እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት መሬት መተኪያ የሌለው ሀብት ነው። ብዙ ነገራቸው ከመሬት ጋር የሚያያዝ ነው። በመሆኑም ይህንን መተኪያ የሌለው ሀብት በአግባቡ እና ለሚፈለገው አግልግሎት ማዋል፣ በቁጠባና በጥንቃቄ ማስተዳደር ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ሆኖም በሀገራችን የመሬት አጠቃቀም ከባድ ችግር የሚስተዋልበት ሆኖ ቆይቷል። ችግሩ ዛሬም ቀጥሏል። በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬም የቅሬታ ማዕከል ተብለው ከሚወሰዱት አንዱ የመሬት አስተዳደር ጉዳይ ነው። ዘርፉን ከቅሬታ ምንጭነት ለማላቅ ጥረቶች ቢደረጉም እስከ ዛሬ ችግሩ አልተቀረፈም።
በከተማዋ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመሬት ማኔጅመት ሥርዓት ለመዘርጋት በተለያዩ ጊዜያት ጥረት ተደርጓል። የከተማዋን መሬት ማኔጅመንት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ከብልሹ አሰራሮች የጸዳ ለማድረግ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የካዳስተር ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረት ቢደረግም ከተማ አስተዳደሩ በሚፈለገው ልክ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በተደገፈ እና ከሌብነት በጸዳ መንገድ ማቅረብ አልቻለም። ሥርዓቱን ለመዘርጋት ጥረት ቢደረግም እስካሁን ድረስ የተሰራው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
የካዳስተር ሥርዓት ከተጀመረ 12 ዓመታት ገደማ ቢያስቆጥርም በተግባር ረገድ ገና በጅምር ላይ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ መረጃዎች ያመላክታሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ዘርፍ የሚስተዋሉ ግድፈቶችን ለማረም አሁንም አዲስ ሶፍትዌር በማልማት ላይ ይገኛል። ሶፍትዌሩን የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በቅርቡ ተካሂዷል። የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ሶፍትዌሩን የማበልጸግ ስራውን እየሰራ ይገኛል።
መተግበሪያው በህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎች፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓተቶች አላስፈላጊ መንገላታቶችን እና ስርቆቶችን የሚያስቀር ነው ተብሏል። ከኤጀንሲው በመውሰድ የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር የመረጃ ሥርዓት ሶፍትዌር በመልማት ላይ የሚገኘው የአፍሪኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ዘይኑ እንደሚሉት፤ የአዲስ አበባ የመሬት መረጃዎች የተቀናጀ እና ኮምፕዩተራይዝድ የሆነ አይደለም። አንድ የመሬት ይዞታ ባለቤት ፋይሎቹ በቀላሉ የማይገኙበት እና ፋይሉን እንኳን ለማስወጣት ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠየቅበት ነው።
አዲስ በመበልጸግ ላይ የሚገኘው ሶፍትዌር በመሬት ዘርፍ የሚስተዋሉ እነዚህን ችግሮችን በመሰረታዊነት የሚፈታ ነው። የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ዘርፍ ሁሉም ነገሮች ኮምፕዩተራይዝድ ከተደረጉ በኋላ አዲስ የሚበለጽገው ሶፍትዌር ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል። ኮምፕዩተር ውስጥ ከገባ በኋላ መረጃዎችን በቀላሉ እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ መያዝ ያስችላል። መረጃው ቢጠፋ ወይም ቢቃጠል እንኳ ያለ እንግልት በቀላሉ መልሶ ማግኘት ይቻላል። በአጠቃላይ መረጃ ተቃጠለ ወይም ጠፋ የሚባል ነገር አይኖርም። መተግበሪያው ይህን መሰረታዊ ችግር የሚፈታ እንደሆነ አቶ ባህሩ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ሰርሞሎ እንደሚሉት፤ በመሬት ዘርፍ የሚስተዋሉ ዋና ችግሮችን ለመቅረፍ በፕሮጀክት እና ከፕሮጀክት በተለየ አግባብ በውስጥ አቅም ጥረቶችን እያደረገ ነው። የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር የመረጃ ሥርዓት ሶፍትዌር በከተማዋ በመሰረታዊነት የመሬት አስተዳደር ዘርፍን ላቅ ወዳለ ደረጃ የሚያደርስ ነው።
ፕሮጀክቱ አራት ዋና ዋና ዓላማዎችን ማንገቡን የጠቆሙት አቶ አብርሃም፤ የመጀመሪያው ዓላማው የዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂ መፍትሄ በመጠቀም የከተማ አስተዳደር ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚሰጠውን ወቅታዊ አገልግሎት ውጤታማነት ማሻሻል፣ የመሬት ማኔጅመንት ቢሮ ከሌሎች ተጠሪ ተቋማት ጋራ እስከ ወረዳ ድረስ በቀላሉ መረጃን እንዲጋሩና እንዲለዋወጡ ማስቻል፣ ከመሬት እና መሬት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ውጤታማ አስተዳደርን ማረጋገጥ እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን ሊከላከል የሚችል ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ጠቁመዋል።
ሲስተሙ ከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን የመሬት ሪፎርም የበለጠ በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እንዲሁም በዘርፉ የሚነሳውን የህዝብ እንግልት ለማስቀረት የሚያግዝ ነው። በ195 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የሚሰራ ሲሆን ፕሮጀክቱን በዘጠኝ ወራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ለስራው የሚያስፈልጉ መረጃዎች ተሰብስበው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተገባ ሲሆን ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲደረግ ከከተማው መሬት ተቋማ አንስቶ እስከ ወረዳ ድረስ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ ተጥሎበታል።
በተለይም በመሬት ተቋም የሚታየውን ብልሹ አሰራሮች ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል ለመለወጥ፣ የመሬት አያያዝ ሁኔታ በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ አቅም የሚፈጥር ነው።
እንደ አቶ አብርሃም ማብራሪያ የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር የመረጃ ሥርዓት ሶፍትዌር ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ለከተማ አስተዳደሩ አራት ጥቅሞችን የሚያስገኝ ይሆናል። ዘመናዊ የመሬት ባንክ ሥርዓት በመፍጠር የከተማውን የመሬት ሀብት ከብክነትና ከህገ ወጥ ወረራ የጸዳ ማድረግ፣ የመሬት ዘርፍ አገልግሎት በዘመናዊ አሰራር እና ቴክኖሎጂ ሲታገዝ በተሟላ መልኩ ለነዋሪውም ሆነ ለባለሀብቱ የተሻለ አገልግሎት እና ኢንቨስትመንት ማሳለጥ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዶክመንት አያያዝ ሥርዓት መተግበር እንዲሁም ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ተጠሪ ተቋማት ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጥ ሲሆን ሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች አገልግሎታቸውን በዚህ ሲስተም ይሆናል።
የአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀይሉ ሉሌ እንዳሉት፤ የከተማውን የመሬት ዘርፍ ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉት ጥረቶች ፍሬ ሊያፈሩ ያልቻሉት በቴክኖሎጂ ስላልተደገፉ ነው። እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መከተል ሲቻል ነው። አሁን ኤጀንሲው የጀመረው የቴክኖሎጂ የማበልጸግ ስራ ችግሩን ለመቅረፍ የላቀ ሚና ይኖረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ፣ የተንዛዛ፣ ተገልጋይን የሚያሰለች፣ እንዲሁም ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው ያሉት አቶ ሀይሉ ሶፍትዌሩ ወሳኝ እና በመሬት ዘርፍ አሁን ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ፊት ሊያሻግር የሚችል መሆኑን አብራርተዋል።
ቴክኖሎኖጂዎች ችግሮችን መፍቻ መንገዶች እንጂ በራሳቸው ችግሮችን መፍቻ አይደሉም ያሉት አቶ ሀይሉ፤ ችግሮች ለመቅረፍ የሰው እገዛ የሚፈልግ በመሆኑ ቴክኖሎጂውን ሊጠቀም የሚችል ብቃት ያለው፣ የተመሰገነ፣ በሥነ ምግባሩ፣ በእውቀቱ እና በክህሎቱ የዳበረ ምስጉን ባለሙያ የመፍጠር ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ እንዳሉት፤ የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ስራዎች አንዱ የቴክኖሎጂ ልማት ስራ ነው። በቴክኖሎጂ ረገድ ሰፊ ስራ ባለመሰራቱ በብዙ ቦታዎች የከተማ አስተዳደሩ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ አልተቻለም።
መሰል ቴክኖሎጂዎች ለከተማዋ ለኢኮኖሚም፣ ለማህበራዊም ወሳኝነት ያለው ነው። በተለያዩ ጊዜያት መሰል ቴክኖሎጂዎችን ለማልማት የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል። ቴክኖሎጂውን በፍጥነት በማልማት ረገድ ችግር ይስተዋላል። የመሬት ዘርፍ የሚተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ለማልማት ጥረቶች ቢደረጉም በተለያዩ ምክንያቶች ሶፍትዌሮቹ ሳይበለጽጉ ዓመታት ተቆጥረዋል። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ከተጀመሩ በኋላ የመጓተት ሁኔታ እንደሚስተዋል አቶ ጃንጥራር ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ጃንጥራር ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በተለያዩ ዘርፎች የሚካሄዱ የቴክኖሎጂ ስራዎችን በማሰባሰብ እየሰራ ነው። በመሬት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ስራዎችን እየሰራ ነው። እነዚህ ስራዎች በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ለማስኬድ የሚያስችል ነው። ይበል የሚያሰኝ ነው። አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በአንድ በኩል በሰው እጅ በሚሰሩበት ወቅት ስራውን ለማጠናቀቅ የሚወስደውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪን የሚቀንሱ በመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት ያያቸዋል ። ሶፍትዌሩ ተጠናቅቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
አዲሱ ፕሮጀክት ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ወደ ስራ ሲገባ በአንድ በኩል የከተማ አስተዳደሩ የሚሰጠውን አገልግሎት ያፋጥናል፤ በሌላ በኩል ሰው ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በቂ መረጃ አግኝቶ ወደ ልማት እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የመሬት ማኔጅመንት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ መደገፍ በየቦታው አገልግሎት ለማግኘት ተሰልፎ የሚታውን ህዝብ እና በአገልግሎት እጦት ምክንያት በየቦታው የሚፈጸመውን ሙስና ለማምከን አጋዥ ነው። ቴክኖሎጂው ለመሬት መረጃ ሥርዓት ትልቁ እና ዋና ለሆነው ለካዳስተር ሥርዓት ትግበራ አንድ አቅም እና ጉልበት የሚሆን ነው። ሶፍትዌሩን ለምቶ ወደ ስራ ሲገባ ዘመናዊ ካዳስተርን ለመገንባት አቅም ስለሚሆን በመረጃ ሥርዓት የተጠናከረች አዲስ አበባን እውን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
አዲሱ ሶፍትዌር ፍትሃዊነትን በማሻሻል ለከተማ አስተዳደሩ አዲስ እድል የሚጨምር እንደመሆኑ ለነገ የሚባል ስራ አይደለም ያሉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013