አቤል
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ከወራት በፊት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ ካካሄደ እና የሽብር ቡድኑን ህወሓትን ከደመሰሰ በኋላ በሀገር ውስጥ በጦሩ ግንባር የተሸነፉት የህወሓት ጀሌዎች የጦርነት አውድማውን ወደ ዓለምአቀፉ የዲፕሎማቲክ መድረክ በመውሰድ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውንን ለመበቀል የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ይገኛል።ለዚህ ዘመቻቸው በዋነኝነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጀመረችው ሰላማዊ ግንኙነት ያላስደሰታቸው እና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንድነት ራስ ምታት የሆነባቸው አካላት ፤ የህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ አዲሱን የውጫሌ ውል እንድትፈርምላቸው የሚፈልጉ ኃይሎች ፤ የተዳከመች እና እርስ በርሷ የምትጠላለፍ ኢትዮጵያን ለብሄራዊ ጥቅማችን መከበር አስፈላጊ ናት የሚሉ ኃይሎች እና ሌሎችም በአጃቢነት ከተሸናፊው የጁንታው ሀይል ጋር አብረው ተሰልፈዋል።
የጁንታው ሀይል በጦር ግንባር ያጣውን ድል በዋሽንግተን ኮሪደሮች እና በብራስልስ አዳራሾች ለመቀዳጀት ትግል ላይ ነው። ለዚህም እንዲሆን በአንድ ጎን የፖለቲካ ደላሎችን (ሎቢስትስ) ቀጥሯል። የምእራባውያኑ ሚዲያም በተቻለው መጠን የኢትዮጵያን መንግሥት ለማጠልሸት የሀሰት ዘገባዎችን በመፈልፈል ተጠምዷል። ለዚህ ደግሞ ከዚችው ስሟ ከሚጠፋው ኢትዮጵያ የተዘረፈ በሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር ይከፈላቸዋል። በእርግጥ ይህ ሁኔታ በምዕራቡ ፖለቲካ የተለመደ ነው። በአንድ ጎን በሚዲያዎቻቸው በኩል የማዋከብ እና ስም የማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በፖለቲካ አመራሮቻቸው በኩል የኢኮኖሚ እና የሚሊተሪ ጫና በመፍጠር ሀገራትን እነሱ ለሚፈልጉት አቋም የማስገዛት ታሪክ አላቸው።በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውም ይሄ ነው።የአሸባሪው ጁንታ ደጋፊዎች ደግሞ አሁን እያካሄዱ ያሉት ለዚህ የምእራባውን ጫና ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ነው። ታዲያ እንዲህ አይነቱን በውስጥ እና በውጭ ኃይሎች በቅንጅት በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ እንዴት መግታት ይቻላል ያልን እንደሆነ ከመፍትሄዎች አንዱ እና ዋነኛው ሀገር ወዳዱን ዲያስፖራ ለሀገሩ የሉአላዊነት ዘብ እንዲሆን ማድረግ ማስቻል ነው።
በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ዲያስፖራው እስካሁንም አልሰነፈም። የቅርቡን እንኳ ብንመለከት በትናንትናው እለት በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በሰላማዊ ሰልፍ ለሀገሩ ሉአላዊነት ያለውን አቋም በግልጽ አንጸባርቋል።የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ላከበሩ እንደ ደቡብ አፍሪካ ላሉ ሀገራት ምስጋናውን ቸሯል ፤ ከዚያ በተቃራኒው ለቆሙ ደግሞ እጃቸውን ከሀገራችን ውስጣዊ ጉዳይ እንዲያወጡ አሳስቧል።ከአንድ ቀን ቀደም ብሎም ዲፌንድ ኢትዮጵያ የተሰኘ ቡድን በእንግሊዝ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመሆን በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እና ኤርትራውያንን አስተባብሮ የቡድን 7 ሀገራት ስብሰባ በሚያደርጉባት የደቡብ ምእራብ እንግሊዟ የኮርመንዌል መንደር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ የሚካሄደውን አግባብነት የሌለው ጫና አውግዟል።
ይህ የሚደነቅ ተግባር ነው። መሰል የዲያስፖራ እንቅስቃሴዎች ወትሮውንም በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ የሆነውን የዲያስፖራ ተሳትፎ ወደ አዲስ ከፍታ የሚወስድ ነው። ነገር ግን ከዚህም በላይ የዲያስፖራው ተሳትፎ መጨመር አለበት። ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አንድ ጠቃሚ እርምጃ ነው። ይሁንና ከዚህም ከፍ የሚል ተሳትፎ ይፈለጋል። በተለይም በዲፕሎማሲው ሥራ ላይ መንግሥት እንደ መንግስት እየሰራ ካለው ሥራ በተጨማሪ ዲያስፖራው ያለውን የኢኮኖሚ አቅም በማስተባበር እና ያሉትን የግንኙነት መስመሮች በመጠቀም በፖሊሲ አውጪዎች ላይ ትክክለኛ ግንዛቤ መፍጠር መቻል አለበት።
እስካሁን ከሚታየው ሁኔታ መረዳት የሚቻለው በዋሽንግተንም ሆነ በብራስልስ ያሉ ፖሊሲ አውጪዎች ኢትዮጵያ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንድም ሆን ተብሎ የተንሻፈፈ ሁለትም ከእውቀት ማነስ የሚመነጭ የግንዛቤ ዝንፈት እንዳለባቸው ታይቷል። ከጁንታው ኃይል ጋር በነበራቸው እና ባላቸው ጥብቅ የጥቅም ትስስር የጁንታው ከስልጣን መወገድ የሚከነክናቸው እንዳሉ ሁሉ ለአፍሪካ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ካላቸው አነስተኛ ግንዛቤ አንጻር የሚሳሳቱም ብዙ ናቸው።የተሳሳተ ግንዛቤ ደግሞ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ እና የተሳሳተ ፖሊሲ ማርቀቅ ሊመራ ይችላል።የተሳሳተ ፖሊሲ ምን ሊያመጣ እንደሚችል በሊቢያ ፤ በየመን፤ በኢራቅ፤ በአፍጋኒስታን ውጤቱን አይተናል።ባራክ ኦባማ በሊቢያ፤ ጆርጅ ቡሽ በኢራቅ ላይ ለፈጸሙት እና ላመኑት ስህተት መንስኤው እንዲህ አይነት ከተሳሳተ መረጃ የሚመነጭ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።ይህ ስህተት በኢትዮጵያም ጉዳይ ላይ እንዳይፈጠር ትክክለኛውን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ቀናት ሚኒስትሮቻቸውን፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉን ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤውን እና አንጋፋ ዲፕሎማቶችን ወደተለያዩ ሀገራት በመላክ ትክክለኛውን ግንዛቤ የማስጨበጥ የዲፕሎማሲ ሥራ ሰርተዋል። እነዚህ ልኡካን ከቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።ውይይቱ ግን ቀጣይ መሆን አለበት።ስለዚህ ይህን ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ውይይቱን የማስቀጠል ሥራ መስራት የዲያስፖራው መሆን አለበት።ዲያስፖራው በተለይ የፋይናንስ አቅሙን በማስተባበር ተአማኒነት እና ተሰሚነት ካላቸው የፖለቲካ ደላሎች (ሎቢስትስ) የተወሰኑትን በመቅጠር ጉዳዩ እለታዊ ክትትል እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል።
በጁንታውም ሆነ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሊያደርጋት የሚችል በቂ እውነት አላት።ነገር ግን ይህን እውነት ማወጅ እና በሱ አሸናፊ መሆን ሥራ ይጠይቃል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በጁንታው ተከፋይ ሆነውም ይሁን በሌሎች ርእዮተ ዓለማዊ አጀንዳ ተመርተው በኢትዮጵያ ላይ የማያቋርጥ የሚዲያ ወከባ እየፈጠሩ ያሉት የምእራቡ ሚዲያዎች እውነትን በመያዝ መመከት አለባቸው። ለዚህም የዲያስፖራው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በነዚህ የአንድ ወገን መረጃ ብቻ በሚነዛባቸው ሚዲያዎች ላይ ፍትሀዊ ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ ወሳኝ ተግባር ነው። በዲያስፖራው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በሰብአዊነት ስም የሚሰራጨውን ቅጥፈት በጽሁፍም ይሁን በምስል እንዲሁም በቀጥታ ስርጭት በመግባት መሞገት አለባቸው።
በመጨረሻም በዲያስፖራ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዛሬ የሚያደርጉት ትግል የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት ከማስከበር አንጻር ያለውን ፋይዳ ዛሬ ሳይሆን ነገ ታሪክ እንደሚያስታውሰው መገንዘብ አለባቸው። ዲያስፖራው እስከዛሬ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ቤት በመላክ ኢኮኖሚው ወደለየለት የውጭ ምንዛሪ ድርቅ እንዳይገባ አድርጓል። ለህዳሴ ግድቡ ከፍተኛ መጠን ያለው ቦንድ ገዝቷል። ማንኛውም አይነት ተፈጥሮአዊም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ ሲያጋጥም ያለ መታከት ደግፏል።ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ያደረገው ድጋፍ ነው። ህግ የማስከበር ዘመቻው ከተካሄደ በኋላም ከኤርትራውያን ዲያስፖራ ጋር በመሆን በዲፕሎማሲው ዘርፍ የአቅሙን አግዟል።አሁንም የሚፈለገው ይህ ድጋፍ ደረጃው ከፍ እንዲል ነው።ይህ ድጋፍ ለመንግሥት የሚደረግ ድጋፍ አይደለም።ለሀገር የሚደረግ ድጋፍ ነው።ሀገርን ስለመደገፍ ደግሞ ለዲያስፖራው አይነገረውም። የሚያውቀው እና የኖረበት፤ በደስታም የሚያደርገው ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013