ምርጫ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የማዕዘን ድንጋይ ነው።ፍትሃዊ ምርጫ በተካሄደባቸው ሀገራት ሰላምና ዕድገት ያብባሉ፤ኢፍትሃዊና አደሏዊ የምርጫ ሂደትና ውጤት ባለባቸው ሀገራት ደግሞ ሰላምና ብጥብጥ ይነግሳሉ፤ልማትና ዕድገት ይቀጭጫሉ።ይህንኑ በመረዳትም አብዛኞቹ በልማትና በዕድገት የገፉ ሀገራት ፍትህ በሰፈነበት ህዝባዊ ምርጫ አሸንፎ ስልጣን በያዘ ፓርቲ የሚመሩ ናቸው።አፍሪካ ውስጥ ሲሆን ግን ይሄ እውነታ አይሰራም።
አብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን ላለመልቀቅና በምርጫ ላለመሸነፍ ሲሉ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ህዝብ የሚያደናግሩ ናቸው።ይሄ እውነታ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በእኛም ሀገር ሆኖ የምናውቀው የአደባባይ ሀቅ ነው።ግን ለምንድነው የአፍሪካ መሪዎች የዚህን ያክል የስልጣን ጥመኞች የሆኑት? መልሱን ካወቃችሁት ንገሩኝ።እኔ ግን ከሀገር ይልቅ ራስን የማስቀደም አባዜ የፈጠረው የራስ ወዳድነት ልክፍት ነው እላለሁ።ለህዝብ ከመኖር ይልቅ ለራስ መኖርን የመረጠ ጭንቅላት የፈጠረው አሉታዊ ተጽዕኖ ነው እላለሁ።እኔ ግን በእውቀትና በአመክንዮ ከመመራት ይልቅ በስሜትና በከሸፈ እሳቤ መኖራችን የፈጠረው ክፍተት ይመስለኛል።ሀገራችን ኢትዮጵያም ለዘመናት በዚህ እርባና ቢስ ስርዓት ውስጥ ያለፈች ናት።በዚህም ብዙ ነገራችንን አጥተናል።ህዝብ ባልቀደመበት፣ ቅድሚያ ለሀገር የሚል እሳቤ ባልተፈጠረበት ሀገርና ህዝብ ውስጥ የሚመጣ ነውጥ እንጂ ለውጥ የለም።አብዛኞቹ ትላንትናዊ መከራዎቻችን ከዚህ አመለካከት ውስጥ የወጡ ናቸው።አብዛኞቹ የኢትዮጵያ መልኮች በዚህ አጉል ስርዓት ተኩለው ያለፉ ናቸው።አሁን ላይ እኚህን ድሮአዊ መልኮቻችንን ለማጥፋት ነው መከራ እያየን ያለንው።ዛሬ ላይ ብዙ ነገር እየሆንባቸው ያሉ ችግሮቻችን እነዚያ ጋፍ መልኮቻችን የፈጠሯቸው ስለሆኑ ነው።
አብዛኞቹ ችግሮቻችን ከመሪዎቻችን እውቀት ማነስ አሊያም ከሀገርና ከትውልድ ይልቅ እራስን ከማስቀደም የሚነሱ ናቸው እላለሁ።ህዝብ መሪውን ነው የሚመስለው።መሪ የሚመራውን ህዝብ አጠንክሮ የመፍጠር ግዴታ አለበት።እውቀት ያለው መሪ ሀገርና ህዝቡን ለመለወጥ ይተጋል እንጂ ያልመረጠውን ህዝብ አታሎ ስልጣን ላይ ለመቆየት አይተጋም።ያለፉት ታሪኮቻችን በዚህ የመሪና የተመሪ ርዕዮት ዓለም ውስጥ ያለፉ ናቸው።ሀገር በህዝቦች የተቀናጀ እሳቤ የምትፈጠር ናት።ስልጣን ለመያዝም ሆነ በስልጣን ለመቆየት የህዝቦች የበላይነት የተረጋገጠበት አብላጫ ድምጽ ያስፈልጋል።ሀገር በመረጠችው ስትመራና አጭበርብሮ ስልጣን በያዘ ስትመራ አንድ አይደለም።ሀገር በመረጠችው ስትመራ መሪና ተመሪ እኩል ያስባሉ።አንድ አይነት ራዕይ ይተልማሉ።አንድ አይነት ህልም ይገነባሉ።አንድ ልብ፣ አንድ ሀሳብ ይሆናሉ።ሀገር ለመለወጥ በሚደረገው ማንኛውም ትግል ውስጥ ከፊት በመሰለፍ አሻራቸውን ያሳርፋሉ።ሀገር ዋሽቶና አታሎ ስልጣን በያዘ ስትመራ ግን ህዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ነው የሚሆኑት።ለጋራ ጥቅም በጋራ ከመስራት ይልቅ ተለያይቶ መቆምን የሚመርጡ ይሆናሉ።ከመነጋገር ይልቅ ለምንም ነገር ኃይልን በመጠቀም የሚፈልጉትን በጉልበት ለማስፈጸም የሚተጉ ይሆናሉ።ከውይይት ይልቅ ጦርነትን በማስቀደም ሀገርና ህዝብ የሚያውኩ ይወጣቸዋል።አንዱ በአንዱ ላይ ቂም በመያዝ ከልማት ይልቅ ለጥፋት ይነሳሳሉ።
የሀገራችን መጻኢ ተስፋ ግን ይሄን ሁሉ መጥፎ ገጽታ የሚሽር ነው።የሀገራችን አሁናዊ ቁመና የተበላሹ ትላንትናዊ መልኮቻችንን የሚያሳምር ነው።ከፊታችን መቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ የሚጠብቁት ታሪካዊ ምርጫ አለ።ሀገርና ህዝብ በአንድ ላይ ነጋቸውን ሊጽፉ የሚጠብቁት መልካም አጋጣሚ ከፊታችን ብዙ በረከትን ይዞ እየመጣ ነው።በዚህ ምርጫ ላይ የብዙዎቻችን ብሩህ ነገ አለ።በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ላይ የብዙዎቻችን ነገ ተስሏል።ሀገር የዋጁ፣ ትውልድ የቃኙ የብዙዎቻችን መልካም አጋጣሚዎች ከዚህ እውነታ ውስጥ የሚፈልቁ ይመስለኛል።ምርጫ የመሪንና የተመሪን ተዓማኝነት ይፈልጋል።ምርጫ ለሀገር በረከት ይዞ የሚመጣው እንዳለፉት ምርጫዎች በውሸት ተለብጦ ሲቀርብ ሳይሆን በሀሳብ ብልጫ ሲቃኝ ብቻ ነው።ለሀገራችን መነሳት ብሎም ለብዙዎቻችን ራዕይ እውን መሆን ከፊታችን ያለው ታሪካዊ ምርጫ መተኪያ የለውም።ሁላችሁም እንደምታውቁት በኢትዮጵያ ታሪክ እስካሁን ድረስ አምስት የሚሆኑ የምርጫ ስርዓቶች ተካሂደዋል።ምርጫ የሚለውን ስም ይያዙ እንጂ ምርጫ ለመባል ያልደረሱ እንደነበሩ ብዙዎች ይናገራሉ።ሀብት ከማባከን ውጪ ለኢትዮጵያ ጠብ የሚል ነገር እንዳላስገኙ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።ይልቁንም እነዚህ ምርጫዎች በማህበረሰቡ ላይ ያደረሱት ስነ ልቦናዊ ጫናም እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው።ከትላንት እስከዛሬ አብዛኞቹ ችግሮቻችን ምርጫ ወለድ ናቸው።ለህዝብ ነጻነትን ስለማንሰጥ፣ ፍትሀዊና ተዓማኝነት ያለው ምርጫ አድርገን ስለማናውቅ ሁሌ ምርጫ በመጣ ቁጥር የንጹሀን ደም እንደፈሰሰ ነው።ሁሉም ምርጫዎች ከህዝባዊነት ይልቅ አንድን ፓርቲ መሰረት አድርገው ተጀምረው ያለቁ ነበሩ።ሁሉም የምርጫ ስርዓቶች ከገለልተኝነት ይልቅ በገዢው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ቅሬታ የሚነሳባቸው ሆነው ያለፉ ናቸው።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግን በብዙ ነገሩ ካለፈው የተለየ ነው።እንዳውም በኢትዮጵያ ታሪክ የምርጫ ህግና ደንብን የተከተለ የመጀመሪያው ሀገራዊ ምርጫ ይመስለኛል።እኔን ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ይሄን ምርጫ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነው።በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ያለችውን አዲሷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ከፊታችን ያለውን ምርጫ የምንጠብቅ ብዙዎች ነን።ያልተወለደችውን ግን ደግሞ በብዙዎቻችን ነፍስ ውስጥ የተጸነሰችውን የጋራ ምድራችንን ለመውለድ ነገን የምንጠብቅ ነን።የኢትዮጵያ ብሩህ ነገዎች ከእንግዲህ የሚፈጠሩ ይመስለኛል።የምንናፍቃት ሀገራችን ከእንግዲህ የምትነሳ ይመስለኛል።ጨለማዎቻችንና ኋላ ቀርነታችን በዚህ በያዝነው የምርጫ ሰሞን የሚያበቁ የመስለኛል።ከፊታችን ያለው ጊዜ የኢትዮጵያ የድህነትና የኋላ ቀርነት ማብቂያ የተቃረበ ይመስለኛል።
የችግሮቻችን ፈጣሪዎች እኛው ነን።የዘመናት ችግሮቻችን በራሳችን የተፈጠሩ ናቸው።አሁን ላለንበት መጥፎ የህይወት ገጽ ተጠያቂዎች ራሳችን ነን።ማንም የእኛን እጣ ፈንታ ወስኖ ድሀና ኋላ ቀር አልሆንም።ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት ከእኛነት ይልቅ እኔነትን አስበልጠን ድሀ ሆነናል።ለስልጣን ካለን ስር የሰደደ ጥማት ሌላውን ገለን ራሳችንን ስናኖር ከርመናል።ከእንግዲህ ይሄ ክፉ ልክፍት ማብቃት አለበት።ከእንግዲህ ይሄ መጥፎ ገጽታ መታደስ አለበት።ከእንግዲህ በአዲስ አስተሳሰብ ለአዲስ ነገር የምንነሳበት የብልጫ ዘመን እንዲሆንልን ሁላችንም መስራት ይኖርብናል።ሀገር ማለት ህዝብ እንደሆነ መማር አለብን።ሀገር ማለት እኔና አንተ እንደሆንን ማወቅ አለብን።ካለ እኔና አንተ ሀገር ምንም ናት።ካለ ሀገርም እኔና እናንተ ምንም ነን።ለምንም ነገር ህዝብ እና ሀገር ይቅደሙ። ከፊታችን የእኔና የአንተ ብሎም የሀገራችን የወደፊት እድል የሚወሰንበት ተስፋ ያዘለ ምርጫ አለ፤ በዚህ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ሀገር ለማሻገር በሚደረገው ህዝባዊ ትግል ውስጥ ተሳታፊ በመሆን የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል።
ሀገር በአንድና በሁለት ሰው ብርታት አትለወጥም።ለውጥ የአንድነት ውጤት ነው።ብልጽግና የብዙ እጆች፣ የብዙ ጭንቅላቶች ቅንጅት ነው።ለሀገራችን እኔም እናንተም እናስፈልጋታለን።የሀገርና የህዝብ ለውጥ ከእኔና ከእናንተ አስተሳሰብ የሚጀምር ነው።ብዙዎቻችን በአስተሳሰባችን ሳንለወጥ ራሳችንንም ሆነ ሀገራችንን ለመለወጥ የምንሞክር ነን።በዚህ የህይወት ዘይቤ ውስጥ ልዕልና የለም።እስከዛሬ ትልቅ ሆነን ትንሽ ሆነን ኖረናል።ለሀገራችን ማድረግ ያለብንን ሳናደርግ፣ ለራሳችንም ሳንበጅ ቀርተናል።አሁን ግን በአዲስ ሀይል የምንነሳበት ለሁላችን አዲስ ቀን ነው።አሁን ላይ የብዙዎቻችን ችግር ውስጣዊ ለውጥ በሌለበት ውጪአዊ ለውጥ ለማምጣት መልፋታችን ነው።አሁን ላይ ሀገራችንም ሆነች ህዝባችን በአስተሳሰቡ የላቀ ማህበረሰብ የሚፈልጉበት ወቅት ላይ ነው።የላቀ አስተሳሰብ ሀገር ከምትገነባባቸው ማህበራዊ እሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው።ምርጫ ሰሞን ላይ እንደመሆናችን ከእያንዳንዳችን ነገሮችን በአስተውሎት የምናይበት የላቀ እሳቤ ያስፈልገናል።ምርጫና የላቀ አስተሳሰብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት የተሻለ ነው የምንለውም በዚህ ምክንያት ነው።
ለምንም ነገር ህዝብ የስልጣን ባለቤት ነው። መንግሥት በህዝቦች የላቀ ተሳትፎ ካልተመረጠ ትርጉም አይኖረውም።ባለፈው የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት ውስጥ መንግሥት ለመመስረት ህዝብ ስልጣን አልነበረውም።መንግሥት ራሱን የሚመርጠው ራሱ ነበር።በዘንድሮው ምርጫ ግን ይሄ ሁሉ የለም።ስልጣን የህዝብ ነው።ህዝብ ያልመረጠው ፓርቲ መንግሥት እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ነው።ፓርቲዎች ለሀገር የሚጠቅም ሀሳብ ይዘው በነጻነት ሀሳባቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።የላቀ አስተሳሰብ በምርጫ ስርዓት ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ አለው።ከጥንት እስከዛሬ ኢትዮጵያውያን ሀሳብ አላጣንም።ያጣነው አድማጭ ነው።ያጣነው ከእኔነት የወጣ ህዝባዊ አይን ነው።ይሄ ሁሉ የሀገራችን ድሮአዊ ጋፍ መልክ በመቀየር ላይ ነው።ህዝብን ያስቀደመ በሀገር ሉአላዊነት ላይ የማይደራደር ትውልድ በመገንባት ላይ እንገኛለን።ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ቀን እጅግ ብሩህ እንደሚሆን የብዙዎቻችን ተስፋ ነው።ይህ ተስፋችን አብቦ ፍሬውን እናይ ዘንድ የሁላችንም የጋራ ርብርብ ይጠይቃል።
የምርጫ ካርድ ከወሰድን፣ ወስደንም የሚሆነንን ከመረጥን ኢትዮጵያን ከሚያሻግሩት ውስጥ ነን።ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የበኩላችንን የምንወጣ ከሆነ የሀገራችን የትንሳኤ አብሳሪዎች እንሆናለን።የነገዋ ብሩህ ኢትዮጵያ በዚህ የምርጫ ውጤት ላይ የቆመች ናት እላለሁ።ብዙ ነገራችን ልክ የሚመጣው የዚህን ምርጫ ውጤት ተከትሎ ነው እላለሁ።ለሁላችንም የተስፋ ብርሀን በሆነው በዚህ ታሪካዊ ምርጫ ላይ በመሳተፍ የሀገራችሁን የከፍታ ማማ እንድትገነቡ ከፊት ቁሙ እላለሁ።ትላንትና ከምርጫ ጋር ተያይዘው የተነሱ በርካታ ሀገራዊ መከራዎችን አሳልፈናል።እኔነት በወለደው ልክ በሌለው የስልጣን ጥም በርካታ ህዝባዊ ኪሳራዎች እዛም እዚም ነበሩ።ትላንትና በዛ ሰሞን በነበሩ የይስሙላ ምርጫዎች እዚች ሀገር ላይ ምን ያልሆነ አለ? በውሸት ፕሮፓጋንዳ ህዝብን እያታለሉ፣ በእብለት በማስመሰል ሀገርና ህዝብ ሲበደል ኖሯል።የሀሳብ የበላይነት መክኖ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ብዙ ማጭበርበሮች ደርሰዋል።ትላንትና ለብዙዎቻችን ዘግናኝ ጊዜ ነበር።ጸዓዳ ቀኖች ናፍቀውን፣ ብሩህ ማለዳዎችን ስንጠብቅ ነበር።
መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ የከፍታ ጊዜ ነው።ይሄ ስለመሆኑ በርካታ አመላካች ነገሮች እያየን ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነው።ይህ ምርጫ የብዙ ነገር መጀመሪያ ነው።ከፍታዎቻችን ሁሉ ከዚህ ምርጫ በኋላ የሚመጡ ናቸው።ዛሬን የመሰሉ በርካታ ነገዎችን ለመፍጠር ፍትህን የሚሻ፣ ሀጢዐትን የሚጸየፍ እውነተኛ ትውልድ ያስፈልጋል።በሀገር ጉዳይ ላይ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን።ካለእኔና አንተ መንግሥት ብቻውን የሚፈጥረው ተዐምር የለም።የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል።እስከዛሬ ከጨለማ የሚያወጣ ሀይል እያለን ሳንጠቀምበት ቀርተናል።ከእንግዲህ ግን ይሄ አይኖርም ምክንያቱም የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ነውና።አበቃሁ።ቸር ሰንብቱ።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013