
አዲስ አበባ:- ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነጻ ተቋማትን የማለማመድ የፖለቲካ ሽግግር ነው ሲሉ የህግ ባለሙያው አቶ ቸርነት ሆርዶፋ ገለጹ።
አቶ ቸርነት በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫ በዓይነቱ የተለየ ነው። ከዚህ በፊት ነፃ የዴሞክራሲ ተቋማት አልነበሩም። አሁን እየተሰራ ያለው ነፃ ተቋማትን የማለማመድ የፖለቲካ ሽግግር ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገር ጥቅም ይልቅ ሥልጣን ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ በመጠቆምም፤ ዴሞክራሲያዊና ነፃ ተቋማት እንዲዳብሩ መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የዴሞክራሲ ልምምድ በሌለበት ሀገር ውስጥ የፓርቲዎች ዋና ተልዕኮ መሆን የነበረበት ሥልጣን መያዝ ሳይሆን የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲዘረጋ መሥራት ነበር ብለዋል። የዴሞክራሲ ሥርዓትና ነፃ ተቋማት እንዲዳብሩ ሁሉም የበከሉን እንዲወጣም አቶ ቸርነት አሳስበዋል።
የምርጫን ጉዳይ የሚመለከቱ ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎችን በፍጥነት መወሰንና ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።
የፍትሕ ተቋማት የሚወስኑትን ውሳኔ ፖለቲካዊ መልክ ማስያዝ ተገቢ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።
‹‹የፍርድ ቤትን ውሳኔ ፖለቲካዊ መልክ የምናስይዘው ከሆነ ዴሞክራሲ አንገነባም›› ያሉት አቶ ቸርነት፤ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሲወስኑ የተፈረደለት አካል ሲያደንቅ የተፈረደበት ይወቅሳል ይህ ደግሞ ፍትሐዊ ተቋምን አያጎለብትም ብለዋል።
አንዳንዶች ለራሳቸው ሲወሰን ተቋሙ ገለልተኛ፣ በራሳቸው ላይ ሲወሰን ደግሞ ተቋሙ ነፃ ያልሆነ እያደረጉ የሚኮንኑ ከሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት አይገነባም ብለዋል።
ምርጫ ቦርድም ሆነ ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ሥራቸውን ነው የሰሩት ተብሎ መታየት አለበት። ተቋማቱም የአሰራር ሥርዓታቸውንና ህጉን መሰረት አድርገው መሥራት አለባቸው ብለዋል።
‹‹ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ነፃነትና ግላዊ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል›› ያሉት አቶ ቸርነት፤ በተቋም ደረጃ ፍርድ ቤቱ ከፖለቲካዊ ተቋም ተለይቶ በነፃነት መሥራት አለበትም ብለዋል።
እንደ አቶ ቸርነት ማብራሪያ፤ ግላዊ ነፃነት ሲባል በባለሙያዎቹ የሙያ ነፃነት ያላቸውና ገለልተኛ የሆኑ መሆን አለበት። እነዚህን ያሟላ ፍርድ ቤት ነፃና ገለልተኛ ይባላል ብለዋል። በምርጫ ወቅት ጉዳዮችን ለመመልከት የተቋቋሙ ችሎቶች የሚመደቡ ዳኞች ገለልተኛ ብቻ ሳይሆን የምርጫ ጉዳዮችን በጥልቀት የሚያውቁ ሊሆኑ ይገባቸዋልም ብለዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም