እንሆ ኢትዮጵያ በተፋፋመ ምጥ ውስጥ ናት:: ምርጫው በሰላም ተጠናቆ፤ ውጤቱ ተገልፆ፤ ፓርቲዎች የህዝቡን ውሳኔ እና የምርጫውን ውጤት በፀጋ ተቀብለው መስከረም ደርሶ መንግስት እስኪቋቋም ያልጓጓ ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት ያጠራጥራል:: የ2013 አገር አቀፍ ምርጫ ሊከናወን ሁለት ቀናት ብቻ ቀሩት:: አሁን የጥሞና ጊዜ ነው:: አዎ ጥሞና ያስፈልጋል:: ከጥሞናው በፊት በፋና ቴሌቪዥን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጨረሻ ዙር የማጠቃለያ ክርክር መድረክ በአንድነት ፓርክ ተካሂዷል::
በክርክሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣ ብልፅግና፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ፣ ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተሳትፈዋል:: የጥሞና ጊዜ በመሆኑ ማን ምናለ የሚለውን ለማለት አይፈቀድም:: የእነርሱን ሃሳብ ማስተዋወቅ አልፈለግኩም:: ነገር ግን መጨረሻ ላይ የቀረበው ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ቢሆንም ፓርቲዎች ግን ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም ነበር:: ይህ እኔን ጨምሮ በአንድ ላይ የፓርቲውን ክርክር ስንከታተል የነበርን ሰዎችን ድንጋጤ ውስጥ ከቶን ነበር::
‹‹ጥያቄው ኢትዮጵያ በእናንተ እጅ ውስጥ ናት:: የህዝቡን በድምፅ የሚገለፅ ውሳኔ ፓርቲያችሁ ይቀበላል?›› የሚል ነበር:: መልሳቸው ግን በሚያሳዝን መልኩ ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሁሉም ግራ የተጋባ ነበር:: ገና ሳይወዳደሩ የምርጫውን ውጤት ላለመቀበል ማንገራገር ምን ለማለት ይሆን? ጥያቄው ራሱ አገራችሁ በእጃችሁ ናት፤ ውጤቱን በፀጋ ከተቀበላችሁ ሰላም ትሆናለች:: ውጤቱን በፀጋ ካልተቀበላችሁ የከፋ አደጋ ይጋረጥባታል የሚል መልዕክት ያዘለ ነው:: እነርሱ እንደ አንድ አገር እና ህዝብ ወዳድ አገር ለመምራት የተዘጋጀ ፓርቲ የሚፈልጉት አገር ችግር እንዳይገጥማት መጠንቀቅ መሆን ሲገባው፤ ምላሻቸው ‹‹ምርጫ በዕለቱ የሚሰጥ ድምፅ ላይ ብቻ የተመሰረተ ሳይሆን ቅድመ ምርጫን የያዘ ሂደት ነው:: የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ችግር ነበረበት፤ ስለዚህ የምርጫውን ውጤት ለመቀበል የምንወስነው ወደ ፊት ነው::›› በሚል ያለፈውን በመናገር የተጠየቁትን ጥያቄ በቅጡ ሳይመልሱ ያለፉ አሉ:: ይሄ አካሄድ ‹‹ ይህቺ ጠጋ ጠጋ…›› የሚያስብል አይነት ነው::
ተወዳዳሪ አይፈራም:: የሚፈራ እና የፈራ ፓርቲ መወዳደር የለበትም:: ገና ለገና እሸነፋለሁ በሚል ስጋት ብሸነፍ ደግሞ ምርጫው ችግር አለበት በሚል ለመውቀስ እንዲመቸው እና አሁን ላይ ምርጫውን በፀጋ እቀበላለሁ ማለቱ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም በሚልበት ወቅት ማጣቀሻ ሆኖ እንዳይቀርብበት መጠንቀቁ ያሳቅቃል:: እሸነፋለሁ የሚል ስጋት ውስጥ መሆኑንም ያመለክታል:: ያው መቼም ‹‹ያሰቡት ይሆናል::›› ይባል አይደል:: ያው እኔም ያሰቡት ይሆንባቸው ከሆነ የሚሆነው እንደሚያሰጋ ገምቼ ነው::
አንድ ፓርቲ ብቻ አይደለም:: ሌሎችም ፓርቲዎች የተጠየቁት ሌላ የሚመልሱት ሌላ ነበር:: ‹‹የምንሰራው ለኢትዮጵያ ጥቅም ነው›› በሚል በቀጥታ የምርጫውን ውጤት በፀጋ እቀበላለሁ ከማለት ይልቅ ግራ የሚያጋባ መልስ የሰጠ አለ:: በተመሳሳይ መልኩ ሌላኛውም ኢትዮጵያ በእናንተ እጅ ውስጥ ናት:: የህዝቡን በድምፅ የሚገለፅ ውሳኔ ፓርቲያችሁ ይቀበላል? በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ‹‹እኛ የምንሰራው ለነፃነት እና ለዕኩልነት ነው::›› በሚል ቀጥተኛ መልስ ሳይሰጥ በደፈናው ጥያቄውን አልፎታል:: ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ ለቀረበው ጥያቄ ግልፅ እና ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ‹‹ግባችን ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ኢትዮጵያ እንድትሻገር ነው›› በሚል ህዝብ የሚጠብቀውን እና የጓጓለትን ሃሳብ ሳይገልፁ አደፋፍነው አልፈውታል::
እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላምን አጥብቀን እንሻለን:: የምንፈልገውም በህዝብ የተመረጡ ፓርቲዎች እንዲመሩን ብቻ ነው:: የምርጫ ውጤትን አልቀበልም በሚል ምክንያት አገር እንድትበጠበጥ አንፈልግም:: ‹‹የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም›› ይባል አይደል:: በቅርብ በአፍሪካ አገራት የምርጫን ውጤት በፀጋ አለመቀበል ምን ያህል አገርን አለመረጋጋት ውስጥ ከመክተት አልፎ አገር እንደሚያፈርስ አይተናል:: ስለዚህ ፓርቲዎች የፓርቲ ደጋፊዎች እና መላው ኢትዮጵያውያን ምርጫውን በሚመለከት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው:: በተለይ ፓርቲዎች በክርክር መድረኩ ላይ እንዳሳዩት ዓይነት ማንገራገርን በማጠናከር የእነርሱን ክፍተት ወደ ደጋፊያቸው አልፎ ወደ ህዝብ ካስገቡት አደጋው የከፋ ይሆናል:: ስለዚህ እባካችሁ ፓርቲዎች ‹‹አገር ለመገንባት እየተወዳደርን ነው›› ብላችሁ አገር ለማፍረስ አትንደርደሩ::
6ኛው አገር አቀፍ ምርጫን ተሸንፋችሁ ቢያልፍም፤ ከአምስት ዓመት በኋላ 7ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ስለሚደርስ በዛ ጊዜ ደግሞ የተሻለ ዕድል የምታገኙበት ሁኔታ ስለሚፈጠር የግድ የዛሬን ካላሸነፍኩ ሞቼ እገኛለሁ በሚል አገርን አደጋ ላይ አትጣሉ:: አገር ለመምራት ከሚነሳ ፓርቲ የሚጠበቀው ትዕግስት እና አርቆ አሳቢነት ነው:: ጠላት ላሰናዳው ድግስ ማዳመቂያ ከመሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል::
አዎ! ለተረዳው አሁን ላይ አገር በተፋፋመ ምጥ ውስጥ ናት:: ምጥ ላይ የሆነች እናት በሰላም መገላገሏ ለልጆቿ ትልቅ ስኬት ነው:: በምጥ ሳቢያ ከሞተች ልጆችም በቅጡ አያድጉም፤ እየተገፉ፤ እየተሰደቡና እየተኮረኮሙ ተዋርደው የማንም መጫወቻ ይሆናሉ:: ኢትዮጵያን በገዛ ጥፋታችን አናጥፋት:: ልጆቿ የማንም መጫወቻ እንዲሆኑ አሳልፈን ለአውሬ አንስጣት::
ኢትዮጵያ ከ110 ሚሊየን በላይ ህዝቦች ያሏት፤ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፤ የማደግ ተስፋዋ እንደአፍና አፍንጫ የተቀራረበ ቢሆንም መጠንቀቅ ያሻል:: ምክንያቱም የህዝብ ብዛቷ እና የተፈጥሮ ሃብቷ ትልቅ ፀጋዎች ቢሆኑም፤ መጥፊያ መርዞቿ ሊሆኑም ይችላሉ:: እንደህዝቡ ብዛቷ የተለያየ አስተሳሰብ እና እምነት ይኙበታል:: ይሄ ልዩነት በመጥፎ መልኩ እንዲጎለብት ከተደረገ ቤንዚል ተርከፍክፎ እሳት ከተጫረ የሚሆነው ያስፈራል:: ስለዚህ ፓርቲዎች ቤንዚል ከማርከፍከፍ እና እሳት ከመጫር መጠንቀቅ የሚጫሩ እሳቶች ካሉም በጥንቃቄ እንዲጠፉ ማድረግን ወቅቱ ይጠይቃል::
በተፈጥሮ ሃብት መታደሏም በአንዳንዶች ዘንድ ባለመወደዱ እና ኢትዮጵያ ድሃ እንደሆነች እንድትቀር በመፈለጉ ይህ በራሱ የወቅቱ ትልቅ ፈተና መሆኑ አያጠያይቅም:: አገሪቱ በተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትጠቀም የሚፈልጉ ሃይሎች አገር በምርጫው ምክንያት ተበጠበጠች እንዲባል ብቻ ሳይሆን እንድትበጠበጥም አጥብቀው የሚፈልጉ በመሆኑ ፓርቲዎች ማሰብ እና ማስተዋል አለባቸው:: ይህ ማለት የኢትዮጵያን ውድቀት የሚሹ ለዛም ለማመቻቸት የሚሰሩ ሃይሎች ሥራቸውን የሚሰሩት በቀጥታ ጦርነት በማወጅ ሳይሆን እኛኑ ኢትዮጵያውያኑን በመጠቀም ሊሆን እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል:: ጠላት ግለሰብን በጥቅም በመደለል ሊያማልል እና ሊያሳምን የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል:: ሁሉም ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ቀድሞ ማሰብ ይጠበቅበታል:: በተለይ ከተወዳዳሪ ፓርቲ መሪዎች እና እጩ ተመራጮች እንዲሁም ከመላው የተወዳዳሪ ፓርቲ አባላቶች እና ከደጋፊዎች አስተዋይነት የሚፈለግበት ጊዜ ነው:: ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2013