ቀኖች ሁሉ ባላቸው ርዝማኔ እኩል ናቸው ተብለው ቢታሰቡም አንዳንድ ቀኖች ግን ከሚሸከሙት ታሪካዊ ክንውን ጋር ተያይዞ ጎላ ብለው መታየታቸው እውነት ነው። እንዲህ ዓይነት ዕድል ከገጠማቸው ቀናት መካከል የካቲት 23ን ለማሳያነት ማንሳት ይቻላል። ይህቺ ቀን እንደሌሎቹ ቀናት የ24 ሰዓታት ባለቤት ብትሆንም በእነዚያ ውስን ሰዓታት በተከናወነው ሉዓላዊነትን የማስከበር ልዩ ተጋድሎና መስዋዕትነትና ከትግሉ ጋር ተያይዞ በተገኘው ድል ዕለቷ በኢትዮጵያውያን ልብ የተለየች ቀን እንድትሆን አድርጓታል።
የትናንትናዋ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ይህን ዕድል ከተጎናጸፉና በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ታሪክ በመልካም ምሳሌነት ከሚወሱ ቀናት አንዷ ለመሆን በቅታለች። አዎን ትናንት ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በቁጥር ለስድስተኛ ጊዜ በዓይነቱ ደግሞ የመጀመሪያ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ምድር ተከናውኗል። በዚህች ታሪካዊ ቀን ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከጫፍ ያለምንም የጾታ፣ የእምነትና የቋንቋ ልዩነት በነቂስ ወጥተው ይበጀኛል ይሻለኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምጽ ሲሰጡ ውለዋል።
በትናትናው አገር አቀፍ ምርጫ በጫጉላ ላይ ያሉ ሙሽሮች፣ ገና በአራስቤት ያሉ እመጫቶች፣ ነፍሰጡሮችና በተለያየ ህመም ውስጥ ያሉ ህሙማን ማንኛውም ችግርና ሁኔታ ሳያግዳቸው የሚወዷት ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ የምንረዳው ትልቅ እውነታ ቢኖር ኢትዮጵያውያን አገራቸው እንድታሸንፍ የማይከፍሉት መስዋዕትነት አለመኖሩን ነው።
መራጩ ሕዝብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የተላለፈለትን ቅስቀሳ ሲከታተልና ማንን እንደሚመርጥ በጽሞና ሲያስብ ከቆየ በኋላ ለሚፈልገውና ይበጀኛል ለሚለው አካል ድምጹን ለመስጠት ወደምርጫ ጣቢያ የተመመው ገና ጨለማው ሳይገፍ ከሌሊት አንስቶ ነበር። ሕዝቡ የአየር ጸባይና ሁኔታ ሳያግደው ረጃጅም ሰልፎችን ሁሉ ታግሶ ወረፋውን በመጠበቅ ታሪክ ሰርቶ ኢትዮጵያ አንድታሸንፍ ማድረግ ችሏል። የምርጫውን ሂደት አስመልክቶ የተለያዩ ፓርቲዎች አመራሮች በሰጡት አስተያየት ከጥቃቅን ችግሮች ውጪ የምርጫው ሂደት ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር መስክረዋል።
ብልጽግናን ወክለው በጂማ ዞን በሻሻ ላይ የተወዳደሩት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ በሰጡት አስተያየት «በአጠቃላይ በዚህ ምርጫ መንግሥትንና ሕዝብን አምነው በምርጫ ለተሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ። ቢያሸንፉም ባያሸንፉም ቢመረጡም ባይመረጡም በዚህ ምርጫ ከውጭ ያለውን ተቃውሞ አንሰማም ብለው የተሳተፉትን በሙሉ ምስጋና አቀርብላቸዋለሁ» ብለዋል። ኢዜማን በመወከል በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ላይ የተወዳደሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት «የዛሬው ምርጫ ሰፊ የሕዝብ ንቅናቄ የታየበት ትርጉም ያለውና ብዙ ተስፋ የተደረገበት ነው» ሲሉ ተናግረዋል። አብንን ወክለው በጣና ሁለት ምርጫ ጣቢያ ላይ የተወዳደሩት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔም ምርጫውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት «እንደመርህ ሕዝባችን የሚሰጠውን ማናቸውንም ውሳኔና ድምጽ አብን አክብሮ የሚቀበል መሆኑን እገልጻለሁ» ብለዋል።
የሕዝብ አገዛዝ የሚል ትርጉምን ያዘለው ዴሞክራሲ ከጥንተ መሠረቱ ዜጎች የሚወክሏቸውን ሰዎች በነፃነት መምረጥ የሚችሉበት ሥርዓት ነው። ይህንን መሠረታዊ መነሻ በማጤንም የዴሞክራሲ ስኬት የሚመዘነው በአንድ ፓርቲ ማሸነፍ ሳይሆን ለመሸናነፍ በተሄደበት የምርጫ ሂደት ነው። ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያችን ትናንት በተካሄደው ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማን አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ሆናለች።
ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው በአገራችን ከዚህ ቀደም በስመ ዴሞክራሲ ወደ አምስት የሚደርሱ ምርጫዎች ተከናውነዋል። ይህም የሕዝብን ቅሬታ ከመውለዱም በላይ ድህረ ምርጫ በተካሄዱ ግጭቶች በርካታ የሰው ሕይወት አካልና ንብረት ጠፍቷል። ይህም በአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ሊያብብ ነው ብለው በጉጉት የጠበቁ ብዙ ዜጎችን ተስፋ ከማስቆረጡም በላይ የአገራችንን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ አበላሽቷል።
ድህረ ለውጥ ግን ይህ አካሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተለውጦ የዴሞክራሲ ሥርዓት ተስፋ በመልካም ሁኔታ ፈንጥቋል። በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ወደአገራቸው እንዳይገቡ ተከልክለው የነበሩ ዜጎችና ፓርቲዎች በነፃነት ወደአገር ቤት መግባት፣ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት መስፈን፣ ነፃ የዴሞክራሲ ተቋማት ማበብብም ለዚህ ውጤት መገኘት በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ትናንት የተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የእነዚህ ሁሉ የለውጥና የሪፎርም ሥራዎች ድምር ነው። ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን መያዝ ያለበት በምርጫ ካርድ ብልጫ ያገኘ አካል ብቻ ነው በሚል መርህ መላ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ከሌሊት እስከ እኩለ ሌሊት ተለሰፈው በመምረጥ አገራቸው ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ አድርገዋል። ከምርጫው ጎን ለጎንም የሚወዷትን አገራቸውን አረንጓዴ በማልበስ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። በዚህም መላ ኢትዮጵያውያንና ወዳጆቻቸው ሀሴትን ሲላበሱ ጣልቃ ገቦችና የኢትዮጵያን ክፉ የሚመኙ አካላት ደግሞ አፍረዋል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2013