
ሞገስ ጸጋዬ
ጭሬ:- በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር መካከል የሚፈጠር ግጭት እንደማይኖር፣ ግጭት የሚፍጥሩ ካሉም አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ የኮማን ድፖስቱ አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ደስታ አቢቼ አስታወቁ።
በሰሜን ሸዋ ዞንና በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ነዋሪዎች የተሳተፉበት የእርቅ ሥነሥርዓት በጭሬ ከተማ ትናንት በተካሄደበት ወቅት ሌተናል ጀነራል ደስታ እንደገለጹት፤ በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር መካከል የሚፈጠር ግጭት አይኖርም፣ ግጭት የሚፍጥሩ ካሉም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል።
የተገኘውን ሰላም ለማስተጓጎል፣ ግጭቶች እንዲቀጥሉ ለማድረግ የጥፋት ሃይሎች የተለያዩ ስልቶችን መንደፋቸውን ደርሰንበታል ያሉት ሌተናል ጀነራል ደስታ ፤ ጠንካራ ክትትል እየተደረገ በመሆኑ ድጋሚ የሚደፈርስ ሰላም እንደማይኖር አስታውቀዋል።
እርቅ ማለት ሰላም፣ ፍቅር፣ ልማት፣ ነጻነት ነው።የምንታረቀው ለስም ብቻ ሳይሆን ለእውነተኝ ሰላምና ፍቅር ነው። እርቁ ሰላም ማስፈን አለበት፣ ጠላቶቻችንን ማሳፈርና የሀገር አንድነትን ሊያጠናክር ይገባዋል ብለዋል።
ግጭት ፈጥረው በሁለቱም ህዝቦች መካከል የተደበቁትን ወንጀለኞች በመጠቆም በህግ እንዲቀጡ ለማድረግ የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ ያመለከቱት ሌተናል ጀነራል ደስታ ፣ የንጹሃን ቤት በማቃጠል፣ እንዲሰደዱ በማድረግ ሀገርን ለማፍረስ የሚሰሩ ሃይሎች በአስቸኳይ እጅ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
‹‹ወንጀል ፈጻሚዎች የት እንዳሉ እናውቃለን። ቀንና ማታ እየተቀያየሩ የሚያድሩበትን ቦታ ሁሉ እናውቃለን። ይህ ሳይሆን በግድ የሚያዙ ከሆነ ቅጣቱ የከፋ ነው›› ብለዋል።
ይህ እርቅ ምቹ ሁኔታን ካልፈጠረ እርቅ አይደለም። እርስ በርስ በመግባባት፣ በመነጋገር እና በመወያየት ወደ ቀድሞው ሰላም እና አንድነት መመለስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አርሶ አደሮች ለሰላም ሲሉ ጠላትን ታግሰዋል። የሁለቱ ዞኖች ህዝብ፣ ጀግና ሰላም ወዳድ በመሆኑ የጠላት ሃይሎች ባሰቡት ልክ እንዳይሳካላቸው ማድረግ እንደቻሉም አስታውቀዋል።
ሌት ተቀን በመስራት የጠፋውን ሰላም በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስፈን መቻሉን ያመለከቱት ሌተናል ጀነራል ደስታ ፣ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ከምንጊዜም በላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ በሰላም ገበያ ወጥቶ እንዲመለስ፣ ቀድሞ የነበረው የንግድ ልውውጥና ትስስር እንዲቀጥል እና የሰላም ንፋስ እንዲነፍስ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት እና የጸጥታ ሃይሉ እየሰራ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች ለዘላቂ ሰላም ወንጀለኞችን በማጋለጥ ማገዝ አለበት ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም