እንኳን አደረሳችሁ! እንኳን አደረሰን! ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለዘመናት ተርበዋል፤ተጠምተዋል። በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስምም ብዙ ተነግዶባቸዋል። ዛሬ ድምፃቸውን የሚሰጡበት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግን የዴሞክራሲ ረሃባቸውን ማስታገስ፣ ጥማታቸውን ማርካት የሚጀምሩበት ነውና እንኳን አደረሳችሁ! ለማለት ወደናል።
ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ልክ እንደ ታላቅ አውዳመታችሁ በጉጉት ስትጠብቁት የኖራችሁት ቀን እነሆ ዛሬ ነው። የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ታሪክ እየቀየረ ለሚገኘው ለእዚህ ድምፅ መስጫ ቀን ደርሳችኋል።
ሀገራችን ከቁጥር አንጻር ስድስተኛውን ምርጫ እያካሄደች ትገኛለች፤ ይህ የሚሆነው ግን ከቁጥር እንጻር ብቻ ነው። ዴሞክራሲያዊ ከመሆን አኳያ ግን የዘንድሮው ምርጫ የመጀመሪያው ነው። ያለፉት ምርጫዎች ከማስመሰል ባለፈ የዴሞክራሲያዊ ምርጫነት ጠረኑም ጨርሶ አልነበራቸውም። የዴሞክራሲ ጠረን በዚህ ምርጫ ነው ማወድ የጀመረው።
ለዚህ ታላቅ ቀን መድረስ የተቻለው በርካታ ዜጎች በየዘመኑ ውድ ህይወታቸውን ሰውተው፣ ታስረው፤ ተገርፈው፣ ተሰደው ነው። ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች የሆኑትንም ቤቱ ይቁጠራቸው። መንግሥታት እየተቀያየሩ የዴሞክራሲ ጭላንጭል መጣ ሲባል እየቀረ፣ ተጸነሰ ሲባል እየጨነገፈ፣ ተወለደ ሲባል እየጠፋ አያሌ ዓመታት አልፈዋል። ይህ ቀን በእዚህ ሁሉ መስዋእትነት የተገኘ ታሪካዊ ቀን ነው።
ዛሬ በብዙ መልኩ ወሳኝ መሆናችንን የምናሳይበት ነው። ይመራናል የምንለውን ፓርቲ በካርዳችን እንመርጣለን፣ አይበጀንም የምንለውን ደግሞ እንቀጣለን። ማንም ያሸንፍ ማን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በማካሄድ ኢትዮጵያ እንድታሸነፍ ግን እናደርጋለን። ምርጫው መካሄድ የለበትም ሲሉ የነበሩትን ጠላቶቻችንን ድምፃችንን በመስጠት ምርጫው ከመካሄድ ምንም ምድራዊ ኃይል እንደማይገድበው እናረዳቸዋለን። ከዚሁ ጎን ፤ልጎን ለኢትዮጵያችንም የሚገባትንና የሚያምርባትን አረንጓዴ ልብሷን እናለብሳታለን!
ዜጎች ውድ መስዋዕትነት የከፈሉበት ይህች ቀን ላለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታትም በዜጎች ዘንድ በጉጉት ስትጠበቅ ቆይታለች። መንግሥት ምርጫውን የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሆን ለማድረግ በእጅጉ ሠርቷል። ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር በገባው ቃል መሰረት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ መደላድሎችን ፈጥሯል። ጨርሶ ገለልተኛ ያልነበረውን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስና ነፃነቱን ጠብቆ ሊሠራ በሚችል መልኩ አቋቁሟል፤ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ተደርጓል። ፍርድቤቶችና የመገናኛብዙሃን ባለስልጣንን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃ ሆነው መንቀሳቀስ ችለዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎችን ሲገፋና ሲጨቁን የነበረው የምርጫ ህግ ተሻሽሏል። ፍርድ ቤቶች በነፃነት መሥራት በሚያስችላቸው መልኩ ተዋቅረዋል። ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትም በነፃነት ሊንቀሳቀሱ በሚችሉበት መልኩ ተደራጅተዋል። በዚህ መደላድል ላይ ተሁኖ ነው እንግዲህ ይህ ምርጫ እየተካሄደ ያለው። እስከ አሁን ከተካሄደው አጠቃላይ የምርጫው ሂደት መረዳት እንደሚቻለውም ምርጫው በዴሞክራሲያዊ አግባብ እየተፈጸመ መሆኑን ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ 37 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል። 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 120 የግል ተወዳዳሪዎች በምርጫው ለመወዳደር ተመዝግበው ቅስቀሳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከ102 የሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ 45 ሺ የሀገር ውስጥ ታዛቢዎችም የድምፅ መስጠቱን ሂደት ለመታዝብ ተሰማርተዋል። የአፍሪካ ህብረትን የመሳሰሉ ታዛቢዎችም ተሰማርተዋል። እስከ አለፈው ዓርብ ድረስም 89 ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ዘገባዎችን ለመሥራት ፈቃድ ወስደዋል። እነዚህ መረጃዎችም ምርጫው በስኬት ጎዳና እየተጓዘ መሆኑን ያመለክታሉ።
የእስከአሁኑ የምርጫው ሂደት በራሱ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ጭላንጭል እየታየ መሆኑን ያመለክታል። ዴሞክራሲን መተግበር የረጅም ጊዜ ሂደት ነው። ይህ በሀገራችን የታየው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ይበልጥ እንዲሰፋ መሥራት ቀጣዩ ሥራ ይሆናል። በዛሬው ድምፅ የመስጠት ሂደት እንዲሁም በቀጣይ የምርጫውን ውጤት ተከትሎ በሚኖሩት ሂደቶች ደግሞ ጭላንጭሎቹን ወደ ሙሉ ብርሃን ማሳደግ ይገባል።
ይህን ለማድረግ ሁሉም ነገር በመራጩ እጅ ውስጥ ይገኛል። መራጩ ዛሬ በካርዱ በሚገባ መጠቀምና ሁሉም ለመምረጥ የተመዘገበ ዜጋ ድምፁን ይመራኛል ለሚለው ፓርቲ በነፃነት መስጠት ይኖርበታል። ሁላችሁም በምርጫው ሂደቶች በማለፍ ስትዘጋጁ እንደመቆየታችሁ ድምፃችሁን በመስጠት ታሪኩን ማሳመር ይጠበቅባችኋል። ይህ አንዱ አብይ ጉዳይ ነው።
እንደሚታወቀው ምርጫውን ለማወክ ያሰፈሰፉ ኃይሎች በውስጣችንም በዙሪያችንም አሉ። እነዚህ ኃይሎች የጥፋት ተልእኳቸውን ለማስፈጸም ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ አርፈው ይቀመጣሉ ተብሎ አይታሰብም። ሐሰተኛ መረጃ ሊያሰራጩ ይችላሉ። ስለሆነም ከእነዚህና መሰል መረጃዎች ራስን መጠበቅና ማጋለጥ ይገባል። በምርጫው ውጤት ላይ ቅሬታ ቢኖር እንኳ የመጠያቂያው መንገድ ተመቻችቷል። በዚህ የምርጫ ሂደት ከምርጫው ፍትሐዊነት አኳያ የተከናወኑ ተግባሮች በሀገራችን ያለፉት ምርጫዎች ጨርሶ ያልታዩ ናቸው። በቦርዱ ውሳኔ ላይ ክስ የመሰረቱ ወይም ቅሬታ ያቀረቡ ፓርቲዎች ፍትህ ሲያገኙ ተመልክተናል። ይህ ደግሞ ብትከስ ምን ታመጣለህ የሚለው የቀድሞው አሠራር አሁን ላይ ታሪክ ሆኖ መቅረቱን ይመሰክራል።
በዛሬው ዕለት የመላው ዓለም ዓይንና ጆሮ ኢትዮጵያ ላይ ነው። ስለሆነም ድምፃችንን ይመራናል ላልነው ዕጩ በመስጠትና ምርጫውን ዓለምን ባስደመመ መልኩ በማጠናቀቅ ጠላቶቻችን እንደተለመደው ውርድት እንዲከናነቡ፣ ወዳጆቻችን ደግሞ አንጀታቸውን እንዲያርሱ ማድረግ ይኖርብናል። ይህን በማድረግም በምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለመላው ዓለም ማሳየት ይገባናል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013