የአእምሮ ህመም መነሻው አንድም ሌላም ሊሆን ይችላል። በአእምሮ ህመምም የተነሳ ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ፤ ጉዳት አድራሾችም ከቁጥጥር ውጪ በሆነው የአእምሯቸው ክፍል የተነሳ ጉዳት አድርሰው ወንጀለኛ የሚባሉበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ጉዳት አድራሾቹ በተለያየ ወንጀሎች ውስጥ ከገቡ በኋላ ይህን ችግር ለመፍታት የሚሰራ የህክምና ዘርፍ መኖሩን ከአንጋፋው የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህን የህክምና ዘርፍ ከመደበኛው የአዕምሮ ህክምና ጎን ለጎን የሰብ-ስፔሻሊቲ (Subspeciality) ፕሮግራም በብቸኝነት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የፎረንሲክ ሳይካትሪ ተጠቃሽ ነው። ፎረንስኪ ሳይካትሪ ምን እንደሆነና በዚህ ዘርፍስ ምን ያህል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በአማኑኤል ሆስፒታል ሜዲካል ዶክተር ሔኖክ ይትባረክ ያካፈሉትን እነሆ ለጤና ገፃችን ብለናል። መልካም ንባብ።
ለመሆኑ ፎረንሲክ ሳይካትሪ ምንድን ነው?
ፎረንሲክ ሳይካትሪ ከወንጀል እና የፍትሃ ብሄር ጉዳይ ጋር ተያይዞ በሚነሱ ማናቸውም የፍርድ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በፍርድ ቤቱ አልያም በቅርብ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠርጣሪ ግለሰቦች ድርጊቱን የፈፀሙት በአዕምሮ ህመም ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ሲገመት የሚደረግ ምርመራ ነው።
ይህ ምርመራ ተጠርጣሪው የአዕምሮ ታማሚ ከሆነ ውሳኔ አkሰጣጡ ላይ ከግምት እንዲገባ አልያም በተቃራኒው በአዕምሮ ህመምተኛ ሰበብ በማህበረሰቦች ላይ የሚፈጠሩትን ወንጀሎች ከህግ ባለሙያዎች ጋር አብሮ በመስራት ፍትሃዊ ውሳኔ የሚሰጥበት የምርመራ ሂደት ነው።
የምርመራው ሂደት ለአንድ ተጠርጣሪ ከአንድ ወር እስከ ሁለት ወር ጊዜን የሚወስድ ሲሆን፤ ሂደቱም እጅግ አድካሚ የምርመራ ሂደት ነው።
ይህም በሆስፒታሉ አስራ አንድ ተለይተው የተዘጋጁ የተኝቶ ህክምና አልጋ ያሉት ሲሆን፣ ከሚወስደው ረጅም የምርመራ ጊዜ እና በብቸኝነት አማኑኤል ሆስፒታል ላይ ብቻ መሠራቱ የተጠባባቂ ታካሚዎችን የወረፋ ቁጥር ከ1900 በላይ እንዲደርስ አድርጎታል።
ተጠርጣሪዎች ከሚከሰሱባቸው ወንጀሎች መካከል ከብዙ በጥቂቱ ወደ አስራ ዘጠኝ የሚደርሱ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ሲሆኑ እነዚህን የወንጀል አይነቶች በአራት ንዑስ ክፍሎች ለይቶ ማየት ይቻላል።
አንደኛው ስነ ህይወታዊ (አካላዊ) የወንጀል አይነት ነው፤ ይህ ማለት የህይወት ማጥፋት (የግድያ ወንጀል)፤ የህይወት ማጥፋት ሙከራ ወንጀል፤ ፆታዊ ጥቃት፤ አካላዊ ጥቃት ወንጀሎች ናቸው።
ሁለተኛው ስነ ልቦናዊ ይህ ማለት የማታለል (ማጭበርበር)፤ የሀሰት የምስክር ቃል መስጠት፤ የፍርድ ቤት ውሳኔን መተላለፍ፤ ከማሳደግ እና ከጉዲፈቻ ልጅ ጋር ተያይዘው የሚነሱ የሀሰት የይገባኛል ወንጀሎች፤ የተለያዩ የውንብድና ስራዎች፣ ግድያ፣ ጥቃት ለመፈፀም የሚደረጉ የማስፈራራት፣ እና የዛቻ ሙከራዎች ናቸው።
ሶስተኛው ማኅበራዊ ወንጀሎች የሚባሉት ሲሆኑ ይህም የሽብርተኛነት ወንጀል፤ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን የማድረስ ወንጀል፤ የስርቆት ወንጀል፤ ማኅበረሰብን ለሁከት እና ብጥብጥ የመዳረግ ወንጀል፤ ሰዎችን አስገድዶ (አግቶ) የማቆየት ወንጀል፤ ንብረት የማውደም ወንጀሎች ናቸው።
አራተኛው በህግ የተከለከሉ አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀም ወይም የማዘዋወር ወንጀል፤ በህግ የተከለከሉ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፤ በህግ የተከለከሉ የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀም፤ በህግ የተከለከሉ ቦታዎች፣ እንዲሁም ስራዎች ላይ የተከለከሉ አደንዛዥ ዕፅ የመጠቀም ወንጀሎች ናቸው።
በጠቅላላው እስከ አሁን በአማኑኤል ሆስፒታል በሁሉም የወንጀል አይነቶች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ የምርመራ ውጤታቸውን በማድረስ ወደ 1200 ተጠርጣሪዎች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፣ በሚያሳዝን መልኩ ከ50% በላይ የሚሆኑት በግድያ ወንጀል የተያዙ መሆናቸው የችግሩ አሳሳቢነት ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑ፤ ከዚሁ አኳያ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባ መሆኑን ያመለክታል።
አያይዞም በምርመራው ሂደት በባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው ጫና ብዙ ከመሆኑ አንፃር የተለያዩ መዘዞች ክስተቶች አይቀሬ ነው። ለምሳሌ ያህል “ውጤት በአስቸኳይ አልደረሰም” በሚል ትዕዛዝ ባለሙያዎች እንዲሁም ሀላፊዎች ለአላስፈላጊ እንግልት ከመዳረጋቸው በተጨማሪ እስከ መታሰር የሚደርሱባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፤ ይሁንና ሆስፒታሉ ተግዳሮቶቹን ሁሉ ተቋቁሞ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል አሁንም ድረስ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።
የስራውን ውስብስብነት እና አያይዞም የሚከሰቱትን የፍትህ ጥያቄዎች አስቸኳይ መልስ እንደሚሹ ከግምት ያስገባወ ሆስፒታሉ፤ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር የችግሩን ውስብስብነት በማስረዳት እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን፤ የሁሉንም የክልል ጤና ተቋማት ርብርብ እና ድጋፍ ላይ በመስራት በቀጣይ የክልሎችን አቅም በማጠናከር ላይ ይገኛል።
በአቅራቢያችን ያለ የእእምሮ ህመም ተጠቂ የከፋ ጉዳት ሳያደረስ ወደ ህክምና ማምጣትም የችግሩን አሳሳቢነት የሚቀንሰው ሊሆን ይችላል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013