ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ መርሀ ግብር እጅግ አስገራሚና አስደማሚ በሆነ መልኩ ተጠናቋል። የምርጫው ጊዜያዊ ውጤትም በምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ ለህዝብ በሚታዩ ቦታዎች ተለጥፈዋል። ምርጫው ለሀገራችን በቁጥር ስድስተኛ ቢሆንም በዲሞክራሲ ልምምድ ግን የመጀመሪያው የምርጫ ጊዜ እንደነበር ልብን ሞልቶ መናገር ይቻላል።
በምርጫ ቦርድ እና በፍትህ ተቋማት ጥንካሬ ፣ በመንግስት ቁርጠኝነት ጭምር በምርጫው ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት የአቅማቸውን ያክል ጥረት አድርገዋል፤ በዚሁ መሰረት ምርጫው ያለምንም ኮሽታ በሰላማዊ መንገድ ተከናውኗል። ይሄ ተቋማቶችን የሚያስመሰግንና በዲሞክራሲው አንድ እርምጃም ሀገራችንን ያራመደ ነው።
ለምርጫው ዲሞክራሲያዊነት ሌላው መሰረት የጣለው መራጩ ህዝብ ነው። መራጩ ህዝብ የምርጫን አስፈላጊነት በማመን ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ጭምር ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ የራሱን ኃላፊነት በሚገባ ተወጥቷል። ሰኔ 14 በተካሄደው የድምጽ አሰጣጥ መርሀ ግብር ላይ መራጩ ህዝብ የሌሊቱ ቁር ፣ የቀኑ ዝናብና ጸሀይ ሳይበግረው፣ ረጃጅም ሰልፎች ሳያሰለቹት በነቂስ ወጥቶ ይመራኛል፤ ያገለግለኛል ብሎ ላመነበት ፓርቲ ድምጹን ሰጥቷል።
ህዝብ በሀገር ላይ ሰላም እንዲሰፍን፣ ጠንካራ መንግስት እንዲመሰረት፣ ሟርተኞች እንደሚያስቡትና እንደሚመኙት ሀገር እንዳትበታተን ማድረጊያው ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ምርጫ መሆኑን ጠንቅቆ ማወቁንም በተግባር አሳይቷል። ምርጫው ለቀጣይ የሀገራችን ሰላም ዋናው መሳሪያ መሆኑንም በመረዳት ነው በነቂስ ወጥቶ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ሲመርጥ ያመሸው።
ሌላው የዲሞክራሲ ስርዓት መገንቢያው መንገድ ግልጽ ፣ ነጻና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተፎካክሮ ማሸነፍ ነው። ከፖለቲካ ፓርቲዎች የታየውም ይሄው ነው። በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድ ያወጣውን መስፈርት አሟልተው ወደ ምርጫ ውድድሩ ሜዳ ገብተዋል። ለደጋፊዎቻቸውም የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ከርመዋል። ይሄን ሁሉ የቅድመ ምርጫ የዝግጅት ወቅት በሰላም አልፎ በውድድሩ ሜዳ ላይ ገጥመዋል። ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩ በተከባበረና ስነምግባር በተላበሰ መልኩ ተፎካካሪነታቸውን በየመድረኩ አሳይተዋል። ወደ መንግስት ስልጣን መምጫው ምርጫና ምርጫ ብቻ መሆኑን አምነውና ተቀብለውም ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል።
በምርጫው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ችግሮችን እየተጋፈጡና እያስተካከሉ ሰላማዊ ትግል እንደሚያደርጉ አስቀድመው አስታውቀዋል። ከምርጫው በኋላም የሚመጣውን ውጤት በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ደጋግመው ገልጸዋል። በምርጫው ዋዜማም በጋራ ማዕድ ቆርሰው ለመልካም ውጤትና ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ቃል ገብተዋል። ይሄ ሁሉ በሀገራችን የመጀመሪያው ነው። በሌሎች የሰለጠኑ ሀገሮች ላይ ስናይ እና ስንመኝ የነበረውን የዲሞክራሲ መንገድ ያሳዩበት ሁኔታን ለመመልከት ችለናል። ይሄ በጣም የሚያስደስትና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ተግባር ነው።
በመንግስት ላይ የታየው ለሀገራችን የሚበጃት ምርጫና ምርጫ ብቻ ነው የሚለው ቆራጥ አቋም ፣ የምርጫ ቦርድ የተደራጀበት መንገድና ጥንካሬው ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም የመራጩ ህዝብ የምርጫ ተሳትፎ በሀገራችን ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የራሱን አሻራ አሳርፏል።
ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ማከናወን ስንችልና ስናጠናቅቅ የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ናት። የኢትዮጵያ ምርጫ የሚጠቅመውና ምርጫ ባይደረግ ደግሞ በትርምስ የሚጎዳው ኢትዮጵያዊው መሆኑን በማመን ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የአቅሙን ርብርብ አድርጓል። በኢትዮጵያ ምርጫ እጁን ወደ ሀገራችን የሚጭን ማንም የውጪ ሀይል ሊገባ አይገባም የሚል ጠንካራ አቋም አራምዷል።
ይሄንን በማድረግም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ተችሏል። ለዚህ ነው በዚህ ምርጫ ያሸነፈችው ሀገራችን ናት። ያሸነፈው ህዝባችን ነው የምንለው። የተሸነፉትም የውጪ ጣልቃ ገቦች፣ በሀገራችን የዲሞክራሲ ጭላንጭል እንዳይታይ ከውስጥና ከውጪ ሆነው ሲታትሩ የነበሩ ኃይሎች ናቸው። ለኢትዮጵያ ህዝብ ግን ምርጫው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ምርጫ በሀገራችን ሰላም ማስፈኛ መሳሪያ ነው። በዚህ እሳቤ የመጀመሪያውን የዲሞክራሲ መሰረት ጥሎ አልፏል።
አሁን ከሁሉም ወገን የሚጠበቀው ከሀሰተኛ መረጃ ራስን ማቀብና ከምርጫ ቦርድ የሚገለጸውን ውጤት በጸጋ መቀበል ነው። ያሸነፈውን ፓርቲ መልካም የስራ ዘመን ተመኝቶ፤ በሀገር ጉዳይ ላይ ተባብሮ ለመስራት መዘጋጀትም ነው። ይሄ ሲሆን ዛሬ መሰረቱ የተጣለው የዲሞክራሲ ሂደት ነገ ወደ በለጸገ ዲሞክራሲ መድረሱ አይቀሬ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም