ፍትሐዊነት ሰብዓዊ እሴት ነው ፣ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የተሰጠው ፍጥረታዊ ጸጋም ነው። ስለሆነም ፍትሐዊነት ከዘር እና ከሃይማኖት በላይ የሆነና ከወገንተኝነትና ከመንደርተኝነትም ያለፈ ዓለምአቀፋዊ እሴት ነው። በተለይ ባለንበት ዘመን ፍትሐዊነት የሰው ልጆች በዘመናት ከሄዱበትና ብዙ ዋጋ ካስከፈላቸው መንገድ መመለስ የሚያስችል ትልቁ አቅም ነው።
ዓለም ባለፉት ሺ ዓመታት ፍትህ አልባ በሆኑ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቡ በወለዳቸው ግብሮች ከፍያለ ዋጋ ለመክፈል ተገዳለች። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰው ልጆች በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች በተዛባ ፍትሕና መዋቅራዊ በሆነ ኢፍትሐዊነት ለሞት፣ ለእንግልትና ከፍ ላሉ ስቃዮች ተዳርገዋል።
የሰው ልጆች ሰብዓዊ እሴቶች በራስ ወዳድነትና ባልተገባ ወገንተኝነት ተጠልፈው ፤ ሰውነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ተግባራት በየዘመኑ ተፈጽመዋል። ጥላቻ በወለደው ጽልመት ሚሊዮኖች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ማን አለብኝነትና እብሪት በወለዳቸው ጦርነቶች ሚሊዮኖች ለህልፈት ተዳርገዋል። ሀገራትም ፈርሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቡድን ተጠቃሚነት እና ልዕልና በተገመዱ ሴራዎች ዋጋ ያልከፈለ ማህበረሰብ የለም። በአንድም ይሁን በሌላ ሁሉም ከፍ ያለ ዋጋ ከፍሏል። የትናንት ሕይወቱ ጠባሳዎች የቱንም ያህል የጠፉ ቢመስሉም ታሪክ ግን ሊረሳው የሚችላቸው እውነታዎች አይደሉም።
ስለ ፍትሕ ያልጮኸ ማህበረሰብ የለም ፤ ስለፍትህ የጮሁባቸው ዓመታት የቱንም ያህል የራቁ ቢመስሉምና አሁን ያለው እውነታ ትናንቶችን የረሳ ቢሆንም ስለፍትህ የሚጮሁ ጩኸቶች ዘመናት ተሻጋሪ ድምፆች ናቸው። ለእነዚህ ድምፆች ቦታ ያለመስጠት የሚያስከፍለው ዋጋም የፍትህ ያህል ከፍያለ ነው።
ዛሬያዊ እውነታዎች ላይ ቆሞ ለፍትሕ ጆሮ መንፈግ ሊያስከፍለው የሚችለው ዋጋ የነገ ባለተራ እንደሚያደርግ ከትናንት ታሪኮች መማር ይገባል። በቀደመው ዘመን ፋሽስቶች ኢትዮጵያን በወረሩበት ወቅት በሊግ ኦፍ ኔሽን እንደ ሀገር
ያቀረብነው የፍትሕ ጥያቄ ሰሚ ያጣበት ሁኔታ የቱን ያህል ኢፍትሐዊነት ዋጋ እንደሚያስከፍል ዓለም ያስተዋለበት ነው።
ኢፍትሐዊነትን በየትኛውም የአስተሳሰብ መሰረት ላይ ቆሞ ለመሸከም መሞከር በየትኛውም የሀገራት ሆነ የማህበረሰብ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ አትራፊ ሆኖ የተገኘበት ወቅት የለም። ያተረፈ የመሰለበት የታሪክ ምዕራፍም ቢሆን ከመጀመሪያው የሁለተኛው ስህተት እንደሚባለው ጊዜ ጠብቆ በብዙ ኪሳራ መወራረዱ የማይቀር ነው።
በእብሪት፣ በማናለብኝነትም ሆነ በግዴለሽነት ከዚያም በላይ ከፍ ባለ ራስ ወዳድነት ለፍትሕ ጥያቄዎች ጆሮ መንፈግ በራስ ላይ ኢፍትሐዊነትን የመጥራት ከፍ ያለ ስህተት ነው። የሚያስከፍለውም ዋጋ ለፍትሕ ከሚጮኸው ድምፅ የሚተናነስ ስለመሆኑ ማስተማመኛ አይኖረውም። ማንም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የዘራውን ማጨዱ ፍጥረታዊ ህግ ነው።
ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን፤ ከዛም አልፈን እኛ ትናንት ላይ ሆነን የከፈልነውን ዋጋ ዛሬ ላይ ሆነው ለሚከፍሉ ሕዝቦች የብርሃን ጮራ ሊፈነጥቅ በሚችል የመንቃትና የመቆም ፤ ከዚያም አልፈን የመሄድና የመሻገር መንገድ ላይ እንገኛለን። ይህ በዘመናት መካከል በነበሩ አባቶቻችን የተጸነሰ የመሆን ተስፋ ዛሬ ስጋና ደም ለብሶ ህያው ተስፋ ሆኗል።
ይህ ህያው የሆነ የተስፋ ጽንስ ድንገት የተፈጠረ ሳይሆን ከብዙ መከራና ስቃይ ፤ከብዙ መነሳትና መውደቅ ፤ ከብዙ ቁዘማና ቁዘማ ከወለደው ግራመጋባት ውስጥ በዘመናት መካከል የተጸነሰ ነው። ብዙ ዋጋ የተከፈለበትና በብዙ ዋጋዎች የተሸመነ ነው። ከፍያለ ልዕልናም የሚጎናጽፍ በትውልዶች መካከል የተጠበቀ ነው።
ይህ የተስፋ ጽንስ የሚያድገው እንደቀደሙት ዘመናት የሀገራት ልዕልና ሰብዓዊ አሴቶችን በመጨፍለቅ ሳይሆን ሰብዓዊ እሴቶችን መሰረት አድርጎ ነው። ጅማሬውን በይቅርታ፣ በፍቅርና በመደመር ላይ ያደረገውም ለዚህ ነው። ማንንም የመጉዳትም ሆነ በማንም ጉዳት ላይ የሚነሳና የሚሰለጥን አይደለም።
ወዳጅነትን እና ጉርብትናን ፤ ቤተሰብነትን እና ዕጣ ፈንታን መጋራትን ከዚያም በላይ ፍትሐዊነትን መሰረት ያደረገ ነው። እኛ እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገርና ህዝብ ዕጣ ፈንታችንን የመወሰን መብት አለን ፤ ዛሬ ላይ ዕጣ ፈንታችን አገራዊ ብልጽግና ነው ብለን ወስነናል። ይህ ካለን ፍጥረታዊ ቁመና የሚመነጭ ፍጥረታዊ መብታችን ነው። በዚህ መብት መደራደር አመጽም ፤ እርግማንም ነውና አንሞክረውም።
ይህንን መብት ለመገዳደር መሞከር ከፍያለ ሰብዓዊ ወንጀል ነው። በማን አለብኝነት ይሁን በግዴለሽነት ይህንን መብታችንን እየተገዳደሩ ያሉ ሀገራት እየሄዱበት ያለው መንገድ የወንጀል መንገድ መሆኑን በአግባቡ ሊረዱት ይገባል። ወንጀሉ ሊያስከፍል የሚችለውም ዋጋ የወንጀሉን ክብደት የሚሸከም እንደሚሆንም ማሰብ አይከፋም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2013