ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ምርጫ ነው። ምርጫ ዜጎች ይበጀኛል፤ ይወክለኛል ፤ ችግሮቼን ይቀርፍልኛል፤ ሰላምና ድህንነት ያረጋግጥልኛል፤ ልማትና ብልጽግና ያጎናጽፈኛል ብለው ለሚያምኑበት ፓርቲ ወይም ተወካይ ድምፃቸውን የሚሰጡበት ሂደት ነው።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 38 በተደነገገው መሰረትም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያውያን አምስት ምርጫዎችን አካሂደዋል። ስድስተኛውን ምርጫ ለማካሄድ ትኩረታቸውን ሁሉ ምርጫው ላይ አድርገው ከርመዋል። ዕለቱም ደርሶ ምርጫው ሊከናወን የአንድ ቀን ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። በነገዋ ታሪካዊ ዕለትም ኢትዮጵያውያን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚያስተዳድሯቸውን መሪዎቻችውን ይመርጣሉ።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በ673 የምርጫ ክልሎች የሚደረግ ሲሆን ፣ ለዚህም ሲባል 49,407 የምርጫ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል። ከ37 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ በላይም ተመዝግቦ ምርጫውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ህዝብ ቁጥር በላይ የሆነው ይህ መራጭ የሀገሪቱን ዕጣ ፋንታ የመወሰን አቅም አለው። በምርጫው የተመዘገበ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ካርዱ ዋጋ መኖሩን የሚያረጋግጠው ነገ በሚሰጠው ድምፅ ነው።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ በዓይነቱ የተለየ ነው። ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፤የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች እንደሚሳተፉበት የሚታመንበትና ለወደፊቱ የሀገሪቱ የምርጫ ክንዋኔዎችም እንደመስፈንጠሪያ የሚያገለግል ታሪካዊ ምርጫ ነው።
በዚህ ታሪካዊ ምርጫ መሳተፍ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት በርካታ ችግሮች እንድትወጣና በአዲስ የዴሞክራሲ መሰመር ውስጥ እንድትገባ የሚደርግ ነው። በምርጫው መሳተፍ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጭም ሊያፈራሩሷት ከሚመኙ ጠላቶች ለማዳንም ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ይታመናል።
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት። የኑሮ ውድነት፤ ሥራ አጥነት፤ የጸጥታ ችግር፤ጽንፍ የወጣ ብሄርተኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት የመሳሰሉ ችግሮች የተደራረቡባት ሀገር ነች። እነዚህ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙና ሀገሪቱና ህዝቧ ባለፉት ዓመታት ከገቡባቸው ችግሮች እንዲላቀቁ ምርጫው ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል። ከዚሕ የተነሳም በዚህ ምርጫ መሳተፍ ሀገራችን ከእነዚህ ችግሮች ለመታደግ መፍትሔ የመሆን ያህል ይቆጠራል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በመንታ መንገድ መካከል አልፋለች። በአንድ በኩል ህውሓትና ጀሌዎቹ ከውጭ ባዕዳን ተልዕኮ በመቀበል ሀገሪቱን ለማመስ እና ሁከት ማዕከል ለማድረግ ሲጥሩ ከርመዋል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እሳትን በመለኮስ ዜጎች በማንታቸው እንዲጠቁ፤ እንዲገደሉና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ ለውጡ ስር እንዳይዝ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውለዋል።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በሚለኩሷቸው እሳቶች የዜጎች ህይወት በከንቱ እንዲጠፋ በማድረግ ህብረተሰቡ እንዲማረርና በመንግሠት ላይ እምነት እንዲያጣ በማድረግ ሀገሪቱ እንዳትራጋጋና እንድትፈርስ በርካታ ሴራዎች ሲሸረቡ ቆይተዋል። ሦስቱ ሰኔዎች በማለትም የተለያዩ የሴራ ወጥመዶች በማዘጋጀት ሀገሪቱን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት ያለመታከት ሠርተዋል።
በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ወደ መኮላሸት ደረጃ ደርሶ የነበረውን የህዳሴ ግድብ በአዲስ መልክ የግንባታ እና የሃይድሮ ሜካኒክ ሥራው እንዲፋጠን በማድረጓ የተበሳጩ ሀገራት ኃያላን ሀገራትን ጭምር በማሰለፍ የኢትዮጵያን ልማት ለማደናቀፍ ፍላጻቸውን ወርውረዋል። አልሳካ ሲላቸውም በባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ በመጣል የኢትዮጵያ ህዝብንና መሪዎቿን ለማንበርከክ ዛቻና ማስፈራርያቸውን አሽጎድጉደዋል።
በአሜሪካና በአውሮፓ ሳንባ የሚተነፍሱትን ሚዲያዎች በማሰለፍ የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። ሆኖም ግን አስተዋይ፤ለሉአላዊነቱ ቀናኢ፤አይበገሬ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት በሀገሪቱ ላይ የተቃጡ ሴራዎችን በማምከን በምርጫው ዋዜማ ላይ ደርሰናል።
ከእነዚህ ሁሉ ጫናዎችና መከራዎች ጎን ለጎንም የሀገሪቱን የወደፊት ተስፋ የሚያመላክቱ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። በአስገራሚ ፍጥነት ፕሮጀክቶች ተሠርተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀርበዋል። በሀገር በቀል የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በመመራትም ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ የውጭ ንግድ አድጓል ፤ቴሌን የመሳሰሉ ተቋማት በከፊል ለግል ባለሀብቱ በማዘዋወር ሀገሪቱ ከውጭው ዓለም እኩል በቴክኖሎጂ እንድትራመድ መሰረት ተጥሏል። ወደ ጠፈር ሳተላይት በማምጠቅም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ውስጥ አሻራዋን ማሳረፍ ጀምራለች።
በአጠቃላይ ሀገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከገባችበት የሁከተና የትርምስ አዙሪት ውስጥ ለመውጣትና የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ የልማትና ዴሞክራሲ ተግባራትን መሰረት ለማስያዝ በነገው ዕለት የሚካሄደው ምርጫ የማይተካ ሚና አለው። ይህንን እውነታ በአግባቡ በሰከነ አዕምሮ በመረዳት ዜጎች የወሰዱትን የመራጭነት ካርድ በመጠቀም ሀገሪቱን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 ቀን 2012 ዓ.ም