መኖሪያ ቤት ለዜጎቿ ተደራሽ ማድረግ ፈተና የሆነባት አዲስ አበባ ዛሬ ችግሩ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተረዳችበት ወቅት ይመስላል። ለዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያየ መንገድ የቤት ልማቱን ሊያቀላጥፉና የዜጎችን የዕለት ተዕለት ጥያቄ ሊመልሱ የሚያስችሉ በርካታ የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮጀክቶች በከተማ አስተዳደሩ ሲወጠኑ ተመልክተናል። ከውጥኖቹ መካካልም በህገወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን እጅግ ለተቸገሩና ለአቅመ ደካሞች ከመስጠት ጀምሮ በቤት ልማት ፕሮጀክቶች ልምድ ያላቸውን የውጭ አልሚዎች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመጋበዝ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ቤቶች ለመገንባት እያደረገ ያለው ጥረት ይጠቀሳል።
የበርካታ ዜጎች የዕለት ተዕለት ሰቀቀንና ምሬት የሚገለጽበትን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለልም ከተለመደው ውጪ በሆነ መንገድ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የግድ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል። እኛም በዚሁ አምዳችን ባለሙያዎቹ መፍትሔ ናቸው ያሏቸውን እና ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራቸው ያሉ ሥራዎችን ስናቀርብ ሰንብተናል።
በዛሬው ዕትማችንም ለመኖሪያ ቤት ችግር ትርጉም ያለው ምላሽ ለመስጠት ከገባባት ቆፈን ተላቆ ባለፉት ሁለት የለውጥ ዓመታት ብቻ ከ12 እስከ 14 ወለል የሚረዝሙ ስምንት ብሎኮችን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች አስገንብቶ ለምርቃት ያበቃውን የፌዴራል ቤቶች ልማት የሥራ እንቅስቃሴን ለመዳሰስ ወደናል።
ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ የህንጻ ግንባታ ቴክኖሎጂን በመከተል የግንባታ ጥራት ያላቸውን በአይነታቸው ልዩ የሆኑ የመኖሪያና የንግድ ሱቆችን በአዲስ መልክ አስገንብቶ ብቅ ካለ ሰነባብቷል። በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው ተግባራት እጅግ አበረታች ከመሆናቸው በላይ ለቀጣይም ትልቅ ተስፋን ማስታጠቅ የቻለ ተግባር ሆኗል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቅርቡ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ሥራ የገባው ሲሆን የሪፎርም ሥራ ሰርቶ በተሰማራበት የቤት ልማት ዘርፍ ያስመዘገበው ፈጣን ዕድገት ይበል የሚያሰኝ ነው። ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአይነቱ እጅግ የተለየና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን እጅግ በፈጠነ የግንባታ ጊዜ ለመገንባት ባደረገው ጥረት ከሰሞኑ ከመልካም ጅምሮቹ መካከል የተወሰኑትን መመልከት ተችሏል። ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች አስር ሳይቶች ላይ ከሁለት ሺ በላይ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
በከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነትን ጭምር ወደ ሥራው የገባው ኮርፖሬሽን ግንባታን በጀመረበት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአስሩ ሳይቶች መካካል በአሁን ወቅት የአራቱን ሳይቶች ግንባታ በተለየ የጥራት ደረጃና የቤቶች ስፋት ግንባታውን አጠናቅቆ ለምረቃ አብቅቷል። በዋናነት ቤቶችን የመገንባት፣ የማከራየትና ገቢ የመሰብሰብ፣ የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች በአግባቡ የመጠበቅና ግብዓቶችን የማቅረብ ተልዕኮ ተሰጥቶት የሚሰራ ተቋም ነው።
ይሁን እንጂ ለበርካታ ዓመታት እነዚህን ተግባራት ትርጉም ባለውና ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ሲያደርግ አልታየም። በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ በአዲስ መልክ እራሱን አደራጅቶ ወደ ሥራ በገባበት ቅጽበት ተጨባጭ ለውጦችን በማስመዝገብ ውጤት ማምጣት ችሏል።
በከተማዋ የሚስተዋለውን ውስብስብ የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ከመሰረቱ መቅረፍ እንዲቻልም ኮርፖሬሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የተቋሙን ተልዕኮ መሸከምና ማስፈጸም የሚችል መዋቅራዊ አደረጃጀት በመፍጠር፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት፣ በህግ አግባብ የኮርፖሬሽኑን ቤቶች የመጠበቅ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን የመዘርጋት፣ አዳዲስ የሕግ ማዕቀፎችንና ማኑዋሎችን በማዘጋጀት እንዲሁም ነባሮቹን በመከለስ የአሰራር ሥርዓቱን የማጠናከር ሥራ ሰርቷል።
በቤቶች አስተዳደር የተመዘገቡ ውጤቶችን በተመለከተም ኮርፖሬሽኑ የቤቶች ቆጠራ በማከናወን የህዝብና የመንግስት ሀብት የሆኑ የቤቶችን ቁጥርና አይነት፣ የሚገኙበትን አድራሻ፣ የተጠቃሚ አይነት፣ የገቢ መጠን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን አደራጅቶ በመያዝ እና ዘመናዊ በማድረግ ለውሳኔ አሰጣጥ አመቺ ሆኗል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የኮርፖሬሽኑ የሀብት መጠን ለማወቅ በገለልተኛ አካል በማስጠናት የቤቶቹ ዋጋ 71 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተረጋግጧል። ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚስችለውን ከ99 በመቶ በላይ ካርታ አውጥቷል። ያለአግባብ ከኮርፖሬሽኑ እጅ ወጥተው የነበሩ ቤቶችንም ማስረጃ አሰባስቦ በህግ አግባብ 18 ቤቶችን ከ40 ዓመት በኋላ ወደ ኮርፖሬሽኑ መመለስ ችሏል። ይህም ለቤት ልማት እጥረቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
ኮርፖሬሽኑ ታድያ ላለፉት 28 ዓመታት መደበኛ ሥራው የሆነውን የንግድና የመኖሪያ አፓርትመንቶች ግንባታን ወደ ጎን በመተው ድባቴ ውስጥ ገብቶ ከርሟል። ይሁንና ከሶስት ዓመታት ወዲህ የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ከገባበት ድባቴ በመንቃት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከምንም ተነስቶ በተጨባጭ መሬት መውረድ የቻሉና አበረታች ሥራዎችን ሰርቶ አሳይቷል። ከተሰሩት ሥራዎች መካከልም k2B+G+10 እና 3B+G+10 አንስቶ እስከ 3B+G+21 እንዲሁም በሀገሪቱ አዲስ በሆነ ቴክኖሎጂ በገርጂ አካባቢ የተገነባው ሰፊ የመኖሪያ መንደር ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ለበርካታ ዓመታት ከመደበኛ ሥራው ተገልሎ በከተማዋ ሥር ለሰደደው የመኖሪያ ቤት እጥረት መፍትሔ ካለመስጠቱ በተጨማሪ እሴት ሳይጨምር ነባር ቤቶቹን ብቻ በማስተዳደር ከሁለት አስርት አመታት በላይ የተጓዘው ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ወደ ቀደመው ተግባሩ ተመልሶ ይበል የሚያሰኝ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በቅርቡም ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ካስገነባቸው የመኖሪያና የንግድ ህንጻዎች መካከል ስምንት ብሎኮችን ማስመረቅ ችሏል።
ለምረቃ የበቁት ቤቶችም በአዋሬ፣ ቶታል ተዘንአ ሆስፒታል፣ መካኒሳና ቦሌ ሳይቶች የተገነቡ አራት የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች፣ እንዲሁም ገርጂ ሁለት ህንጻዎች በጥራት፣ በጊዜ፣ በወጪ፣ በአይነታቸው፣ በስፋታቸው ወዘተ ከተለመደው የቤት ልማት ግንባታ በተለየ ሁኔታ የተገነቡ ናቸው። የተለየ እንዲሆን ካደረጋቸው ሁኔታዎች መካከልም የዕቃ ማስቀመጫ እስቶሮች፣ የጋራ መጠቀሚያ ቦታዎች፣ የሰራተኛ ክፍል ከመታጠቢያና ከመጸዳጃ ቤት ጋር መያዙ፣ የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣ የህጻናት ማቆያ ቦታዎች፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች፣ በቂ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የኢንተርኔት መስመሮች፣ የጋራ ማጠቢያ ክፍሎች፣ መጠባበቂያ ጀነሬተሮች፣ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ፣ ለእያንዳንዱ ሳይት ራሱን የቻለ የመብራት ትራንስፎርመር ያላቸው መሆናቸው የቤቶቹ ልዩ ባህሪያት ሲሆን፤ ቤቶቹ ባለ ስድስት መኝታ ክፍሎች መሆናቸው ሌላው መለያቸው ነው።
ከእነዚህ ቤቶች በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ለአቅመ ደካሞች አገልግሎት መስጠት የሚችሉ 50 መኖሪያ ቤቶችን ገርጂ አካባቢ እየገነባ ሲሆን በአሁን ወቅትም 26 መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለርክክብ ዝግጁ ሆነዋል። ኮርፖሬሽኑ ያስገነባቸው አጠቃላይ የመኖሪያ ህንጻዎች በከተማዋ ስር ሰዶ የቆየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል የላቀ ድርሻ አለው። የመኖሪያ ቤት እጥረቱን ከማቃለል ባለፈም ከ5000 በላይ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ግንባታዎቹ በራሳቸው ለአካባቢዎቹ ከሚሰጡት ውብት በተጨማሪ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታን ያበረክታል።
ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ እጅግ ዘመናዊና ጥራታቸውን የጠበቁ የመኖሪያ እንዲሁም የንግድ አፓርትመንቶችን ባጠረ ጊዜ እየገነባ ይገኛል። አጠቃላይ በአስር ሳይቶች ላይ ከሁለት ሺ ቤቶች በላይ ለመገንባት አቅዶ በእንቅስቃሴ ላይ ያለው ኮርፖሬሽን በመጀመሪያ ምዕራፍ አራት ሳይቶችን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ችሏል።
በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ትርጉም ባለው መልኩ ለማቃለል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የግድ መሆኑን ያመነበት ኮርፖሬሽኑ እጅግ ባጠረ ጊዜ ጥራት ያላቸውን ቤቶች ገንብቶ ማሳየት ችሏል። ይህም በሀገሪቷ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተስፋፋ ለመጣው የመኖሪያ ቤት እጥረት ሁነኛ መላ ስለመኖሩ አመላካች ነው። ለዚህም ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች አስገንብቶ ለምረቃ ያበቃቸው የመኖሪያ ቤቶች ዋቢ ምስክሮች ናቸው።
ኮርፖሬሽኑ በዋናነት ነባር የሆኑትን የመንግስት የኪራይ ቤቶችን ጨምሮ በራሱ ይዞታ ላይ አዳዲስ ግንባታዎችን በመገንባት በተለይም የፌዴራል መስሪያ ቤት ሰራተኞች ማዕከል በማድረግ እየሰራ ያለበት ሁኔታ አለ። ይሁንና ኮርፖሬሽኑ በአሁን ወቅት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ቤቶችን እያስገነባ ባለበት ፍጥነት በቀጣይ በርካታ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳለው ከወዲሁ ያመላክታል። በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ባለው ይዞታ ሥር የሚገኙ ሰፋፊ መሬቶችን በመጠቀም የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህም የኮርፖሬሽኑን ገቢ በማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ኮርፖሬሽኑ የሚገነባቸው አፓርትመንቶች እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ በመሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በኩልም ተሞክሮዎችን እያሰፋ ይገኛል። ለአብነትም በገርጂ እያስገነባ ያለው እጅግ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የአዲሱ ትውልድ የግንባታ ቴክኖሎጂ እየተባለ የሚጠራው የ‘Aluminum Formwork system’ ሲሆን ጊዜንና ወጪን የሚቆጥብ፣ ጥራትን የሚጨመር አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂ ነው። ይህም የግንባታ ኢንዱስትሪውን ሊቀይረው እንደሚችልም ይታመናል።
ኮርፖሬሽኑ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ በምዕራፍ አንድ አጠናቅቆ ካስመረቃቸው የመኖሪያና የንግድ ህንጻዎች በተጨማሪ ገርጂ የመኖሪያ መንደርን ጨምሮ በምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት የጀመራቸው የመካኒሳ፣ የአዋሬ፣ የቦሌና የቅዱስ ጊዮርጊስ ግንባታዎችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ክትትል እያደረገ ይገኛል። ግንባታቸው ሲጠናቀቅም ኮርፖሬሽኑ እየገጠመው ያለውን የመኖሪያና የንግድ ቤቶች የኪራይ አቅርቦት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቃልል ከመሆኑም በላይ የሚገነቡት ቤቶች የኮርፖሬሽኑን የሀብት መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምሩ ይሆናል።
ኮርፖሬሽኑ የመጪው ዘመን ተስፋዎችን በውል በመረዳት በቤት ልማትና አስተዳደር ዘርፍ መሪ ተቋም ለመሆን ያስቀመጠው ራዕይ እውን የሚያደርጉ ተግባራትን ከጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ጋር በማስተሳሰር ነገን ዛሬ የመገንባት ተግባርን በቀጣይ ዕቅድ በተያዘላቸው የቤት ግንባታ ምዕራፎችና የቤት ልማት ፕሮግራም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
የፋይናንስ አቅምን ከማሳደግ አንጻር ከነበረበት ሶስት መቶ ሚሊዮን በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ መሰብሰብ እንዲችል ሆኗል። ገቢውም መልሶ ለልማት እንዲውል የተደረገ ሲሆን ከልማት በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ባደረገው ጥረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ግማሽ ቢሊዮን የሚገመት ወጪ በማድረግ ሀገራዊ ለሆኑ የልማት ሥራዎች፣ ድጋፍ ለሚሹ አካላትና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለተጎዱ ተከራይ ደንበኞች የኪራይ ቅናሽ በማድረግ ለማህበረሰቡ እፎይታን ሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪም ለአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የመኖሪያ ቤቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ባጠረ ጊዜና በከፍተኛ ጥራት 50 ቤቶችን በራሱ ይዞታ ገንብቶ ለማስረከብ ባቀደው መሰረት በአሁን ወቅት 26 ቤቶችን ገርጂ አካባቢ ገንብቶ ለወረዳው አስረክቧል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013