አገራችን ኢትዮጵያ ናይል ለሚባለው የዓለም ረጅሙ ወንዝ በጥቁር ዐባይ አማካኝነት 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታዋጣ ናት። ይሁን እንጂ የታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት በዋናነት ግብጽና ሱዳን ለናይል ምንም አይነት አስተዋጽኦ ሳያደርጉ የወንዙ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆነው እልፍ አዕላፍ ዓመታት ቆይተዋል።
በተለይ ግብጽ ለናይል ወንዝ አንድ እፍኝ ውሃ አስተዋፅኦ ሳታደርግ በላይኞቹ የናይል ተፋሰስ (የናይል ወንዝ ምንጭ በሆኑ) አገራት ላይ የምትሰነዝረው ዛቻና ማስፈራሪያ የሚያስገርም ነው። ግብጽ የምትባል እፍረት የለሽና ይሉኝታቢስ አገር የናይል ወንዝ ብቸኛ ባለቤት እንደሆነች በመግለጽ በወንዙ ላይ የዘመናት ብቸኛ ተጠቃሚነቷን የሚነካ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቀሴ ቢደረግ የደም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነች በተለያዩ አጋጣሚዎች ስትገልጽና ስትዝት መስማት የተለመደ ሆኗል።
ሆኖም ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ክልል ውስጥ በሚገኝ በጥቁር ዐባይ ላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በ2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ላይ ጀምራ ያለማንም የውጭ ድጋፍ በራሷ የገንዘብ ምንጭ ግድቡን አሁን ላይ ከ80 በመቶ በላይ ማድረሷ ይታወቃል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት መርህን አንግባ በሉዓላዊ ግዛቷ ክልል ውስጥ እየገነባች ያለችው ግድብ ቢሆንም ቅሉ ለዘመናት ብቻዋን መብላት የለመደችው ግብጽ በተለይ የግድቡ የውሃ ሙሌት ተሞልቶ ከመጠናቀቁ በፊት ታሪካዊ የውሃ ድርሻየ ካልተከበረ የግድቡ የውሃ ሙሌት በመቃብሬ ላይ ይሁንብኝ በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች ትገኛለች። በአንጻሩ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ውል ሳይሆን በፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት መርህ ወንዙን እንጠቀም የሚል አቋም ይዛ እያራመደች ትገኛለች። ውድ አንባቢዎቻችን ይህ ጉዳይ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር እንዴት ይታያል የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በዚህ ጽሁፋችን ለመዳሰስ እንሞክራለን።
ስለ ዐባይ ወንዝ የተፈረሙ ስምምነቶች
የዐባይ ወንዝን በተመለከተ የመጀመሪያው ስምምነት የተፈፀመው እ.ኤ.አ በ1891 ጣሊያን ከእንግሊዝ ጋር ያደረገቸው ስምምነት ሲሆን፤ ጣሊያን በአትባራ ወንዝ ላይ ግድብ ላለመስራት የተስማማችው ነው። ሁለተኛው ስምምነት ደግሞ እ.ኤ.አ በ1902 በእንግሊዝ እና በአፄ ሚኒልክ የዐባይ ወንዝን የሚደፍን ነገሮችን የሚከለክል ቢሆንም፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ መንግስታት የዘውድ ምክር ቤት በኩል ስላልፀደቀ ተቀባይነት የለውም።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላፀደቀችው የእንግሊዝኛው እና የአማርኛው ትርጉም የተለያዩ በመሆናቸው ነበር። ግብፅ ታሪካዊ መብቶቼ ለምትላቸው መነሻ የሆኑት ስምምነቶች ደግሞ በግብፅና በሱዳን መካከል እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 ለላይኛውና ለመካከለኛው ተፋሰስ ሀገራት አንድ ጠብታ ውሃ ሳያስቀሩ ሙሉ በሙሉ ለረሳቸው የተከፋፈሉበት ነው። እንግሊዝ ከሌሎች የቅኝ ገዥ ሀገራት ጋር ያደረገችው ስምምነቶችም አሉ። በአብዛኛው በስምምነቶቹ የአንበሳውን ድርሻ የወሰደቸውም ግብጽናት። ይሁን እንጂ እነዚህ ስምምነቶች የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመሆናቸው የአፍሪካ ህብረትም የማይቀበላቸው ስምምነቶች ናቸው።
ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረት የተቀበለው ስምምነት የድንበር ስምምነትን ብቻ ነው። እ.ኤ.አ በ1978 በቬና በፀደቀው ኮንቬሽን መሰረትም ሀገራት ከቅኝ ግዛት ሲላቀቁ መውረስ ያለባቸው ድንበር እንጂ ሌሎች መብቶችን እና ግዴታዎችን እንዳልሆነ ያስቀምጣል።
የኢትዮጵያ አቋምና ዓለም አቀፍ የህግ ተቀባይነቱ
የናይል ወንዝ ትልቁ ድርሻ አመንጪ ኢትዮጵያ ናት። የናይል ወንዝ የውሃ መጠን የጥቁር ዐባይ ውሃ ካልተጨመረበት ጥቅሙ ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለዚህ ውሃው የላይኛው፣ የመካከለኛውና የታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት እንጂ የግብፅና የሱዳን ብቻ አይደለም። በመሆኑም ግብጽ በዐባይ ወንዝም ሆነ በናይል ወንዝ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ብቸኛ ተዋናይ መሆን የለባትም፤ ይሄንንም ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ብሎም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዟት ይገባል።
ከዚህ አኳያ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 21/1997 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለመጓጓዣነት የማይውሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም አስመልክቶ ባወጣው ኮንቬንሽን መሰረት፤ የወኃ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን በሚጠቀሙበት ጊዜ የእኩል (ፍትሐዊ) አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ መርህን በዋነኝነት መከተል እንዳለባቸው ያስቀምጣል።
የአፍሪካ ህብረት የስምምነት ስነድም በአንቀጽ 3 እና 4 ላይ መገንዘብ እንደሚቻለው የህብረቱ መሰረታዊ ዓላማዎችና መርሆች የአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የአባል ሀገራት አንድነትና ትብብርን ከመጠበቅ ባሻገር ሀገራት በልዑዓላዊ ግዛታቸው የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት ዕውቅና የሚሰጥ እና የሚፈቅድ ነው።
በሌላ በኩል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 1 እና 2 ላይም በተመሳሳይ መልኩ የድርጅቱ መሰረታዊ ዓላማዎችና መርሆች የተደነገጉ ሲሆን፤ በአባል ሀገራት መካከል በሁሉም መስኮች እኩልነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።
ስለሆነም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብጽና ሌሎች የዐባይ ተፋስስ ሀገራት የዐባይን (የናይልን) ወንዝ ውሃ እና የውሃ ሀብቶች በእኩልነትና በፍትሐዊነት በጋራ መጠቀም ይችላሉ። ነገር ግን ግብጽ የናይል ወንዝ ብቸኛ ባለቤትና ተጠቃሚነኝ በማለት ኢትዮጵያና ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት አይጠቀሙም በማለት ፍትሐዊ የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍልን የሚቃረን ስራ እንድትሰራ የሚፈቅድ የሀገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ህግ የለም።
በቬና የቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 11 እና 34 ላይ እንደ ተመለከተው በሀገራት መካከል የሚከናወን ማንኛውም አይነት ስምምነት ፍላጎት ባልገለጹ ሀገራት ላይ አስገዳጅነት እና ተፈፃሚነት የለውም። በተለይም የስምምነቱ አንቀጽ 34 ድንጋጌን ስንመለከተው በአንድ ውል ላይ አንድ ሀገር ነፃ ፍላጎት ካልገለጸች የምታገኘው መብትም ሆነ የሚጣልበት ግዴታ አይኖርም። ኢትዮጵያም በሌለችበት በተደረጉ ስምምነቶች ተገዥ አትሆንም በእርሷ ላይ ተፈፃሚነትም የላቸውም። ምክንያቱም በመርህ ደረጃ አንዲት ሀገር በግዛት ክልሏ ላይ ፍፁም የሆነ የሉዓላዊነት ስልጣን አላት። ስለዚህ ዐባይ የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ ከዚህ አንፃርም መታየት አለበት።
ኢትዮጵያ በግዛት ክልሏ ስር የሚገኝ ማንኛውንም ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ የመጠቀም መብት አላት። በአንድ ወቅት ቱርክና አሜሪካ የሌሎቹን ተፋሰስ ሀገራት በሚጎዳ መልኩ ተጠቅማችኋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው የሉዓላዊነት መብት መጠቀማቸውን እንጂ የጣሱት ዓለም አቀፍ ህግ እንደሌለ መከራከሪያ ነጥብ አቅርበው ነበር። ይህም ከፍጹማዊ የግዛት ሉዓላዊነት ኃልዮት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሆኖ “የሀርሞን ቀኖና የሚል ስያሜ” አግኝቶ ነበር። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የምትመርጠው በእኩልና በፍትሐዊነት በስምምነት (በድርድር) እና በመተባበር ተጠቃሚነትን ነው።
ይህ አቋሟ ከዓለም አቀፍ ህጎች አንፃርም ሲታይ ትክክለኛ አቋም ነው። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ የዐባይን ወንዝ በሉዓላዊ ግዛቷ ስር ስለሚገኝ ብቻ ከመካከለኛውም ሆነ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ተለይቼ የተፋሰሱን ውሃ ለብቻየ መጠቀም አለብኝ የሚል አቋም የላትም። ይልቁንም በጋራ የመጠቀምና የመልማት የሚል አቋም ነው ያላት። ለዚህም ነው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዲጸድቅና በማጽደቅ ረገድ ኢትጵያ ትልቁን ድርሻ የተወጣችው። በመሆኑም ኢትዮጵያ የዐባይ ውሃን በፍትሀዊና ምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም መርህዋን አጠናክራ በማስቀጠል የጀመረችውን ትብብር አጠናክራ ማስቀጠል አለባት።
ምንጭ:- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013