ስመጥርና ጥናታዊቷ የደብረ ብርሃን ከተማ ከተመሰረተች ከስድስት መቶ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡ ከተማዋ ሸዋን ማዕከል አድርጋ የኢትዮጵያ የስልጣኔ መሰረትና መናገሻ እንደነበረች የተለያዩ የታሪክ ምሁራንና ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡
ይሁንና የደብረ ብርሃን ከተማ እድሜዋና እድገቷ ተቃራኒ ሆኖ በርካታ አመታት አልፈዋል፡፡በተለይ ደግሞ ከአስር ዓመት በፊት የነበረው ሁለንተናዊ ጉዞዋ ይህንን የሚያሳይ እንደነበር ከተማዋን በቅርብ የሚያውቃት ይመሰክራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተማዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለፈውን የኋሊት ጉዞ በመቅበር ያንቀላፋችበትን ጊዜ ለማካካስ እየታተረች ትገኛለች፡፡ ከአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቷ ደግሞ የባለሀብቶች አይን ማረፊያ አድርጓታል።
ከተማዋ በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከተማ በመሆኗ የባለሀብቶች ፍሰትና የህዝቧ ቁጥር ከግዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣አገራዊ ፋይዳቸው የጎላ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዳረሻ እየሆነች መጥታለች፡፡ እድገቷ እየተፋጠነ የበርካታ ኢንዱስትሪዎች ማዕከል የመሆን ግስጋሴ ላይ ትገኛለች፡፡
እንደሚታወቀው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚጠይቅ፣ አዋጪ ቴክኖሎጂ የሚፈልግ፣ የተሻለ መሰረተ ልማት የሚያሻውና በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ካፒታልን የሚጠይቅ ነው:: መንግስት ይህን ዘርፍ ለማጐልበት በአገሪቱ በተመረጡ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቷል፡፡በመገንባትም ላይ ይገኛል፡፡የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተገነቡባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ ደብረ ብርሃን አንዷ ናት፡፡
በከተማዋ የተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክም የእድገት ሩጫዋ ዋነኛ ሞተር ሆኗል፡፡በ75 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ፈሰስ የተደረገበት የኢንዱስትሪ ፓርኩም ከሁለት አመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅትም በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ ባለሃብቶች ወደ ስራ ገብተዋል፡፡በርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገርም የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትም ጀምረዋል፡፡የኢንዱስትሪ ሰላም በሰፈነባት ከተማ በተገነባውና አስፈላጊው የውሃ፣የሃይልና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የተማሉለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ስምንት ሼዶች አሉት፡፡በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ13 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማዋ ወደ ስራ ከገቡ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንቶች ባሻገር በአሁኑ ወቅት በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶችም በርካታ ናቸው። ከሰሞኑም የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርም በተገኙበት በደብረ ብርሃን ከተማ ከስድስት ቢልየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አስር ኢንደስትሪዎች ለምርቃት በቅተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከተማ በመሆኗ የባለሀብቶች ፍሰትና የህዝቧ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው ያመላከቱት፡፡‹‹ከተማዋ በሁሉም መስኮች የልማትና እድገት ተስፋ ያላት በመሆኗ ልንጠቀምባት ይገባል›› ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፣ ከተማዋ የሀገሪቱና የክልሉ አማራጭ ከተማ እንድትሆን እና በቀጣይ በከተማዋ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉና ባለኮከብ ሆቴሎች እንዲበዙ እንደሚሰራ ነው ያመላከቱት፡፡
ከፍተኛ የሆነ ካፒታል ያስመዘገቡና ሰፊ የስራ ዕድል ከፈጠሩ አስር ኢንዱስትሪዎቹ መካከልም ዋን ዌይ ቴክስታይልና ጋርመንት ፋብሪካ፣ ቻንግል ችፑድ ፋብሪካ፣ ደብረ ብርሃን ፕሪ ኢንጅነሪንግ ሪፎርስመንት ባር ፣ ኤ ዋን ማርብል ማምረቻ ፣ ጀኬ ማብሰያ እቃዎች ማምረቻ፣ አር ዜድ ኤክስ ኮንፎርት ማምረቻ ፣ ጁኒፐር ግላስ ብርጭቆና ጠርሙስ ፋብሪካ፣ ቫይሮ ጋርደን ፕላስቲክ ፋብሪካ ፣ ሰለሞን ፋንቱ ወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ሰን ዱቄት ፋብሪካ ይገኙበታል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ ስመጥርና ጥናታዊ ከተማ መሆኗን የገለፁት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ፣ ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት እድገቷ እየተፋጠነ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከተማ ሆናለች ነው ››ያሉት፡፡
አሁናዊ የኢንቨስትመንት ፍሰት በሚመለከት የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃን ገብረ ህይወት በነራቸው ቆይታ እንደሚገለፁት፣ በደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንቱን አሁናዊ ሁነት ለተመለከተ ከቀደመው ይልቅ ከፍተኛ ለውጦች ስለመኖራቸው በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ ከአምስት መቶ ሃምሳ በላይ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች 560 ሄክታር መሬት በመውሰድ ወደ ስራ የገቡ ናቸው፡፡
በከፍተኛ ካፒታል የተገነቡና የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ኢንቨስትመንቶች የአገሪቱን ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ከማጎልበት እንዲሁም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባሻገር የስራ እድል ፈጠራ ረገድ የሚያበረክቱት ፋይዳ እጅጉን ልቆ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡እነዚህ ኢንደስትሪዎችም እስካሁን ለ20 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ከቀናት በፊት የተመረቁት ፕሮጀክቶች ከወዲሁ ለስድስት ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡
ከባለፉት ሶስት አመትታ ወዲህ 40 ሄክታር መሬት ወስደው ወደስራ የገቡት እነዚህ ፕሮጀክቶች፣ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ለሃያ ሁለት ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ የሚገልፁት የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃን፣ ሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ሲጠናቀቁ ደግሞ በአጠቃላይ ከ70 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸው ነው ያመላከቱት፡፡
ከተማዋ ፋይዳቸው የጎላ የኢንቨስትመንት መዳረሻና እድገቷ እየተፋጠነ የበርካታ ኢንዱስትሪዎች ማዕከል የመሆን ግስጋሴ ላይ ለመገኘታቸው ታዲያ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ በከፍተኛ መጠን ለመጨመሩ ከሚጠቀሱ መሠረታዊ ምክንያቶች መካከልም ከተማዋና አካባቢዋ ለዘርፉ ምቹ መሆን፣ የማህበረሰቡ ሰፊ የልማት ጥያቄና ራሱም የሰላሙ ጠባቂ መሆኑ፣ ከተማ አስተዳደሩ በተቀናጀ መንገድ ችግሮችን መፍታቱ መጣሩና የአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻሉ ለከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰት ሁነኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በተለይም የአዋሽ አንኮበር የደረቅ ወደብ መንገድ መገንባት፣ ከተማዋ በርካታ የቱሪስትና የተፈጥሮ መስህብ ባለቤት መሆኗ የአካባቢው ማህበረሰብ ልማት ወዳድና ለልማት ተባባሪ መሆኑ ለኢንቨስትመንቱ ፍሰትና እድገት ተጨማሪ አቅም በመሆን ይጠቀሳሉ።
በአንድ አገር ወይንም ከተማ ኢቨስትመንት ሲጎለብቱና ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ የሚያረክቱት ፋይዳ እንደተጠበቀ ሆኖ አስፈላጊው የቅድመ መከላከል ስራ እስካልተሰራ በአካባቢ ላይ የሚያሳድሩት ተፅእኖ ቀላል አይደለም፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመርም ከአካባቢ ብክለት አንፃር ሲቃኝም የራሱ መልክ ነው፡፡ይሁንና በከተማዋ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ህግ አንድ ፕሮጀክት ብክለት አለመኖሩ ሳይረጋገጥ የግንባታ ፈቃድ አይሰጥም፡፡ከዚህ ባሻገርም የጋራ የብክለት ማስወገድ ስርዓት እንዲኖር እንዲሁም በመልሶ ለአገልግሎት ማዋል ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ይገኛል፡፡
ቀደም ባሉት አመታት በደብረ ብርሃን ከተማ ላይ በተገነባው የፌደራል ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ አለም አቀፍ ካምፓኒዎች ባለሀብቶች ሀብታቸውን ፈሰስ ለማድረግ ከፍተኛ መሻት ቢኖራቸው ፍላጎታቸው እንዳይሳክ የሚያደርግ አንድ ችግር ነበረባቸው፡፡እሱም የፍሳሽ ማጣሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ይህ ችግርም ዋነኛ የኢንቨስትመንቱ እንዲሁም የባለሀብቶች ዋነኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይሁንና ከወራት በፊት ችግሩ የፌደራል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የኢንዱስትሪ ፓርኩ የፍሳሽ ማጣሪያ የግንባታ ውል ስምምነት ተፈርሟል፡፡ከ331 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት ይህ ፕሮጀክትም ከጥቂት ወራት በኸላ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
ከተማዋ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በምታደርገው የሩጫ ሂደት ሁሉም አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡በተለይም ለከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዋነኛ ማነቆው መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ አድርጎ አለማቅረብ
ይጠቀሳል፡፡ የኢንቨስትመንት ዋነኛ መሰረት የኢንዱስትሪዎች ዋስትና የሆነው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ሌላኛው ፈተና ነው። የተወሰኑ የኢንቨስተሮች የግንባታ ስራ ጀምረው ማቋረጣቸው ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡
ከሁሉ በላይ ግን የመሰረተ ልማት ተደራሽነትና ውስንነት ጎልቶ እንደሚታይ በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡በተለይ የሃይልና የሃይል ማስተላለፊያ (ትራንስፎርመር) እጥረት፣የውሃና የመንገድ አለመሟላትም ኢንቨስትመንቱ በታሰበው ልክ እንዳይስፋፋ አድርገውታል፡፡
የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤትም መሰል ችግሮቹን ለመሻገር የእርምት እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ወደ ስራ ያልገቡትን ባለሀብቶች በየደረጃው ድጋፍ በማድረግ ማስተካከል ካልቻሉ ከማስጠንቀቂያ እስከ መንጠቅ የደረሰ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡
ከመብራት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ችግር በክልሉ መንግስት ድጋፍ መስመር እንዲዘረጋ ተፈቅዶና ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡የመንገድ መሰረተ ልማት ችግርን ለመፍታት ከፌደራል ከክልል እና ከከተማ ድርሻ ባሻገር ባለሀብቶች በራሳቸው አቅም ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን በተመለከተም የከተማዋና የአካባቢውን አቅሞች በሙሉ አሟጦ ለመጠቀም እየተሰራ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም፣ ከተማዋ በመሪ ማዘጋጃ ቤት መተዳደር ከጀመረችበት ከ1941 ዓ.ም ጀምሮ ሶስት መዋቅራዊ ፕላኖችን አሳልፋለች፡፡ይሁንና ሁሉም ፕላኖች በአሰራርም በአፈፃፀምም ክፍተት ነበረባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የደብረ ብርሃን ከተማን ፈጣን እድገት አሁናዊ ሁኔታ ያማከለ ለቀጣይ 30 አመት ሊያገለግል የሚችል መዋቅራዊ ፕላን ለማዘጋጀት የሚያስችል እቅድ ይፋ ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅትም እቅዱን ወደ ተግባር ለመቀየርም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ይህም ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት በተለይም የባለሃብቶች ቀልብ ይበልጥ እንድትማርክና ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጎልበት ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013