የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ ስለ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘንድ የሚታወቁትን፣ በአደባባይ የሚታዩትን፣ በእለት ተእለት የሚፃፉ የሚነገሩትን እውነታዎች ማንሳት ሳይሆን፤ በምትኩ የተዘነጉትን፣ አንዳንዴም እውነት ሁሉ የማይመስሉትን፣ በተለያዩ አውዶች ሊጠቀሱ እየተገባቸው ችላ የተባሉትን፤ ብርሀናቸው የደበዘዘውን (ለማፍካት) ወዘተ፤ እንዲሁም በወቅት-ዘመናቸው አንፀባራቂ፤ ለተቀረው ዓለም ብርሀን ፈንጣቂ የነበሩትን ማስታወስና በአሁኑም ሆነ መጪው ትውልድ ዘንድ ተገቢውን ትኩረት ያገኙ ዘንድ የማቀበል ሙከራ ነው።
ከታላቁ መጽሐፍ፤ ከሚታወቀው ጥቅስና ጥቅሱ ከዋለው ውለታና ከማይታወቅለት ፋይዳው እንጀምር።
በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በተደጋጋሚ በዓለም ታሪክ ውስጥ የሚጠቀሱትን መጽሐፈ መዝሙር ምዕራፍ 68 ቁጥር 31 (በተለይ ይህ ጥቅስ ከ”ኢትዮጵያዊነት” ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ከፍ ብሎ መታየትና ለአፍሪካውያን ነፃ መውጣት በመታገያና ማታገያነት፤ በአገራት ብሄራዊ መዝሙራት ውስጥም ገብቶ መልእክትን በማጉላትና ማስተጋባት በኩል አገልግሏል – የጋርቬይን ሥራዎች ልብ ይሏል።) ውስጥ ያለተወዳዳሪ (42 ጊዜ በማለት ድሮ ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ በከፍተኛ ትጋትና ልፋት የደረሰበትን ዛሬም ድረስ፣ በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን፤ በተለያዩ ስሞች ከ57 ጊዜ በላይ መጠቀሷን ባለመገንዘብ ያንኑ የሚደግሙና ደጋግሙ አሉ) በቀዳሚነት የተጠቀሰች፤ ‹‹ሀገር የጋራ ሃይማኖት የግል›› የሚልና ከዛሬው “መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው” ከሚለው የጠለቀ አስተሳሰብ ያፈለቀችና ዘመን ተሻጋሪ መርህን የተቀበለች፤ በሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ “የጋራ ደህንነት”
(collective security) ፅንሰ ሀሳብን ያፈለቀች (ዛሬ ሌሎች ጩሉሌዎች ወስደውት የራሳቸው አድርገውታል)፤ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያደረባት (ባለፈው ዓመት በተደረገ “የቱ ነው ከሁሉም የተሻለ ሃይማኖተኛ ህዝብ/አገር?” የሚል ጥያቄን በሚመልስ አለም አቀፍ ጥናት ከመቶ 98 በማምጣት አንደኛ መውጣቷን ያስቧል።) ምኑ ቅጡ- የቱ ተወርቶ የቱ … ነው ነገሩ። እንቀጥል፤
አገሬ በሰራችው የነጭ የበላይነትን የመደምሰስ ታሪክ ምክንያት የዓለምን የታሪክ ማማ የተቆጣጠረች፤ ከማንም በፊት ሴት መሪዎችን (ከዮዲት ጊድዖን/ጉዲት (960_1000 ዓ/ም) ጀምሮ) ያፈራችና የሥርአተ ፆታ እኩልነትን ያረጋገጠች ፊት መሪ፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ለተፈጠረውና ለመላው አፍሪካውያንና ጥቁር ህዝቦች የመታገያና ማታገያ፤ መላው አፍሪካውያንን ወደ አንድነት ለማምጣት (አፍሪካዊ ወንድማማችነት) በተዋጣለት መሳሪያነት ሲያገለግል ለነበረው ፍልስፍና – “ኢትዮጵያኒዝም” ምንጭ – ኢትዮጵያ!!!
ኢትዮጵያ ከማንም በፊት የነበረች፤ እስካሁንም ከነሙሉ ማንነቷ ያለች፣ ዮፍታሄ “ጥንተ ተደንግሎ” እንዳለው ከነብኩርናዋ ያለች አማላይ (በተለይ በተፈጥሮ ሀብትና ፀጋዋ – “What plants are found only in the Highlands of Ethiopia?”ን ጎግል ቢያደርጉ ከማመን አቅምዎ በላይ ዝርዝሮችን ይመለከታሉ፤ ከወቅታዊ ፅሁፎችም “Why Agriculture is promising Investment in Ethiopia?” ቢመለከቱ አገርዎ ያሏትን ጥቅጥቅ ያሉ ሀብቶች በሚገባ ይረዳሉ)፤ በዛሬው ዘመን ብርቅዬ የሆኑትን ሁሉ (ባህላዊ ህክምን፣ አዝርእት፣ ስነ ፈለክ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ ኪነጥበብ … በጣም ብዙ ብዙ (ካስፈለገ “Wonderful Ethiopians of the Ancient Cushite Empire” ይዞ ጥቅልል) ለዓለም ያበረከተች፤ ቴክኖሎጂን፣ በተለይም ለኮምፒዩተር መፈጠር መሰረቱን (“Base” የሚባሉትን መሰረታዊያን “0” እና “1”ን ለዓለም ያበረከተች (ካስፈለገ “Ancient math of Ethiopia amazing method of Mathematics calculation” የሚለውን ዘጋቢ ፊልም እየደጋገሙ መመልከት) አስደማሚም፤ አስገራሚም አገር ነች – ኢትዮጵያ!!!
የጀግኖች፣ የኩሩዎች፣ አይነኬ-አይበገሬዎች … (ካስፈለገ፣ ይህ አገላለፅ አጉል እራስን መካብ መስሎ ከታየ የቦብ ኔዌልን “Ethiopia: Pride, identity and purpose”ን በሳል መጣጥፍ ማንበብ ነው።) አገር ነች – ኢትዮጵያ!!! (“ልጆቼ ዛሬ እንደምታዩኝ እንዳይመስላችሁ” ስትል አይሰማችሁም??)
የሉሲ መገኛዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያለ ተወዳዳሪ ለዩኔስኮ ከደርዘን በላይ ቅርሶችን (የጽሑፉን ከደመርነው ሰማይ ነው) ያበረከተች፣ በዓለም የመካከለኛው ዘመን ፍልስፍና እውን መሆን (እድሜ ለዘርአያእቆብ) ቀዳሚዋ አገር፤ የአባይ ስልጣኔ መነሻ፤ በዓለም ሰላም ማስከበር ተግባር (UN peacekeeping operations) በ2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችና በተዋጣለት ወታደራዊ አስተዋጽኦ ተደጋግሞ የተመሰከረላት አገር – ኢትዮጵያ!!!
የዛሬው የአፍሪካ ህብረት (የቀድሞው OAU የአሁኑ AU)ን፣የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት(ኦኤዩን ከመወጠን እስከ መመስረትና መምራት፤ በተለይም አፍሪካ የሞኖሮቪያና ካዛብላንካ ብሎክ በሚል ለሁለት በተሰነጠቀችበት ወቅት ገለልተኛ አቋምን በመያዝና የአስታራቂነት ሚናን በመጫወት የዛሬዋን አፍሪካ እውን ያደረገች አገር – ኢትዮጵያ!!!
የዓለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅ (IMF) እና የአለም ባንክ መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ አይኤምኤፍ ማኔጅመንት ውስጥ “የኢትዮጵያ ዴስክ” የነበረ መሆኑን ተከትሎ የሁለቱ (በተለይ አይኤምኤፍ እዚህ አ.አ ቢሮ ነበረው) ባንኮች የጋራ ማኔጅመንት ሰብሳቢ/ሊቀመንበር (እ.አ.አ በ1965) በመሆን ድርጅቱን ለአንድ ዓመት የመራች፤ ኢኮኖሚዋ “የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ” (ዝርዝሩን የፈለገ የወቅቱን የተለያዩ ሥራዎች ኃላፊ አስፋው ዳምጤ ጋ ሀሎ ይበል) በሚል ምድብ ስር የነበረችው፤ ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅትም ፊቷን በማዞር እንዲመሰረት “ያስገደደች” መስራች አባል ነች – ኢትዮጵያ!!!
ከኢትዮጵያዊው የኒው ዮርኩ ዲፕሎማት (ሀዲስ አለማየሁ) ጭንቅላት ፈልቅቆ፣ በንጉሱ ተመክሮበትና ይሁንታን አግኝቶ በአፍሪካ መሪዎች ፀድቆ ወደ ተግባር የተቀየረው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) ባለውለታ፤ በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት አባል (charter member) የነበረች አገር – ኢትዮጵያ!!!
በአለም የሥነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ያለ ተወዳዳሪ ጉልህ ስፍራን የያዘች (እስከ ዛሬ በተደረጉ ጥናቶች ንግስተ ሳባን ያህል የተጠና አለመኖሩን ሁሉ ልብ ይሏል)፤ ከኢትዮጵያ 4ሺህ 317 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኙት የህንድ ባለ ስልጣናት “ለዛሬዋ ህንድ የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ሳይሉ የማያልፏት፤ ማድሄያ ፕራድሽ (MP) ከተማ በስሟ፣ “የህንድ ኢትዮጵያ” (India’s Ethiopia) የሚል ስያሜ ያላት አገሬ – ኢትዮጵያ!!!
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1951 ዓ/ም ጀምሮ በየአመቱ ለ50 አፍሪካውያን ወጣቶች ነፃ የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) ትሰጥ የነበረች (ብዙዎቹ የአፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከአአዩ የተመረቁ ነበሩ)፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የአፍሪካ ተማሪዎች ህብረት የሚባል ተቋቁሞ በነፃ እንዲንቀሳቀስ ስታደርግ የቆየች ዲሞክራት አገር – ኢትዮጵያ!!! በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ የሆነው ልቦለድ ርእስ በስሟ የሆነው አገሬ – ኢትዮጵያ!!!
ከ1896 አንስቶ በዓለም ላይ ስሟ እንደ ጧፍ ሲያበራ የነበረችው፤ በተለይም ከ1935–36 ባለውና፣ “ሟች አውሬ ገዳዩን ያስመሰግናል” እንዲሉ፣ የጣሊያንን እየጋለቡ መምጣትና በመጣችበት እግሯ እያነከሰች መመለሷን ተከትሎ ከራሳቸው ከጣሊያኖች ጀምሮ፣ ዓለም “ቪቫ ኢትዮጵያ”፣ “ቪቫ ምኒልክ!!!” ያለላት (ካላመንክ ከብዙዎች አንዱ የሆነውን “The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire”ን አንብብ) አገር፤ በምስራቅ አፍሪካ ሀያል (a major power in the Horn of Africa) የሆነች አገር፤ የውሀ ማማ (ግብፅ እንዳትሰማ …) አገር – ኢትዮጵያ!!!
“አፋጀሽኝ” የሚላት ዮፍታሄ ንጉሴ “ጥንተ ተደንግሎ …” ሲል የሚገልፃት ኢትዮጵያ፤ ጥላሁን ገሰሰ ባልታወጀው ብሄራዊ መዝሙሩ “የኛ መመኪያ” መሆኗን የሚነግረን ኢትዮጵያ፤ በዓለም እውቅ ሳይንቲስቶች፣ ፈላስፎች፣ ተመራማሪና አሳሾች ወዘተ አብዝታ የተፈለገች፣ የተጠናች፣ የተመረመረችና ገና ብዙ ብዙ የሚጠና የሚመረመር … “ጉድ” እንዳላት የሚነገርላት ሀገሬ፤ በቱሪዝም ሀብቷ ብቻ የአፍሪካን ህዝብ መቀለብ የሚችል ሀብት ያላት መሆኑ በጥናት የተረጋጠላት ኢትዮጵያ፤ በ1959 ዓ/ም በዳካር (ሴኔጋል) በተካሄደው የመጀመሪያው የጥቁር ዓለም ክብረ በዓል ላይ “ኮከብ ሀገር” የሚል ማእረግን የተሸለመችና በስፍራውም ተገኝታ ያከበረች (በንጉሥ ኃይለስላሴ አማካኝነት – ለበርካታ ዝርዝሮች የኤርሚያስ ሁሴንን “እሳትና ውሃ” ይመልከቱ)፤ ከ2ሺህ 500 ዓመት በፊት መንግስት የመሰረተች፤ ከ4ሺህ 000 – 6ሺህ 000 የግብርና ስራን በመጀመር ለዓለም ያስተዋወቀች (አመድ አፋሽ ብትሆንም) አገሬ – ኢትዮጵያ!!!
“ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ …” ተብሎ የተገጠመላት፣ “አበበ ቢቂላ ያገባሻል …” ተብሎ የተዜመላት፤ “አርብ አርብ ይሸበራል …” ወዘተ “ማህፀነ ለምለም” አገር – ኢትዮጵያ!!!
“የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ፤
ልብ አድርገህ ተመልከት፤
ኢትዮጵያ የተባለችው፤
አንደኛ እናትህ ናት
ሁለተኛ ዘውድህ ናት
ሶስተኛ ሚስትህ ናት
አራተኛ ልጅህ ናት
አምስተኛ መቃብርህ ናት፤” ተብሎ በዘመን ተሻጋሪ ቃል ግጥም (አፄ ዮሀንስ) ሁለመናነቷ የተዘረዘረላት ሀገሬ – ኢትዮጵያ!!!
በአክሱም ዘመነ መንግስት (100 AD — 940 AD) ከሱዳን የሚሮዊንና የኑቢያ በከፊል ግዛቶች እንዲሁም ቀይ ባህርን ተሻግሮ በደቡብ አረቢያን፣ የመን በሚባለው አካባቢ የሂሞያርና የሳባን ግዛቶች ያጠቃለለ የግዛት ወሰን የነበራት፤ በዚሁ ዘመን በምድርም በባህርም ይዋጋ የነበረ የጦር ሰራዊት የነበራት (“የኢትዮጵያ ሰራዊት እና የጦርነቶች ታሪክ”ን ይመለከቷል።) ጠንካራ አገር -ኢትዮጵያ!!!
ግብፅን ያስተዳደረችና ያቀናች (በተለይ ከ1874 – 1876) የነበረች (“The Negro: III. Ethiopia and Egypt”ን መጥቀስ ይቻላል) አገር (Aithiopes, Aethiopia, Ityop’p’ya, Abyssinia, Cush, Kushites . . .) አቢሲኒያ – ኢትዮጵያ!!!
በእድሜዋ፣ አንጋፋነቷ፣ የዓለም መሪነቷ፣ የዳበረ ማንነቷ፣ ለዘመናት የተገነባ ታሪኳን፣ በአገርና አገረ መንግስት ግንባታ ቀዳሚነቷ (ዛሬ እንደ አዲስ ያነታርኩናል)፤ “The Ethiopian Empire” (መንግሥተ ኢትዮጵያ) በሚል የሚታወቅ መንግስት የነበራት መሆኗን ወዘተ በተመለከተ አንቱታን ያተረፉ ፀሀፍት ሳይቀሩ በቅድመ ክርስቶስ (BC) ጀምሮ እራሷን የቻለች አገር የነበረች መሆኗን ሲገልፁ “it’s generally agreed that Ethiopia developed as a country in 980 BCE [Before the Common Era].” ያሉላት አቢሲኒያ – ኢትዮጵያ!!!
(ከላይ የጠቀስነው የDrusilla Dunjee Houston (ጃንዋሪ 20 1876 – ፌብሯሪ 8 1941) ተጠቃሽ መጽሐፍ (Wonderful Ethiopians of the Ancient Cushite Empire) በእነዚህና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፋ አድርጎ የሄደ በመሆኑ ማንበቡ ይመከራል።) እዚሁ ላይ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ … በአንድ ያስተዳደር የነበረውን የአክሱም ስርወ መንግስት ጨምሮ የአቢሲኒያን ጥንካሬና ማንነት ማወቅ ይቻላል። (“ልጆቼ ዛሬ የምታዩኝን እንዳልመስላችሁ” ስትል ይሰማል እንበል?)
የአገር በቀል እውቀት ባለቤት፣ የዳበረ ማህበረ-ባህላዊ እሴት፣ ለሌላው ዓለም የተረፈ የትምህርት ፍልስፍና (የእጓለን “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤን” እና የብሩህ ዓለምነህን ሦስቱን ኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ያተኮሩ ስራዎች ያነቧል፤ ተጨማሪ ካስፈለገም የዩኔስኮን ድረ-ገፅ ይጎበኟል) ያላት፣ ባለ pentatonic (ከዚህ ጋር ያሬዳዊ ዜማን፣ ማህሌታይን ያስቧል)፣ መንዙማን በ1907 የፈጠረች፤ ከአፍሪካ በራሷ ቋንቋ ሥነፅሁፍን በማበርከት (“ጦቢያ” – በአፍሪካ ሥነ ፅሁፍ ላይ እርቀው የሄዱት ዶ/ር መላክነህ መንግሥቱ “የመጀመሪያው የአፍሪካ ሥነ ፅሁፍ” ያደርጉታል)፤ በአለም ብቸኛዋ የ12 ሰአት የጊዜ አቆጣጠር (12-hour time system) ያላት፤ የፓን-አፍሪካኒዝም፣ የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ መፈጠሪያ ማህፀን፣ ወዘተርፈ ያላት አገሬ – ኢትዮጵያ!!!
በተለያዩና በርካታ ጥንታዊያን የአለም ሥነፅሁፍ ሊቃውንት እጅግ ብዙ ብዙ የተባለላት (ከእነዚህም አንዱ የሆነውን፣ በ “O Mother Race!” በሚል የሚጀምረውንና በፖል (Paul Laurence Dunbar) የተፃፈውን “The Complete Poems of Paul Laurence Dunbar/Ode to Ethiopia” (በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1926 በፊት እንደተፃፈ የሚነገርለት ይህ ስራ ዘንድሮ (ጁን 14/2021) እንደገና ታትሟል) አንጀት የሚያላውስ ግጥም ያነቧል)፤ በሊጉ (League of Nations) ላይ በመገኘት የሊጉን ዘረኝነት (የኢምፔሪያሊዝምን ማንነት) አይን ከሰበከት እያገላበጠች ለአለሙ ሁሉ ያሳየች፤ የነበረው የዓለም ስርዓት ቆም ብሎ እራሱን እንዲፈትሽ ያደረገችና እስካሁንም ድረስ ምድር አንቀጥቅጥ የሆነ ንግግር/መልእክትን (ንጉስ ኃይለስላሴ) ለታሪክ ያኖረች፤ ለፓን አፍሪካኒዝም ወገቧን አስራ የሰራች ኢትዮጵያ – አገሬ!!!
በ2ሺህ 355 ሜትር (7ሺህ 726 ጫማ) ከፍታ (altitude) ላይ የምትገኝ፤ በዚህም ምክንያት ከአፍሪካ በመጀመሪያ፤ ከአለም በ3ኛ ደረጃ ላይ ያለች ዋና ከተማ (አዲስ አበባ) ያላት (ቢታወቅበት ይህ እራሱ ብር ነበር) ፤ በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት ተራሮች ከ70 በመቶ በላይ የሚገኙባት፤ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኘው እሳተ ጎመራ 26 በመቶው የሚገኝባት (ደንከል ዲፕረሽን)፤ ከ4ሺህ 500 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ተራሮች መገኛ፤ የመካከለኛው ዘመን “ፍትሀ ነገስት” ባለቤት፤ ገፆችን ባገላበጡ ቁጥር ጥንታዊነቷን፣ ጀግንነቷ፣ ነፃነቷን፣ ሀገረ መንግስትነቷን ወዘተ አጣምሮ የያዘ፤ “Ethiopia is the oldest independent country in Africa.” የሚል አረፍተ ነገር በወርቅ ቀለም ተፅፎ የሚያገኝላት፤ በ”ትላልቅ አይኖች” አሳሳል ጥበብ አለም ያወቃትና ያደነቃት ወዘተርፈ ናት አገሬ – ኢትዮጵያ!!!
የድሮው የጥቁር አንበሳ ሰራዊት፤
“እናት ኢትዮጵያ ውዲቱ ውዲቱ፣
ላንቺ የማይረዳ ሳለ በህይወቱ፣
በረከትሽን ይንሳው እስከለተ ሞቱ።” በማለት ከፍ ባለ ድምፅ ይዘምርላት የነበረችው (ይህንን በአሁኑ ዘመንም ጥላሁን ገሠሠ “የጠላሽ ይጠላ … ብድሩ ይድረሰው … “ ሲል በበለጠ አጎልብቶ አዚሞታል) አገሬ፤ ተነግሮ፣ ተዘፍኖ፣ ተፅፎ ወዘተረፈ የማያልቅ ታሪክ ባለቤት – ኢትዮጵያ!!!
አብዝቶ በሚወዳት ልጇ፤ በዮፍታሄ “ምስክር” ትያትር (“እሳትና ውሃ” ገጽ 233 ላይ ተፅፎ እንዳገኘነው) እንውጣ፤
የእኛማ ሀገር የእኛማ ሀገር፣
መትሁተ ገጣሪ መልእክተ ፍጡር።
ምን ያለሽ ሞኝ ነሽ ምን ያለሽ ተላላ፤
ወርቅ ተሸክመሽ መቅረት ወደኋላ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013