአውሮፓ ህብረት ልኡክነት የሚመጡም አይሆንም፡፡ ይህ አጋጣሚ ግን ያሳየው ነገር ቢኖር ወደ ኢትዮጵያ ለስራ ከሚመጡ ልኡካን አንዳንዶቹ ቀና እና አዎንታዊ አመለካከት ይዘው እንደማይመጡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን የላኪዎችንም ፍላጎት ለማሳካት የማይረዳ ነው፡፡ እነዚህንም ዕኩይ ተግባራት በመረዳት ኢትዮጵያውያን በምርጫው በመሳተፍ በማያዳግም መልኩ ለባዕዳንና ለካህዲያን ምላሽ ሰጥዋል፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013