ኢትዮጵያ የራሷን ነጻነት አስጠብቃ ከመኖሯና ለሌሎችም የነጻነትና ተስፋ ምድር ከመሆኗም በሻገር አፍሪካዊያን የራሳቸውን ውሳኔ ካለማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው እንዲወስኑና በአንድ ላይ ሆነው ድምጻቸው እንዲሰማ ያደረገች የአፍሪካ ብርሃን ነች። መላው አፍሪካ በከፍተኛ ችግር ውስጥ በነበረበት ዘመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተችና እስከ አፍሪካ ህብረት ምሰረታም ድረስ በግንባር ቀደምትነት የዘለቀች ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ የውጭ ሀገራትን ጣልቃ ገብነት አምርራ በመቃወምና ሉዓላዊነቷንና ነጻነትዋን አስጠብቃ በመጓዝ ዛሬም እንደትላንቱ ታሪክ በመስራት ላይ ትገኛለች። የተለያዩ ፈተናዎች ቢጋረጡባትም መንግስቷና ህዝቦቿ ሉዓላዊነታቸውን ላለማስደፈር ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ባዕዳን ጋር እልህ አስጨራሽ ግብግብ በማድረግ ላይ ናቸው።
የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ የውጭ ኃይላት የተለያዩ ሴራዎችን በመጠንሰስ ግንባታውን ለማደናቀፍ ያልቆፈሩት ድንጋይ የለም። ኢትዮጵያ ሰላሟ እንዲናጋና የሁከት ማዕከል እንድትሆንም በውስጥ ለሚንቀሳቀሱ አጥፊ ኃይሎች የገንዘብና የቁስ ድጋፍ በማድረግ ግንባታው እንዲስተጓጎል ለማድረግ ሞክረዋል። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡን እንደዓይኑ ብሌን የሚጠብቀው በመሆኑ የጥፋት ሃይሎች ምኞት ቀቢጸ ተስፋ ሆኖ ቀርቷል። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ትኩረታቸውን ህዳሴ ግድብ ላይ አድርገዋል።
የኢትዮጵያን ውድመትና መፈራረስ ሁልጊዜም የሚመኙት የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ባዳዎች ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ከወዲሁ ለማጠልሸትና ተቀባይነት ለማሳጣት በየቀኑ የጥቃት ቀስታቸውን እየወረወሩብን ይገኛሉ። አንድ ጊዜ ምርጫው ዝቅተኛውን የምርጫ መስፈርት አያሟላም በሌላ ጊዜ ብሄራዊ መግባባት ሳይደረግ ምርጫ መካሄድ የለበትም የሚሉ ማወናበጃ ሃሳቦችን በማምጣት ምርጫውን ለማጠልሸት ሲሯሯጡ ከርመዋል። አሁን አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምርጫውን ለማካሄድና የራሳቸውን የወደፊት ዕጣ ፋንታ በራሳቸው ለመወሰን መቁረጣቸውን ሲያውቁ ምርጫው በመካሄዱ ላይ ተቃውሞ የለንም ሆኖም ግን የራሳችንን የኮሚኒኬሽን መሳርያ ይዘን ገብተን ምርጫውን እንድንታዘብ ይፈቀድልን የሚል የሀገሪቱን ሉኣላዊነት የሚፈታተን ጥያቄ ይዘው ብቅ ብለውም ነበር። ሆኖም ግን በሉዓላዊነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎባቸዋል።
በተለያዩ ጫናዎች የህዳሴውን ግድብ ማስተጓጎል እንደማይሆንላቸው ያመኑት እነዚህ የውጭ ሃይሎች ምርጫውን ተገን በማድረግ ሀገሪቱን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ከወዲሁ አታሟቸውን በመደለቅ ላይ ይገኛሉ። በተለይም በድህረ ምርጫ ወቅት በተቃዋሚ ስም የሚንቀሳቀሱ ግብረአበሮቻችውንና ባንዳዎችን ከጎናቸው በማሰለፍ ሀገሪቱን ወደ ትርምስ በመክተት ኢትዮጵያውያን ከጀመሩት የልማት ጎዳና እንዲደናቀፉ በዛቻና በማስፈራርያ ጭምር ጫና በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን ኢፍትሃዊነትን የመመከት የቆየ አኩሪ ባህልና ታሪክ ያላቸው ህዝቦች በመሆናቸው ለዚህ ጫናና ማስፈራሪያ የሚንበረከኩ አይደሉም። ታሪክ ህያው ነውና የዛሬ ትውልዶችም እንደትላንቱ ለጋራ ጥቅም መቆምን እና ኢፍትሃዊ አካሄዶችን መቃወምን ብሎም ታግሎ ማሸነፍን ከትላንት የወረሱት ባህላቸው ነውና ዛሬም ሆነ ነገ ትግሉ ይቀጥላል።
ለኢትዮጵያ ህልውናና ክብር የምንቆም ኢትዮጵያውያን የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ባዕዳዎች በምርጫ ስም ሀገሪቱን ለማተራመስ ቆርጠው መነሳታቸውን በመረዳት ከወዲሁ ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርብናል። ለማንም ግልጽ ሊሆን የሚገባው ነገር ቢኖር ምርጫው የኢትዮጵያውያን መሆኑና የምርጫውንም ውጤት መወሰንና መበየንም የሚችሉት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነው። ስለዚህም የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳይ ውስጥ በመግባት ምርጫውን ብሎም ሀገሪቱን ለማወክ የሚያደርጉትን ዕኩይ ተግባር ኢትዮጵያውያን በጽኑ የሚቃወሙት ነው። ምርጫው የኢትዮጵያውያን ነውና ሂደቱንም ውጤቱንም ሉዓላዊ ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊተውለት ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2013