የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ15 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በከተማዋ ሰባት ሜጋ ፕሮጀክቶችን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለአገልግሎት ለማዋል ከያዘው ዕቅድ 70 በመቶ መድረሱንና ቀሪው በ2014 በጀት አመት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
ተጠሪነቱ ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቶቹ በተመደበላቸው ጊዜና ገንዘብ እንዲከናወኑ በተያዘው ዕቅድ መሠረት 24 ሰአት በመሥራት አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አፈጻጸማቸውን 70 በመቶ ማድረስ ተችሏል። በከፊልም ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረግ የተቻሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡በተያዘው የሥራ ባህልም ቀሪዎቹ ሥራዎች በ2014 በጀት ለማጠናቀቅ የግንባታ ስራው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡
ሁለት ዋና ተልዕኮች ተሰጥቶት ከ2012ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባው ጽህፈት ቤቱ በተለይም በግንባታ ዘርፉ ከሚያከናውናቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች የእግረኛ መንገድን ጨምሮ የመስቀል አደባባይ፣የታላቁ ቤተመንግሥት የመኪና ማቆሚያና ሁሉንአቀፍ ግንባታ፣የማዘጋጃ ቤት ዕድሳት፣ በትራንስፖርት ዘርፉ የአንድ መስኮት መስጫ ማዕከል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንስቲትዩሽናል አካዳሚ፣ ቤተመጽሐፍት፣ አድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ጽህፈት ቤቱም አፈጻጸማቸውን በመከታተል፣በመቆጣጠርና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
ከሜጋ ፕሮጀክቶቹ በቅርቡ የተመረቀው መስቀል አደባባይ ከዚህ ቀደም በሥፍራው ያልነበሩ ከአንድ ሺህ 300 በላይ የመኪና ማቆሚያ፣ከአንድ መቶ በላይ መታጠቢያና ከ20 በላይ መፀዳጃ ቤቶች፣ 30 የንግድ ሱቆችን የያዘና እነዚህ ሁሉ 24 ሰአት አገልግሎት ሲሰጡ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሥራቸው እንዳይስተጓጎል ከግንባታው ጋር ጀኔሬተር አብሮ መሟላቱን ነው ያስረዱት። አደባባዩ ለእይታም ማራኪ እንዲሆን፣ለጥላና ለመነፋሻ አየር የሚሆን የአበባ ማስቀመጫ ሥፍራዎችም አብሮ መመቻቸቱ እንዲሁም በተመሳሳይ ከዩኒቲ ፓርክ ጋር በዋሻ ተገናኝቶ እየተከናወነ ያለው ባለአራት ወለል ያለው ግንባታ ከአንድ ሺ በላይ መኪኖችን ለማቆም የሚስችል ሲሆን በውስጡም መገበያያና መዝናኛ ማካተቱን ከሥራ አስኪያጁ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይዘቱን ሳይቀይር በመከናወን ላይ ያለው የማዘጋጃ ቤት ህንፃ እድሳትም በከፊል የተጠናቀቀው ክፍል ዘመናዊ መልክ የያዘ መሆኑ አገልግሎት ለሚሰጠውም ሆነ ለተገልጋዩ ምቾት በሚሰጥ መልኩ መደራጀቱ፣ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር በድልድይ እንዲገናኝ ተደርጎ የኪነህንፃ ጥበቡን ጠብቆ የከተማ ገጽታውን በሚለውጥና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ መታሰቡ፣በተመሳሳይ ሌሎችም አንዱ ከሌላው ጋር እንዲገናኝ ተደርገው በመከናወን ላይ ያሉት በአይነታቸውም በይዘታቸውም የተለዩ የፕሮጀክቶች ግንባታ የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን እንደስሟ አበባ የማድረግ ቁርጠኝነት ማሳያዎች መሆናቸውን የትላልቅ ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሽመልስ ያስረዳሉ ፡፡ በግንባታ ዘርፉ የተሰማሩት አብዛኞቹ የውጭ ዜጎች ቢሆኑም ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎችም አብረው እንዲሰሩ መደረጉ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ እንዲጎለብት ማስቻሉም የፕሮጀክቶቹ ሌላው ጥቅም መሆኑን ነው ያስረዱት ፡፡
ነባር ግንባታዎችን በማስፋፋትና በማሻሻል የከተማ አስተዳደሩን በሚመጥን መልኩ በመከናወን ላይ ያለው የሜጋ ፕሮጀክቶች ሥራ የከተማዋን ነዋሪም ቀልብ እየሳበና ተስፋም እያሳደረ መሆኑን ከአንዳንዶች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡
አለማመስገን ንፉግነት መሆኑን በመጥቀስ ባዩት የፕሮጀክት ግንባታና አፈጻጸም መደመማቸውን ከገለጹት መካከልም በከፊል የእድሳት ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በበቃው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትና ካቢኔ ጉዳዮች ቢሮ ኤክስኪዩቲቭ ሴክረተሪ ወይዘሮ አይናዲስ መኮንን ናቸው። መጥፎ ጠረን፣ ፍሳሽና በኮምፖርሳቶ የተከፋፈለ ክፍል፣በአጠቃላይ ለእይታም ለጤናም ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ባለጉዳዮችም እየተቿቸው ለስራም ባለጉዳይ ለማስተናገድም ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ረጅም አመት መሥራታቸውን ያስታውሳሉ ፡፡
ወይዘሮ አይናዲስ የዛሬ ሁለት ወር የሚሰሩበት ቢሮ ከአመት እድሳት በኃላ ሲያዩትና ሥራ ሲጀምሩ የነበራቸው ስሜት መግለጽ ከሚችሉት በላይ ፍጹም የተለየ ሆኖ ነው ያገኙት፡፡ በፊልም የሚያዩትን የተለያዩ ሀገራት የሥራ ቦታ እስኪመስላቸው ድረስ መደመማቸውን ይገልጻሉ። ከተሰራ የማይቀየርና የማይቻል ምንም ነገር እንደሌለም የተገነዘቡበትና ለራሳቸውም ልምድ የወሰዱበት ነው። በንጹህ ቦታ መሥራት የሥራ ተነሳሽነትን ይጨምራል፣ አዕምሮንም ይቀይራል፤ ተስተናጋጁም አገልግሎት ለሚሰጠው የመንግስት ተsማትና ባለሙያ ክብር ይኖራቸዋል ሲሉ ይናገራሉ ፡፡ አጠቃላይ የእድሳት ሥራው ሲጠናቀቅ የውብ አዲስ አበባ ከተማ ተምሳሌት እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል፡፡
ሌላዋ ቦሌ አራብሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መአዛ መንግሥቱ እና በንብ ባንክ በጥበቃ ሥራ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሪት ሙላቷ አበበ፤ የአዲስ አበባ ከተማን ውብ ለማድረግ በአጭር ጊዜ በተሰራው ሥራ መደነቃቸውን ነው የገለጹት ፡፡ ‹‹ቀድሞ ተሰርቶ ቢሆን የከተማዋ ዕድገት የት በደረሰ ነበር›› ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ፡፡ተተኪው ትውልድ ንጹህና ውብ በሆነች ከተማ ውስጥ ሲማርና ሲሰራ በሀገሩ ጥሩ ተስፋ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ብዙ መጽዳት ያለባቸው የከተማዋ አካባቢዎች መኖራቸውንና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ሲበቁ የሚሰጡት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት ቀጥሎ የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ በዚህ ረገድም የከተማዋ ገጽታ ብቻ ሳይሆን፣ዜጎች በሚፈጠርላቸው የሥራ ዕድል ኑbቸው ይለወጣል፡፡ በፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሥራ ብቻ ከስምንት ሺህ ዘጠኝ መቶ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ሲጠናቀቁ ደግሞ የበለጠ ለተለያየ የስራ ዕድል ምቹ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ከተማዋ ስታድግና የሰዎች ኑሮ መለወጥ ሲጀምር የሰዎች አእምሮም አብሮ በመቀየር ፖለቲካው ላይ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ አቶ ሽመልስ ያስረዳሉ ፡፡
በመከናወን ላይ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከልም የእግረኛ መንገድ ሥራን ጨምሮ ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት ያለው ተመርቆ ለአገልግሎት መዋሉን፣የማዘጋጃ ቤት የዕድሳት ሥራም በከፊል መጠናቀቁንና የሌሎችም ግንባታዎች አፈፃፀም አበረታች ነው በሚባል ደረጃ ላይ እንደሆነ የጠቆሙት ኢንጂነር ሽመልስ ለአፈጻፀሞቹ መፋጠን እየተለወጠ የመጣው ለነገ የማይባል የሥራ ባህል ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡
ለአብዛኞቹ ግንባታዎች በመሀል ከተማ ውስጥ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የትራፊክ ፍሰቱን ተቋቁመው መከናወናቸው ፣ የግብአት አቅርቦት ፣ የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታና ለሌሎችም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ለግንባታ አስተዳደር ትምህርት የተገኘባቸው ተሞክሮዎች እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ፣ውብና ዘመናዊነትን የተላበሱ ፕሮጀክቶች ናቸው። ከፈጠሩት የስራ ዕድልና የከተማ ልማት በተጨማሪ ለነዋሪው የአይን ማረፊያ መሆን ችለዋል። በቀጣይም የከተማው ድምቀት፣ የቱሪስት መስህብና የገቢ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ነዋሪው አእምሮውን የሚያሳርፍበት፣ ንጹህ አየር የሚቀበልበት፣ የሚዝናናበት፣ እውቀት የሚገበይበት… ለኑሮ ምቹና ተመራጭ እንደስሟ አበባ የሆነች ከተማ የማድረጉ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013