
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ አበባ፡- ፕሮጀክት ጀምሮ በመጨረስ የማንታማ፣ ያልነውን እስከምንፈጽም የማንተኛ እና ቃል የገባነውን ለመፈጸም በእጅጉ የምንተጋ መሆናችንን በተደጋጋሚ አሳይተናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ጋር ትናንት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፤ እኛ ፕሮጀክት ጀምሮ በመጨረስ የምንታማ አይደለንም። ያልነውን ለመፈጸም የማንተኛ ያልነውን ለመፈጸም በእጅጉ የምንተጋ መሆናችንን በተደጋጋሚ አሳይተናል ብለዋል።
አሁንም መሰረተ ድንጋይ ያስቀመጥንባቸው እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ለዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም ላያልቅ የተጀመረ አንድም ፕሮጀክት እንደሌለ አመልክተዋል።
‹‹በእርግጥ በአሁኑ ሰዓት መጀመር ሳይሆን ማስመረቅ ላይ ነን ያለነው ፤ ይህም ምን አልባት ለምርጫ ነው የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ እኛ ግን ከምርጫ በኋላም ማስመረቁን እንቀጠልበታለን።ምርጫው ሰኞ ነው፣ ከሰኞ በኋላ ያሸነፈው ፓርቲ መንግስት የሚመሰርተው መስከረም መጨረሻ ነው።እስከ መስከረም መጨረሻ እያስመረቅን እንቀጥላለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ምርጫ የይስሙላ ሳይሆን ዜጎች የሚያምኑበት ፣ ትክክለኛ ፣ የሚፈልጉትንና የተሻለ ሃሳብ ያለው ፓርቲ የሚመርጡበት እንዲሆን አስበን እየሰራን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ይሁን፣ የተሻለና ተአማኒ ይሁን የሚለው ዋናው የታገልንበት አንደኛው አጀንዳ ነው።እሱን ማሳካትም የትግሉን ፍሬ ከማየት የሚቆጠር እንደሆነ አመልክተዋል።
ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትመችና ዜጎች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ሰርተው የሚያተርፉበትና ህይወታቸውን የሚቀይሩበት ኢትዮጵያን እንፈጥራለን። ሉአላዊነቷ የተከበረች፣ የተፈራችና የግዛት አንድነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን እናጸናለን ብለዋል።
ብልጽግና ቢመረጥ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት ለማረጋገጥ ዋና ዋና ምሰሶዎች መሰረቶች እንጥላለን ብለን እናስባለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ፕሮጀክት ጀምረን እየጨረስን እንገኛለን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቶች እያረጋገጥን ነው።እነዚህን በተሻለ ደረጃ በምንገባው ቃል ልክ እንፈጽማለን ብለዋል።
ጠንካራ ተቋም ካልተገነባ ኢኮኖሚውንም ሆነ ሰላምን ማረጋገጥ ስለማይቻል ዴሞክራሲንና ጠንካራ ተቋም እንገነባለን። በሚቀጥለው አምስት ዓመት ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት በተለየ ሁኔታ ውስጥ በብዙ መንገድ እድገት እንድታስመዘግብ ለረጅም ጊዜ እድገት በምታመጣባቸው ዘርፎች መሰረት የምትጥልበት ጊዜ ይሆናል። አሁን በጀመርነው አግባብ ከቀጠልን ብዙ ነገሮች መስመር ይይዛሉ የሚል እምነትም ተስፋም እንዳላቸው አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም