ለምለም መንግሥቱ
‹‹የአትክልት ሥፍራ የጥበብ ማዕከል›› ይላል ርዕሱ። በርዕሱ ሥር የተሰጠው ማብራሪያም ‹‹የአትክልት ሥፍራ የጥበብ ማዕከል ፤ ከቤት ውጪ የሥነጥበብ አውደርዕይ እና የባህል ለውውጥ ማከናወኛ ቦታ ነው። በውስጡም አንድ ድንኳን የተወጠረ ሽፋን መተላለፊያ አለው። ማዕከሉ ያረፈበት ቦታ በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ካሬ ሜትር ይሆናል። የመተላለፊያ ኮሪዶር ከፍታው ስድስት ነጥብ አምስት ሜትር ሲሆን፣16 ሜትር ርዝመት እና 800 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መጠለያ ነው። ቦታው የቡና ሥነ-ሥርዓት፣ የዕደጥበብ ገበያዎች፣ የሥነ ዐውደ ርዕዮች የሚከናወኑበት የአትክልት ሥፍራና ከተማ ማስጌጥ ሥራዎችን የሚያስተዋውቅ ነው። የወዳጅነት አደባባይ፣የእንግዳ መቀበያ እና የባህል ልውውጥ ማዕከል በመሆንም ያገለግላል። ልዩ የባህል ምርቶችን የያዘና ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የሚገናኙበት መድረክ ነው›› ይላል። በወዳጅነት ፓርክ ውስጥ የጎብኝዎች ቦታ መግለጫ ላይ የተወሰደ ነው።
ልዩ ስሜት የሚፈጥሩ፣የመንፈስ እርካታ የሚሰጡ፣ አዕምሮን የሚያረጋጉ፣ ዕይታን የሚስቡ፣ የተለያዩ ዕፅዋቶችና ቀልብን የሚስቡ አበባዎች፣ ውሃ በአጠቃላይ ልምላሜ በወዳጅነት ፓርክ ውስጥ ይታያል። ያዝናናል። ለማስታወሻም ፎቶ ያስቀራሉ። በቴሌቪዥን መስኮት የምናየውና በሥፍራው ተገኝተው የጎበኙትን በአድናቆት ከነገሩን ሰዎች በአዕምሯችን ከሳልነው የሌሎች ሀገሮች የፓርክ ይዞታና አገልግሎታቸውን እዚሁ በሀገራችን ማየት ብቻ ሳይሆን መጠቀም ጀመርን። ‹‹ዕድሜ የሰጠው ብዙ ያያል›› አይደል።
በፓርኩ ውስጥ የሚታየው ልምላሜ እንዲህ ለማስደመም ምስጢሩ አንድና አንድ ነው። ‹‹ለምለሟ ሀገሬ›› ተብሎ የተዘፈነላት ኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት የደን ሀብቷ ተራቁቶና ለዓይናችን አረንጓዴ እስኪናፍቀን ድረስ ተመናምኖ የነበረው ልምላሜ እንዲመለስ መደረጉ፣ሌላው ጥበቃና እንክብካቤ ተደርጎለት ባማረ ሁኔታ አረፍ ብለው የሚዝናኑበት፣ጥሩ አየር የሚያገኙበት ቦታ መመቻቸቱ፣ለከተማዋ ገጽታ መለወጥና የተስተካከለ ሥነምህዳር መፈጠሩ ለየት ያደርገዋል። እንዲህ እንደ ወዳጅነት ፓርክ ሰፋ ያለ፣በውስጡም የተለያየ አገልግሎት መስጫ ያለው ዘመናዊ በመሀል ከተማ የለማ ፓርክ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተለመደ ባይሆንም፣በዘመናቸው ለከተማዋ ጌጥ የነበሩ፤ሠርግና የተለያዩ ዝግጅቶችን በማስተናገድ ዘመን የተሻገሩ እንደ ብሄረጽጌ፣ሸገር፣ፒኮክ… የመሳሰሉት መናፈሻዎች ፈርቀዳጅና ለአሁኑ መሠረት መሆናቸው አይዘነጋም።
በወዳጅነት ፓርክ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ እየተዝናናሁ አንዳንድ ነገር ታዘብኩ። ስለፓርኩም የአንዳንድ ጎብኝዎችንም ስሜት ጠየኩ። በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ሳምንት የሚካሄድበት ወቅት ስለነበር የአስሩም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የባህል እሴቶቻቸውን እያስተዋወቁ ሥለነበር ቤተሰብ፣ ጓደኛሞች፣ በትምህርትቤት፣ በቡድንና በግል የጎብኝዎችም ቁጥር ከፍተኛ ነበር። የመስተንግዶ መስጫዎችም እንዲሁ የበዙ ነበሩ።
ጎብኚው ያየውን እያደነቀ ፣ እየበላና እየጠጣ ይዝናናል። ቆሻሻም በዚያው ልክ ይመነጫል። በተወሰኑ ርቀቶች ላይ የቆሻሻ መጣያ ተዘጋጅቷል። ግን ልብ ያለው ሰው አልነበረም። ፓርኩ ገና ብዙ ጎብኝዎችን ያስተናገደ ባለመሆኑ እንኳን ቆሻሻ ለመጣል አረንጓዴውን ሥፍራ ለመርገጥ ያሳሳያል። አንዳንዶች እንዲህ ያለ ስሜት የተሰማቸው አይመስሉም። የውሃ መያዣ ፕላስቲክና የተጠቀሙባቸውን የተለያዩ ነገሮች ሲጥሉ ነበር።ከሥር ከሥር እየተከታተለ የተጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎችን በማንሳትና የመፀዳጃ ቤቶችንም ንጽሕና በመጠበቅ የፅዳቱን ሥራ የሚያከናውን ድርጅት ግን ከስር ከስር ማፅዳቱ ላይ አልቦዘነም። በወቅቱ ሥራውን ሲያከናውን የነበረው ድርጅት ለኢትዮጵያ ሳምንት ብቻ የሚሠራ መሆኑን ነው የተገነዘብኩት። የጎብኝዎችን የጥንቃቄ ጉድለት እንደታዘብኩት በጊዜያዊ የፅዳት ክትትልና ቁጥጥር ብቻ መሆን እንደሌለበት ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝቤያለሁ። የፅዳቱን ሥራ ቋሚ ከማድረግ በተጨማሪ ጎብኝዎች ቆሻሻ በዘፈቀደ እንዳይጥሉና በማስወገጃ ቦታ እንዲጠቀሙ በድምፅ የታገዘ መልዕክት ቢተላለፍ የተሻለ ይሆናል። በተለይ እርጥበት ባለበት ቦታ ቆሻሻ ሲጠራቀም ለጤና ችግር የሚያጋልጥ ብክለት ሊፈጠር እንደሚችል ፓርኩን የሚያስተዳድረው አካል ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል።
በፓርኩ ውስጥ ሲጎበኙና በኢትዮጵያ ሳምንት ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር በነበረኝ ቆይታ የሁሉም ምላሽ ‹‹ደስ ብሎናል›› የሚል ነበር። በተለይም ተማሪዎቻቸውን ሲያስጎበኙ የነበሩ ትምህርትቤቶች ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ለአረንጓዴ ልማት ቦታ ሰጥተው ችግኝ እንዲተክሉ፣ተገቢውን እንክብካቤም እንዲያደርጉና በቀጣይ ለሥራው እንዲነሳሱ ለማስቻል ወደ ሥፍራው እንደወሰዷቸውና ተማሪዎችም በሃሳቡ እንደሚስማሙ ነበር ያነጋገርኳቸው መምህራኖቻቸውና ተማሪዎች የነገሩኝ።
የፍሬህይወት ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ስፖርት መምህር መሐመድ ናስር፤ ፓርኩን ተማሪዎች እንዲጎበኙት በግላቸውም ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው።ስለፓርኩ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ባዩ ጊዜ እርሳቸውም ለመጎብኘትና ተማሪዎቻቸውም እንዲያመልጣቸው አልፈለጉም ነበር። ‹‹ወዳጅነት ፓርክን ጎበኙ ማለት ኢትዮጵያን ሙሉ እንዳዩ ይቆጠራል። በተለይም የኢትዮጵያ ሳምንት መሆኑ ደግሞ የበለጠ ልዩ ስሜት ይሰጣል። ዕውቀትም ይቀስማሉ። ተማሪዎቹ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በፈረቃ ስለሚማሩ ጊዜያቸውን ትምህርታዊ በሆነ ጥሩ ቦታ ቢያሳልፉ የተሻለ እንደሆነ ትምህርት ቤቱም አምኖበት ነው ለማስጎብኘት የተነሳሳው›› በማለት አስረድተዋል።
እንደ መምህር መሐመድ ማብራሪያ፤አካባቢውን ከብክለት የሚከላከል፣ በአረንጓዴ ልማት የሚሸፍንና ለአካባቢ ልማት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ዜጋን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ለማፍራት እንዲህ ያሉ ፓርኮችን እንዲጎበኙ ማድረግ ተገቢ ነው። ይሄን ለማበረታታት ደግሞ መንግሥት ተማሪዎች በነፃ ገብተው እንዲጎበኙ ማበረታታት አለበት። አሁን የመግቢያ 50 ብር እና ለተለያዩ ወጪዎች መክፈል የቻሉ ተማሪዎች ናቸው የጎበኙት።
ከፍሬህይወት ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎብኝዎች መካከል ተማሪ የኃላ ዮናስ የተለያዩ ዕፅዋቶች፣ፏፏቴ ውሃ፣ንጹሕ አየር በውስጡ ያለው ፓርክ ስትጎበኝ የመጀመሪያዋ እንደሆነና በቆይታዋም በቴሌቪዥን መስኮት ካየችው በላይ እንደወደደችው ተናግራለች። እርስዋም ሆነች የዕድሜ እኩዮቿ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተገንዝባለች። አካባቢን አረንጓዴ በማልበስ ውብ ቦታ መፍጠር እንደሚቻል ከጉብኝቱ መማር መቻሏን ገልጻለች።
‹‹የምድር በረከት፣የባህልና ቋንቋ ሀብት እያለን ምንም ሳናጣ በዘርና በቋንቋ ለምን እንደምንጣላ አይገባኝም›› በማለት በፓርኩ ውስጥ ባዩት ነገር በመደሰት ስሜታቸውን የገለጹልኝ ሌላዋ ጎብኝ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሠራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ምሥራቅ ጋሻው ናቸው። አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሆነው ግን ወዳጅነት ፓርክ ለጉብኝት እስኪበቃ ድረስ አላዩም። የኢትዮጵያን የባህል እሴቶች የያዘ አረንጓዴ የለበሰ ፓርክ ከዜጎችም ባለፈ ለቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ገቢ በማስገኘት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። ከፓርኩ የሚገኘው ገቢ ብቻ በችግር ላይ ለሚገኙ ዜጎች መተዳደሪያ እንደሚውል ወይዘሮ ምሥራቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የወዳጅነት ፓርክ ዓይነት በከተማዋ እንዲበዙ የአረንጓዴ ልማቱ እንዲጠናከርና እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም በልማቱ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
በፓርኩ ውስጥ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሳምንት የተለያዩ አካባቢዎችንና ክልሎችን የሚወክሉ ባህላዊ፣ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህቦችና የዕደጥበብ ውጤቶች ይዘው ከቀረቡት ክልሎች መካከል የአማራ ክልል አንዱ ሲሆን፣የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ባለሙያ አቶ ሙላት መኳንንት አካባቢያቸውን ይወክላሉ ብለው ያመጧቸውን እሴቶች ያቀረቡበት ቦታ ለእሴቶቹ ማሳያ እጅግ ተስማሚ የሆነና ደስ የሚል እንደሆነ ነው ያስረዱት። ወዳጅነት ፓርክ የለማበት ቦታ ንጽሕናው የተጓደለና ቤተመንግሥቱ በሚገኝበት ቦታ የማይመጥን እንደነበር መረጃው እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ሙላት አካባቢው በአረንጓዴ ተውቦ ኢትዮጵያ ውስጥ ነኝ እስከማለት ያደረሳቸው ድንቅ ለውጥ ማየታቸውን የናገራሉ።
እንደ አቶ ሙላት ገለጻ፤በአማራ ክልል ብዙ የሚያስደስቱና የሚያስደምሙ እንደነላልይበላ፣ራስደጀን ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ። ነገር ግን የማይመችን ቦታ ሰው ሠራሽ በሆነ መንገድ የሚመች ስፍራ በማድረግ ረገድ ወዳጅነት ፓርክ ለእርሳቸው የመጀመሪያ መማሪያ ነው። ተደስተውበታል። በተለይ ምሽት ላይ ውበቱ ልዩ ሆኖ ነው ያገኙት። በተለይም የባህል እሴቶች እንዲህ ውብ በሆነ ቦታ መታየታቸው መስህብነታቸው የበለጠ እንዲጨምር ያደርጋል። በመሆኑም የወዳጅነት ፓርክ ልማቱ ተጠብቆ ከየአቅጣጫው የሚመጣው ማህበረሰብ እንዲጠቀምበት ማድረግ እንደሚገባና ተጠቃሚውም በአግባቡ ጠብቆ የፓርኩ የአገልግሎት ጊዜ እንዲረዝም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል።
ሌላው ሃሳባቸውን ያካፈሉን አቶ እንዳለ ወልዳማኑኤል ይባላሉ። የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስፖርት ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው። አካባቢው የነበረውን ይዞታ ከሌሎች ከሰሙት መረጃ ውጪ አያውቁትም። በኢትዮጵያ ሳምንት አጋጣሚ በማየታቸውና ስለአካባቢው መመስከር መቻላቸው አስደስቷቸዋል።‹‹ከስሜት በዘለለ መልዕክትም ጭምር አለው። ከተሠራ የማይለወጥ ነገር እንደሌለ ወዳጅነት ፓርክ ማሳያ ነው›› ብለዋል።
በእርሳቸው ምልከታም አንድነት ፓርክ በሁሉም ነገር የተደራጀ ነው። ከልምላሜው በተጨማሪ በውስጥ የተለያዩ የአገልግሎት መስጫዎች፣ ባህላዊ መገለጫዎች፣ በአጠቃላይ ሀገራዊ ነገሮችን የያዘ ለጎብኝዎች ምቹና ሳቢ የሆኑ ነገሮች መካተታቸው ትምህርትም የሚገኝበት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል።
ከረዩ ደበላ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ መሆኑን የነገረኝ ወጣት ቦሩ ፈንታሌ የአካባቢውን ባህል፣ታሪክና የተፈጥሮ እሴቶች ለሌላው ለማቅረብ በሥፍራው ቢገኝም እርሱም ከዚህ ቀደም ለማየት ዕድል ያላገኘውን የፓርክ ልማት ለማየት በመቻሉ ተደስቷል። ብዙ ነገሮችን በአንድ ቦታ በማመቻት፣ብዛት ያላቸው ሰዎች የሚጎበኙት የአረንጓዴ ልማት ቦታ በማየቱም ትምህርትም እንዳገኘበት ይናገራል። እንዴት እንደተሠራና በማን እንደተሠራ ጭምር በመጠየቅ ግንዛቤ ማግኘት ችሏል። የአረንጓዴ ልማት አስፈላጊነትን ቢገነዘብም ብዙ ነገሮችን የያዘ በአንድ የተከለለ ቦታ ይኖራል ብሎ ግን አልጠበቀም። ሌሎችም የአካባቢው ወጣቶች እንደርሱ የመጎብኘት ዕድል ቢያገኙ ምኞቱ ነው።
ወዳጅነት ፓርክ ለመዝናኛነት ከመዋል ባለፈ ለአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ መለወጥና ለአካባቢ ስነ ምህዳር መጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ ይታመናል። አዲስ አበባ ከተማ በዙሪያዋ ከከበቧት ኢንዱስትሪዎች የሚወጣው ጭስና የተለያየ ብናኝ ለብክለት ተጋላጭ እንደሆነች በተደጋጋሚ ተነግሯል። ከኢንዱስትሪ የሚወገዱትን ጨምሮ ከተሽከርካሪ የሚወጣ ጪስ የመተንፈሻ አካልን ጨምሮ የተለያየ የጤና እክል በማስከተል ሰዎችን፣እንስሳትንና ዕፅዋትንም እንደሚጎዳ እንዲሁ በተለያየ ጊዜ የተነሳ ጉዳይ ነው።በመሆኑም እንደ ወዳጅነት ፓርክ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በአዲስ አበባ ከተማ ሊጠናከሩ ይገባል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን እንደስሟ አበባ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ጥረቱ ውጤታማ እንደሚሆን ነዋሪዎቿ ይጠብቃሉ። የለማውን መጠበቅና መንከባከብ እንዲሁም አካቢን ንጹሕ በማድረግና ለልማቱ በመተባበር ደግሞ ነዋሪዎች የውዴታ ግዴታ እንዳለባቸው መዘንጋት አይገባም። ሁሉም ነገር እንደታሰበው ያማረና የተሳካ የሚሆነው ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ሲችል ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013