
በጋዜጣው ሪፖርተር
ጅማ ፦ “በምርጫው ዴሞክራሲን እንተክላለን፣ ዛፍም እንተክላለን” መላው ዓለም በምርጫ ቀን ይጋጫሉ ብሎ ሲጠብቅ፤ እኛ ችግኝ ተክለን ፍቅርን እናስተምራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ ።
የጅማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ብልጽግና ፓርቲን በመደገፍ ትናንት ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መልእክት “ መላው ዓለም በምርጫ ቀን ይጋጫሉ ብሎ ሲጠብቅ፤ እኛ ችግኝ ተክለን ፍቅርን እናስተምራለን “ ብለዋል።
የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመርነውን ስራ ለማሳካት የሚያቆም ኃይል የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ይዘን ከኢትዮጵያ አልፈን ለአፍሪካ ብርሃን እንደምናመጣም አመልክተዋል።
በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያን አንድነት ከማስጠበቅ አልፈን የአፍሪካን ቀንድ የአፍሪካ ክንድ ማድረግ ዓላማ ይዘን እየሰራን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከመፍረስ እንድትድን ያደረግናት በአንድነት፣ በህብረትና በመደማመጣችን እንደሆነ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የአፍሪካ ቀንድን የአፍሪካ ክንድ” ማድረግ እንደምንችል አስታውቀዋል።
ከብልጽግና ፓርቲም ይሁን ከሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ ህዝብን የሚሰርቅና የሚያማርር ለአገሪቷም እንደማይጠቅም ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የምትፈልገው ልማቷንና ብልጽግናዋን የሚያረጋግጥ ፓርቲ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በምርጫው የሚፎካከሩ ሃይሎች ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ኢትዮጵያን ለማገልገል የተዘጋጁና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር የሚሰሩ ከሆነ መልካም እንዲገጥማቸው እመኛለሁ ብለዋል።
ጅማ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት መገለጫ ናት።ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር ፈርጥ የሆነች ከተማ እንደሆነች ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በጥቅሉ እንደ ጅማ ውብና አረንጓዴ እንዲሆን ሁሉም ሰው ችግኝ ይትከል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጅማ መገለጫ የሆነችው ባለ ሶስት እግር መቀመጫ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ትርጓሜ እንዳላት ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፤ ለኢትዮጵያ ብሎም ለመላው አፍሪካውያን ሰላምና ብልጽግና ተመኝተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሣ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሰጡት ባለው በሳል አመራር ኢትዮጵያ የተከበረች፣ የአንድነትና የእኩልነት አገር እንድትሆን በጽናት እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በብዙ መሰናክሎች ውስጥ በማለፍም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስና ‘’ድንቅ’’ ብቃታቸውን ማሳየታቸውንም ገልጸዋል።
በጅማው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሣ እንዲሁም ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም